ጥቅምት 10 - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Tuesday, October 22, 2019

ጥቅምት 10


✞✞✞ እንኩዋን ለቅዱሳን ሰማዕታት "ባኮስ ወሰርጊስ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞
+"+ ቅዱሳን ባኮስ ወሰርጊስ +"+
=>ሰማዕትነት በክርስትና ለሃይማኖት የሚከፈል
የመጨረሻው ዋጋ (መስዋዕትነት) ነው:: ሰው ለፈጣሪው
ሰውነቱን ሊያስገዛ: ሃብት ንብረቱን ሊሰጥ ይችላል::
ከስጦታ በላይ ታላቅ ስጦታ ግን ራስን አሳልፎ መስጠት ነው::
+ራስን መስጠት በትዳርም ሆነ በምናኔ ውስጥ ይቻላል::
የመጨረሻ ደረጃው ግን ሰማዕትነት ነው:: "አማን መነኑ
ሰማዕት ጣዕማ ለዝ ዓለም: ወተዓገሡ ሞተ መሪረ
በእንተ መንግስተ ሰማያት" እንዳለው ቅዱስ ኤፍሬም
ሶርያዊ ሰማዕትነት ማለት መራራውን ሞት ስለ ፍቅረ
እግዚአብሔር ሲሉ መታገስ ነው::
+እርሱ ቅሉ መድኃኒታችን ክርስቶስ የሰማይና የምድር
ጌታ ሲሆን ኃፍረተ መስቀልን ታግሦ ሙቶልን የለ!
በዓለም ያሉ ብዙ እምነቶች ስለ መግደል በቀጥታም ሆነ
በተዘዋዋሪ ያስተምራሉ:: ክርስትና ግን መሞትን እንጂ
መግደልን የሚመለከት ሕግ የለውም::
+እርሱ ባለቤቱ "ጠላቶቻችሁን ውደዱ: የሚረግሟችሁን
መርቁ: ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ" ብሎናልና:: (ማቴ.
5:44) ነገር ግን ዕለት ዕለት ራሳችንን በሃይማኖትና
በምግባር ካልኮተኮትነው ክርስትና በአንድ ጀምበር
ፍጹም የሚኮንበት እምነት አይደለምና በፈተና መውደቅ
ይመጣል::
+በተለይ የዘመኑ ክርስቲያን ወጣቶች ልናስተውል
ይገባናል:: የቀደሙ ወጣት ሰማዕታት ዜና የሚነገረን
እንድንጸና ነውና::
¤እስኪ ለዛሬ ደግሞ በአጭሩ የቅዱሳን ባኮስና ሰርጊስን
ዜና እንካፈል::
+እነዚህ ቅዱሳን የዘመነ ሰማዕታት ፍሬዎች ናቸው::
ባኮስ እና ሰርጊስ (ሰርግዮስ) ከልጅነት ጀምሮ ባልንጀሮች
ናቸው:: በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን በሮም ግዛት ሥር
መክስምያኖስና ዲዮቅልጢያኖስ እስከ ነገሡበት ዘመን ድረስ በአንጻሩም ቢሆን ሰላም
ነበር::
+ታዲያ በዚህ የሰላም ጊዜ 2ቱ ቅዱሳን ሥራ
አልፈቱም:: ጾምን: ጸሎትንና በጐ ምግባራትን ሁሉ
ይከተሉ ነበር:: ለመከራ ዘመን ስንቅ የሚሆነን በሰላሙ
ዘመን የተያዘ ስንቅ ነውና::
+በዚያው አንጻር ደግሞ ሠርቶ መብላት ይገባልና ሥራ
ሲፈልጉ መክስምያኖስ ሠራዊት መሰብሰብ ጀመረ::
እነርሱም ከሠራዊቱ ዘንድ ተቆጥረው የምድራዊ ንጉሥ
ጭፍሮች ሆኑ:: በእርግጥ በዘመናችን ለክርስትና
አይመቹም ከሚባልላቸው ሥራዎች አንዱ ውትድርና
ነው::
+ነገር ግን ብዙ ቅዱሳንን ስትመለከቷቸው ሙያቸው
ይሔው ነበር:: ቅዱሳን ባኮስና ሰርጊስ ጊዜው የሰላምም
ይሁን የጦርነት ይጾማሉ: ይጸልያሉ: ይመጸውታሉ::
እንዲህ እንዲህ እያሉም ዘመናት አለፉ::
+ከቆይታ በሁዋላ ግን ሰይጣን ያደረበት ንጉሡ
መክስምያኖስ ጣዖት አመለከ:: አዋጅም አውጥቶ
ክርስቲያኖችን ያሰቃይ: ይገድልም ያዘ:: ቅዱሳኑ ይህንን
ሲሰሙ አዘኑ::
+ቁጭ ብለውም ተወያዩ:: በልባቸው ፍቅረ ክርስቶስ
ይነድ ነበርና ወጣትነታቸው: መልካቸው: ተወዳጅነታቸው
ሁሉ ሊያታልላቸው አልቻለም:: እንደ አንድ ልብ መካሪ:
እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ስለ ሃይማኖት ሊሰው ወሰኑ::
+በማግስቱም ንጉሡ ወደ ሾመው የቅርብ አለቃቸው
ቀረቡና "የምንነግርህ ነገር አለን" አሉት:: "እሺ"
ሲላቸው በወገባቸው ያለውን የክብር መታጠቀያና የክብር
ልብሳቸውን በፊቱ ወረወሩለትና "እኛ የክርስቶስ ጭፍሮች
ነንና ከዚህ በሁዋላ ላንተ: ለጣዖት አምላኪው
አንታዘዝም" አሉት::
+መኮንኑ ነዶታልና አስገረፋቸው: አሳሰራቸው:: በረሃብና
በጥም: በብዙ መክፈልተ ኩነኔም አሰቃያቸው:: እነርሱ
ግን ጽኑዓን ነበሩና አልቻሏቸውም:: ጥቅምት 4 ቀን በሆነ
ጊዜ ግን 2ቱን ለያዩዋቸው::
ቅዱስ ባኮስን ለብቻው ወስደው ትልቅ ድንጋይ በአንገቱ
ላይ አሠሩበትና ባሕር ውስጥ አሰጠሙት::
+ነፍሱም ከስጋው ስትለይ ባሕር ወደ ዳር
አስወጣችው:: በአካባባቢውም "ባባ" እና "ማማ"
የሚባሉ ባሕታውያን ነበሩና እግዚአብሔር እንዲገንዙት
አዘዛቸው:: ሲሔዱም ቅዱስ ሥጋውን አንበሳና ተኩላ
ሲጠብቁት አግኝተው: በታላቅ ዝማሬ ገንዘው: በራሳቸው
ተሸክመው ወስደው: በበዓታቸው ውስጥ ቀበሩት::
+ቅዱስ ሰርጊስን ደግሞ ለ6 ቀናት ካሠሩት በሁዋላ
በዚህች ቀን እጁንና እግሩን በእንጨት ላይ ቸንክረው:
በእንስሳት ጭራ ላይ አስረው ሲጐትቱት ውለዋል::
አንገቱን በሰየፉት ጊዜም አንዲት ወጣት ደሙን ተቀብላ
በረከትን አግኝታለች:: የመከራ ዘመን ካለፈ በሁዋላም
ለቅዱሳኑ ቤተ ክርስቲያን ታንጾ በዚህች ቀን ተቀድሷል::
ተአምራትም ታይተዋል::
=>አምላከ ሰማዕታት ጽንዓት: ትእግስታቸውን አሳድሮ
ከበረከታቸው ይክፈለን::
=>ጥቅምት 10 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን
በዓላት=
1.ቅዱሳን ባኮስና ሰርጊስ (ሰማዕታት)
2.ቅዱስ ዮሐንስ መስተጋድል
3.አባ አውማንዮስ ሊቀ ዻዻሳት
=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
2.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
3.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
4.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ)
5.ቅድስት ዕሌኒ ንግስት
6.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ
7.ቅዱስ እፀ መስቀል
=>+"+ ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ: ወይስ
ጭንቀት: ወይስ ስደት: ወይስ ራብ: ወይስ ራቁትነት:
ወይስ ፍርሃት: ወይስ ሰይፍ ነውን?
'ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን:: እንደሚታረዱ በጐች
ተቈጠርን'
ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው::
በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች
እንበልጣለን:: +"+ (ሮሜ. 8:35-38)
<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

Post Bottom Ad