ጥቅምት 9 - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Tuesday, October 22, 2019

ጥቅምት 9


+" ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ "+
✞✞✞ ደጉ ሐዋርያ ቅዱስ ቶማስ ከኢትዮዽያ እስከ ሕንድና ባርቶስ በደረሰች ስብከቱ እጅግ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን ሠርቷል:: 'አሐደ እምተአምራቲሁ' እንዲሉ አበው ከእነዚህ ዛሬ አንዱን እንመለከታለን::
+ቅዱስ ቶማስ ጐና ወደምትባል የሕንድ አውራጃ መግቢያ ፈሊጥ ቢያጣ ጌታ ወርዶ አበኒስ ለሚባል ነጋዴ ባሪያ አድርጐ ይሸጠዋል:: በመጀመሪያ በንጉሡ ሠርግ ቤት ውስጥ ተአምራትን አሳይቶ ሕዝቡን ከነ ሙሽሮቹና ንጉሣቸው አሳምኗል::
+ቀጥሎ ግን ጎንዶፎር ለሚባል ሌላ ንጉሥ 'ቤተ መንግስት ሥራ' ተብሎ ይላካል:: ሐዋርያውም ንጉሡን "የማንጽበትን ወርቅና ብር ስጠኝ" ብሎት ይሰጠዋል:: ንጉሡ ዘወር ሲል ግን "ወእሁብ ዘንጉሥ ለንጉሥ-የምድራዊው ንጉሥ ለሰማያዊው ንጉሥ እሰጣለሁ" እያለ ገንዘቡን ሁሉ ለነዳያን በተነው::
+ገንዘቡ ሲያልቅበት "ንጉሥ ሆይ! መሠረቱ ታንጿልና ለግድግዳው ላክልኝ" ይለዋል:: ሲልክለት ይመጸውተዋል:: አሁንም "ንጉሥ ሆይ! ለጣሪያው ላክልኝ" ይለውና ይመጸውተዋል:: መጽሐፍ እንደሚል ምጽዋት ለሐዋርያው ልማዱ ነውና::
+በመጨረሻ ግን ንጉሡ ሲመጣ ባዶ መሬት ላይ ነዳያን ገንዘቡን ሲበሉት አገኘ:: ተበሳጭቶም ቅዱስ ቶማስን ይገድለው ዘንድ አሠረው:: በዚያች ሌሊት ግን የንጉሡ ወንድም ጋዶን ሙቶ ሐዘን በሆነ ጊዜ ሐዋርያው አስነሳው::
+ጋዶንም ለቅዱሱ ሰግዶ በሰማይ ለንጉሥ ጐንዶፎር ትልቅ ቤት ታንጾ ማየቱን ተናገረ:: ንጉሡና ሠራዊቱም በፊቱ ሰግደው አመኑ:: አጥምቋቸውም ሔዷል::
+" ቅዱስ እስጢፋኖስ ካልዕ "+
+በዚህ ስም ከሚጠሩ ቅዱሳን ሊቀ ዲያቆናቱ ቅድሚያውን ሲይዝ ዛሬ የምናከብረው ቅዱስ ደግሞ 'ካልዕ እስጢፋኖስ' (ሁለተኛው) ይባላል:: 2ቱም 'ቀዳሜ ሰማዕት' ይባላሉ:: ዋናው በሐዋርያት ዘመን ቀድሞ እንደተሰዋ ሁሉ ሁለተኛው በዘመነ ዲዮቅልጢያኖስ ርጉም ቀድሞ ተሰይፏል::
+ቅዱሱ የተወለደው በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን አጋማሽ ሲሆን በአንጾኪያ ቤተ መንግስት ውስጥ ከነበሩ ልዑላንና የጦር መሪዋችም አንዱ ነበር:: በዝምድና ደረጃም የታላቁ ቅዱስ ፋሲለደስ የእህቱ ልጅ ነው:: በቤተ ፋሲለደስ ከማደጉ የተነሳም የእርሱ ልጅ እንደ ሆነ በገድሉ ተጠቅሷል::
+ቅዱስ እስጢፋኖስ ካልዕ ማለት መልክ ከደም ግባት የተባበረለት: ጾምና ጸሎትን የሚወድ: የነዳያን አጉራሽ: ኃያል የጦር ሰውና ተወዳጅ ክርስቲያን ነው:: ያ ክፉ አውሬ በዓለም በሚገኙ ምዕመናን ሁሉ ላይ ሞትና ስቃይን ሲያውጅ በአካባቢው የነበረ ይኼው ቅዱስ ነው::
+በቦታው ከነበሩ ብዙ ሺህ ሰዎች ንጉሡን ደፍሮ የተናገረው አንድም አልነበረም:: ቅዱስ እስጢፋኖስ ግን ለክርስቶስ ቀና:: ከሕዝቡ መካከልም እየሮጠ አልፎ በንጉሡ ፊት አዋጅ የሚያነበውን ወታደር ቀማውና በአደባባይ ያችን የክህደት ደብዳቤ ቦጫጭቆ ጣላት::
+ንጉሡንም "ሰነፍ" ሲል ገሠጸው:: እጅግ የተቆጣው ንጉሡ ግን ቅዱሱን በሰይፍ ሰንዝሮ ከ2 ከፈለው:: አካሉ መሬት ላይ ሲወድቅ ራሱ ግን በዓየር ላይ ሁና ለ3 ቀናት ትንቢትን ተናገረች:: ለዚያ አስጨናቂ የመከራ ዘመንም በር ከፋቹ ቅዱስ እስጢፋኖስ ካልዕ ሆነ::
+" ቅዱስ አትናስዮስ ብጹዕ "+
+ይህ ቅዱስ አባት ደግሞ ባለ አስደናቂ ታሪክ ነው:: ዜና ሕይወቱ ሲሰማ ጣዕመ ነፍስን ያድላል:: ተወልዶ ባደገባት ሶርያ በመናኝነቱ የሚታወቀው ቅዱስ አትናስዮስ ሕይወቱ በጽሙና የተሞላ ነበር:: በገዳም ገብቶም በዓት ለይቶ ሰውነቱን ለእግዚአብሔር ሲያስገዛት ዘመናት አልፈዋል::
+በዘመኑ የአንጾኪያ ፓትርያርክ አርፎ ነበርና ለመንበሯ የሚገባውን ሰው ፍለጋ በየበርሃው ዞሩ:: ነገር ግን ከቅዱሱ አትናስዮስ የተሻለ ሰው አላገኙም:: እርሱ መጻሕፍትን ጠንቅቆ የሚያውቅ: ለመንጋውም የሚራራ በጐ እረኛ ነውና ይዘውት ወደ ከተማ መጡ::
+በሃገራቸው ባሕል መሠረት ሊቀ ዻዻሳት የሚሾመው የሁሉም አሕጉረ ስብከት ዻዻሳት ባሉበት ነውና ጠበቁ:: ሁሉ ተገኝቶ በሶርያ የሰልቅ ዻዻስ የነበረው አባ እልመፍርያን ግን ዘገየ:: ለ50 ቀናት ጠብቀው አባ አትናስዮስን 'ፓትርያርክ ዘአንጾኪያ' ብለው ሹመውት ተለያዩ::
+በ51ኛው ቀን አባ እልመፍርያን ሲደርስ በዓለ ሲመቱ መጠናቀቁን ሲነግሩት ተቆጣ:: "እኔ በሌለሁበት የተሾመው አይሠራምና አትናስዮስን ፓትርያርክ ብሎ የሚጠራ ሁሉ የተወገዘ ይሁን" ብሎ ወደ ሰልቅ ተመለሰ:: ቅዱስ አትናስዮስ ይህንን ነገር ሲሰማ ፈጽሞ አዘነ::
+ከቀድሞውም አስገድደውት እንጂ እርሱ ሹመቱን ፈልጐ አልመጣም:: ልክ በዘመኑ እንደምንመለከተው ቅዱሱ መልሶ ማውገዝ ይችላል:: ለዚያውም በሥልጣን ይበልጠዋል:: ቅዱሱ ግን ለግል ክብሩ ሲል ቤተ ክርስቲያንና ምዕመናን ሲከፈሉ ማየትን አልወደደም::
+ደቀ መዝሙሩን ጠራውና "ልጄ! እሺ በለኝ: ነፍሴ ትመርቅሃለች:: እኔ ለ1 ዓመት መንገድ ስለምወጣ አንተ በእኔ ፈንታ እዘዝ: እሠር: ፍታ:: ሕዝቡ ከጠየቁህ ወደ ገዳም ሔዷል በላቸው" ብሎት ከመንበረ ዽዽስናው ወጣ:: እጅግ የነተበ የበርሃ ልብሱን ለብሶ: ለ1 ቀን በእግሩ ተጉዞ ሰልቅ ውስጥ ደረሰ::
+ወደ አባ እልመፍርያን ዘንድ ገብቶም በፊቱ ሰገደ:: "አባቴ! ነዳይ ነኝና አስጠጋኝ?" ብሎ ለመነው:: አባ እልመፍርያንም ከመነኮሳቱ ጋር እንዲኖር ፈቀደለት::
+ቅዱስ አትናስዮስ ፓትርያርክ ሲሆን ወገቡን ታጥቆ ያገለግል ገባ:: ውሃ ይቀዳል: ዳቦ ይጋግራል: ቤቶችን ይጠርጋል: መጸዳጃ ቤቶችን ያጸዳል: የመነኮሳቱን እግር ያጥባል:: በዚህ ሁሉ ላበቱ እየተንጠፈጠፈ በሰውነቱ ላይ ይወርድ ነበር::
+አባቶች ትጋቱንና ትሕትናውን ሲያዩ ለዲቁና አጩት:: ዻዻሱም ጠርቶ "ዲቁና ልሹምሕ" ቢለው ፓትርያርኩ ቅዱስ አትናስዮስ አለቀሰ:: "ምነው?" ቢለው "አባቴ! በነውር ተይዞብኝ ነው እንጂ ዲቁናስ አለኝ" አለው:: አሁንም ለ7 ወራት በዲቁና አገልግሎት ቆይቶ ቅስና ተሾም ቢሉት እንደ ቀደመው እያለቀሰ መለሰላቸው::
+ልክ በዓመቱ ግን ለአንዲት ሃገረ ስብከት ዻዻስ ያደርጉት ዘንድ በዕለተ እሑድ ተሰበሰቡ:: ቅዱስ አትናስዮስ እንዲተውት እያለቀሰ ለመናቸው:: "ለሹመቱ ትገባለህ" ብለው ግድ ሲሉት ግን "ምሥጢር ልንገራችሁ" ብሎ "ፓትርያርኩ አትናስዮስ ይሏችኋል እኮ እኔ ነኝ" አላቸው::
+የሰማውን ነገር ማመን ያቃተው አባ እልመፍርያን ደንግጦ በግንባሩ መሬት ላይ ወደቀ:: እየተንከባለለም አለቀሰ:: "ወየው ለእኔ! ጌታየን አትናስዮስን እንደ አገልጋይ ላዘዝኩ" እያለም ተማለለ:: በአካባቢው የነበሩ ዻዻሳት: ካህናት: መነኮሳትና ምዕመናንም ከቅዱስ አትናስዮስ የትህትና ሥራ የተነሳ ፈጽመው አደነቁ::
+መንበረ ዽዽስና አምጥተው እየዘመሩ ተሸክመውት ዞሩ:: ቅዳሴንም ቀድሶ ሥጋውን ደሙን አቀብሏቸው ታላቅ ደስታ ሆነ:: በማግስቱም ቅዱሱን ባማረች በቅሎ ላይ አስቀምጠው: አባ እልመፍርያን በእግሩ (በራሱ ፈቃድ) እየተጓዘ በታላቅ ዝማሬ አንጾኪያ ደረሱ::
+በዚያም ታላቅ የአንድነት በዓል ተከበረ:: ታላቁ እረኛ ቅዱስ አትናስዮስ እነሆ በዚህ መንገድ ቤተ ክርስቲያንን ከ2 ከመከፈል ታደጋት:: ቅዱሱ ሲጋደል ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፏል::
✞✞✞ ቸሩ አምላክ እንዲህ ለመንጋው የሚራሩ እረኞችን አይንሳን:: ከሐዋርያው: ከሰማዕቱና ከደጉ ፓትርያርክም ጸጋ በረከትን ይክፈለን::
✞✞✞ ጥቅምት 9 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
2.ቅዱስ እስጢፋኖስ ካልዕ (ሰማዕት)
3.ቅዱስ አትናስዮስ ብጹዕ
4.ቅዱስ ስምዖን ሰማዕት
5.ቅዱስ ሊዋርዮስ ሊቀ ዻዻሳት
6.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
7.ቅዱስ ቄርሎስ ሊቀ ዻዻሳት
8.አቡነ መዝገበ ሥላሴ ጻድቅ (ኢትዮዽያዊ)
9.አፄ ዳዊት ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮዽያ (ግማደ መስቀሉን ያመጡ)
✞✞✞+ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ:: የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ:: እንዲሁም ጐበዞች ሆይ! ለሽማግሌዎች ተገዙ:: ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ:: እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና:: ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል:: ✞✞✞ (1ዼጥ. 5:3)
<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

Post Bottom Ad