ነገረ ቅዱሳን (ክፍል 1) - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Saturday, October 26, 2019

ነገረ ቅዱሳን (ክፍል 1)

ምዕራፍ አንድ


1.ነገረ ቅዱሳን
1.1. ትርጓሜ፦
    ወደ ነገረ ቅዱሳን ጠቅላላ ትምህርት ከመግባታችን በፊት አንዳንድ ቃላትን ተርጉመን ማለፋችን ትምህርታችንን የጠራና የተረዳ ያደርገዋል “ነገረ ቅዱሳን” የሚለው ስያሜ ሁሉም ቅዱሳን የሚጠሩበት ገዥ የሆነ ጥቅል ስም ነውና።
1.1.1.  ነገር፦ “ነገር” የሚለው ቃል በቤተ ክርስቲያን አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አጉልቶ ለማሳየት የሚረዳና የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን የሚጠቀሙበት ገላጭ ቃል ነው።ለምሳሌ ነገረ መለኮት፣ነገረ ድኅነት፣ነገረ ማርያም …………………እንዲባል።
1.1.2.  ቅዱስ፦ “ቅዱስ” የሚለው ቃል “ቀደሰ” ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ነው።ትርጉሙም፦ አመሰገነ፣አከበረ፣ለየ፣መረጠ ማለት ይሆናል።ቅዱስ የሚለው ቃል በዕብራይስጥ ቅዳሺ፣ በሱርስት( የሶሪያ ጥንታዊ ቋንቋ) ቃዲህ፣በዐረብኛ እንደ ግዕዙ ቅዱስ ይባላል።ትርጉሙም ተመሳሳይ ነው።
 1.2.የባሕርይና የጸጋ ቅድስና
1.2.1.የባሕርይ ቅድስና፦
    ቅድስና፣ቅዱስ፦ከሁሉም በላይና ከሁሉም በፊት ይህ ቃል ጥቅም ላይ የሚውለው (የሚያገለግለው) ለሠራዊት ጌታ ለቅዱስ እግዚአብሔር ነው።ቅዱስነት የባሕርይ ገንዘብነቱ ለእግዚአብሔር ብቻ ነው።ይህም ማለት ቅድስናው ከእርሱ የማይለይ ከማንም ያልተቀበለውና የማይቀበለው፣ማንም ሊወስድበት የማይችለው፣ለሌላ ሲሰጥም የማይጐድልበትና የማይከፈልበት የራሱ ገንዘብ ብቻ ማለት ነው።ቅድስና እና እግዚአብሔር ተለያይተው ሊነገሩ አይችሉም አይገባምም በእግዚአብሔር ዘንድ ከቅድስና በስተቀር ሌላ ነገር አይታሰብም በቅድስናው ርኩሰት፣በጻድቅነቱ ሐሰት፣በባዕልነቱ ንዴት(ድኅነት) የሌለበት ነውና።

ስለዚህም ሱራፌል ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ የተነሣ ተሞልታለች።በማለት የባሕርይ ቅድስናውን በምስጋና ገልጠዋል።ኢሳ6፥3፣ራዕ 4፥8።እግዚአብሔር የባሕርይው መገለጫ ሁኖ የሚጠራበት ስሙም ቅዱስ የሚለው ነው። እግዚአብሔር ከአማልክትና ከክፋት ሁሉ የተለየ የተፈራና የተከበረም ስለሆነ የሚመስለውና የሚተካከለውም የሌለ ብቸኛ ቅዱስ ነው። “እስመ አልቦ ቅዱስ ከመ እግዚአብሔር ወአልቦ ጻድቅ ከመ አምላክነ……..1ሳሙ 2፥2፣“መኑ ይትኤረዩ ለእግዚአብሔር በደመናት ወመኑ ይመስሎ ለእግዚአብሔር እም ደቂቀ አማልክት አኮኑ ስቡሕ በምክረ ቅዱሳን”መዝ 88፥6 ተብሎ ተወድሷል።
1.2.2. የጸጋ ቅድስና
    የጸጋ ቅድስና ማለት ከቅዱስ እግዚአብሔር በስጦታ የተሰጠ የተገኘ ማለት ነው።ተደጋግሞ እንደተገለጸው በባሕርዩ ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር ብቻ ስለሆነ የፍጡራን ቅድስና መገኛውና ምንጩ እርሱ ብቻ ነው።ሰው ወይም ማናቸውም ነገር ለእግዚአብሔር አገልግሎት ሲለይ ቅዱስ ይባላል።ኢያ 6፥19 ሰው ወይም ማናቸውም ነገር ቅዱስ የሚሆነው ከእግዚአብሔር የተነሣና ለእግዚአብሔር የተለየ ስለሚሆን ነው።እግዚአብሔር ቅዱስ በመሆኑ ለእግዚአብሔር የሆነ ሁሉ ቅዱስ መሆን አለበት።ዘሌ 19፥2፣1ጴጥ 1፥15።
  1.3.ቅዱሳን
     ቅዱስ የሚለው ቃል አንድን ነጠላ ነገር የሚያመለክት ሲሆን፣ቅዱሳን የሚለው ደግሞ ብዛትን የሚያመለክት ነው።በዚህ ሥልጠና የምንመለከተውም ነገረ ቅዱሳን ስለሆነ በባሕርዩ ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር በረድኤት ያደረባቸው፣በጸጋ የተዋሃዳቸው፣እግዚአብሔርን በፍጹም ሃይማኖት፣በተቀደሰ ሕይወትና በመልካም ተጋድሎና የአገልግሎት ሕይወት በማገልገል ከራሳቸው አልፈው ለሌላው ሰው በረከት (ጥቅም) የሆኑትን ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔር ቅዱሳን ብሎ ይጠራቸው ዘንድ አያፍርም “አነ እቄድሰ ርዕስየ ከመ ይኩኑ ቅዱሳን በጽድቅ በእውነት ቅዱሳን እንዲሆኑ እኔ ራሴን ስለ እነርሱ እቀድሳለሁ”በማለት የሰው ልጅ ቅዱስ ይሆን ዘንድ ራሱን የተቀደሰ መሥዋዕት አድርጐ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን በማፍሰስ ቅድስናን እንደሠጠ ተናገረ።ዮሐ 17፥19።

   በመሆኑም የቅዱሳን ቅድስና የጸጋ ቅድስና ነው ማለት ነው።ቅዱስ የሚለው ቃል ለእግዚአብሔርም ከሰው ወገን ቅዱሳን ለሆኑም የሚነገርና በቅጽልነት የሚያገለግል ከሆነ እንዴት ተለይቶ ይታወቃል?የሚል ጥያቄ ሊፈጥር ይችል ይሆናል ቅዱስ የሚለው ቃል ደረጃውና መጠኑ የሚታወቀው በሚቀጸልለት ባለቤት ነው እንጂ በቃል ብቻ አይደለም።
v ቅዱስ እግዚአብሔር ስንል የእግዚአብሔር ሁለንተናዊ ነገር
v ከፍጡራን መካከል ቅዱሳን የሆኑትን ቅዱስ ብለን ስንጠራ ተጋድሎውን የአገልግሎቱን ሕይወት የተገባለትን ቃል ኪዳን እናስባለን ማለት ነው።
ለምሳሌ፦ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ።(ዮሐ 8፥12)በማለት ስለ ራሱ ብርሃንነት ተናግሮአል።ደቀ መዛሙርቱንም እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ ብሏቸዋል።(ማቴ 5፥14)ብርሃን የሚለው ቃል አንድ ዓይነት ሲሆን በክርስቶስና በደቀ መዛሙርቱ መካከል ያለው ልዩነት ግን የፈጣሪና የፍጡር፣የባሕርይና የጸጋ ተብሎ ይለያል።
   ስለዚህ “ቅዱስ፣ብርሃን” የሚሉት ቃላት የሚታወቁት በመልእክታቸውና በክብደታቸው መጠን ነው ማለት ነው።ወንጌላዊው ዮሐንስ የክርስቶስንና የመጥምቁ ዮሐንስን ብርሃንነት ሲያነጻጽር “ወለለሁሰ ኢኮነ ብርሃነ ጻእሙ ዓለ መጽአ ሰማዕተ ይኩን በእንተ ብርሃን-ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ እርሱ (መጥምቁ ዮሐንስ) ብርሃን አልነበረም”።ብሏል ዮሐ 1፥8 ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዮሐንስ መጥምቅ ሲመሰክር “እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ” ብሎ ብርሃንነቱን መስክሮአል።
  1.4. ነገረ ቅዱሳን መማር ለምን ያስፈልጋል?
   ልዑለ ባሕርይ ቅዱስ እግዚአብሔር በነቢዩ ኢሳይያስ አድሮ ሲናገር “ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም ወደ ወላዶቻችሁም ወደ ሣራ ተመልከቱ አንድ ብቻውን በሆነ ጊዜ ጠራሁት ባረክሁትም አበዛሁትም” (ኢሳ 51፥2)።በማለት በዓይነ ሕሊና ወደ ቅዱሳኑ እንድንመለከት መክሮናል።ወደ ቅዱሳኑ ስንመለከት፦

1.4.1. የእምነት ጽናትን እንማራለን
  ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እምነት ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው።ለሽማግሌዎች የተመሰከረላቸው በዚህ ነውና” በማለት የተመሰከረላቸውን ዋና ዋናዎቹን ስማቸውን፣ማዕረጋቸውንና ግብራቸውን በእምነት ጽናት ተስፋ ያደረጉት ሁሉ እንደተፈጸመላቸው በማስረጃነት ጠቅሷቸዋል።(ዕብ 11፥1-40)።
     1.4.2.በረከት እናገኛለን
በረከት በጻድቅ ራስ ላይ ነው፣የጻድቅም መታሰቢያ ለበረከት ነው።ምሳ 10፥6።እንደተባለ ቅዱሳኑን በማክበር በረከት እናገኛለን እግዚአብሔር አብርሃምን …………………….እባርክሃለሁ፣ስምህንም አከብረዋለሁ፣ለበረከትም ሁን፣የሚባርኩህንም እባርካለሁ፣የሚረግሙህንም እረግማለሁ።ዘፍ 12፥2 በማለት ስሙን የሚያከብሩትን፣በቃል ኪዳኑ የሚታማመኑትን እንደሚባረካቸውና አብርሃምን ለበረከት እንዳደርገው እናስተውላለን።አብርሃምን የመሰሉና በቅድስናና በተጋድሎ በአገልግሎት ጸጋ ከአብርሃም የሚልቁ ቅዱሳን ሁሉ የበረከት ምንጭ ናቸው።
    1.4.3.መንፈሳዊ  ሕይወት እንማርባቸዋለን
   ቅዱሳን ሕይወታቸው በጾም በጸሎት በስግደት በትሕትና በተስፋ በትዕግሥት እና በአርምሞ በዝምታ የተሞላ ነው።ከእግዚአብሔር ጋር፣ከበጐና ክፉ ሰዎች ጋር በመከራና በደስታ ጊዜ ሕይወታቸውና የኑሮ ፍልስፍናቸው (ዘይቤያቸው) እንዴት እንደ ነበር መማር እንችላለን። “የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ የኑሮአቸውን ፍሬ  እየተመለከታችሁ በእምነታችሁ ምሰሉአቸው”።ዕብ 13፥7 እንዲል።
    1.4.4.የተጋድሎ ውሎአቸውን እንድናውቅ ይረዳናል
   አስቀድመን እንደተናገርነው የቅዱሳን ሕይወት በተጋድሎ የተሞላ ነው ጌታችን በወንጌል  “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ነገር ግን አይዞአችሁ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ”።ዮሐ 16፥33።በማለት እንደተናገረው በፍጹም እምነትና ትዕግሥት በመከራ መካከል አልፈዋል በሰይፍ ተመትረዋል፣በመጋዝ ተሰንጥቀዋል፣በእሳት ተቃጥለዋል፣ተሰደዋል፣ተርበዋል፣ ተጠምተዋል፣ታርዘዋል።ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ “ወንድሞች ሆይ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ
ደስታ ቁጠሩት”።ያዕ 1፥2 እንዳለ መከራውን ሁሉ በደስታ ተቀብለውታል የተጋደሉትም እስከ ሞት ድረስ ነው።ራዕ 2፥10።በዚህ ጉዞአቸው ሁሉ በአሸናፊነት የተወጡ የሃይማኖት ጀግኖች ናቸው።
       1.4.5. በቃል ኪዳናቸው እንድንጠቀም ያደርገናል
  ከዘመነ አበው ጀምሮ የነበሩ ቅዱሳን በእምነታቸውና በአካሄዳቸው በሕይወታቸው ፍጻሜም እግዚአብሔርን ደስ ስለ አሰኙት የተለየ ቃል ኪዳን ተቀብለዋል።ይህም ቃል ኪዳን የሚጠቅመው በእነርሱ ቅድስናና ተጋድሎ የሚያምኑትን፣በምልጃቸውና በጸሎታቸው የሚተማመኑትን ሰዎች ነው።
        1.4.6. አሠረ ፍኖታቸውን እንድንከተል
    ከእርሻ ሜዳ የተጠራው ነቢዩ ኤልሳዕ እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስና በእሳት ሠረገላ ወደ ሰማይ ሊወስደው በወደደ ጊዜ ኤልያስን ኤልሳዕን፦እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ልኮኛልና በዚህ ቦታ ቆይ ቢለውም ኤልሳዕ ግን ሕያው እግዚአብሔርን በሕያው ነፍስህ እምልልሃለሁ አልለይህም ነበር ያለው።2ነገ 2፥1 ኤልያስን የተከተለ ኤልሳዕ በረከቱ እጥፍ ሁኖ ስለ አደረበት፦
·       በመጐናጸፊያው የዮርዲያኖስን ወንዝ ከፈለ
·       የሞተውን በአካለ ሥጋ እያለና ከሞተ በኋላ ማስነሣት ችሏል
·       የመረረውን ውኃ ማጣፈጥ ችሏል
·       እህል በጠፋበት ዘመን ማበርከት ችሏል
·       በሃይማኖታዊ አቋም ከነገሥታት ጋር ታግሏል
v ሐዋርያው ቅዱስ አትናቴዎስ
v ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
v ኢትዮጲያዊው ሊቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ………ሃይማኖታዊ ጽናታቸው በመከራ ጊዜ ትዕግስታቸው የጸሎት ሕይወታቸው በጥንቃቄ የተሞላ ስብዕናቸውና ክርስቲያናዊ ስነ ምግባራቸው የአገልግሎት ትጋታቸው ዛሬ ላይ ለምናገኘው አቅምና ብርታት ይሆናል የሄዱበትን ፈለግ እንድንከተል ያደርገናል።

      

1.5.የነገረ ቅዱሳን ትምህርት ምንጮች
ይቀጥላል…..ክፍል ሁለት ይጠብቁ   

Post Bottom Ad