ነገረ ድኅነት (ክፍል ሦስት) - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Saturday, March 21, 2020

ነገረ ድኅነት (ክፍል ሦስት)

ሰው የዳነው እንዴት ነው?

(አትሮንስ ዘተዋሕዶ መጋቢት 12 ቀን 2012 ዓ.ም ) መዳናችን (ድኅነታችን) የተገኘው በእኛ ሥራ መልካምነት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ከሞት ወደ ሕይወት ያሸጋገረው እርሱን የሚያስደስትና እንዲያ እንዲያደርግለት የሚያበቃው የተቀደሰ ሕይወት ስለነበረው አይደለም፡፡ በኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ሰው የዳነው በእግዚአብሔር ቸርነት (ጸጋ) ነው፡፡ የሰው ድኅነት የእግዚአብሔር የቸርነቱ ስጦታና ለሰው ያለው የማይለወጥ ፍቅር ውጤትና መገለጫ ነው፡፡ የእኛን የቀደመ ሁኔታና እግዚአብሔር እንዴት እንዳዳነን ሐዋርያው ግልጽ በሆነ ሁኔታ እንዲህ ሲል ያስተምረናል፡-

“እኛ ሁላችን ደግሞ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፣ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን፡፡ እንደ ሌሎችም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለጸጋ ስለሆነ ከወደደን ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወትን ሰጠን፣ በጸጋ ድናችኋልና፡፡ በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለጠግነት ያሳይ ዘንድ ከእርሱ ጋር አስነሣን፤ በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን፡፡” ኤፌ. 2.3-8፡፡

ሰው ሁሉ በአዳም በደል ምክንያት “የቁጣ ልጅ” ነበር፤ ሁሉም በኃጢአት ምክንያት የሞተ ነበር፡፡ ሮሜ 8:10፡፡ አሁንም ይኸው ሐዋርያ ስለዚሁ ጉዳይ ሲናገር ለደቀ መዝሙሩ ለቲቶ በላከው መልእክቱ እንዲህ አለ፡-

“እኛ ደግሞ አስቀድመን የማናስተውል ነበርንና፤ የማንታዘዝ፤ የምንስት፤ ለምኞትና ለልዩ ልዩ ተድላ እንደ ባሪያዎች የምንገዛ፣ በክፋትና በምቀኝነት የምንኖር፤ የምንጣላ፤ እርስ በርሳችን የምንጠላላ ነበርን፡፡ ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው ጥምቀትና በመንፈስ መታደስ አዳነን እንጂ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለነበረው ሥራ አይደለም፡፡” ቲቶ. 3:3-5፡፡

ጌታችንና መድኃኒታችንም እግዚአብሔር ሰውን የወደደውና ያዳነው እንዲሁ በአባታዊ ፍቅሩ መሆኑን ሲገልጽ፡- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን (ሰውን) እንዲሁ ወዷልና” አለ፡፡ ዮሐ. 3:16 የወደደን እንዲሁ በቸርነቱ እንጂ እንዲወደን የሚያደርግ መልካም ሥራ ስለነበረን ወይም እኛ ስለ ወደድነው አይደለም፡፡ ሰውማ በራሱ ጥፋት ከአምላኩ ፊት የኮበለለ ነበር፡፡ ጌታችን በጠፋው በግ ምሳሌ እንደ ተናገረው የጠፋውን አዳምን “የሰውን ልጅ በሙሉ” ይፈልገውና ወደ ቀደመ ክብሩ ይመልሰው ዘንድ ከሉዐላዊ መንበሩ ወርዶ ፈለገው፤ ባገኘውም ጊዜ ለመፈለግ በደከመው ድካም ሳይቆጣው፣ ሳይገርፈው፣ በእግርህ ሂድ ሳይለው በማግኘቱ ተደስቶ በጫንቃው ላይ ተሸከመው፡፡ በጠፋው ልጅ ምሳሌ እንደ ተናገረው ያጠፋውን ጥፋትና የበደለውን በደል ሳያሰብ አዘነለት፣ በፍጹም ፍቅር ተቀበለው፣ የሰባውን በማረድ (የራሱን ቅዱስ ሥጋውን በመቁረስና ክቡር ደሙን በማፍሰስ) በዓል አደረገለት፡፡ “ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኗል፣ ጠፍቶም ነበር ተገኝቷልም፤ ደስ እንዲለን ፍሥሐም እንድናደርግ ይገባናል” አለ፡፡ ሉቃ. 1511-32

ቅዱስ ጳውሎስም ይህንኑ ሲገልጽ፡- “እናንተንም ነውርና ነቀፋ የሌላችሁና ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ያቀርባችሁ ዘንድ፣ በፊት የተለያችሁትን፣ ክፉ ሥራንም በማድረግ በአሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን አሁን በሥጋው ሰውነት በሞት በኩል አስታረቃችሁ” አለ፡፡ ቆላ. 121-22 ይህን ሁሉ አጠቃልሎ “ወሶበ እንዘ ጸሩ ንሕነ ለእግዚአብሔር ተሣሃለነ በሞተ ወልዱ - እግዚአብሔር ጠላቶቹ ሳለን በልጁ ሞት ታረቀን” አለ፡፡ ሮሜ. 5:10 ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም- “እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፣ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ” በማለት የዳንነው ክርስቶስ በቸርነቱ በተቀበለው ሕማምና መከራ መሆኑን ይነግረናል፡፡ 1 ጴጥ 2:24፡፡

ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም እንዲህ ይላል፡-

“በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፤ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና፡፡ ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተሥረይ ይሆን ዘንድ ልጁን አንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም፡፡” 1ዮሐ. 4:9-10

የወደቀውንና የሞተውን የሰው ልጅ ያዳነው የእግዚአብሔር ቸርነት እንጂ የእርሱ ሥራ አይደለም፡፡ ሰው በሥራው ብቻ የሚጸድቅ ቢሆን ኖሮ በብሉይ ኪዳን የነበሩ ደጋግ አባቶች ለመዳን ክርስቶስ ባላስፈለጋቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም እንኳ በደጋግ ሥራቸው በኃጥአን ላይ የሚደርሰው መከራ ሙሉ በሙሉ ባይደርስባቸውም ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ በአዳም በደል ምክንያት የተዘጋችውን ገነት እስኪከፍታት ድረስ ከሲኦል መውጣትና ወደ ገነት መግባት አልቻሉም፡፡ በኃጢአት ምክንያት ከመጣው ፍዳ አንዷንም ፈቀቅ ማድረግ አልቻሉም፡፡ ስለዚህ እኛን ያዳነን የክርስቶስ ቸርነት እንጂ ሥራችን አይደለም ማለት ነው፡፡ እንደ ሥራችንማ ቢሆን እግዚአብሔር ሰው ኾኖ ኃጥአን ለሆንነው ለእኛ መከራ ይቀበል ዘንድ የሚያበቃው የትኛው ሥራችን ነበር? በእኛ ሥራ ቢሆንማ ኖሮ እንኳን ይህ ሁሉ ቸርነት ሊደረግልን ቀርቶ ከተደረገልን ቸርነት አንዷንም እንኳን ባላገኘን ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ስጦታ በዋጋ የሚገዛ አይደለም፡፡

በኃጢአት ድካም ሳለን በቸርነቱ የወደደንና ያዳነን መሆኑን በማድነቅ ሐዋርያው እንዲህ ይላል፡-

“ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቷልና፡፡ ስለ ጻድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና፤ ስለ ቸር ሰው ግን ሊሞት እንኳ የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቷልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል፡፡” ሮሜ. 5:6-9፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ በሚገባ እንደ ገለጸው እኛ ጻድቃን ሆነን ክርስቶስ ቢሞትልን ኖሮ ምናልባት ብዙም ላይደንቅ ይችል ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ለጻድቅ ሰው ተላልፎ የሚሞት ምናልባት ይገኝ ይሆናልና ነው፡፡ ነገር ግን ኃጢአተኞች ሳለን ስለ እኛ መሞቱ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍጹም ፍቅርና የቸርነቱን ገናናነት ያስረዳል፡፡ ለምሳሌ ለሞት የሚያበቃ ወንጀል ሠርቶ ሞት ለተፈረደበት ኃጢአተኛ ሰው “እኔ እሞትለታለሁ” ብሎ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ማን ነው? ክርስቶስ ለእኛ ያደረገው ይህንን ነው፤ በኃጢአታችን ሞት የተፈረደብን “የሞት ሰዎች” ሳለን በፍጹም ፍቅሩ ስለ እኛ ራሱን ቤዛ አድርጎ ሰጠ፣ ሞተልን፤ በሞቱም ከሞት አዳነን፣ ሕይወትን ሰጠን፡፡ ይህ የእርሱ የጸጋ ስጦታ ብቻ ነው፡፡ ኢሳ 53:4-6 ይህን ሁሉ ቸርነት ያደረገልን፣ የሞት ሰዎች ሳለን በማይነገር ፍቅሩ ሕይወትን የሰጠን አምላካችን እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን አሜን፡፡

2.3 ሰው ለመዳን ምን ያስፈልገዋል?

ሰውን ያዳነው የእግዚአብሔር ጸጋ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ነገር ግን ይህን መዳን ለመፈጸምና በተሰጠው የመዳን አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን ከእያንዳንዱ ሰው የሚጠበቅ ነገር አለ፡፡ ሐዋርያው የእግዚአብሔርን የማዳን ነገር ሲገልጽ፡- “እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው” በማለት ንጹሐ ባሕርይ የሆነ ክርስቶስ ስለ እኛ ኃጢአት “ኃጥእ” ተብሎ መከራ በመቀበሉ የእኛ ኃጢአት መወገዱንና በእርሱ “ኃጥእ” መባል እኛ “የእግዚአብሔር ጽድቅ” መሆናችንን ገለጸ፡፡ በመቀጠልም እንዲህ አለ፡- “አብረንም እየሠራን የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ እንዳትቀበሉ ደግሞ እንለምናለን” 2 ቆሮ. 5:21 6:1 ይህም ማለት እግዚአብሔር ያደረገልንን የማዳን ጸጋ ለመቀበል ከእኛ የሚጠበቀውን (ምንም እንኳ የምናደርገው ነገር ለጸጋው ምንም የማይመጥንና እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም) ነገር ሳናደርግ እንዳንቀር ነው፡፡ ይህም እያንዳንዳችን ማድረግ ያለብን የራሳችን ድርሻ ያለ መሆኑን በግልጽ የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ከእርሱ የሚጠበቅበትን ለማይፈጽም ሰው የእግዚአብሔር ሰውን ማዳን ብቻ በራሱ ተጠቃሚ አያደርገውም፡፡

አንድ ሰው ለመዳን የሚከተሉትን መፈጸም ይኖርበታል፡፡

1. እግዚአብሔር ሰውን ለማዳን በፈቃዱ ያደረገውን ነገር ሁሉ ማመንና መቀበል (እምነት)፡-

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ከመወለድ ጀምሮ ለሰው ሲል ያደረውን - መጠመቁን፣ ዞሮ ማስተማሩንና ያስተማረውን ቃልና ትእዛዝ ማመንን፣ መከራ መቀበሉን፣ በመጨረሻም በራሱ ፈቃድ ለእኛ ሲል መሞቱን፣ መቀበሩንና በሦስተኛው ቀን መነሣቱን እና በአርባኛው ቀን ወደ ቀደመ ክብሩ ማረጉን . . . በአጠቃላይ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምታምነውን ሁሉ በፍጹም ልብ ማመን ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ያደረገውን ልዩ ቸርነትና እናምነው ዘንድ የገለጠውን እውነት የማያምን ሰው ሊድን አይችልም፡፡

እግዚአብሔር ያደረገውን ቸርነትና የፈጸመውን ድኅነት ለማያምን ሰው ለእርሱ ልክ የሰው ድኅነት እንዳልተፈጸመና ገና እንዳልዳነ ይሆንበታል፡፡ ይህም ማለት በኢየሱስ ክርስቶስ የማያምን ሰው አሁን እየኖረበት ያለው ዘመኑ ዘመነ ወንጌል ዓመተ ምሕረት ቢሆንም  እርሱ ግን በዘመነ ኦሪት በዓመተ ፍዳ እንደ ነበሩት ሰዎች ይሆናል ማለት ነው፡፡ በእርግጥ እንዲያውም በዚያ ዘመንም ወደፊት በዘመነ ወጌል የሚሆነውን በእምነት አሻግረው ያዩና በተስፋ የጠበቁ ደጋግ አበው ነበሩ፡፡ ከዘመኑ ሳይደርሱ እንደ ደረሱ ሆነው ሥጋዌው ከፊታቸው ግልጽ ብሎ እየታያቸው ዕለቱን እንደ ተፈጸመ እያደረጉ ትንቢት የተናገሩ ነቢያትም ነበሩ፡፡ አሁን በዘመነ ወንጌል በዓመተ ምሕረት እየኖረ የማያምን ኢአማኒ ሰው ግን ከዘመነ ብሉይ እንደ ነበሩት አሕዛብ ያለ ነው፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በኢየሱስ ክርስቶስ ያላመነን ሰው ምን እንደሚገጥመው ሲናገር፡- “በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም” ያለው ለዚህ ነው፡፡ ዮሐ. 336

ጌታችን በቅዱስ ቃሉ፡- “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው፣ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም” በማለት ማመን የሕይወት መንገድ መሆኑን አስተምሯል፡፡ ዮሐ. 524፡፡ እንዲሁም “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር እንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና፡፡ … በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል” በማለት በእርሱ ማመን የድኅነት መሠረት ሲሆን አለማመን ደግሞ የፍርድና የሞት መንገድ መሆኑን ግልጽ ባለ ቃል አስረዳ፡፡ ዮሐ. 318  ዮሐ. 4:5 ዮሐ. 5:10

ጌታችን “የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀበሉት፣ ከአንተም ዘንድ እንደ ወጣሁ በእውነት አወቁ፣ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ” በማለት እምነት እርሱ የነገረንን ቃል መቀበልና ማመን መሆኑን ተናግሯል፡፡ ዮሐ. 178 በአጠቃላይ እግዚአብሔር እርሱን ማወቅ በምንችለው መጠን እናውቀውና እናምነው ዘንድ፣ ወደ እውነት ይመራን ዘንድ በቅዱስ መጽሐፍ የገለጠውን እውነት መቀበልና ማመን ለድኅነት የግድ ነው፡፡ “ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ፣ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና” እንደ ተባለ፡፡ ዕብ. 116

ሃይማኖት የድኅነት መሠረት ነው፡፡ ቤት ያለ መሠረት ሊቆም እንደማይችልና በአየር ላይ ሕንፃ መገንባት እንደማይቻል ሁሉ የዘለዓለማዊ ድኅነት መሠረትም ሃይማኖት ነው፡፡ ለመዳን አንድ አምላክ የሆነውንና በአንድነቱ ውስጥ ልዩ ሦስትነት ያለውን የሕያወ ባሕርይ የእግዚአብሔርን ህልውናውን፣ ፈጣነቱን፣ አዳኝነቱን … ማመን፣ የእግዚአብሔር ወልድን ሥጋዌውን፣ ሞቱን፣ ተዋሕዶውን፣ ትንሣኤውን፣ . . .  ማመን ለመዳን ሊታለፉ የማይችሉ ቁልፎች ናቸው፡፡ ያለዚህ እምነት ወይም ከዚህ የወጣ እምነት አያድንም፡፡     

Post Bottom Ad