መልእክተ አትሮንስ ዘተዋሕዶ - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

መልእክተ አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ
በዚህ የጡመራ መድረክ ገዳማት፣ አድባራት፣ አብያተ ክርስቲያናት፣ የአብነት ት/ቤቶች፣ የፀበል ቦታዎች፣ ታሪካዊ ቦታዎች ፤ ቤተ መዘክሮች፣ አብያተ መፃሕፍት፣ ሰንበት ት/ቤቶች እና ሌሎችም መካነ ታሪኮች እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን መዓዛ የሆኑ የቅዱሳን፣ ፃድቃን፣ ሰማዕታት፣ ደናግል፣ መነኮሳት፣ ነቢያት ሐዋርያት፣ አበው ወእማት፣ መምህራን፣ ሊቃውንት፣ ጳጳሳት፣ ወንድሞችና እህቶች አርአያነት ያላቸው ሰዎች ዜና መዋዕል፣ ገድል፣ ትሩፋት፣ ብሒል የሚዘከርበት የሀገራችን የሚንቀሳቀሱ እና የማይንቀሳቀሱ ቅርሶች ፤ በዓላት፤ ዕሴቶች እና ሌሎችም የሚዳሰሱበት ይሆናል፡፡
በዚህ የጡመራ መድረክ (Blogging site) የሚወጡትን የተለያዩ ጽሁፎችን፣ ሥዕሎችን፣ ቪዲዮዎችና የተለያዩ መረጃዎች የጡመራ መድረኩ ባለቤት በተለያየ ጊዜ ታትመው የወጡ መጻሕፍት፣ መጽሔት፣ ጋዜጣ፣ ዜና መዋዕሎች፣ በራሪ ወረቀቶች እና ድረ ገጾች (websites) በዋቢነት ከመጠቀሙም ባሻገር የተለያዩ ቦታዎችን በአካል በመሔድ የሚያደርጋቸው ቅኝቶች ግብዓቶች ናቸው፡፡
የጡመራ መድረኩ ተሳታፊዎች ወደፊት በሚሰጡት፣ የነቃ፣ የጎላ፣ እና የሰላ ምክር እና አስተያየት ለሁላችንም መልካም የትምህርት መድረክ እንደሚሆን ተስፋዬ ነው፡፡ የጅማሬም የፍፃሜም ባለቤት እግዚአብሔር ሁላችንም ያጽናን፡፡
የአባቶቻችን ዕምነታቸው ፀጋ በረከት ረድኤታቸው
ጥርጥር የሌለባት ንጽሕት ተዋሕዶ ዕምነታቸው በእኛ ዘንድ ፀንታ ትኑር::

 በቅድሚያ ልናውቅ የሚገባን ነገር አለ።  እሱም ሃይማኖታችንን ጠንቅቀን ማወቅ እና ቅዱሳን አባቶቻችን የሄዱበትን የሃይማኖት መንገድ መከተል ነው። ለምሳሌ፤የሕይወትና የክብር ባለቤት ወደ ሆነው የባህርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረጉትን ጉዞ የሚያሳይ ስለሆነ በዚህ ብሎግ ላይ የምናስተላልፋቸው መልእክቶች  የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፤ ቀኖና እና ትውፊትን የጠበቀ ከመሆኑም በላይ ከአባቶቻችን የወረስናቸውን  ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የጠበቀ ትምህርት፤ መዝሙሮች፤ ስብከቶች፤    እና ሌሎች ጥሩ ምክር አዘል ቁም ነገሮችን አትሮንስ ታስተላልፋለች::
1) ፍኖት ማለት መንገድ ማለት ነው:: በመጽሐፍ ቅዱስ የሰው ሕይወት በመንገድ ተመስሏል:: በመንገድ ላይ ሳለህ በጠላትህ እወቅበት ማለቱ በዚህ ዓለም ሕይወትህ በጠላት ዲያብሎስ ላይ ጠቢብ ሁንበት ማለት ነው:: ማቴ 5;25:: የሰው ሕይወት በመንገድ የተመሰለው በመንገድ ላይ አንዱ ሲወጣበት ሌላው አንዱ ሲወርድበት ሁሉም ወደ አሰበው ሲደርስበት እንደሚኖር ሁሉ በዚህ ዓለም ሕይወትም አንዱ ጽድቅ ሠርቶ ከክብር ወደ ክብር ሲሸጋገርበት ሌላው ደግሞ በሚያልፍ ዘመኑ ፍዳው የማያልፍ ኃጢአት ሲሠራ ኖሮ በወደደው ኃጢአት እንደ ጠፍ ጨረቃ ከክብር እያነሰ ስለሚሄድበት ነው:: ቅዱሳን መንገድ በተባለ በዚህ ዓለም ሕይወታቸው በጠላታቸው በዲያብሎስ ላይ አውቀውበት እርሱን ጠቅጥቀው አልፈው ለክብር የበቁ ሲሆን ይህ ብሎግም ይህንኑ የቅዱሳን ጥበብና ተጋድሎ በአጠቃላይም

2) ሰው የፈጣሪውን ሕግ በማፍረሱ ምክንያት ወደዚህ ዓለም ቀጥሎ ወደ አምላኩ የሚያደርሰውን እውነተኛ መንገድ አጥቶ አምስት ሽህ አምስት መቶ ዘመን ሲባዝን ኖረ:: ይህ ዓመተ ፍዳ ሲያልቅ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነስቶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆኖ ወደዚህ ዓለም መጥቶ ሰውን ከፈጣሪው ጋር የሚያገናኘውን እውነተኛውን መንገድ አስተማረ:: ገላ 4;4:: እርሱም "አነ ውእቱ ፍኖተ ጽድቅ ወሕይወት - የጽድቅና የሕይወት መንገድ እኔ ነኝ" በማለት ከፈጣሪው አንድነት ተለይቶ ከክብር ተራቁቶ የነበረውን የሰው ልጅ ወደራሱ አንድነት ሊያዋህደው እንደመጣ አስረዳ:: እርሱን በፍጽም ሕይወታቸው ለሚመስሉት ወደ ሕይወትና ክብር የምትወስደውን ጠባብ መንገድ በቃል ያስተማረና በተግባር ሠርቶ ሥሩ ያለ ቅዱሳንን የጠራ የተቀበለና ያከበረ እውነተኛው ፍኖተ ቅዱሳን ኢየሱስ ክርስቶስ ለወዳጆቹ ያለውን ፍቅርና ተቆርቋነት እንዲሁም ያዘጋጀላቸውን ክብር ስለሚያስረዳ የአትሮንስ ብሎግ ጉዞአችን ቅዱሳን አባቶቻችን የተከተሉትን መንገድ መከተል ነው።
3) ነቢየ እግዚአብሔር ሆሴዕ "ይህን ነገር የሚያስተውል ጠቢብ የሚያውቃትም አስተዋ ማነው? የእግዚአብሔር መንገድ ቅን ነው ጻድቃንም ይሄዱበታል ተላላፊዎች ግን ይወድቁበታ" ብሎ የጻድቃንን እና የኃጥአንን መንገድ ልዩነት አስረድቷል:: ሆሴ 14:9 ጠቢቡ ሰሎሞን" የጻድቃን መንገድ እንደ ንጋት ብርሃን ነው ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል" ይላል ምሳ 4:18  
ስለዚህ አትሮንስ ዘተዋሕዶ ብሎግ ጻድቃን የሄዱበትን ቅንና ርቱዕ የሆነውንና እግዚአብሔር ቅድስናን እና ፍጹምነትን ለሚሹ ያዘጋጀው መንገድ ስለሚያሳይ አትሮንስ ዘተዋሕዶ ብሎግ የምታስተላልፋቸውን ቁም ነገሮች በየጊዜው እንድትከታተሉ ስትል ጥሪዋን ታስተላልፋለች።

የቅዱሳን በረከታቸው እና ረድኤታቸው አይለየን::

Post Bottom Ad