
የአሥራ አምስት ዓመቷ ወጣት ታላቋ ሰማዕት ቅድስት ማሪና
(ማርግሬታ) ዘአንጾኪያ የክርስቶስ ደቀመዛሙርት ለመጀመሪያ
ጊዜ ክርስቲያን በሚባል ስም በተጠሩበት በአንጾኪያ
(የሐዋ.12፥26) ጣዖት አምላኪ ከሆኑ ቤተሰብ
በዲዮቅልጥያኖስ ዘመነ መንግስት በ290 ዓ/ም አከባቢ
የተወለደች ታላቅ ሰማዕት ናት ። አባቷ የጣዖት ካህን ሲሆን
ስሙም ኤዴስዩስ ይባላል ። ወላጅ እናቷን በልጅነቷ በሞት
ምክንያት ካጣች ወዲህ አባቷ ትጠብቃት ዘንድ ለአንዲት
ሞግዚት ሰጣት ። ብላቴናይቱ ቅድስት ማሪና ስለ ክርስትና
ሃይማኖት ምንም ዕውቀት አልነበራትምና በሞግዚትነት ታሳድጋት
ዘንድ የተቀበለችው ክርስቲያን ሴት ነ...በርችና ስለ ክርስትና
ሃይማኖት ፣ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ፣ ስለ ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ የማዳን ሥራ ከልደቱ እስከ ትንሣኤው ድረስ እንዴት
በድንግል ማኅጸን በድንግልና ተጸንሶ በድንግልና እንደተወለደ ፤
በመጨረሻም በኅቱም ድንግልና ተጸንሶ በድንግልና እንደተወለደ
ሁሉ ትንሣኤውም መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በድንቅ ተአምራት
በሥልጣኑ በኃይሉ ሙስና መቃብርን ድል አድርጎ እንደተነሳ ፣
በዕለተ አርብ በመከራ የደቀቀው ሰውነት በትንሣኤው ብርሃን
ታድሶ መንሣቱን ፣ ዳግመኛም ወደ መጣበት ወደ ሰማይ ካረገ
በኋላ እኛን ወደ እሱ ሊወስደን በዳግም ትንሣኤ እንደሚያስነሣን
፣ ለሰው ልጆች ያለውን ጥልቅ ፍቅር እያሰተማረቻት አሳደገቻት ።
ቅድስት ማሪና ይህን መንፈሳዊ ዕውቀት በጥልቀት የተረዳችው
በ12 ዓመቷ ሲሆን በዚህ በእውነተኛው አፍቃሪ በክርስቶስ ፍቅር
ተማርካ የሰማዕትነትን አክሊል የተቀዳጀችው በ15 ዓመቷ ነው ።
ለዚህ የሰማዕትነት ክብር እንድትበቃ ያደረገቻት ሞግዚቷ በግ
ጠባቂ ነበረችና ከዕለታት አንድ ቀን ስለ ቅዱሳን ሰማዕታት ገድል
እና በሰማያዊው መንግሥት ያገኙትን የሰማዕትነት የክብር
ሽልማት አክሊል ስትነግራት ወጣቷ ሰማዕት ቅድስት ማሪና
ከመጀመሪያው ጀምሮ በወጣትነት ልቧ በክርስቶስ ፍቅር
ተማርካለችና በድንግልና ጸንታ ፣ እንደ ቅዱሳኑ ሰማዕታት እሷም
የሰማዕትነትን ገድል ስለክርስቶስ ፍቅር ስትል እንድምትጋደልና
በሰማዕትነት ደምም የክርስትና ሃይማኖት መሠረት የሆነውን
ጥምቀት መጠመቅ እንዳለባትም ለራሷ ቃል ገባች ። የክርስትናን
ሃይማኖት በግልጥ እስከምተሰብክበት ጊዜ ድረስ በሃይማኖት
ጸናች ። ነገር ግን አባቷ ክርስቲያን የመሆኗን ነገር ሲሰማ
ክርስቲያኖችን ይጠላ ስለነበር እንደ ልጁ አያያትም ነበር ።
በኮፕቲክ ኦርቶዶክስ የቅዱሳንን ሕይወት በሚያዘክረው በሐምሌ
(አቢብ) ወር ቀን 23 በሚነበበው ስንክሳር ላይ የቅድስት ማሪና
አባት በ15 ዓመቷ እንደሞተ ተገልጧል ።
+
ከዕለታት አንድ ቀን ቅድስት ማሪና ከሞግዚቷና ከሠራተኞች ጋር
በግ ለመጠበቅ በወጣች ጊዜ የአገሩ ገዥ የነበረው
“ኦሊምሪዮስ” = (ሎፋሪዩስ እብሮቱስ)” በመንገድ ላይ ሲያያት
በልቡ ተመኛት ። ወታደሮቹንም ወደ እርሱ ይዘው እንዲያመጧት
ወደ ቅድስቲቱ ዘንድ ሰደዳቸው ። ነገር ግን ለወታደሮቹ እሷ
ክርስቲያን እንደሆነች ገልጣ ነበርና በኃይል እንዲያመጧት
ዳግመኛ አዘዛቸው ። ቅድስት ማሪናን ወደ ገዥው ዘንድ
ሲያቀርቧት ገዥውም ሚስት እንድትሆነው የጋብቻ ጥያቄ
አቀረበላት ። ይህንንም ሊጠይቅ የቻለበት ምክንያት ክርስቲያን
ሆናለች የሚባለውን ነገር ስለሰማና እሷን በመውደዱ
በመበሳጨቱ ነበር ። ገዥውም የፊጥኝ ታሥራ የመጣችው
ብላቴናይቱ ቅድስት ማሪናን ለሚያመልከው ጣዖት መሥዋዕትን
እንድታቀርብና አምላኳንም እንድትክድ ጥያቄ ቢያቀርብላትም
ቅሉ እሷ ግን አምላኳን እንደማትክድና የእሱንም ጥያቄ
እንደማትቀብል ገለጠች ። ግብዣውን ያልተቀበለችለት ገዥው
“ኦሊምሪዮስ” = (ሎፋሪዩስ እብሮቱስ)” ማንነቷን ከየትም
እንደመጣች በድጋሚ ስጠይቃት ቅድስት ማሪና እንዲህ በማለት
ነበር ማንነቷ ከምታመልከው አምላክ ጋር በድፍረት የተናገረችው
። ሃይማኖቷንም እንዲህ ብላ መሰከረች “በጌታችን በኢየሱስ
ክርስቶስ የማምን ክርስቲያን ነኝ ስሜም ማሪና ይባላል” በማለት
መለሰችለት ። ሆኖም ግን ገዥው ወደ እሱ አሳብ ሊያመጣት ፣
የምትፈልገውንም ነገር እንደሚሰጣትና ሚስቱ ብትሆነው በግዛቱ
ሁሉ እንደምትከብር ፤ ወደ አምልኮ ሥፍራ በመሄድ መሥዋዕትን
ከዕጣን ጋር እንድታቀርብና ለጣዖታቸው እንድትሰግድ አጥብቆ
በማለዳት ጊዜ ወጣቷ ድንግል ቅድስት ማሪና ግን “ለፈጣሪዬ
የማቀርበውን የአምልኮት ስግደት ፤ የሚቀርብለትን ክብር
ለማያውቀውና ለማያስተውለው ፣ በድንና ሕይወት ለሌለው
ጣዖት አልሰግድም ፣ አላቀርብምም” በማለት በክርስቶስ ላይ
ያላትን የእምነት ጽናት ገለጠች ።
በዚህም ምክንያት ቅድስት ማሪናን እያሰቃዩዋት ሰውነቷን
ማበጠሪያ መሰል በሆነ ብረት በመግፈፍ በሰውነቷም ላይ
ኮምጣጤ ፣ ጨው ፣ ሎሚ አንድ ላይ አድርገው በመቀባት
ያሰቃይዋት ጀመር ። ቅድስቲቱ ግን ይህን ሁሉ መከራ በትዕግስት
ትቀበለው ነበር ። የምትሞትም መስሏቸው ወደ እስር ቤት
ወሰዷት ። በዚህ በእሥር ቤት ሳለች የጌታ መልአክ መጥቶ
የቆሰለውን መላ ሰውነቷን ፈወሰ ። በጸሎት ላይም ሳለች
እጆችዋንም በትዕምርተ መስቀል አምሳል አመሳቅላ ስትጸልይ
ሰይጣን አስፈሪና ግዙፍ ሆኖ በዘንዶ መልክ መጣባት ። ያን
ጊዜም ከግዙፍነቱና አስፈሪነቱ የተነሳ ቅድስቲቱ ፈራች ።
ሰውነቷም ተንቀጠቀጠ ። ያን ጊዜም ያ ዘንዶ አፉን ከፍቶ ዋጣት
። በዘንዶ ሆድ ውስጥ ሆና በመስቀል ምልክት አማትባ ስትጸልይ
ዘንዶው ለሁለት ተሰንጥቆ ሲሞት ቅድስቲቱ ግን በሕይወት
ተገኘች ። በእግዚአብሔርም ጥባቆት ምንም ዓይነት ጉዳት
ሳይደርስባት ከዘንዶ ሆድ ውስጥ ወጣች ።
+
ሀገረ ገዥው በሚቀጥለው ቀን ከእስር ቤት ቅድስት ማሪናን ወደ
እሱ እንዲያመጧት ወታደሮቹን ባዘዘው መሠረት ይዘው ከፊቱ
አቆሟት ። የሆነውንም በማየትና ፍጹም ጤነኛ መሆኗን ሲያይ
እጅግ በጣም ተደነቀ ። እንዲህም አላት “ማሪና ዛሬ ጥንቆላሽ
ምስክር ሆነ ። አድምጭኝ ። አምላካችንን አምልኪ ፣ ብዙ ድንቅ
ነገር ይደረግልሻል ፣ የገባሁትንም ቃል እፈጽምልሻለሁ”
በአግራሞትም ቅድስት ማሪና ወደ ገዥውና ወደ ዲዳው ጣዖት
እያየች ቁርጥ የሆነውን ቃል እንዲህ ስትል ተናገረች “ እኔ
ሰማይና ምድርን የፈጠረ ፣ የሕያው እግዚአብሔርን ልጅ ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስን አምልካለሁ ፤ አልፈራህምና በእኔ ላይ
ልታደርግ የምትፈልገውን ሁሉ ማድረግ ትችላለህ” ። በዚህን
ጊዜ በቁጣ የተሞላው ገዥ ባለጎማ መንኮራኩር ላይ ሰቅለዋት
ሥጋዋን እንዲቆራረጥ አዘዘ ። ጭፍሮቹም በታዘዙት መሠረት
ሲፈጽሙ ሥጋዋ ግን ተከታትፎ ይወድቅ ነበር ። በአምላኳ ዘንድ
በሰማዕትነት የምታርፍበት ገና ስለሆነ እስከ ሞት ድረስ
የታመነችለት አምላኳ የተፈጨውን ሥጋ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ሕይወትን ሰጥቶ አስነሳው ። በቅድስት ማሪና ላይ ምንም ምን
ዓይነት ጉዳት ሳይታይባት በሕይወት መኖሯ ያበሳጨው ገዥ ወደ
እሥር ቤት ዳግመኛ እንዲወስዷት አዘዘ ። በእስር ቤት ሳለችም
ሰይጣን ሊፈታተናት ቀርቦ እንዲህ አላት “ማሪና ሆይ የገዥውን
ቃል ብታከብሪ ለአንቺ ሊያደርግ ያሰበውን መልካም ነገር
ታገኛለሽ እሱም በምድር ሁሉ ላይ ስምሽን ከፍ ከፍ ያደርገዋል”
ብሎ ሲነግራት ወጣቷ ብላቴናይቱ ቅድስት ማሪና ዲያብሎስ
መሆኑን አውቃ ወደ እሱ ዘንድ ሔዳ ፀጉሩን ያዘች ። የብረት
ዘንግም ይዛ እየመታች “ሰይጣን ሆይ ይህን ምክርህን አቁም”
በማለት ተናገረችው ። በሰው ልጆች ላይ የሚያደርገውን ሥራ
እስኪገልጥላት ድረስ እንዳይንቀሳቀስ በመስቀል ምልክት
አሰረችው ። ያንጊዜም በዘንጉ ስትመታው እንዲህ እያለ መናገር
ጀመረ “የምድራዊ ፍላጎትን መልካምም ይሁን ክፉ ፣ ዝሙትን ፣
ሐሰትን ፣ ሥርቆትን የማስፈጽመው እኔ ነኝ ። ካላሸነፍኩት
እንቅልፍና ስንፍናን በማምጣት እቃወመዋለሁ በዚህም እሱ
አይጸልይም አምላኩንም ስለኃጢአቱ ይቅርታ አይጠይቅም” ።
እስካሁን ድረስ እያደረገች ያለውንም ተጋድሎ በሰዎች አድሮ
የሚያመጣባት እሱ እንደሆነም ነግሯታል ። የ15 ዓመት ወጣት
ቅድስት ማሪና ዓለምን የሚያንቀጠቅጠውን አስጨናቂውን ጥንተ
ጠላት ከእግዚአብሔር ዘንድ ባገኘችው በአምላኳ ኃይል
አንቀጠቀጠችው ። በኃይልም ወደ እሷ ዳግም እንዳይቀርብ
በእግዚአብሔር ኃይል ፣ በክርስቶስ ስም አባረረችው ።
የቅድስት ማሪናን የእምነት አቋም የተመለከተውና የእምነት
ምስክርነቷ የሰማው ገዥው በቁጣ ቃል ወታደሮችን ክፉና አሰቃቂ
የሆነ ሥቃይን እንዲያሰቃዩዋት አዘዘ ። በወጣትነቷ የአምላኳን
ፍቅር በመከራ ልትገልጥ የታደለችውን ቅድስት ማሪናን ወታደሮቹ
በእንጨት ላይ አስረዋት ሰውነቷን በመቆንጠጫ ይሰነጣጥቁት
ነበር ። እሷ ግን ለሁልጊዜ “ወላጅ እንደሌላቸው ልጆች
አልተዋችሁም ወደ እናንተ እመጣለሁ” (ዮሐ.14፥18) ብሎ
የተናገረውን የአምላኳን ቃል በማስታወስ በእምነት ጸናች ።
ሰውነቷን በመቆንጠጫ ከሰነጣጠቋት በኋላ ከነደሙ ወደ እስር
ቤት ወሰዷት ። በመከራ ጊዜ የማይለየው አምላኳ በእስር ቤት
ሳለች መልአኩን ልኮ ፈወሳት ። በማግስቱም ከእስር ቤት
አውጥተው ከልብስ አራቁተዋት (እርቃኗን) ከግንድ ጋር በማስር
በእሳት አቃጠሏት ። እሷ ግን በመለኮታዊ ጥባቆት በሚደንቅ
ሁኔታ በሕይወት አለች ። እንዲህም ብላ ጸለየች ፦ “አምላኬ
ሆይ በአንተ ስም ወደ እሳቱ እንድገባ እንደፈቀድክልኝ ሁሉ
በጥምቀት ውኃ ውስጥም እንድገባ ፍቀድልኝ” ። በዙሪያዋ
ስቃይዋን ለማየት ከቆሙት መካከል ገዥው ነበርና “ውኃ” ስትል
ስለሰማ እርቃኗንም እንድትሆንና በትልቅ ድስት ውስጥ እርሳስና
ውኃን አንድ ላይ እንዲያፈሉና በዚያም ውስጥ እንዲጨምሯት
አዘዘ ። ቅድስት ማሪናም አምላኳን እንዲህ ስትል ጠየቀች
“ይህንን የጥምቀት ውኃ አድርግልኝ” ። ጌታችንም መልአኩን
በርግብ አምሳል ላከላት ።
+
እሷም በገንዳው ውስጥ “አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ
በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን” እያለች ተደፈቀች ። ከሰማይም
እንዲህ የሚል ድምፅ ተሰማ “ ማሪና ሆይ በጥምቀት ውኃ
ተጠምቀሻል” እሷም ተደሰተች ። በውኃ ውስጥም ሳለች ብርሃን
ቦታውን ሞላው ። ነጭ ርግብም በአፏ ወርቃማ አክሊል ይዛ
ከሰማይ ወረደች ። የታሰረችበትም ሰንሰለት ተፈታ ። በውኃ
ውስጥም ቅድስት ሥላሴን ታመሰግን ዘንድ ለምስጋና ቆመች ።
በሰውነቷም ላይ አንዳች የመቃጠል ምልክት ሳይኖር ተፈወሰች ።
በዚህ አምላካዊ ድንቅ ተአምር የዳነችውን ቅድስት ማሪናን
የተመለከቱት ሁሉ በማሪና አምላክ በማመን ከዚህ በኋላ
ክርስቲያን መሆናቸውን በድፍረት ሲናገሩ አገረ ገዥው በቁጣ
እንዲገደሉ ትእዛዘ በሰጠው መሠረት ከ15 ሺህ ሕዝብ በላይ
በዕለቱ ተገደሉ ። ቅድስት ማሪናም አንገቷ በሰይፍ ተሰይፎ
እንድትገደል ተወሰነ ።
አንገቷ እንዲሰየፍ በታዘዘው መሠረት ሰያፍይዋ አንገቷን ሊሰይፍ
ከከተማው ውጭ ይዟት ሔደ ። ሰያፊውም ወጣቷን ቅድስት
“እመቤቴ ማሪና ሆይ ብርሃናዊ አክሊልን የያዘ የጌታን መልአክ
አያለሁ” ብሎ ሲነግራት ቅድስት ማሪና “ጸሎቴን እስክጨርስ
ድረስ እባክህን ጥቂት ታገሰኝ” ብላ ከመለሰችለት በኋላ
እጆችዋንም ዘርግታ ያለማቋረጥ ጸለየች ። ከዚህም በኋላ
ሰያፊውን (የቅድስቲቱን አንገት ሚቀላውን/ የሚቆርጠውን) “በል
የወደድከውንና የታዘዝከውን መፈጸም ትችላለህ” ብላ አንገቷን
ሰጠች ። ነገር ግን ሰያፊው “ይህን አላደርገውም” ሲላት
ቅድስቲቱም የተዘጋጀለትን አክሊል እንዳያጣ ከማስጠንቀቅ ጋር
የታዘዘውን እንዲፈጽም “ይህን ካልፈጸምክ በእግዚአብሔር
መንግሥት ምንም ክብር የለህም ፣ ከእግዚአብሔር ክብር
ተካፋይ ልትሆን አትችልም” በማለት ነገረችው ። ያኔ ሰይፉንም
ወስዶ እሷ ከሰየፋት በኋላ “በቅድስት ማሪና አምላክ
በእግዚአብሔር አምናለሁ” ብሎ ራሱንም ሰይፎ ከጎኖ ወደቀ ።
በእግዚአብሔር ፈቃድ ቅድስት ማሪና በወጣትነቷ የሰማዕትነትን
አክሊል በ15 ዓመቷ ሐምሌ 23 ቀን ተቀዳጀች ። እግዚአብሔር
አምላክም ዛሬም በቅድስቲቱ ምልጃ ለሚታመኑ ሁሉ ብዙ ድንቅ
ተአምራትን ይሠራላቸዋል ። በስሟም በሽተኞችን ይፈውሳል ።
የዚህች ቅድስት ሰማዕት ልዩ ምልክት በስዕሏ ላይ እንደምናየው
“ሰይጣንን ጸጉሩን (ቀንዱን ፣ ጆሮውን) ይዛ በአንድ እጇ
የሰማዕትነት ምልክት የሆነውን የዘንባባ ዝንጣፊ ከመስቀል ጋር
ይዛ ነው ። ከዚህም በተጨማሪ የቅድስቲቱ ስም በግሪክኛው
ቋንቋ “H AGIA MARINA = = ኢ አጊያ ማሪና” የሚል ተጽፎ
ይገኛል ። ስለዚህ በአገራችን እየታተመ የሚወጣው ስዕል ላይ
“ክርስቶስ ሠምራ” ስለሚል ይህ ትክክለኛ እንዳልሆነና የክርስቶስ
ሠምራን ሕይወት ታሪክ ስንመለከት ሰይጣንን በእጇ እንዳልያዘች
ከመረዳታችንም ባሻገር በእድሜም ፣ በመልክም ፣ በትውልድ
አገርም የማይመሳሰሉ መሆናቸውን ልብ ይሏል ።
አምላከ ቅድስት ማሪና ከወደጁ በረከትን ያድለን
የሰማዕቷ የቅድስት ማሪና የጸሎቷ ኃይል ፣ የምልጃዋም በረከት
ዘውትር ከሁላችን ጋር ይሁን ።
+++
#ኢትዮጵያዊቷ_ጻድቅ_ቅድስት_ክርስቶስ_ሠምራ
✞
ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ የተወለደችው ከደጋ ክርስቲያን
ቤተሰቦች በብሔረ ቡልጋ ልዩ ስሙ ቅዱስ ጌየ በሚባልበት
አከባቢ ሲሆን የአባቷ ስም ደርሳኒ የእናቷም ስም ዕሌኒ ይባላል
። እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ የትዳር ሕይወትን
እስከምትይዝ ድረስ ቤተሰቦቿ መልካምና ፍጹም ክርስቲያናዊ
በሆነ አስተዳደግ ነበር ያሳደጓት ። ከቤተሰቦቿ ጋር በነበረችበት
ጊዜ ለምናኔ ሕይወት መሠረት የሆናትን ቅዱሳት መጻሕፍትን
በሚገባ ተምራለች ። ይህ መሠረት ሆኗት ከሠምረ ጊዮርጊስ
ጋር የመሠረተችው የትዳር ሕይወት አሥራ ሁለት ልጆችን
ከወለደች በኋላ ነበር ያላትን ሀብት ንብረት ጥላ አንድ ልጇን ይዛ
ለምናኔ የወጣችው ። ለምናኔዋ መጀመሪያ ገዳም ያደረገችው
ደብረ ሊባኖስን ሲሆን በዚያ ጽኑ ተጋድሎን ተጋድላለች ።
በገድሏ ላይ እንደተጻፈው የመጨረሻ ልጅዋ በመልአኩ እጅ
ወደሰማይ የተነጠቀው ከዚሁ ቦታ ነው ።
+
ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ በአምሳለ ኮከብ እየመራት
በጌምድር ወሰዳት ። በዚያም በባሕር ውስጥ ሰውነቷ የዓሳ
መመላለሻ እስኪሆን ድረስ ለአሥራ ሁለት ዓመት ጽኑ ተጋድሎን
ተጋድላለች ። በምድርም ላይ በቁመቷ ልክ ጉድጓድ አስቆፍራ
በአራቱም ማዕዘን ጦርን አስተክላ እንደሌባ የፍጥኝ በትእምረተ
መስቀል ታስራ ለአሥራ አንድ ዓመት በመጋደል በጸሎት ጸንታ
ቆመች ። በእነዚህ በተጋድሎዎቿ ወቅት ጌታችን እየተገለጠ
ያበራታታትና ያጽናናት እንደነበር ገድሏ ይናገራል ። ስሟም “በትረ
ማርያም” ተብሎ እንዲጠራም የሰየመው እሱ ነው ። እጅግ
የሚደንቀውና ከአምላኳ ዘንድ ሞገስን ያገኘችው የሁላችንን
ጠላት ጌታ እንዲታረቀው መለመኗ ነው ። ይህ ልመና ጌታችንን
አስደንቆታል ። ፈቃዷን እንዲፈጽም መልአኩን ከእሷ ጋር ወደ
ሳጥናኤል ዘንድ ልኮታል ። ምንም እንኳ ሰይጣን የመመለስ ልብ
ባይኖረውም ስትጠራው ጎትቶ ዐይኖቹ ውስጥ እንዳስገባት በኋላ
በእግዚአብሔር ቸርነት ከደበቀበት አውጥቶ ለቅዱስ ሚካኤል
እንደሰጠው በዚህም ብዙ ነፋሳትን ወደ ገነት ይዛ እንደገባች
ገድሏ ይናገራል ። በመጨረሻም እናታችን ቅድስት ክርስቶስ
ሠምራ ለ23 ዓመታት ጽኑ የሆነ ገድልን ተጋድላ ነሐሴ 24 ቀን
በክብር አርፋለች ። ይህም ሲሆን ገድሏን የጻፈው በጌታችን
ትእዛዝ ቅዱስ ሚካኤል ሲሆን ለ25 ዓመት እንደተጋደለች አድርጎ
እንዲጽፍ በታዘዘው መሠረት ገድሏን ጽፎ በዙሪያዋም 10
የብርሃን አክሊላትን አስቀምጦ የቅድስት ክርስቶስ ሠምራን ነፍስ
በይባቤ መላእክት በክብር አሳርጓታል ።
+
እንግዲህ ከታሪኩ እንደተረዳነው የእናታችን የክርስቶስ ሠምራ
ስዕል ከቅድስት ማሪና ዘአንጾኪያ ጋር የማይመሳሰል መሆኑን ነው። ከሁለቱ ቅዱሳን ገድል እንደተረዳነው የሰይጣንን ጆሮ ወይም
ጸጉር ይዛ የምትታየው ታናሽ ብላቴና የሆነችዋ የ15 ዓመቷ
ታላቅና ቅድስት ሰማዕት ማሪና ናት ። ኢትዮጵያዊቷ ጻድቅ
እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ግን ሰይጣንን ከጌታ ጋር
ለማስታረቅ ብትሞክርም አልተሳካላትም ። እሱ ይዟት ዐይኑ
ውስጥ ደበቃት እንጂ አልያዘችውም ። ነገር ግን በተጋድሎዋ
በክርስቶስ ኃይል አሸንፈዋለች ። ከዚህም በተጨማሪ ምንም
እንኳ የቅዱሳን መልክ በተጋድሎአቸው እንደ ፀሐይ የበራ
ቢሆንም የሁለቱንም መልክ በአገር ዜግነት ስንወስድ ፍጹም
የማይመሳሰሉ ናቸው ። የቅድስት ማሪናን ስዕል ቅድስት ክርስቶስ
ሠምራ ብሎ ማሳተም በራሱ ስህተት ነው ። ምክንያቱም ቅድስት
ማሪና ኢትዮጵያዊ መልክ የላትምና ። እናታችን ቅድስት ክርስቶስ
ሠምራ ግን በትውልዷ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ናት ። ስለሆነም
በአገራችን እየታተሙ የሚወጡት ቅዱሳት ስዕሎች ታሪካቸውን
የጠበቁና የስዕሉን ባለቤት በጥንቃቄ ሊገልጡ የሚችሉ ሆነው
ቢታተሙ ሰውን ከስህተት ስለሚያድን በተለይ በውጭው ዓለም
ተስለው የሚመጡት ቅዱሳት ስዕሎች ባለቤትነታቸውን ሊገልጡ
የሚችሉ ስም በተለያየ ቋንቋ የተጻፈ ስለሆነ ያንን የቋንቋውን
ባለቤት በማስነበብና ትርጉሙን በማወቅ ቢታተሙ መልካም ነው
እንላለን ። ይህ ከሆነ ከስህተታችን በመታረም የበለጠውን
በማድረግ ፣ ትውፊቱና ባህሉን ፣ መንፈሳዊ ምሥጢሩን ባለቀቀ
መንገድ በአገራችን የሚታተሙት ቅዱሳት ስዕላት ላይ ትኩረት
በመስጠት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚመለከታቸው ክፍሎች
ከመንፈሳዊ አባቶች ጋር በመወያየት ይበለጥ ግንዛቤን ልንወስድ
ይገባናል ።
+
የሰማዕቷ ቅድስት ማሪና (ማርግሬታ) ዘአንጾኪያ የሰማዕትነት በረከት ፣ የጻድቋ የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ምልጃዋ ዘውትር አይለየን ። ሃይማኖታችንን ከወራሪ መናፍቃን ፣ አገራችንን ከጠላት ወራራ ከመከራ ከሥቃይ ይጠብቅልን ለዘላለሙ አሜን።
ምንጭ:- ድንግል ማርያም መላዕክት ፃድቃን ሰማዕታት ያማልዱናል ፔጅ
፠፠፠፠፠
ቀደምት ሊቃውንት ሁለት ዓይን የተሰጠን በአንዱ የራሳችን በሌላው
የሌላውን ለማየት ነው፡፡ ሁለት ጆሮ የተሰጠን በአንዱ የራሳችንን
በሌላው የሌላውን ለመስማት ነው፡፡ ሁለት እጅ የተሰጠን በአንዱ
ለመስጠት በሌላው ለመቀበል ነው፡፡ ሁለት እግር የተሰጠን በአንዱ
ወደራሳችን በሌላው ወደ ሌላው ለመሄድ ነው ይሉ ነበር፡፡
፳፩ ፳፩ ፳፩ ፳፩ ፳፩
ቤተክርስቲያን ባህረ ጥበባት
አትመረመርም እጅግ ጥልቅ ናት
የሲኦል ደጆች አይችሏትም
ቤተክርስቲያን አትታደስም!
የሐዋርያት ጉባኤ ስለሆነች ስለአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰላም
እንማልዳለን!
(መጽሐፈ ሚስጢር)
የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን
መላእክት ተራዳኢነት፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት፣
የቅዱሳን አበው መነኮሳት፣ የቅዱሳት አንስት፣ የደናግላንና የቅዱሳን ሁሉ
ምልጃና ቃል-ኪዳናቸው ባለንበት ከሁላችን ጋር ይሁን!!!
†† † † ††
ለአባ ሕርያቆስ ፤
ለቅዱስ ኤፍሬም ፤
ለቅዱስ ያሬድ ፤
ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
ለአባ ይስሀቅ
የተገለጸች እመቤታችን እኛንም በበረከት እና በረድኤት ትጎብኘን ፤
ከልጅዋ ከወዳጅዋ ከመድኃኔዓለም ዘንድ ታማልደን ፤ አሜን!!!
†† † † ††
ከዋክብት የሚያመሰግኑት
በስማቸውም የሚጠራቸው:
የፀጋው ብዛት የማይታወቅ
ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ለሐዋሪያት
እንዲሁም ለቀደሙ አባቶቻችን ምሥጢሩን እንደገለጽክላቸው ለእኛም
ግለጽልን። አሜን አሜን አሜን!!!
†† † † ††
ወ ስ ብ ሐ ት ለ እ ግ ዚ አ ብ ሔ ር
ወ ለ ወ ላ ዲ ቱ ድ ን ግ ል
ወ ለ መ ስ ቀ ሉ ክ ቡ ር