ባሕረ ሐሳብን ማን ደረሰው? - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Wednesday, May 29, 2019

ባሕረ ሐሳብን ማን ደረሰው?


ባሕረ ሐሳብን ለማወቅ ብዙ አባቶች ተመኝተው ነበር። ይሁን እንጂ ሁሉ የሚሆነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና የመንበረ እስክንድርያ አስራ ሁለተኛ ሊቀ ጳጳስ ለነበረው ለቅዱስ ድሜጥሮስ ተጸልጾለታል። ድሜጥሮስ ማለት መስታወት ማለት ነው። መስታወት፦ በጥርስ ያለውን እድፍ በጸጉር ያለውን ጉድፍ እንደሚያሳይ ሁሉ ድሜጥሮስም የተሰወሩ በዓላትን እና አጽዋማትን አሳይቶናል፤ አንድም ድሜጥሮስ ማለት መነጽር ማለት ነው። መነጽር፦ የራቀውን አቅርቦ የረቀቀውን አጉልቶ የተበተነውን ሰብስቦ እንደሚያሳየው ሁሉ ድሜጥሮስም የራቁ አዝማናትን አቅርቦ የተበተኑ አጽዋማትን ሰብስቧልና  መስታወት ተብሏል።

                                                ቅዱስ ድሜጥሮስ

ድሜጥሮስ ባጭር ታጣቂ፣ እርፍ አራቂ፣ ዲኮ ታጣቂ፣ ነገር አዋቂ፣ ፍርድ ጠንቃቂ  መስተገብረ ምድር/ገበሬ/ ነበረ። በሞያው ምንም ዓይነት የቤተከርስቲያን ሞያ ያልነበረው ነገር ግን ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቆ የሚኖር ምዕመን ነበር። የድሜጥሮስ ኣባት ደማስቆ ወይም አስተራኒቆስ ይባል ነበር። ይህ የድሜጥሮስ አባት አርማስቆስ ወይም አስተራኒቆስ የሚባል ወንድም ነበረው። ይኖሩበት የነበረው ዘመን ዘመነ ሰማዕታት ስለነበረ ሁለቱ ወንድማማቾች ከሀገራቸው ተሰደው በባዕድ ሀገር ይኖሩ ነበር። በምድረ ዓላውያን ክርስቲያኖች ያነሱበት ዓላውያን የበዙበት ስለሆነ የድሜጥሮስ አጎት ከመሞቱ በፊት ሴት ልጁን  ለሌላ ለአሕዛብ እንዳይድርበት ለድሜጥሮስ አባት አምሎት ሞቶ ነበር። በኋላ ድሜጥሮስም ሆነ የአጎቱ ልጅ ስሟ ልዕልተ ወይን/የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የሚጠሩበት ስም ነው/ ለአቅመ አዳምና ለአቅመ ሔዋን ደርሰው ስለነበር ለሌላ ለአሕዛብ ድረናቸው ሕንፃ ሃይምኖት ከሚፈርስ ዘመዳሞችን አጋብተን ሕንፃ ስጋ /የዝምድና ግንኙነት/ ቢፈርስ ይሻላል በማለት ሁቱን አጋብተዋቸዋል። በጋብቻው ዕለት ስርዓተ መርዓት ወመራዊ ይፈጽሙ ብለው መጋረጃ ጥለውባቸው ሄደዋል። በዚህን ጊዜ ልዕልተ ወይን አምራ አለቀሰች። እንዲህም ብላ ጠየቀቸው፤ እኔን ንቀህ ነው? ወይስ ተዘምዿችንን? እንዴት አህትህ /የአጎትህ ልጅ/ ስሆን እኔን ታገባለህ? አለቸው። እርሱም እኔ አንቺንም ሆነ ተዘምዿችንን ንቄ አይደለም “አላ ከመ እፈጽም ፈቃደ አቡየ- ይልቁንም የአባቴን ፈቃድ ልፈጽም ብዬ ነው’ አላት። እንግዲያውስ ፈቃድሽ ከሆነ አንቺም ሴት እኔም ወንድ እንደሆንን በአዳማዊ ሩካቤ ሳንተዋወቅ መኖር እንችላለን። ለሌላም እንዳያጋቡን ባልን ሚስት መስለን በአንድ ላይ እንኑር አላት። እርሧም ደስ ብሏት ሀሳቡን ተቀበለች። ሁለቱም አንድ ምንጣፍ አንጥፈው፣ አንድ አንሶላ ተጋፈው እያደሩ በድንግልና አርባ ስምንት ዓመት ኑረዋል። ቅዱስ ሚካኤልም እንድ ክንፉን ለእርሱ አንድ ክንፉን ለእርስዋ እየጋረደ አድሮ በጠዋት በአምሳለ ርገብ በመስኮት ወጥቶ ሲሄድ ይታይ ነበር።

በዚህ ዘመን የመንበረ እስክንድርያ አሰራ አንደኛ ሊቀ ጳጳስ የነበረው ዩልያኖስ ወይም ዩልዮስ የተባለው ዕድሜው ገፍቶ አርጅቶ ስለነበር ሕዝቡን ሰብስቦ ከእኔ በኋላ የሚሾመውን ሰው ምረጡ አላቸው። ሕዝቡም ‘’አባታችን እኛ ምን እናውቃለን? አንተ ሱባዔ ገብተህ ጸልየህ ንገረን እንጂ’’ አሉት እርሱም “እናንተም ጸልዩ እኔም እጸልያለሁ” አላቸው። በሶስተኛው ቀን መልአከ እግዚአብሔር ለሊቀ ጳጳሱ ተገልጾ ያለጊዜው ያፈራ የወይን ዘለላ እና የስንዴ ዛላ ይዞልህ የሚመጣው  ከአንተ ቀጥሎ የሚሾመው አርሱ ነውና  እርሱን ሹመው ብሎ ነገረው። በዚህም ዕለት ቅዱስ ድሜጥሮስ እርሻውን ሊያቃና ወደ አዝመራው ሲገባ ያለጊዜው ያፈራ የወይን ዘለላ እና የስንዴ ዛላ አገኘ፤ ወስዶም ‘ለሚስቱ’ ሰጣት። እርሷም “ይህንን እኛ ልንመገበው አይገባም ይልቁንም ወስደህ ለቤተ እግዚአብሔር ሰጥተህ ከሊቀጳጳሱ በረከት ተቀበል’’ ብላ ላከቸው። እርሱም ይዞ ወደ ቤተ እግዚአብሔር ሲሄድ ሊቀ ጳጳሱም ሕዝቡን ሰብስቦ መልአኩ የነገረውን እየነገራቸው እያለ ድሜጥሮስ ገብቶ ስጦታውን ለሊቀ ጳጳሱ አበርክቶ ወጣ። ከወጣ በኋላ ሊቀ ጳጳሱ ለሕዝቡ ከእኔ ቀጥሎ የሚሾመው እርሱ ነው እሺ አይለችሁም ነገር ግን ግድ ብላችሁ አስቀምጡት ብሎ ነገራቸው።

ከጥቂት ቀናትም በኋላ ሊቀ ጳጳሱ አረፈ። ሕዝቡም  መንበር  ባዶውን አያድርምና ድሜጥሮስን ተሾምልን ብለው ጠየቁት። እርሱም ደንግጦ “እኔ በአንድ በኩል ምንም ያልተማርኩ /ጨዋ/ ገበሬ ነኝ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ያገባሁ ሕጋዊ ነኝ እንዴት በንጹህ በማርቆስ ወንበር እቀመጣለሁ? አላቸው። እነርሱም አንተ እንደምትሾም አባታችን ነግሮናል! በማለት ግድ ብለው አስቀመጡት። ከዚህ በኋላ ድሜጥሮስ ሕዝቡን አባታችን ምን ምን ያስተምራችሁ ነበር? ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም አላውቅም ብትለን ነው እንጂ አባታችንማ አንቀጸ ኖሎትን አንቀጸ አባግዕን ተርጉም ያስተምረን ነበር አሉት። በዚህን ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍት/ብሉያትና ሐዲሳት ተገልጸውለት አንቀጸ ኖሎትን አንቀጸ አባግዕን  ተርጉሞ ለሕዝቡ አስተምሯቸዋል።

ድሜጥሮስ እጅግ የበቃ ሰው ነበርና ቀድሶ ሲያቆርብ የሰው ኃጢአት ተገልጾለት ‘’አንተ ለስጋ ወደሙ በቅተሃል ቁረብ፣ አንተ አልበቃህም ተመለስ’’ ይል ነበር። በዚህን ጊዜ ሕዝቡ ‘’በንጹሑ በማርቆስ ወንበር ላይ ከነሚስቱ መቀመጡ አንሶት እርሱ እንዳንቆርብ ይከለክለን ጀመር’’ በማለት በሐሜት ወደቁ በዚህም የሚጎዱ ሆኑ። በዚህን ጊዜ መልአከ እግዚአብሔር ለድሜጥሮስ ተገልጾ ‘’ኢትፍቅድ አድኅኖ ርእስከ አላ ክሥት ዘሀሎ ምስሌከ ወማእከለ ብእሲትከ- በአንተና በእርሷ መካከል ያለውን ሚስጢር ግለጽ፤ ኖላዊሰ ኄር ዘይሜጡ ነፍሶ ቤዛ አባግዒሁ - እውነተኛ እረኛ ለበጎቹ እራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ነውና፤ እራስህን መግለጽ ውዳሴ ከንቱ አይሆንብህም’’ ብሎታል። ድሜጥሮስም መልአኩ እንዳዘዘው ሕዝቡን አንድ አንድ እንጨት ይዘው እንዲመጡ አዟቸዋል። በዕለተ ሰንበትም የተሰበሰበውን እንጨት እንደ መስቀል ደመራ አቃጥሎ ቅዳሴ ገባ። ከቅዳሴም ከወጣ በኋላ በሚነደው እሳት ውስጥ ገብቶ እየተመላለሰ ያጥን ጀመረ። ‘ሚስቱን’ ከምቋመ አንስት ጠርቶ ስፍሒ አጽፈኪ - ልብስሺን ዘርጊ ብሎ ከእሳቱ ፍም እየዘገነ በልብሷ ላይ አድርጎላታል። እርሷም በሕዝቡ መካከል ዞራ ብታፈሰው ከልብሷ ዘሃ አንዲት እንኳን አልጠቆረም። ሕዝቡም አባታችን ይህንን ያደረከው ለምንድን ነው? ብለው ጠየቁት። እርሱም እኔ እሾምበት እከብርበት ብዬ አይደለም ይልቁንም እናንተ በሐሜት እንዳትጎዱ በማለት መልአከ እግዚአብሔር ግለጽላቸው ስላለኝ ነው። ይህ እሳት እኔ እና እርሷን እንዳላቀጠለን ሁሉ ይህን ያህል ዘመን አንድ ምንጣፍ አንጥፈን አንድ አንሶላ ተጋፈን ስንኖር በአዳማዊ ግንኙነት /በሩካቤ / ሳንተዋወቅ እርሷ ሴት እኔም ወንድ እንደሆንን ነው የምንኖረው አላቸው። በዚህን ጊዜ ሕዝቡ “ኦ አቡነ ሥረይ ለነ ኃጢአተነ - አባታችን ሆይ ይቅር በለን” በማለት ከእግሩ ስር ወድቀዋል። እርሱም “ይፍታሕ ወይሥረይ ይኅድግ ወያንጽሕ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ” ብሎ ናዝዋቸዋል። ኑዛዜም በዚህ ጊዜ እንደተጀመረ አባቶቻችን ይናገራሉ።

ቅዱስ ድሜጥሮስ ከ180 ዓ.ም እስከ 222 ዓ.ም ወይንም እ.አ.አ ከ188 – 230 ድረስ ለአርባ ሁለት ዓመት በእስክንድርያ መንበር ላይ በሊቀ ጵጵስና ቆይተል። በዚህ ጊዜ አንድ ታላቅ ምኞትን ይመኝ ነበር። ይኸውም ጾመ ነነዌ፣ በአተ ዐቢይ  ጾም እና ጾመ ሐዋርያት ከሰኞ፤ በዓለ ርክበ ካህናት፣ ጾመ ድኅነት ከረቡዕ፤ በዓለ ዕርገት ከሐሙስ፤ በዓለ ስቅለት ከዐርብ፤ በዓለ ደብረ ዘይት፣ በዓለ ሆሣዕና ፣ በዓለ ትንሣኤ፣ በዓለ ጰራቅሊጦስ ከእሑድ ባይወጡ ባይነዋወጡ በጥንት ዕለታቸው ቢውሉ በወደድኩ ነበር እያለ ይመኝ ነበር። መልአከ እግዚአብሔር ተገልጾ ነገር በምኞት ይሆናልን? ሱባዔ ገብተህ አግኘው አለው። ከሌሊቱ ሃያ ስምንት ሱባዔ ገብተህ አበቅቴ ፤ ከቀኑ ሰባት ሱባዔ ገብተህ መጥቅዕ ይሁንህ ብሎ ነገረው። ምነው ቀኑን አብዝቶ ሌሊቱን አሳነሰው ቢሉ ቀን የተበደለ ሲያስክስ ፣ የተቀማ ሲያስመልስ የተራበ ሲያበላ፣ የተጠማ ሲያጠጣ፣ የታረዘ ሲያለብስ፣ የታሰረ ሲጎበኝ በአጠቃላይ ምግባረ ጽድቅ ሲሰራበት ይውላል። ስለዚህ ሌሊት ከእንቅልፉ  ቀንሶ እንዲጸልይበት አድርጎታል።

ሃያ  ሶስት ሱባዔ ማለት አንድ ሱባዔ ሰባት ቀን ነው፤ ሃያ ሶስቱ ሱባዔ /23 × 7/ = 161 ይሆናል። እዚህ ጋር የምናነሳው አንድ አዋጅ አለ።

አዋጅ፦ ማንኛውም ቁጥር ከሰላሳ ከበለጠ በአውደ ወር /በሰላሳ/ ግደፈው ወይም
         አካፍለው።

ስለዚህ መቶ ስልሳ አንድን በሰላሳ ስንገድፈው /161 ÷ 30/ = 5 ጊዜ ደርሶ 11 ይቀራል። ይህ አስራ አንድ ጥንተ አበቅቴ ይባላል። አበቅቴ ማለት ስፍረ  ሌሊት፣ ቁጥረ ሌሊት ማለት ነው።

ሰባት ሱባዔ ማለት /7 × 7/ = 49 ይሆናል። አርባ ዘጠኝን በሰላሳ ስንገድፈው /49 ÷ 30/ = 1 ጊዜ ደርሶ 19 ይቀራል። ይህ አስራ ዘጠኝ ጥንተ ጥንተ መጥቅዕ ይባላል። መጥቅዕ ማለት ደወል ማለት ነው። ደወል በተመታ ጊዜ የራቁ ይቀርባሉ፣ የተበተኑ ይሰበሰባሉ፤ እንዲሁም ሁሉ ይህ መጥቅዕ የበዓላትና የአጽዋማት መሰብሰቢያ ወይንም ማውጫ ነው።

ሁለቱን ማለትም አበቅቴና መጥቅዕ በአንድ ላይ ተደምረው ከሰላሳ አይበልጡም ከሰላሳ አያንሱም። መጥቅ ሲበዛ አበቅቴ ያንሳል፤ አበቅቴ ሲበዛ መጠቅዕ ያንሳል እንጂ ከሰላሳ አይበልጡም ከሰላሳም አያንሱም። እዚህ ጋር ሁለት አዋጆች አሉ። እነርሱም፦

 አዋጅ፦ 1. አበቅቴ ወመጥቅዕ ክሌሆሙ ኢየዓርጉ እም፴ ወኢይወርዱ እም፴ ወትረ ይከውኑ

           ፴ - አበቅቴና መጥቅዕ ከሰላሳ አይበልም ከሰላሳም አያንሱም ሁልጊ ሰላ  ናቸው።

          2.  ኢይኩን አሐደ ለመጥቅዕ - መጥቅዕ ምንም ያህል ቢያንስ አንድ አይሆንም።

 መጥቅዕ አንድ ሲሆን አልቦ ወይም ዜሮ አበቅቴ ይሆናል። በየአስራ ዘጠኝ ዓመቱ አበቅቴ ዜሮ ይሆናል። ምክንያቱን በተገቢው ቦታ ላይ ይብራራል።

ይቀጥላል… 

Post Bottom Ad