ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ዐረፉ - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Wednesday, May 29, 2019

ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ዐረፉ

Source ; Haratewahido

  • ሥርዐተ ቀብሩ ቅ/ሲኖዶስ በሚወስነው ቀን በመካነ ሰማዕት ቅ/ገላውዴዎስ ይፈጸማል፤
  • ለ41 ዓመታት፣ ከኤጲስ ቆጶስነት እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊነት አገልግለዋል፤
  • ከማሕሌት እስከ ዐውደ ምሕረት፣ በሙሉ የአገልግሎት ትጋታቸው ይታወቃሉ፤
  • በኹለት ቅዱሳን ፓትርያርኮች ምርጫ በዕጩነት ቀርበዋል፤
***
ከሊቅነትና ከደግነት ጋራ በተሟላ የአገልግሎት ሕይወታቸው የታወቁት፣ አንጋፋው የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ዐረፉ፡፡
የ84 ዓመቱ አረጋዊ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ ዛሬ ቅዳሜ፣ ግንቦት 17 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ 11፡30 ላይ፣ ከስኳር እና ከልብ ሕመም ጋራ በተያያዘ የኩላሊት መድከም፣ በሕክምና ሲረዱ በቆዩበት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ዐርፈዋል፡፡
በሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ፣ ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም. ለጅማ ሀገረ ስብከት ኤጲስ ቆጶስነት የተሾሙት ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፡-
• ከ1971 እስከ 1976 ዓ.ም. የጅማ፣
• ከ1976 እስከ 1978 ዓ.ም. የካፋ፣
• ከ1978 እስከ 1981 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣
• ከ1981 እስከ 2001 ዓ.ም. የደቡብ ጎንደር፣
• ከ2001 እስከ 2011 ዓ.ም. የሰሜን ጎንደር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመኾን፣ ቤተ ክርስቲያንን ለ41 ዓመታት በትጋት አገልግለዋል፡፡
ጥንቱንም ለሢመተ ጵጵስና ለመመረጥ ያበቃቸው፣ ከማሕሌት ቁመት እስከ ዐውደ ምሕረት ስብከት የዘለቀው ሙሉ አገልግሎታቸው ሲኾን፣ በሕመም ምክንያት እስከተወሰኑበት ጊዜ ድረስ፣ ከተማና ገጠር ሳይመርጡ በትጋት፣ በደግነትና በሰላማዊነት አባታዊ ሓላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡
his-grace-abune-elsa-on-apostolic-duty
በፊት ስማቸው መሪጌታ አባ ኅሩይ ይባሉ የነበሩት ብፁዕነታቸው፣ በደብረ ጽጌ ገዳም ለዐሥራ አምስት ዓመታት አገልግለዋል፤ ለሢመት ተጠርተው ሲመረጡ፣ በጋሞጎፋ ሀገረ ስብከት በአገልግሎት ላይ ነበሩ፡፡ መጻሕፍተ ሐዲሳትንና ፍትሐ ነገሥትን፣ ከታዋቂው የነታ ገብረ ሕይወት ሐዲስ ተምረዋል፤ የቅኔና የአቋቋም ዐዋቂም ነበሩ፡፡
በአራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ እና በስድስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ምርጫ ወቅት፣ በዕጩነት ከቀረቡት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትም አንዱ ነበሩ፡፡
በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት፣ አፈር ውኃ እናት ወረዳ፣ መካነ ሰማዕት ቅዱስ ገላውዴዎስ ደብር፣ በ1927 ዓ.ም. የተወለዱት የአንጋፋው አባት ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ሥርዐተ ቀብር፣ በኑዛዜያቸው መሠረት በዚያው ቤተ ክርስቲያን እንደሚፈጸም ታውቋል፡፡
his-grace-abune-elsa-on-32-sgga
በመጪው ሰኞ፣ በጎንደር መስቀል ዐደባባይ የስንብት መርሐ ግብር መዘጋጀቱ ተጠቁሟል፤ የሥርዐተ ቀብራቸውን ዕለትና ሰዓት፣ የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ ስብሰባውን በማካሔድ ላይ የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኖ እንደሚያስታውቅ ይጠበቃል፡፡
የብፀዕነታቸው በረከት ይድረሰን፤ አሜን፡፡

Post Bottom Ad