አባ አጋቶን ባሕታዊ +"+
=>ይህንን ቅዱስ የማያውቅ የቤተ ክርስቲያን ሰው ይኖራል ብየ አልገምትም:: እርሱ ታላቅ ጻድቅ: ገዳማዊና የእግዚአብሔር ሰው ሲሆን አንደበቱን ከክፋት ይከለክል ዘንድ ለ30 ዓመታት ድንጋይ ጐርሶ ኖሯል::
+ይህንን ቅዱስ ሊቃውንት ሲገልጹት:
"ክምረ ክምር ጽድቁ እስከ አስተርአየ" ይሉታል:: ትእግስቱ: ደግነቱ: አርምሞው: ትሩፋቱ ከመነገር በላይ ነው:: በነበረበት በ4ኛው መቶ ክ/ዘመንም እንደ ኮከብ ያበራ ታላቅ አባት ነው::
"ክምረ ክምር ጽድቁ እስከ አስተርአየ" ይሉታል:: ትእግስቱ: ደግነቱ: አርምሞው: ትሩፋቱ ከመነገር በላይ ነው:: በነበረበት በ4ኛው መቶ ክ/ዘመንም እንደ ኮከብ ያበራ ታላቅ አባት ነው::
+ታላቁ ገዳማዊ ሰው አባ አጋቶን የታላቁ መቃርዮስ ቅዱስ ልጅ ነው:: ገዳመ አስቄጥስ እልፍ አእላፍ ቅዱሳንን ስታፈራ ይህ አባት ቅድሚያውን ይይዛል:: ምንም በብዛት የሚታወቀው በአርምሞው (በዝምታው) ቢሆንም ባለ ብዙ ትሩፋት አባት ነው::
+የሚገርመው የቀደሙ አባቶቻችን የፈለገውን ያህል መናኝ ቢሆኑም የሰው ጥገኛ መሆንን አይፈልጉም:: "ሊሠራ የማይወድ አይብላ" የሚለውን መለኮታዊ ትዕዛዝ መሠረት አድርገው ከተጋድሎ በተረፈቻቸው ሰዓት ሥራ ይሠራሉ::
+አንዳንዶቹ እንደሚመስላቸው ምናኔ ሥራ መፍታት አይደለምና ሰሌን: ዕንቅብ: ሠፌድ የመሳሰለውን ይሠፋሉ:: ታላቁ አባ አጋቶንም በአንደበቱ ድንጋይ ጐርሶ: በእግሮቹ ቀጥ ብሎ ቆሞ እንቅቦችን ይሠፋ ነበር::
+ለነገሩስ ዛሬ ዛሬ እንኩዋን ወንዶቹ ሴቶችም ብንሆን ይህንን ሙያ እየረሳነው ነው:: ቅዱሱ ግን ይሰፋና ወደ ገበያ ይወጣል:: በጠየቁት ዋጋ ሽጦት አንዲት ቂጣ (ዻኩሲማ) ይገዛል:: የተረፈውን ገንዘብ ግን እዚያው ለነዳያን አካፍሎት ይመጣል እንጂ ወደ ገዳሙ አይመልሰውም::
+ታዲያ አንድ ቀን እንደልማዱ የሠፋቸውን 5 እንቅቦች ተሸክሞ ወደ ገበያ ሲሔድ መንገድ ላይ አንድ ነዳይ (የኔ ቢጤ) ወድቆ ያገኛል:: እንደ ደረሰም ስመ እግዚአብሔር ጠርቶ ይለምነዋል:: አባ አጋቶን ከእንቅቦቹ ውጪ ምንም ነገር አልነበረውምና "እንቅቡን እንካ" አለው::
+ነዳዩ ግን ወይ የሚበላ: ካልሆነም ገንዘብ እንደሚፈልግ ይነግረዋል:: ወዲያው ደግሞ "የምትሠጠኝ ነገር ከሌለህ ለምን ወደ ገበያ ተሸክመህ አትወስደኝም?" አለው:: የነዳዩ አካል እጅግ የቆሳሰለ በመሆኑ እንኩዋን ሊሸከሙት ሊያዩትም የሚከብድ ነበር::
+ጻድቁ ግን ደስ እያለው: ያለማመንታት አንስቶ ተሸከመው:: ከረጅም መንገድ በሁዋላም ከገበያ በመድረሳቸው አውርዶ ከጐኑ አስቀመጠው:: ያ ነዳይ አላፊ አግዳሚውን ሁሉ ቢለምንም የሚዘከረው አጣ:: አባ አጋቶን አንዷን እንቅብ ሲሸጥ "ስጠኝ?" ይለዋል:: ጻድቁም ይሠጠዋል::
+እንዲህ "ስጠኝ" እያለ የ5ቱንም እንቅቦች ዋጋ ያ ነዳይ ወሰደበት:: አባ አጋቶን ግን ምንም ቂጣ ባይገዛ: በሆነው ነገር አልተከፋምና ሊሔድ ሲነሳ ነዳዩ "ወደ ቦታየ ተሸክመህ መልሰኝ" አለው:: አባቶቻችን ትእግስታቸው ጥግ (ዳር) የለውምና ጐንበስ ብሎ በፍቅር አንስቶት አዘለውና ሔደ::
+ካነሳበት ቦታ ላይ ሲደርሱ ይወርድለት ዘንድ ጻድቁ ቆመ:: ነዳዩ ግን አልወርድም አለ:: መቼም እኛ ብንሆን ብለን እናስበውና . . . ምን እንደምናደርግ ይታወቃል:: ጻድቁ ግን ዝም ብሎ ቆመለት::
+ትንሽ ቆይቶ ግን ስለ ለቀቀው ሊያየው ዞር ቢል መሬት ላይ የለም:: ቀና ሲል ግን ያየውን ነገር ማመን አልቻለም:: ደንግጦ በግንባሩ ተደፋ:: ነዳይ መስሎ እንዲያ ሲፈትነው የነበረው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ነበር::
+ክንፎቹን ዘርግቶ: በብርሃን ተከቦ: በግርማ ታየው:: ከወደቀበትም አነሳው:: "ወዳጄ አጋቶን! ፍሬህ: ትእግስትህ: ደግነትህ ግሩም ነውና ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ" ብሎት ተሰወረው:: ጻድቁም በደስታ ወደ በዓቱ ሔደ:: አባ አጋቶን ተረፈ ዘመኑን በአርምሞ ኑሮ ዐርፏል::
+"+ ቅዱስ መጥራ አረጋዊ +"+
=>ቅዱሱ የ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ክርስቲያን ሲሆን በትውልድ ግብጻዊ ነው:: ከልጅነት እስከ እውቀት: ከእውቀት እስከ ሽበት ክርስቶስን ሲያመልክ ኑሯል:: ዘመኑ ክርስቲያኖች ስለ ሃይማኖታቸው ከባዱን ዋጋ (ሕይወታቸውን) የሚከፍሉበት ነበር::
+በወቅቱ ብርቱ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ቢበዙም ብርቱ መንፈሳዊያን ተዋጊ ክርስቲያኖች ነበሩና ውጊያው ተመጣጣኝ ነበር:: ዛሬ ደግሞ ሁሉም በዛለበት ዘመን ላይ ተገኝተናል::
+ቅዱስ መጥራ ካረጀ በሁዋላ ነገሥታቱ "ክርስቶስን ካዱ" እያሉ መጡ:: ቅዱሱ ወሬውን ሲሰማ እጅግ ተገረመ:: ምክንያቱም መድኃኔ ዓለምን መካድ ፈጽሞ የሚታሰብ ነገር አይደለምና:: ቅዱሱ አረጋዊ ስለ 2 ነገር ሰማዕትነትን ፈለገ::
+አንደኛ በክርስቶስ ስም መሞት የክብር ክብርን ያስገኛልና ከዚሁ ለመሳተፍ ነው:: ሁለተኛው ግን ለወጣቶች አብነት (ምሳሌ) ለመሆን ነበር:: መልካም መሪ ባለበት ዘንድ ብዙ ፍሬዎች አይጠፉምና:: ቅዱስ መጥራ እንዳሰበው ወደ መኮንኑ ሒዶ በአሕዛብ ፊት ክርስቶስን ሰበከ:: ስለዚህ ፈንታም ብዙ አሰቃይተው በዚህች ቀን ከተከታዮቹ ጋር ገድለውታል::
=>አምላከ ቅዱሳን ትእግስታቸውን ያሳድርብን:: ከአባቶቻችንም በረከትን ይክፈለን::
=>ጥቅምት 8 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.አባ አጋቶን ባሕታዊ
2.ቅዱስ መጥራ አረጋዊ (ሰማዕት)
3.ቅድስት ሶስናና ልጆቿ (ሰማዕታት)
4.አባ ሖር
5.ቅድስት በላግያ ሰማዕት
1.አባ አጋቶን ባሕታዊ
2.ቅዱስ መጥራ አረጋዊ (ሰማዕት)
3.ቅድስት ሶስናና ልጆቿ (ሰማዕታት)
4.አባ ሖር
5.ቅድስት በላግያ ሰማዕት
=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
2.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
3.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
4.አቡነ ኪሮስ
5.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
6.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)
1.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
2.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
3.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
4.አቡነ ኪሮስ
5.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
6.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)
=>+"+ ጸሎቴን በፊትህ እንደ እጣን ተቀበልልኝ::
እጅ መንሳቴም እንደ ሠርክ መስዋዕት ትሁን::
አቤቱ ለአፌ ጠባቂ አኑር::
የከንፈሮቼንም መዝጊያ ጠብቅ::
ልቤን ወደ ክፉ ነገር አትመልሰው::
ለኃጢአት ምክንያት እንዳልሠጥ::
ከምርጦቻቸውም ጋር አልተባበር::
ጻድቅ በምሕረት ይገሥጸኝ: ይዝለፈኝም:: +"+ (መዝ. 140:2)
እጅ መንሳቴም እንደ ሠርክ መስዋዕት ትሁን::
አቤቱ ለአፌ ጠባቂ አኑር::
የከንፈሮቼንም መዝጊያ ጠብቅ::
ልቤን ወደ ክፉ ነገር አትመልሰው::
ለኃጢአት ምክንያት እንዳልሠጥ::
ከምርጦቻቸውም ጋር አልተባበር::
ጻድቅ በምሕረት ይገሥጸኝ: ይዝለፈኝም:: +"+ (መዝ. 140:2)
✞✞✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞✞✞