የካቲት 16
የእመቤታችን የቅድስት ኪዳነ ምህረት የንግስ በዓል
ኪዳነ ምህረት ማለት የምህረት ቃል ኪዳን ማለት ነው፡፡ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከ33ቱ በዓላተ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡
እመቤታችንም ከጌታችን መቃብር እየሄደች በምትለምንበት ጊዜ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና ምን ልታመጣብን ነው በማለት ሊጣሏት ሲመጡ ጌታችንም ከዓይናቸው ሰውሯታል። አይሁድም ጠባቂ ቢያቆሙ እመቤታችን ዕለት ዕለት መሄዷን አላቋረጠችም። እመቤታችንም እንዲህ ብላ ጸለየች።
ልጄ ወዳጄ ሆይ፤ ከስጋዬ ስጋ ከነፍሴ ነፍስ ነስተህ ሰው በመሆንህ፤
ዘጠኝ ወር ከ5 ቀን በቻለችህ ማሕጸኔ፤
ከአንተ ጋር ሀገር ለሀገር ስለ መሰደዴ፤
መትተህ ልምናዬን ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ አለች።
በዚህ ጊዜ ንውጽውጽውታ ሆነ። መቃብራት ተሰነጣጠቁ። ጌታችንም ከእልፍ ከእላፋት መላዕክቱ ጋር መጥቶ ሰላም ለኪ ማርያም ምን እንዳደርግልሽ ትለሚኚኛለሽ አላት፡፡ እርሷም
መታሰቢያዬን ያደረገውን፤
ስለ ስሜ ለችግረኛ የሚራራውን፤
በስሜ ቤተ ክርስቲያን ያነጻውን፤
መባዕ የሰጠውን፤
ከሃይማኖት ከፍቅር ጽናት ልጁን በስሜ የጠራውን ሁሉ ማርልኝ፤
ከሞተ ስጋ ከሞተ ነፍስ አድንልኝ አለችው፡፡
ጌታችንም ይህን ሁለ እንዳደርግልሽ ቃል ኪዳን ገባሁ። ለኪ በርእስየ ወበአቡየ ሕያው ወበመንፈስ ቅዱስ ብሎ ቃል ገብቶላት አርጓል፡፡
ሌላው ደግሞ በላዔ ሰብ ታሪክ ነው። ይህ ሰው በእመቤታችን ልመና እግዚአብሔር የማረው ሰው ነው። በላኤ ሰብ ማለት ብዙ ሰውን የገደለ በልምድ አማርኛ ሰው በላ ማለት ነው፤ ትክክለኛ ስሙ ግን ስምዖን ይባላል። ቅምር በሚባል አገር የሚኖር እጅግ ባለጸጋ ነበር። እንደ አብርሃም እንግዶችን እየተቀበለ ድሆችን እየመገበ የሚኖር ጻድቅ ነበር። ሰይጣን በዚህ ስራው ቀናበት ሊፈትነውም በሦስት አረጋዊ ሽማግሌዎች ስላሴ ነን ብሎ ተገለጠለት። ልክ እንደ አብርሃም፤ ሐዋርያው ጳውሎስ ሰይጣን የብርሃን መልአክ መስሎ ይመጣል እንዳለ፤ እርሱም ሥላሴ መስለውት ተቀበላቸው ተንከባከባቸውም። ምግብ አቀረበላቸው ምግብ አንበላም የምንጠይቅህን ግን ትፈጽምልን ዘንድ ቃል ግባልን አሉት። ቃል ገባላቸው። እንግዲያውስ የምትወደን ከሆነ አንድያ ልጅህን ሰዋልን አሉት። መጀመሪያ ደነገጠ። ኃላ ግን አብርሃም ልጁን ሊሰዋ አልነበረምን? እኔንም ሊፈትኑኝ ይሆናል ብሎ ለማረድ ተዘጋጀ። ተው የሚለው ድምጽ አልሰማም። አርደው፤ አወራረደው ይዞላቸው ቀረበ። መጀመሪያ ቅመስልን አሉት። ቀመሰው። ወዲያው እነዚያ ሰዎች ተሰወሩበት። እርሱም አዕምሮውን ሳተ። ተቅበዘበዘ። ከዚያ በኃላ ምግብ አላሰኘውም። የሰው ስጋ እንጂ። መጀመሪያ ቤተሰቦቹን በላ። ከዚያም ጓደኞቹን። ጦርና የውኃ መንቀል ይዞ ከቤቱ ወጣ። ያገኘውን ሰው እየገደለ ይበላል። የበላቸው ሰው ቁጥር 78 ደረሰ፤ በመንገድ ተቀምጦ የሚለምን በደዌ የተመታ አንድ ደሃ አገኘ ሊበላው ወደ እርሱ ተጠጋ ግን ቁስሉን አይቶ ተጸየፈው፤ ደሃውም “ስለ እግዚያብሔር ከያዝከው ውኃ አጠጣኝ” አለው “ዝም በል ደሃ” ብሎት አለፈ፤ “ኸረ በውኃ ጥም ልሞት ነው ስለ ጻድቃን ስለ ቅዱሳን” አለው አሁንም ዝም ብሎት ሄደ ለሦስተኛ ጊዜ “ስለ አዛኝቷ ስለ እምዬ ማርያም” አለው፤ ሰውነቱን አንዳች ነገር ወረረው “አሁን የጠራኽውን ስም እስኪ ድገመው ስለ ማን አልከኝ” አለው፤ ስለ አዛኝቷ ስለ እመቤቴ ማርያም አለው፤ ይህቺስ ደግ እንደሆነች በምልጃዋም ከሲኦል እንደምታወጣ ህጻን እያለው እናትና አባቴ ይነግሩኝ ነበር፤ በል እንካ አለው እጁን ዘረጋለት ጥርኝ ውኃ ጠብ አደረገለት ወደ ጉሮሮው አልወረደም የተሰነጠቀ እጁ ውስጥ ገባ እንጂ፤ በለዔ ሰብ ከዚያች ደቂቃ በኃላ አዕምሮው ተመለሰለት እንዲህም አለ “በአንድ ዋሻ ውስጥ ገብቼ ስለ ኃጢያቴ አለቅሳለሁ ስጋዬ ከአጥንቴ እስኪጣበቅ እጾማለሁ ወዮሊኝ ወዮታም አለብኝ አለ፤ ወደ ዋሻ ገባ ምግብ ሳይበላ ውኃም ሳይጠጣ 21 ቀን ኖሮ በርሃብ ሞተ ይላል ተአምረ ማርያም። ጨለማ የለበሱ ሰይጣናት እያስፈራሩ እያስደነገጡ ነፍሱን ወደ ሲኦል ሊወስዷት መጡ፤ እመቤታችን ፈጥና በመካከላቸው ተገኘች፤ ልጄ ወዳጄ ይህችን ነፍስ ማርልኝ አለችው እናቴ ሆይ 78 ነፍሳትን የበላ እንዴት ይማራል አላት፤ የካቲት 16 ቀን በጎለጎታ የገባህልኝ ቃል ኪዳን አስብ ስምሽን የጠራ መታሰቢያሽን ያደረገን እምርልሻለው ብለኸኝ የለምን አለችው፤ እርሱም እስኪ ይህቺን ነፍስ በሚዛን አስቀምጧት አለ ቢያስቀምጧት ጥርኝ ውኃው መዝኖ ተገኘ፤ ስል አንቺ ስል ምሬያታለው ሰባት ቀን ሲኦልን አስጎብኝታችሁ ወደ ገነት አግቧት አላቸው። ቦታሽ እዚህ ነበር እያሉ ሲኦልን አስጎብኝተው ወደ ገነት አገቧት። ልመናዋ ክብሯ የልጇም ቸርነት ከሁላችን ጋር ይሁን።
ምንጭ፤ ተአምረ ማርያም
ድንግል ማርያም በቃል ኪዳኗ አትለየን