ትምህርተ ሃይማኖት (ክፍል አንድ) - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Tuesday, October 22, 2019

ትምህርተ ሃይማኖት (ክፍል አንድ)


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ

1. ሃይማኖት፣ እምነትና መታመን

1.1  ሃይማኖት

ሃይማኖት እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጅ የገለጠው መግለጥ ነው፡፡ እግዚአብሔር ባሕርዩ ረቂቅ አኗኗሩ ምጡቅ ስለ ሆነ የሰውም ሆነ የመላእክት አእምሮ ተመራምሮ ሊደርስበትና ባሕርዩ እንዲህ ያለ ነው፣ አኗኗሩ ይህ ነው ወይም ይህን ይመስላል ሊለው የማይችል ነው፡፡ እርሱ በጊዜና በቦታ የማይወሰን ዘለዓለማዊና ምሉዕ ሲሆን ፍጥረት በሙሉ ደግሞ በጊዜና በቦታ የተወሰነ ስለ ሆነ ውስኑ የማይወሰነውን ሊያውቀውና በምርምር ሊደርስበት አይችልም፡፡

ሆኖም ግን ምንም እንኳ እግዚአብሔር ባሕርዩና አኗኗሩ በራሱ ብቻ የሚታወቅ ረቂቅ አምላክ ቢሆንም እኛ ፈጽሞ የማናውቀውና ስለ እርሱ ምንም ፍንጭ የሌለን ሆነን እንድንቀር አልተወንም፡፡ ከቸርነቱ የተነሣ ዓቅማችን ሊረዳው በሚችለው መጠን ማንነቱን፣ ህላዌውን፣ ባሕርዩን፣ መግቦቱን፣ ፈታሒነቱን፣ ፈቃዱን፣ … እናውቅ ዘንድ በተለያየ መንገድ ገልጦልናል፡፡ ሃይማኖት የሚባለው ይህ እግዚአብሔር በራሱ ፈቃድ እናውቀው ዘንድ ስለ ራሱ የገለጠው መገለጥ ነው፡፡ ስለሆነም ሃይማኖት እግዚአብሔር ራሱን ለእኛ ያሳየበት መንገድ፣ የሰው ልጅ ሊቀበለው በሚችለው መጠን ስለ ራሱ ማንነት ለእኛ የገለጠው እውነታ ነው፡፡ ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ “የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል” እንዳለ፡፡ ዮሐ. 16፡12-13

እግዚአብሔር አንድ ስለ ሆነ፣ ባሕርዩም የማይለወጥ ስለ ሆነ፣ ሃይማኖት (ይህ አምላክ ስለ ራሱ የገለጠው መግለጥ) አንድና የማይለዋወጥ ነው፡፡ ስለዚህም ሊኖር የሚችለው እውነተኛ ሃይማኖት አንድ ብቻ ነው፡፡ ብዙ ሃይማኖቶች አሉ ማለት ግን፣ ወይ እግዚአብሔር በተለያየ ጊዜ የተለያየ ነገር ይናገራል ማለትን፣ አለዚያም ደግሞ ባሕርዩ ይለዋወጣል ማለትን ያስከትላል፤ ሆኖም እነዚህ አስተሳሰቦች ለእግዚአብሔር ሊነገሩ ቀርቶ ሊታሰቡ የማይገባቸው ጸያፎች ናቸው፤ እርሱ በተለያየ ጊዜ እርስ በእርሱ የሚቃረን የተለያየ ነገር አይናርምና፣ ባሕርዩም አይለዋወጥምና፡፡ መለወጥ የፍጡር ባሕርይ እንጂ በእግዚአብሔር ዘንድ መለወጥ የለም፡፡ ስለዚህ ሃይማኖት አንድ ብቻ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት” የሚለው ለዚህ ነው፡፡ ኤፌ. 4፡5 እንዲሁም ሐዋርያው ቅዱስ ይሁዳ “. . . ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ” በማለት ሃይማኖት አንድ ጊዜ ከእግዚአብሔር ለቅዱሳን የተሰጠ መሆኑን በአጽንዖት ገልጿል፡፡
ይሁዳ 3

እንዲሁም ለሃይማኖት መታዘዝና መጠበቅ ይገባል፡፡ “የሰይጣን ዙፋን ባለበት የምትኖርበትን አውቃለሁ፤ ስሜንም ትጠብቃለህ፥ ሰይጣንም በሚኖርበት፥ በእናንተ ዘንድ የተገደለው የታመነው ምስክሬ አንቲጳስ በነበረበት ዘመን እንኳ ሃይማኖቴን አልካድህም” በማለት ሃይመኖቱን ሳይክድ በመጠበቁ አመስግኖታል፡፡ ራእ. 2፡13 ቅዱስ ጳውሎስም “መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ ሩጫን ጨርሼለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄለሁ” በማለት፤ እንደዚሁም “እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ” በማለት ሃይማትን መጠበቅ እንደሚገባ በጽኑ አሳስቧል፡፡ 2 ጢሞ. 4፡7 ዕብ. 4፡14
1.2 እምነት

እምነት እግዚአብሔር የገለጠውን እውነት (ሃይማኖት) አዎ፣ እውነት ነው፣ ትክክል ነው ብሎአሜን” ብሎ መቀበል ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚገልጠው እውነት (ሃይማኖት) በሰው መቀበል ወይም አለመቀበል ላይ የተመሠረተ አይደለም፤ ምን ጊዜም እውነት ነውና፡፡ “ባናምነው እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን ሊክድ አይችልምና” እንዳለ፡፡ 1 ጢሞ. 2፡13 እንዲሁም “የማያምኑ ቢኖሩ አለማመናቸው የእግዚአብሔርን ታማኝነት ያስቀራልን?” እንደ ተባለ፡፡ ሮሜ 3፡3

ነገር ግን ይህን እግዚአብሔር ስለ ባሕርዩ፣ ስለ መግቦቱ በአጠቃላይ እኛ ልናውቀው የምንችለውን ያህል በአባታዊ ቸርነቱ የገለጠውን እውነት (ሃይማኖት) እውነት ነው ብለን ስንቀበለው እምነት ይሆናል፡፡ ይህ ማመንም ከእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ የሚያስገኝ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሔር ከአብርሃም ዘር በመወለድ በዕፅ የተረገመውን ዓለሙን (የሰውን ልጅ በሙሉ) በዕፀ መስቀል ላይ በመሰቀል ይባርከው ዘንድ ፈቃዱ ነበር፡፡ ይኸ የማይለወጥና የማይናወጽ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይህን እውነት ለአብርሃም ሲገልጥለት፣ በዘጠና ዘጠኝ ዓመቱ ልጅ እንደሚወልድና በእርሱ ዘርም አሕዛብ ሁሉ እንደሚባረኩ ሲነግረው ሸምግያለሁ፣ ይህ እንዴት ይሆናል?’ ብሎ ሳይጠራጠር ስላመነ “አብርሃም አመነ፣ እምነቱም ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት” ተባለ፡፡ ዘፍ. 15፡3-6

እንዲሁም ይኽ እግዚአብሔር እርሱ ባወቀ በመለኮታዊ ምክሩ የወሰነው፣ አስቀድሞ ለአዳምና ለሔዋን ገና ከገነት ሲወጡ የሰጣቸው ተስፋ፣ ኋላም ለአብርሃም የነገረው ተስፋ ዘመኑ ደርሶ የሚፈጸምበት ጊዜ ሲደርስ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደ እመቤታችን ተልኮ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካላዊ ቃል በተለየ አካሉ ከእርሷ ሰው ሆኖ በግብረ መንፈስ ቅዱስ እንደሚወለድ ነገራት፡፡ ይኽ ማንም ሰው ሊለውጠው ወይም ሊያስተባብለው ወይም ሊያሻሽለው የማይችለው የእግዚአብሔር አምላካዊ ውሳኔ (ቁርጥ ሃሳብ) (ነገረ ሃይማኖት) ነው፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ይኽን ነገር ስትሰማ ነገሩ ከዚያ በፊት ያልተደረገ፣ ከዚያም በኋላ የማይሆን ስለ ሆነ ግራ ቢገባት “እፎኑ ይከውነኒ ዝንቱ እንዘ ኢየአምር ብእሴ - ወንድ ሳላውቅ ይህ እንዴት ይሆንልኛል? ብላ ጠየቀች፡፡ መልአኩም ሊያስረዳት ሞከረ፡፡ ነገር ግን ማስረዳቱ ብዙም የማያስኬድ ስለ ሆነበት “እስመ አልቦ ነገር ዘይሰአኖ ለእግዚአብሔር - ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና” ብሎ ዘጋ፡፡ እመቤታችንም ነገሩ የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነማ “ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ - አንተ እንዳልከው ይሁንልኝ፣ ይደረግልኝ” ብላ የእግዚአብሔር ቁርጥ ሃሳብና ፈቃድ እንደ ተነገራት በእርሷ እንዲፈጸም ይሁንልኝ ብላ በፍጹም እምነት ተቀበለች፡፡ ይህ በእምነት “ይኩነኒ” ብላ መቀበሏም እግዚአብሔር ቃል በማኅፀኗ በተዋሕዶ እንዲፀነሥ ምክንያት ሆኗል፡፡ የሔዋን እግዚአብሔርን አለማመን ከእግዚአብሔር መለየትንና ሞትን እንዳመጣብን የእመቤታችን ማመን ደግሞ እግዚአብሔር ባሕርያችንን ባሕርዩ አድርጎ ከእኛ ጋር እንዲሆን እና ሞትን የሚያስወግደው የሕይወት በር እንዲከፈትልን መነሻ ምክንያት ሆነን፡፡

በአንጻሩ ደግሞ ለጌታችን መንገድ ጠራጊ ይሆን ዘንድ መንፈቀ ዓመት ተቀድሞ የሚወለደው የመጥምቁ ዮሐንስን የመወለድ ነገር በተመለከተ መልአኩ ገብርዔል ካህን ለነበረው ለዘካርያስ “ዘካርያስ ሆይ፣ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ፣ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፣ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ …” ሲለው በእምነት አልተቀበለም፡፡ ሉቃ. 1፡13-17 ይልቁንም መልአኩን መልሶ “እኔ ሽማግሌ ነኝ፣ ሚስቴም በዕድሜዋ አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ? አለው፡፡ 1፡18 በእምነት ከመቀበል ይልቅ ማረጋገጫ ምልክት ጠየቀ፡፡ በዚሀም ምክንያት ተግሣፅ ደረሰበት፡፡ እምነት እግዚአብሔር የሚሠራውን ሥራ፣ የገለጠውን እውነት እንደ ዘካርያስ ሳጠራጠሩና ምልክት ሳይሹ እንደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአግባቡ ተረድቶ አሜን፣ ልክ ነው፣ ለይኩን ለይኩን ብሎ መቀበል ነው፡፡


በጸሎትና ነገረ ሃይማኖትን በሚናገሩ አንቀጾች መሀልም ሆነ መጨረሻ ላይ “አሜን” የሚለው ቃል የጸሎትና የእምነት መግለጫ ማሳረጊያ ሆኖ የሚነገረው ለዚህ ነው፡፡ ጸሎት ሲሆን ‘የተጸለየው ጸሎት ይሁንልን ይደረግልን’ ለማለት፣ የተነገረው ወይም የተነበበው ነገረ ሃይማኖት ሲሆን ደግሞ ‘አዎ፣ እኔም ይህንኑ አምናለሁ፣ የማምነው ይኸው ነው’ ለማለት ነው፡፡ ለምሳሌም ቅዱስ ጳውሎስ “ከእነርሱም (ከእስራኤላውያን) ክርስቶስ በሥጋ መጣ፣ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው፤ አሜን” ይላል፡፡ ሮሜ 9፡5 አሜን ማለቱ ከዚያ በፊት የተናገረውን - ‘ክርስቶስ ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው’ - የሚለውን አዎን፣ እውነት ነው፣ የእኔም እምነት ይኸው ነው እንደ ማለት ነው፡፡   

1.3  መታመን

መታመን ሲባል እግዚአብሔር የሰጠው ተስፋና የተናገረው ቃል ለእኔም ይሆንልኛል፣ ይደረግልኛል፣ እርሱ ያድነኛል ይመግበኛል …  ብሎ ሙሉ ተስፋንና ተአምኖን በእርሱ ላይ ማድረግ ነው፡፡ ቃሉ ከእምነት ጋር ተቀራራቢነት ያለው ቢሆንም በተለይ ግን በራሳችን ላይ የሚደርሱ ነገሮችን ለመቀበልና ለማሸነፍ በእግዚአብሔር ረዳትነትና አዳኝነት ላይ ያለንን የእምነት መጠን የሚገልጽ ነው፡፡ ለምሳሌም ሠለስቱ ደቂቅ በፊታቸው አስፈሪ የሆነ እሳት እየተንቀለቀለ እያዩ “የምናመልከው አምላካችን ከሚነደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፣ ከእጅህም ያድነናል፣ ንጉሥ ሆይ፣ እርሱ ባያድነን አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምከውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ” ብለው ወደ እሳቱ እስከ መግባት ደርሰው በእርሱ ታምነዋል፡፡ ዳን. 3፡16-18

“ባያድነን እንኳ” ማለታቸው አዳኝነቱን ወይም የሚያድን መሆኑን የመጠራጠር ሳይሆን አንደኛ የእግዚአብሔር ፈቃድ እነርሱ በሰማዕትነት ሞተው እንዲያከብሩት ይሁን ወይም ሌላ ስላላወቁ፣ ሁለተኛ ደግሞ በኃጢአታቸው ምክንያት ሳያድናቸው ቢቀር ያላዳናቸው እርሱ ማዳን ስለማይችል ሳይሆን በእነርሱ ለማዳኑ የበቁ አለ መሆን ምክንያት ስለሚሆን ነው፡፡ ሆኖም አረማዊው ንጉሥ ናቡከደነፆር ይህን ሁሉ ቢነግሩት ስለማይገባው “ባያድነን እንኳ” የሚል ጨመሩለት፤ ከእሳቱ ባያድናቸው አምላካቸውን እግዚአብሔርን ማዳን የማይችል አድርጎ እንዳይረዳ ለጥንቃቄ የተናገሩት ነገር ነው፡፡ ስለዚህ መታመን ሁለንተናችንን በእግዚአብሔር አዳኝነትና አባትነት ጥላ ሥር ማሳረፍ ነው፡፡    

1.4 ሃይማኖት እንዴት ተገኘ?

ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ፡፡ይሁዳ 3

ሃይማኖት፡-

1)     የተሰጠ፣ የተቀበልነው ነው፡፡

እግዚአብሔር ሃይማኖትን ሰጠ፣ እኛ ደግሞ ተቀበልን፡፡ የእኛ ድርሻ መቀበል ነው፡፡ የሰው ልጅ ሃይማኖትን ይቀበላል እንጂ ሃይማኖትን ሊሠራ ወይም ሊያሻሽል አይችልም፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፣ እነርሱም ተቀበሉት፡፡” በማለት የገለጸው ይህን ነው፡፡ ዮሐ. 17፡8

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ያመነውንና የያዘውን ሃይማኖት ከጌታ የተቀበለው መሆኑንና፣ ያን የተቀበለውንም በወንጌል ትምህርት እንዳወረሳቸው ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሲያሳስባቸው እንዲህ በማለት ገልጾላቸዋል፡- “ወንድሞች ሆይ፣ የሰበክሁላችሁን፣ ደግሞም የተቀበላችሁትን፣ በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን፣ በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤ … እኔ ደግሞ  
የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ፡፡” 1 ቆሮ. 15፡1-3 እንዲሁም ስለ ምሥጢረ ቁርባን ባስተማረበት አንቀጽ ላይ “ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ደግሞ ከጌታ ተቀብያለሁና…” ብሏል፡፡ 1 ቆሮ. 11፡23

ወልድ ዋሕድ መድኃኒታችንም “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል?ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም፡- “አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎችም ኤልያስ፣ ሌሎችም ኤርምያስ፣ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት፡፡ እርሱም፡- እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው፡፡ ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ፡- አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ፡፡ ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፡- የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፣ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ፡፡ እኔም እልሃለሁ፣ አንተ ጴጥሮስ ነህ፣ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፣ የገሃነም ደጆች አይችሏትም፡፡” ማቴ. 16፡13-18

በሥጋና ደም አስተሳሰብ (በሰው ምርምርና ሐተታ) ሰዎች ስለ ጌታችን ሊሉት የሚችሉት ያን ጊዜ የነበሩት ሰዎች እንዳሉት ‘መጥምቁ ዮሐንስ፣ ወይም ኤልያስ ወይም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው’ ከማለት ያለፈ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ሰው ሆኖ እያዩት አምላክነቱን መረዳት በሥጋና በደም አስተሳሰብ ሊደረስበት የሚችል ምሥጢር አይደለምና፡፡ ጴጥሮስ ግን የወልድ ዋሕድ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰማያዊ አባቱ አብ የገለጠለትን ነገር - የኢየሱስ ክርስቶስን የአብ የባሕርይ ልጅነት - ስለ ተናገረ ጌታችን አመሰገነው፤ “ስምዖን ሆይ፣ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ” አለው፡፡

መቼም ቢሆን በሃይማኖት እግዚአብሔር የገለጠውን ትተን በራሳችን አስተሳሰብና በሚመስለን መንገድ እንሂድ ካልን ወደ እውነተኛው ሃይማኖት ልንደርስ አንችልም፡፡ በሐዋርያት ዘመን ከነበሩት ዓይነት ሰዎች የተሻለ ነገር ልንል አንችልም፡፡ ከዚያ ለመውጣትና ጴጥሮስ የመሰከረውን ለመያዝ ከሥጋና ከደም አስተሳሰብ መለየት የግድ ይላል፡፡ ጌታችን “ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው፡፡” ያለው ለዚህ ነው፤ ስሙንም፣ ማንነቱንም ሊገባን በሚችለው መጠን የገለጠልን ራሱ ነው እንጂ ሃይማኖት የሰው ልጅ በምርምር የደረሰበት ግኝት አይደለም፡፡ ዮሐ. 17፡6

1)     ሃይማኖት የተሰጠው አንድ ጊዜ ነው - ለቅዱሳን

ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት  … ” ይሁዳ 3

ምግብናው እንደየ ዘመኑ ይለያያል፣ ይዘቱ ግን ያው አንድ ነው፡፡ ለምሳሌ ሕፃን ልጅ በሕፃንነቱ ወተትና ፍትፍትሲያድግ ደግሞ ጠንከር ያለ ምግብ ይሰጠዋል፣ የሰውነት ባሕርዩ ግን ያው አንድ ነው፣ አይለዋወጥም፡፡ ሃይማኖትም በዘመነ አበው፣ በዘመነ ኦሪት፣ በዘመነ ወንጌል የምግብናው ሁኔታ እንደየ ዘመኑሰዎችመረዳት ዓቅምና ሁኔታ ቢለያይም ይዘቱ (ጭብጡ) ግን ያው አንድ ነው፡፡ “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዘመናትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን  ያለው ይህን የሚገልጽ ነው፡፡ ዕብ. 11-2 የቅዱሳን መላእክት፣ የአበው ቀደምት የእነ አዳም፣ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሙሴ፣ ዳዊት፣ የነቢያት፣ ኋላም የሐዋርያትና የሰማዕታት፣ የጻድቃንና የሊቃውንት ሃይማኖት አንድ ነው፡፡

ስለዚህ ሃይማኖት የተሰጠው አንድ ጊዜ፣ ያውም ፈጽሞ (ያለ መቀናነስና ያለ ቀረኝ) ስለ ሆነ ተሐድሶ ወይም ለውጥ አያስፈልገውም ማለት ነው፡፡ ሃይማኖትን ይቀበሉታል፣ ይጠብቁታል፣ ያወርሱታል እንጂ ላድሰው፣ ላሻሽለው አይባልም፤ እንዲያ ከሆነ መጀመሪያ የተሰጠው ሃይማኖት ሕፀፅ ነበረበት፣ ወይም ምሉዕ አልነበረም ያሰኛል፡፡ እግዚአብሔር የሰጣት፣ አባቶቻችን ከእርሱ ተቀብለው ኖረውባት ለእኛ ያወረሱን ሃይማኖት ግን ፍጽምትና አንድ ጊዜ የተሰጠች ናት፡፡ ብልየት እርጅና የለባትም፣ ተሐድሶ ወይም ማደስ የሚለው ቃል ብላሽና ለሃይማኖት ሊነገር የማይችል ጸያፍ ነው፡፡

1)     ሃይማኖት ተጋድሎ ያስፈልገዋል

በሃይማኖት ተጋድሎ የሚያስፈልገው በተሰጠን ሃይማኖት ለመጠቀም እና ለመጠበቅ ነው፡፡ ጌታችን ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው፡፡ የአንተ ነበሩ፣ ለእኔም ሰጠሃቸው፤ ቃልህንም ጠብቀዋል፡፡ ያለው ቃሉን መቀበል ብቻ ሳይሆን መጠበቅም እንደሚገባ ሲነግረን ነው፡፡ ዮሐ. 176 የተሰጠንን አጽንቶ ለመያዝና የሕይወትን አክሊል ለማግኘት እስከ ሞት ድረስ መጋደልና ታማኝነትን በተግባር ማስመስከር የግድ ይላል፤ ኩን መሃይምነ እስከ ለሞት ወእሁበከ አክሊለ ሕይወት - እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን፣ የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ ተብሏልና፡፡ ራእ. 210

እንዲሁም በሃይማኖት ለመጠቀምም ተጋድሎ ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁ በማመን ብቻ መጠቀም አይቻልም፤ ባመኑት ለመጠቀም ተጋድሎ ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እስራኤላውያን በደብረ ሲና ከራሱ ከእግዚአብሔር፣ ኋላም ከሙሴ በተደጋጋሚ የእግዚአብሔርን ቃል በጆሯቸው ቢሰሙም በሰሙት ለማመንና ባመኑትም ለመጠቀም ጥረት ስላላደረጉና ስላልተጋደሉ እንዳልተጠቀሙ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፡- የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም፡፡ዕብ. 42

ስለዚህ፡-

ሃይማኖትን
ü  ይቀበሉታል፣
ü  ይጠቀሙበታል
ü  ይጠብቁታል
ü  ያወርሱታል

እንጂ ማደስ፣ ማሻሻል በሃይማኖት የለም፡፡

2. ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ ማወቅ እንችላለን?

·        በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን ማንም አያውቅም፡፡” 1 ቆሮ. 211-12 
·        ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፣ ከወልድም በቀር፣ ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም፡፡ማቴ. 1127
·        በፈጣሪና በፍጡር መካከል መጨረሻ የሌለው ሸለቆ (ጥልቀት) አለ፡፡. ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ
·        በፈጣሪና በፍጡር መካከል ማንም ሊያልፈው የማይችለው ክፍተት አለ፡፡. ኤፍሬም ሶርያዊ

ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናንዙ ጥልቅ ነገረ መለኮታዊ ትምህርቶችን ባስተማረባቸው በአምስቱ ተከታታይ ትምህርቶቹ (Theological Orations) ላይ ስለዚህ ጉዳይ እንዲህ ይላል፡-

  • “እግዚአብሔር በባሕርዩ ማን እንደ ሆነ እስካሁን ማንም ሰው አላየውም አላወቀውም፣ ወደፊትም ሊያውቀው አይችልም፡፡ በእምነቱ የጸደቀውና እንግዳ መሥዋዕት ያቀረበው ታላቁ አባት አብርሃም እንኳ እንደ ሰው ሆኖ ለተገለጠለት ለእርሱ የሚበላ አቀረበለት እንጂ እግዚአብሔርን እንደ እግዚአብሔርነቱ አላየውም፡፡ የተመሰገነው የእግዚአብሔርን ባሕርይ ስለ መረመረ ሳይሆን እግዚአብሔርን በእምነት ስላመለከ ነው፡፡ ያዕቆብም መላእክት የሚወጡበትና የሚወርዱበት ታላቅ መሰላል አየ፣ በመሥጢራዊ ሁኔታም ድንጋይን በዘይት ቀባ (ይህም ስለ እኛ በተዋሕዶ የሚከብረውን ዓለት - ክርስቶስን የሚያመለክት ነበር)፣ ቦታውንም ቤቴል - የእግዚአብሔር ቤት - ብሎ ሰየመው፤ እንደ ሰው ሆኖ ከተገለጠለት አምላክ ጋርም ታገለ፣ በሰውነቱም የመታገሉን አሻራ (ምልክት) ተሸከመ፣ በዚህም ስሙ ከያዕቆብነት ታላቅና ገናና ወደ ሆነው ስም - ወደ እስራኤልነት - ተለወጠ፡፡ ሆኖም እርሱም ሆነ ከዘሩ ማንም እግዚአብሔርን በእግዚአብሔርነቱ ፊት ለፊት አላዩትም፡፡ ታላቅነቱ ይታወቅና ይለጥ ዘንድ በእሳት ሠረገላ ወደ ሰማያት የተወሰደው ኤልያስም በብርቱው ነፋስም ሆነ በምድር መናወጡ፣ እንዲሁም በእሳቱ ውስጥ እግዚአብሔር አልነበረም፡፡ ከዚያ ተከትሎ በሆነው በትንሽ የዝምታ ድምፅ ውስጥ የእግዚአብሔርን መገለጥ አመለከተው፣ ‘ኤልያስ ሆይ፣ በዚህ ምን ታደርጋለህ?’ የሚል ድምፅም ወደ እርሱ መጣ፤ ባሕርዩን [ያመለከተው] ግን አልነበረም፡፡ 1 ነገ. 19፡11-13 የሶምሶን አባት ማኑሄ የእግዚአብሔርን መልእክተኛ (መልአክ) በማየቱ ብቻ እንኳ እግዚአብሔርን ማየት ይቅርና መልእክተኛውን ማየት እንኳ በሰዎች ዘንድ የሚቻል አይደለም ብሎ በማሰብ ‘እግዚአብሔርን አይተናልና ሞትን እንሞታለን’ እስከ ማለት ደረሰ፡፡ መሣ. 13፡22”

(ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናንዙ፣ አምስቱ ተከታታይ ነገረ መለኮታዊ ትምህርቶች)

ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ደግሞ እንዲህ ይላል፡-

  • “መለኰታዊና ቅዱስ የሆነው ሕይወት [እግዚአብሔር] መለኪያና ስፍር የሌለው የመሆኑ ነገር ለማንኛውም ሰው ግልጽ ሊሆን ይገባዋል፡፡ እርሱ በጊዜ ውስጥ የሚኖር አይደለምና፣ ጊዜ ራሱ የተገኘው ከእርሱ ነው እንጂ፡፡ ፍጥረቱ ሁሉ ግን ከታወቀ መጀመሪያው ወደ ታወቀ ፍጻሜው ይሄዳል፣ በመካከልም በጊዜ በሚለኩ ሂደቶች ውስጥ ያልፋል፤ ስለዚህም ሰሎሞን እንዳለ (ጥበብ 7፡18) ለፍጥረታት መጀመሪያውን፣ መካከለኛውንና መጨረሻውን መለየት ይቻላል፡፡ ሩቅና ምጡቅ፣ ዘለዓለማዊና ቅዱስ፣ ሕያወ ባሕርይ ለሆነው ለእርሱ ግን ስፍርም ሆነ ቦታ የለውም፡፡ የተፈጠሩ ነገሮች ሁሉ ምንም እንኳ የሰው አእምሮ ውስንነት ሊደርስባቸው ላይችል ቢችልም እንኳ በፈጠራቸው በእርሱ ዘንድ የታወቁና የተሰፈሩ፣ በሥነ ፍጥረት ሀልወት ክበብ ውስጥ የታጠሩ ናቸው፡፡ ለተፈጠሩት ነገሮች ሁለ ዳርቻቸውንና ወሰናቸውን ያስቀመጠላቸው ፈጣሪ እርሱ ግን ገደብና ወሰን የለበትም፣ ወሰን ወደ ሌለው ወደ እርሱ አኗኗር የሚደረጉ ፍለጋዎችንና የመለኰታዊ ባሕርይን ጥንት ምንነትና የትመጣነት ለመመርመር ከፍ ከፍ ብለው ሊወጡ የሚሞክሩትን አስተሳሰቦች ሁሉ እጅግ ይረቅባቸዋል፣ ባለመደረስ ውስጥም ይዘጋቸዋል፡፡ የጊዜን ድንበር በመሻገር በፈጣሪና በፍጡራን መካከል ካለው ባሕርያዊ ክፍተት (diastēma) አልፎ ለመሄድ የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ ሁሉ ክፍተት ሊታለፍ የማይቻል መሆኑን ከሚያይበት ደረጃ ላይ ብቻ ይደርሳል፤ የሰው አእምሮና ሃሳብ መለኪያውና ወሰኑ ጊዜ (ho aiōn) እና በእርሱ ውስጥ ያለው ሌላው ነገር ሁሉ ነው፡፡ እነዚህን የሚያልፍ (ከእነዚህ ውጭ) የሆነ ነገር ሁሉ ለሰው አእምሮ ከዓቅሙ በላይና ሊደረስበት የማይችል ይሆንበታል፡፡

  • “የተፈጠረ ነገር ሁሉ አኗኗሩ (ህልውናው) በጊዜ እና በቦታ የተወሰነ ነውና፡፡ ዘለዓለማዊ በሆነው ህልውና ዘንድ ግን ጊዜም ሆነ ቦታ የለም፣ ራሱ ከራሱ ነው፣ ከእነዚህ በፊትና ውጭ ነው፣ በጊዜ የማይለካ ነው፣ ያለፈ እና የወደፊት በሚባሉ የጊዜ ጽንሰ ሃሳቦች የማይከፈል ነው፣ በእምነት ብቻ ልንረዳው የምንችለው ነው፡፡ ጊዜ ነክ የሆኑ ልምዶች በፍጥረት ውስጥ ላሉ ነገሮች ብቻ የሚሠሩና የሚኖሩ ናቸው፡፡ ሁሉ ነገር ዛሬ ለሆነለት ለዚያ ቅዱስና ገናና ህልውና ግን ያለፈውና የወደፊቱ በአንድ አምላካዊ የእውቀት ቅጽበት ጥላ ሥር ናቸው፡፡ . . . ከመጀመሪያ ሁሉ በላይ፣ ከጊዜ ውጭ የሆነው ህልውና እርሱ ለባሕርዩ ፍለጋ የለውም፣ የሚታወቀው ባሕርዩ ሊታወቅ የማይችል በመሆኑ ብቻ ነው፡፡”

(ቅዱስ ጎርርዮስ ዘኑሲስ፣ በእንተ ዩኖሚየስ፣ መጽሐፍ 1፣ ገጽ 36-37)

የእግዚአብሔርን ባሕርይ ማወቅን በተመለከተ ስለ መላእክት ሲናገርም እንዲህ ብሏል፡-

  • “የመላእክት ኃይል ከእኛ ጋር ሲነጻጸር በማንኛውም መንገድ የበለጠ ሆኖ ይታያል፡፡ ሆኖም ሕያወ ባሕርይ ከሆነው ከእርሱ ገናናነት ጋር ሲነጻጸር ግን የእነርሱ ታላቅነት እንኳ ከእኛ የእውቀትና የመረዳት ታናሽነት (ደካማነት) ያንም ያህል የበለጠ አይደለም የሚል ቢኖር ከእውነት የራቀ ነው ሊባል አይቻልም፡፡ በፈጣሪና በፍጡራን መካከል ካለው ባሕርያዊ ርቀት (diastēma) ለእኛም ሆነ ለመላእክት የእግዚአብሔርን ባሕርይ በቀጥታ ለማወቅ የማይቻል ያደርግብናል፡፡ ቀንን ከኋላውና ከፊቱ እንደሚወስኑት ሁለት ሌሊቶች ፍጡራንን ከፊታቸውና ከኋላቸው ይወስናቸዋል፡፡ ጊዜና ቦታ ፍጡራንን ሊያልፉት በማይችሉት ወሰን ይከብባቸዋል፡፡ የሥነ ፍጥረትን መሪነት ልንከተል የምንችለው እስከዚያ ድንበር (መዳረሻ) ድረስ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ላይ ግን የሰው አእምሮ ያቆማል፡፡ የፈጣሪ ባሕርይ ከፍጥረቱ ሁሉ ሕሊና በላይ ነውና፣ መጀመሪያና መጨረሻም የለውምና፣ ከፍጥረት ውስጥ ተነሥቶ በሚደረግ ፍለጋና ጉዞም ሊደረስበት አይችልምና፡፡” 

(ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ፣ ለዩኖሚየስ ሁለተኛ መጽሐፍ የተሰጠ መልስ)

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም እንዲህ ይላል፡-

  • “ብዙ የማውቃቸው ነገሮች አሉ፣ ሆኖም እንዴት ላብራራቸው (ልገልጻቸው) እንደምችል ግን አላውቅም፡፡ እግዚአብሔር በሁሉም ቦታ እንዳለ (ምሉእ በኩለሄ እንደሆነ) አውቃለሁ፡፡ ሆኖም እንዴት ብሎ በሁሉም ቦታ እንደሚኖር ግን አላውቅም፡፡ ዘለዓለማዊ እንደ ሆነና መጀመሪያ እንደ ሌለው አውቃለሁ፤ እንዴት እንዲህ እንደ ሆነ ግን አላውቅም፡፡ አንድ በራሱ ህልው የሆነ ሕያው ህልውናውን ከሌላም ሆነ ከራሱ ሳይቀበል እንዴት ሊኖር እንደሚችል አእምሮዬ ለመረዳት አይቻለውም፡፡ እርሱ የባሕርይ ልጅ እንዳለው አውቃለሁ፣ እንዴት እንደ ሆነ ግን አላውቅም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከእርሱ እንደ ሠረጸ አውቃለሁ፣ መንፈስ ቅዱስ እንዴት ብሎ ከእርሱ እንደ ሆነ ግን አላውቅም፡፡

  • “ዳዊት የእግዚአብሔርን ባሕርይ ማወቅን በተመለከተ ባሰበ ጊዜ ማለት የቻለው ‘እውቀትህ ከእኔ ይልቅ ተደነቀች በረታች፣ ወደ እርሷም ለመድረስ አልችልም’ ነው፡፡ መዝ. 138፡6 ነቢዩ ኢሳይያስ የእግዚአብሔርን ልደት መናገር የሚችል አለመኖሩን በማድነቅ ‘ወመኑ ይነግር ልደቶ - ልደቱን ማን ሊናገር ይችላል?’ በማለት በአግራሞት ይጠይቃል፡፡ ኢሳ. 53፡8 ቅዱስ ጳውሎስም የእግዚአብሔር ፍርዱ የማይመረመር፣ ለመንገዱም ፍለጋ የሌለው መሆኑን በማድነቅ ይናገራል፡፡ ሮሜ 11፡33 እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ያዘጋጀው ሽልማት የማይመረመር ነው (ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው፣ በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንደ ተጻፈ፡፡ 1 ቆሮ. 2፡9)፤ የእግዚአብሔር ሰላም አእምሮን ሁሉ ያልፋል (ፊል. 2፡9)፤ ስጦታውም ሊነገር አይችልም (2 ቆሮ፣ 9፡15)፡፡

  • ታዲያ የእግዚአብሔር ፍርዱ የማይመረመር፣ መንገዱ ፍለጋ የሌለው፣ ሰላሙ አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ፣ ስጦታው ሊነገር (ሊገለጽ) የማይችል፣ ለሚወዱት ያዘጋጀው ነገር በሰዎች ልቡና ያልታሰበ ከሆነ እነዚህ ከእርሱ የሚገኙት ነገሮች የማይመረመሩና የማይደረስባቸው ከሆኑ እነዚህን ያዘጋጀው ራሱ እግዚአብሔርማ ምን ያህል የማይመረመር ነው ይሆን! መናፍቃን ሆይ፣ የተፈጠሩት የማይታወቁ፣ የማይለጹና የማይመረመሩ ሲሆኑ እነዚህን የፈጠራቸው እርሱ ግን ይታወቃል፣ ይመረመራል ከማለት በላይ ምን እብደት አለ?  

  • “መላእክት በእግዚአብሔር መገለጥ ፊት ሲቆሙ ፊቱን እንኳ ማየት የማይችሉ ከሆነ ‘እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ ላውቀው እችላለሁ’ ይል ዘንድ ሰው ማን ነው? . . . ወገኖቼ ሆይ፣ አርዮሳውያንን (አኖሚያኖችን) አእምሯቸው የታመመና የማሰብ ዓቅማቸውን በሕመም ያጡ ሰዎችን እንደምታዩ አድርጋችሁ ልትመለከቷቸውና ልታዝኑላቸው ይገባል፡፡ እግዚአብሔርን በባሕርዩ ላውቀው እችላለሁ ማለት ከአእምሮ መታወክ እንጂ ከጤና የሚመጣ አይደለምና፡፡”

(ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም፣ ስለ መለኮታዊ ባሕርይ አይመረመሬነት)


አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም እንዲህ ይላል፡-

}  “. . . ወኢርቱዕ እንከ ናስተማስሎ በእሳት ምድራዊ እሳትሰ ቦቱ መጠን ወቦቱ አካል ወመለኰትሰ ኢይትከሃል ይትበሃል ዘንተ የአክል ወዘንተ ይመስል - በምድራዊ እሳት እንመስለው ዘንድ አይገባም፣ ለእሳትስ መጠን አለው፣ ልክም አለው፡፡ መለኰት ግን ይህን ያህላል፣ ይህንም ይመስላል ሊባል አይቻልም፡፡” ቁ. 47
}  “አኮ ዘቦቱ ለመለኮት ክበብ ከመ ፀሐይ ወወርኅ ወዐቅም ከመ ሰብእ አላ መንክር ውእቱ ወንቡር ዲበ አርያሙ ኀበ ኢይበጽሖ ሕሊና ሰብእ ወኢዘመላእክት አእምሮ - ለመለኮት እንደ ፀሐይና እንደ ጨረቃ ክበብ፣ እንደ ሰውም መጠን ያለው አይደለም፣ ድንቅ ነው እንጂ፤ የሰው ሕሊና የመላእክትም አእምሮ በማይደርስበት በአርያሙ የሚኖር ነው እንጂ፡፡” ቁ. 48

}  “ወሶበ እኄሊ ዘንተ ይፈቅድ ሕሊናየ ይጽብት ዕመቀ አብሕርቲሁ ለወልድኪ ወያመዐብሎ መዋግደ ምሥዋራቲሁ ለፍቁርኪ ወሶበ እሔሊ ዘንተ ካዕበ ይፈቅድ ሕሊናየ ይዕርግ ላዕለ ወይጻእ በሥውር ወይቅላዕ መንጦላዕተ ምሥዋራቲሁ ለሕያው ወይፈርህ እምነደ እሳት ወኢይበጽሕ እስከ መጠነ መንፈቆሙ ለዐየራት - ይህንም ባሰብኩ ጊዜ ሕሊናየ የልጅሽን የባሕሩን ጥልቅነት ሊዋኝ ይወዳል፣ የወዳጅሽ የመሠወሪያው ማዕበልም ያማታዋል፡፡ ዳግመኛም ባሰብሁ ጊዜ ሕሊናየ ተሰውሮ ወደ ላይ ወጥቶ የሕያው መሠወሪያ የሆነውን ሊገልጥ ይወዳል፣ ከነደ እሳትነቱ የተነሣ ይፈራል፣ ከዐየራት ከእርቧቸው እርቦ አይደርስም፡፡ 

}  “ወሶበ እሔሊ ዘንተ ይፈቅድ ሕሊናየ ይጸዐን መትከፈ ነፋሳት ወይስርር ምሥራቀ ወምዕራበ ሰሜነ ወደቡበ ወውስተ ኩሉ አጽናፍ ይርአይ ህላዌሆሙ ለፍጡራን ወይመጥን ዕመቃቲሆሙ ለአብህርት ያእምር ሉዐሌሁ ለሰማይ ወየአይይ እንተ በኩለሄ ወበኩሉ ይስእን ወይገብእ ኀበ ዘትካት ሉዐሌሁ - ይህንም ባሰብሁ ጊዜ ሕሊናየ በነፋስ ትካሻ ተጭኖ በምሥራቅና በምዕራብ በሰሜንና በደቡብ በዳርቻውም ሁሉ ሊበር ይወዳል፡፡ የፍጡራንን አኗኗር ያይ ዘንድ፣ የአብሕርትንም ጥልቀታቸውን ይለካ ዘንድ የሰማይ ርዝመቱን ያውቅ ዘንድ በሁሉ ዘንድ በሁሉም ይዞራል፣ አቅቶት ወደ ቀደመ አኗኗሩ ይመለሳል፡፡

}  “ወይእዜኒ ኢንኅሥሥ ዕበያቲሁ ወኢንጠናቀቅ ማዕምቅቲሁ ዘኢይክል ልሳነ ነቢያት ወሐዋርያት ለወድሶተ መጠነ ዕበዩ - አሁንም ገናንነቱን አንመርምር፣ ጥልቅነቱንም አንጠናቀቅ፣ የገናንነቱን መጠን ለማመስገን የነቢያትና የሐዋርያት አንደበት የማይቻለው ነው፡፡”

(ቅዳሴ ማርያም፣ ቁ. 44-87)

ይህ አይመረመሬነቱና አይደረሴነቱ ግን የባሕርዩን አለመታወቅ በተመለከተ እንጂ እግዚአብሔር ከማኛውም ነገር በላይ ለፍጥረቱ ቅርብና የፍቅር አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔር በባሕርዩ ሩቅና ምጡቅ፣ ማንም ፍጡር መርምሮ ሊደርስበት መቸም መች የማይቻለው (Transcendent) ሲሆን በፍቅሩ ደግሞ የቅርብ አምላክ (Immanent) ነው፡፡ ሰው ሆኖ በእኛ ባሕርይ የተገለጠ፣ የደቀ መዛሙርቱን እግር እስከ ማጠብ፣ በመስቀል መራራ ሞትን ስለ እኛ እስከ መሞት ደርሶ ፍቅሩን የገለጠ ትሑት የፍቅር አባት ነው፡፡
 
ሙሴም እግዚአብሔርን እባክህ ክብርህን አሳየኝ አለው፡፡እግዚአብሔርም፡- ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም አለ፡፡ እነሆ ስፍራ በእኔ ዘንድ አለ፣ በዓለቱም ላይ ትቆማለህ፤ ክብሬም ባለፈ ጊዜ በሰንጣቃው ዓለት አኖርሃለሁ፣ እስካልፍ ድረስ እጄን በላይህ እጋርዳለሁ፤ እጄንም ፈቀቅ አደርጋለሁ፣ ጀርባዬንም ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም፡፡ዘጸ. 3317-23

ይህን ታላቁ ሊቅ ነባቤ መለኮት ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናንዙ እንዲህ ተርጉሞታል፡-

  • ፊት - የተባለ ባሕርዩ ነው፡፡ “ፊቴ አይታይም” ማለቱ ሰው የእግዚአብሔርን ባሕርይ ሊደርስበት የማይችል መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡  

  • ጀርባ - የተባለው ምንም እንኳ አንድን ነገር በትክክል ለማወቅ የሚያስችለው ፊቱን ማየት ቢሆንም፣ ይህ ካልሆነ ደግሞ ጀርባውን ማየት ከምንም የሚሻል መጠነኛ ግንዛቤ ለማግኘት ይረዳል፡፡ ስለዚህ ፊት የተባለ ባሕርዩን ማወቅ ባንችልም ጀርባ የተባለ ስለ እርሱ ለማወቅ የሚረዱ ነገሮችን ሰጥቶናል ማለት ነው፤ “ጀርባዬን ታያለህ” ማለት ይህ ነው፡፡    
  
 ስለዚህ የምናውቀው ባሕርዩን ሳይሆን ኃይሉንና ሥራውን ነው ማለት ነው፡፡

እግዚአብሔር የተገለጠባቸው (እርሱን የምናውቅባቸው) መንገዶች፡-
በክፍል ሁለት ይጠብቁን.…

Post Bottom Ad