ሰማዕቱ መርቆሬዎስ - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Friday, February 19, 2021

ሰማዕቱ መርቆሬዎስ

 ሰማዕቱ መርቆሬዎስበዚህች ዕለ ጥር ፳፭ ለኛ ለወጣቶች አርአያ የሚሆነውን ቅዱስ መርቆርዮስ መታሰቢያው ነው።
በ200 ዓ/ም አካባቢ እንደተወለደ የሚነገርለት ቅዱስ መርቆርዮስ ውልደቱ ጣዖትን ከሚያመልኩ ቤተሰብ ነበር ፣ ስሙም ፒሉፓዴር ይባል ነበር ። ወላጆቹ ወደ ክርስትና የመጡት በተአምር ነው ስማቸውም ታቦትና ኖኻ ይባላሉ እሱም ክርስትናን ሲቀበል መርቆሬዎስ ሊባል ችሏል ። መርቆሬዎስ ማለት የአብ ወዳጅ ማለት ነው ዳግመኛም የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ ማለት ነው። በጦርነት ኃይለኛ በመልኩ ደመ ግቡና ተወዳጅ የነበረው ቅዱስ መርቆሬዎስ ስለ ክርስትናው መከራን የተቀበለው በሃያ ዓመቱ ነው፣ ዘመኑም በዳኬዎስ ቀዳማዊ ነው፣ ይህም ንጉሥ ክብር ይግባውና ክርስቶስን የካደ ነበር ፣በወቅቱም አንድ ጦርነት አሸንፎ ለሚያመልከው ጣዖት ሊሰዋ በዓልን ሊያደርግ በወደደ ጊዜ ቅዱስ መርቆሬዎስ ከእርሱ ጋር ለማክበር እንደማይተባበር በመግለጹ እንዲሁም በጣዖት አምላኪው ንጉሥ ፊት ክርስቶስን እንደማይክድ እና ለጣዖት እንደማይሰግድ ስለመሰከረ ንጉሥ ዳኬዎስ በቁጣ መርቆርዮስ እንዲገደል በማዘዙ ራሱን በሰይፍ ተቆርጦ የሰማዕትነት አክሊል ተቀዳጀ።
ከመርቆሬዎስ ታሪክ ክርስቲያኖች ምን እንማር?
ዛሬ መታሰቢያውን የምናርግለት ይህ ወጣት ቅዱስ ሰማዕት ከወላጆቹ ባገኘው ትውፊታዊ አምልኮ በአንድ ወቅት ጣዖት አምላኪ ነበር። ልበ ብሩህ በአንድ ተአምር እግዚአብሔርን ይመለከታል ፤ ልበ ደንዳና ደግሞ እንደ ፈርኦን ዐሥር ተአምር ቢያይ እግዚአብሔር የለም ብሎ ይክዳልና ፥ ስንክሳር እንደሚያስነብበን ልበ ብሩህ የነበሩት ወላጆች ወደ ክርስትናው የመጡት በተአምር ነው ። ከጣኦት አምላኪነት ወደ ጽኑ የክርስቶስ ወዳጅ የሄደው ቅዱስ መርቆሬዎስ ዛሬ ቤተክርስቲያን የታነጹለት እና በስሙም ብዙ ተአምር የሚያደርግ ታላቅ ቅዱስ ነው ይህም በተለይ በአሁን ጊዜ በተለያዩ ማህበራዊ ሕይወታችን በተለያዩ ሐይማኖት ስር ያሉ ሰዎች ጋር ስንገናኝ ልባቸው በርቶ መች እንደሚለወጡ አናውቅምና መጥላት እና መናቅ እንደሌለብን ያስተምረናል ፣ ብዙ ጊዜ እግዚአብሔርን እና እመቤታችንን የወደድን መስሎን ሌላ ሃይማኖት ተከታዮችን አጥብቀን ስንጠላ እንገኛለን ፣ነገር ግን እንደ መርቆሬዎስ ቤተሰብ ልባቸው በርቶ መች ሊለወጡ እንደሚችሉ አናቅም እና በእምነታቸው ብቻ ሰዎችን ልንጠላ እንደማይገባን እናያለን ፣ ከመጥላት እና ማግለል ይልቅ በሌላ እምነት ስር ላሉ ሰዎች በፍቅር መጸለይ እና በኛ ውስጥ ክርስቶስን ያዩ ዘንድ በኑሮ የምንመሰክር እውነተኛ የክርስቶስ አገልጋይ ልንሆን ይገባናል ።
2) እኛም ፒሉፓዴር መሆን ትተን መርቆሬዎስ እንድንሆን ያስተምረናል ፣ ጣዖት የግድ የተቀረጸ ምስል ማለት አይደለም ። ከእግዚአብሔር የሚያርቁን ነገሮች በሙሉ ለእኛ ጣዖታቶቻችን ናቸው ። ቅዳሴ እንዳናስቀድስ ፣ መንፈሳዊ ትምህርት እንዳንማር ፣ እንዳንቆርብ ፣ እንዳንመጸውት ያደረጉን ኃጢአቶች ከሆኑ እነዚያ ኃጢአቶች ለእኛ ጣዕዖት ሆነውብናልና እኛም ዳግም መርቆሬዎስ እንሆን ዘንድ በዘወትር ጸሎታችን እንደምንጸልየው ማርያምን ምስክር አድርገን ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል እያልን ጣዖት የሆነብንን ሰይጣን ልንክደው ይገባናል ።
የቅዱስ መርቆሬዎስ ጸሎት እኛን ክርስቲያኖችን ከዚህ ዓለም ፈተና ይታደገን ፤ በረከቱ ከእኛ ጋር ይኑር ለዘለዓለሙ አሜን!

Post Bottom Ad