ሰሙነ ሕማማት ዘረቡዕ
ለምን የምክር ቀን ተባለ?
የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚገባቸው ምክር የጀመሩበት ወይም የያዙበት ቀን ስለሆነ
ነው፡፡ በዚህ ምክራቸው ላይ በጣም ትልቅ ጭንቀት ነበር፡፡ ምክንያቱም ወቅቱ የፋሲካ በዓላቸውን የሚያከብሩበት
በመሆኑ፤ብዙውን ሕዝብም በጌታችን ትምህርት የተማረኩ ተአምራቱን የሚያደንቁ ስለነበር ሁከት እንዳይፈጠር ነው፡፡
በዚህ ጭንቀት ሳሉ ከደቀ-መዛሙርቱ አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ በመካከላቸው በመገኘት የምክራቸው ተባባሪ ሆኖ
ጭንቀታቸውን አስወግዶላቸዋል፡፡ (ማቴ.26፤1-5፣ ቁ14-16፣ ማር.14፤1-2 ቁ.10-11፣ ሉቃ 22፤1-6)
የሐዲስ ኪዳን ካህናትና ምእመናን በዚህ ዕለት በቤተክርስቲያን ተሰብስበው ከእህል ከውኃ ተለይተው መላ
ሰውነታቸውን የሞት ፍርዱን በማሰብና በማልቀስ፣ ነገረ መስቀሉን የሚያወሳውን ሁሉ በመዘመርና በማንበብ እንዲሁም
እስከ ሥርቀተ ኮከብ (እስከ ኮከብ መውጫ) በጾም፣ በጸሎትና በስግደት ተወስነው ይቆዩና ከዚህ በኋላ ወደ ቤታቸው
ይሄዳሉ፡፡
መልካም መዓዛ ያለው ቀንም ይባላል

የዕንባ ቀንም ይባላል
ይህም ይህቸው ሴት በጌታችን እግር ላይ ተደፍታ፣ መላ ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት በዕንባዋ እግሩን አጥባዋለችና፣
በጠጉሯም በእንባዋ ያጠበችውን እግሩን አብሳዋለችና፡፡ (ማቴ.26፤6-13፣ ማር.14፤3-9፣ ዮሐ.12፤1-8) ከዚህ
ልንማር የሚገባው ነገር አለ፤ ይኸውም የራስን ኃጢአት በማሰብ ማልቀስና የተወደደ መሥዋዕት አድርጐ ለእግዚአብሔር
ማቅረብን ነው፡፡ የማርያም እንተ ዕፍረትን ኃጢአት ይቅር ብሎ መብዓዋን የተቀበለ አምላክ ዛሬም በመካከላችን
አለና፡፡