ነገረ ድኅነት (ክፍል ሁለት) - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Saturday, October 26, 2019

ነገረ ድኅነት (ክፍል ሁለት)
1.     ልጅነቱ ተመለሰለት

የጸጋ ልጅነቱንና ክብሩን አጥቶ በባርነት ውስጥ ሆኖና ተዋርዶ ለነበረው የሰው ለጅ ዳግመኛ ከእግዚአብሔር የሚወለድበትንና ልጅነትን የሚያገኝበትን ጥምቀትን ሰጠው፡፡ ይህ የልጅነት ጸጋም ለሌሎች ከእግዚአብሔር ለሚገኙ ጸጋዎች ሁሉ መሠረት ነው፡፡ ልጅ ከሆነ ዘንድ የአባቱን ንብረት ለመውረስ ይችላልና፡፡ ይህንም የአባትና የልጅነት ግንኙነት በውስጡ የሚያድርበት መንፈስ ቅዱስ እንዲመሰክርለት አደረገ፡፡ “የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል” እንዳለ፡፡ ሮሜ. 8:16 እንዲሁም ይኸው ሐዋርያ፡- “ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ፡፡ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ፡፡” ገላ. 4:6 ከእንግዲህ የባርነት መንፈስ ሳይሆን “አባ አባት” ብለን የምንጠራበትን የልጅነት መንፈስ ሰጠን፡፡ ሮሜ. 8:15

እርሱም “ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባሪያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፣ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፤ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና” በማለት በኃጢአት በተፈጠረ የጠብ ግድግዳ ምክንያት ከምሥጢሩ ርቀን ከአንድነቱ ተለይተን በባርነት እንኖር የነበረውን ሁኔታ አስወግዶ የዕርቅና የልጅነት መገለጫ የሆኑትን ፈቃዱን ማወቅንና ከባርነት ነፃ መውጣትን ሰጠን፡፡ ዮሐ. 15:15 “የፈቃዱን ምሥጢር አስታውቆናልና” ያለው ለዚህ ነው፡፡ ኤፌ. 1:9

2.      በኃጢአትና በፍትወታት እኵያት ላይ የመቋቋምና የማሸነፍ ኃይልና ሥልጣን አገኘ

ሰው በበደለና ከእግዚአብሔር በተለየ ጊዜ በሰውነቱ ላይ እንደ አረም በቅለው ሠልጥነውበትና ድል አድርገውት ያስጨንቁትና ይገዙት በነበሩ እኵያት ሕሊናትና ፍትወታት ላይ ሙሉ ኃይል አገኘ፡፡ ለኃጢአት ባሪያ ሆኖ መገዛቱ ቀርቶ ኃጢአትን የሚያሸንፍበት ኃይል አገኘ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ከአንግዲህስ ወዲያ ለኃጢአት እንዳንገዛ የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን” በማለት የገለጸው ይህን ነው፡፡ እንዲሁም “አሁን ግን ከኃጢአት አርነት ወጥታችሁ ለእግዚአብሔር ተገዝታችሁ ልትቀደሱ ፍሬ አላችሁ” አለ፡፡  ሮሜ. 6:6  20-22 7:4-6

3.     ፈጣሪውን እንዲያውቅ ተደረገ
እግዚአብሔር ሰውን በመልኩና በአርአያው የፈጠረው ሩቅ ያልሆነና በእርሱ ዘንድ ያለ የፈጣሪውን አርአያ እያሰበና እየተመለከተ በፍቅሩ ሆኖ በተዘክሮው ጸንቶ አንዲኖር ነበር፡፡ ሰው ግን የተደረገለትን ታላቅ ነገር ረስቶ በጸጋው መጠቀምን ትቶ በአርአያውና በመልኩ የፈጠረውን እግዚአብሔርን ረሳ፤ መርሳት ብቻም ሳይሆን ያገለግሉትና ይጠቀምባቸው ዘንድ የተፈጠሩለትን ከእርሱ በታች ያሉትን የተለያዩ ፍጥረታትንና የእጅ ሥራዎችን አመለከ፡፡ በፈጣሪ ፋንታ ለፍጡር ተንበረከከ፤ ከዚህም በላይ የእግዚአብሔርን ክብር ለዕቃውና ለድንጋዩ፤ ለቁሳቁሱ ሁሉ ሳይቀር ሰጠ፤ ከዚህም ወደ ባሰ ሄዶ አጋንንትንም እስከ ማምለክ ደረሰ፡፡ በጨለማ የተቀመጠ ሰው አገኝ አጣውን እንደሚዳስስ እንዲሁ ሳይመርጥ ያገኘውን ሁሉ የሚያመልክ ሆነ፡፡ ሮሜ 1:9-25 እርሱ ሊገዛቸውና ሊያገለግሉት፣ እንዲሁም የፈጣሪውን ህልውናና ሥራ ለማወቅ እንዲረዱት ለአንክሮና ለተዘክሮ የተፈጠሩለትን ፍጥረታት አመለካቸው፡፡

ነቢዩ ይህን በተመለከተ በማዘንና በመገረም እንዲህ ይላል፡-

“የዝግባን፣ የዞጲንን፣ የኮምቦልንና የጥድን ዛፍ ይተክላል፣ ዝናብም ያበቅለዋል፡፡ ለሰውም ማገዶ ይሆናል፤ ከእርሱም ወስዶ ይሞቃል፣ አንድዶም እንጀራ ይጋግርበታል፤ ከእርሱም አምላክ አበጅቶ ይሰግድለታል፣ የተቀረጸውንም ምስል ሠርቶ በእርሱ ፊት ይንበረከካል፡፡ ግማሹን በእሳት ያቃጥላል፣ ሥጋም ይጠብስበትና ይበላል . . . የቀረውንም እንጨት አምላክ አድርጎ ምስል ይቀርጽበታል፤ በፊቱም ተጎንብሶ ይሰግዳል፣ ወደ እርሱም እየጸለየ፡- አምላክ ነህና አድነኝ ይላል፡፡” ኢሳ. 44:12-17

ሰው ሥነ ፍጥረትን እንዲያ ሲያመልክ በአንጻሩ ግን የራሱን አስገኚና ሥነ ፈጥረትን ሁሉ የፈጠረውን እግዚአብሔርን ረሳው፡፡ በእግዚአብሔር አርአያ የመፈጠር ጸጋ በራሱ ሰው እግዚአብሔርን እንዲያውቅ ያስችለው የነበረ ቢሆንም ሰው ግን በዚህ ፈጣሪውን ማወቅ ባለመቻሉ በሥነ ፍጥረት ያውቅ ዘንድ ሥነ ፍጥረትን ሰጠው፡፡ ወደ ሰማይ ተመልክቶ የሥነ ፈጥረትን ስምምነትና ሥርዓት ተረድቶ ፈጣሪውን ማወቅ ይችል ነበር፡፡ በዚህም ባይችል ሕግ በመስጠት፣ ነቢያትን በመላክ ሌላ ዕድል ሰጠ፡፡ ሰው ግን በጊዜያዊ ተድላ ደስታና በአጋንንት ምትሐት በመታለል ራሱን ወደ እውነት መምራት አልቻለም፡፡

ሰው እንዲህ ፈጣሪውን አውቆ እንዲኖር ለክብር ተፈጥሮ ሳለ ነገር ግን ከእርሱ በታች ያሉትን አስከ ማምለክ ድረስ ተዋርዶ ፈጣሪውን ማወቅ ተስኖት እንዲቀር እግዚአብሔር አልፈቀደም፡፡ ይህም ከቸርነቱ የተነሣ ነው፡፡ ስለዚህ የአግዚአብሔር ቃል ሰው በመሆን ሰውን እርሱን እንዲያውቀው አደረገ፡፡ ሰው ሆኖም “ሰው አንደ ገና ካልተወለደ” አለ፡፡ ዮሐ. 3:3፡፡ ይህም ለሁለተኛ ጊዜ የሚሆን ልደተ ሥጋ ሳይሆን ነፍስ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል እንደ ገና ካልተወለደችና ካልታደሰች ማለቱ ነው፡፡ ሰዎች አወቅን፣ ተጠበብን እያሉ ነገር ግን የጥበብ መጀመሪያ የሆነውን ፈጣሪያቸውን ማወቅ ስላልቻሉ፣ የሰው ጥበብና ዕውቀት ሰፊ ጊዜ ተሰጥቶ ተፈትኖ ስለ ወደቀ አምላክ በሚታይ ሥጋ በመገለጥ ራሱን ለሰው ገለጠ፡፡ 1 ጢሞ. 3:16 ሐዋርያው “ዓለም በጥበብዋ እግዚአብሔርን ስላላወቀች በስብከት በሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኗልና” እንዳለ፡፡ 1 ቆሮ. 1:21

ቅዱስ አትናቴዎስ ስለዚህ ጉዳይ የቃልን ሥጋ መሆን (በእንተ ተሠግዎተ ቃል) በተናገረበት ድርሳኑ ሰፋ አድርጎ በመተንተን እንዲህ ይላል፡-

“ሰዎች እግዚአብሔርን ማሰብ ትተው ለራሳቸው መዋትያን ሰዎችንና አጋንንትን አምላክ አድርገው ማምለካቸውን ባየ ጊዜ ሰውን ወዳጅ የሆነ የዓለም መድኃኒት እግዚአብሔር ወልድ ሥጋን ተዋሐደ፣ እንደ ሰውም በመመላለስ ሰው እርሱን ወደ ማወቅ እንዲመለስ አደረገ፡፡ ፍጥረትን በመፍራት ፍጥረታትን አምላክ ብለው እስኪያመልኩ ከደረሱ. የፍጥረቱ ባለቤት ሰው ሆኖ ሲመጣ ያምኑ ዘንድ፣ ሕሊናቸው ወደ ሰዎች አዘንብሎ አማልክት ናቸው እስከ ማለት ከደረሱ የእርሱን ሥራውን አይተውና ሌሎች ፍጡራን ካደረጉት ጋር አነጻጽረው ከዚያ በፊት እንደ አማልክት ያከብሯቸው ለነበሩት ሁሉ ጌታቸውና ፈጣሪያቸው መሆኑን አውቀው አምልኮታቸውን ወደ እርሱ እንዲመልሱ፣ ርኵሳን መናፍስትን ወደ መፍራት፣ ማመንና ማምለክ ያዘነበሉትንም እነዚያን ክርስቶስ ሲያባርራቸውና ሲያስወጣቸው አይተው እርሱ ብቻ አምላክ እንደ ሆነና ርኵሳን መናፍስት ግን ምንም አለመሆናቸውን እንዲረዱ ነው፡፡

“የሞቱ ሰዎችን (ሙታንን) እንደ ጀግናና እንደ አማልክት የሚያከብሩና የሚያመልኩም ቢሆኑ የጌታን ትንሣኤ አይተው የእነዚያን ሐሰትነትና ጌታችን የፍጡራን ብቻ ሳይሆን የሞት እንኳ ጌታ መሆኑንና ብቸኛው አምላክ እርሱ መሆኑን ያውቁ ዘንድ፡፡ ስለዚህ ምክንያት ጌታችን ሰው በመሆን ተገለጸ፣ የሰዎችን ሥራ ኢምንት የሚያደርግ ሥራ ሠራ፣ ሰውን በማንኛውም መንገድ ቢስት ይመልሰውና ያድነው ዘንድ፣ እውነተኛ አምላክ እርሱ ብቻ መሆኑን ያሳወቀው ዘንድ፡፡ ይህም አምላክ ሰው የሆነበት ሁለተኛው ምክንያት ነው፡፡” [1]

በአጠቃላይ እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥረው በመለኮታዊ ጸጋው አስቦለትና አዘጋጅቶለት የነበረውና በመካከል በገባ ኃጢአት ምክንያት አጥቶት የነበረው ነገር ሁሉ ተመለሰለት፣ በኃጢአት ምክንያት የመጡ ነገሮች ሁሉ ተወገዱ፡፡ 2 ቆሮ. 5:18-19  ቆላ. 1:19-24 ሮሜ. 8:1-4 2 ቆሮ. 3:18


[1] (St. Athanasius, On the Incarnation of the Word, No. 11 - 16)

Post Bottom Ad