ቅድመ ድሜጥሮስ ሕዝቡ በዓላትን እንዴት ያከብር ነበር? - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Wednesday, May 29, 2019

ቅድመ ድሜጥሮስ ሕዝቡ በዓላትን እንዴት ያከብር ነበር?
እግዚአብሔር እምቅድመ ዓለም በልብ የመከረውን በነቢያት ያናገረውን ለመፈጸም በሥጋ ሰብዕ ተገልጿል/። በሥጋ ሰብዕም ተገልጾ ሕግ መጽሐፋዊ እና ሕግ ጠባይዓዊ ሲፈጽም አደገ። ሕግ መጽሐፋዊ ማለት በኦሪት እና በነቢያት ስለእርሱ የተጻፉትን እና የተነገሩትን መፈጸም ሲሆን ለምሳሌ።

·         በስምንት ቀን ቤተ ግዝረት ገብቶ መገዘር፣

·         በዐርባ ቀን ዕጉለ ርግብ ዘውገ መዕነቅ ይዞ ቤተ መቅደስ መግባት፣

·         በዓመት ሶስት ጊዜ ለገቢረ በዓል መውጣት “ለያስተርኢ ተባዕትከ ሠለስተ ጊዜያተ ለለዓመት” እንዲል፣

ሕግ ጠባይዓዊ ማለት በአንድ ሥጋ በለበሰ ሰው የሚንጸባረቁ ባሕርያት ሲሆኑ ለምሳሌ፦

·         በየጥቂቱ ማደግ “በበሕቅ ልሕቀ - በየጥቂቱ አደገ”

·         ለእናቱና ለቤተሰቦቹ መታዘዝ “እንዘ ይትኤዘዝ ለአዝማዲሁ- ለቤተሰቦቹ እየታዘዘ አደገ” እንዲል።
እንዲህ እንዲህ እያለ እስከ ሠላሳ ዓመት ድረስ ቆየ። በሠላሳ ዓመቱ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠመቀ። በዮርዳኖስም “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ወሎቱ ስምዕዎ - ይህ የምወደው ልጄ ነው።” በሚለው ቃል የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አስመስክሮ፤ አልዋለም፣ አላደረም፣ ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ ዐርባ ቀን ዐርባ ሌሊት ጾመ። መዋዕለ ጾሙ ሲፈጸም በሰይጣን በሶስት ነገሮች ይኸውም በስስት፣ በትዕቢት፣ በፍቅረ ንዋይ ተፈተነ። በስስት ቢመጣበት በትዕግስት፣ በትዕቢት ቢመጣበት በትህትና፣ በፍቅረ ንዋይ ቢመጣበት በጸሊዓ ንዋይ ድል ነሳው። ከዚህ በኋላ ምድረ እስራኤል ገብቶ ትምህርትን ማስተማር ተዓምራትን መስራት ጀመረ። የቃሉን ትምህርት የእጁን ተዓምራት አይተው ካስር አህጉር ከብዙ መንደር ተወጣጥተው ያምስት ገበያ ሕዝብ ይከተሉት ነበር። ከእነዚህም መካከል መቶ ሃያ ቤተሰቦችን መርጧል። እነዚህም አስራ ሁለቱን ሐዋርያት /ወረሰየ እምሰብአ ዚአሁ ሐዋርያተ - ከሕዝቡ መካከል ሐዋርያት አደረገ/፤ ሰባ ሁለቱን አርድእት /አርአየ ወኀረየ ካልዓነ ሰብአ - ሰባ ሁለቱንም አርድእት መረጠ/ ፤ በመጨረሻም ሠላሳ ስድስቱን ቅዱሳት አንስት መረጠ። ለእነዚህ መቶ ሃያ ቤተሰቦች ትምህርት አይከፈልባቸውም። ካደረበት ያድራሉ፣ ከዋለበት ይውላሉ።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሶስት ዓመት ከሶስት ወር ዞሮ ካስተማረ በኋላ መጋቢት 22 ቀን “ወበልዕዋ ለወለተ ጽዮን ነዋ ንጉስኪ ጻድቅ ወየዋህ ይመጽዕ ተጽዒኖ ዲበ አድግ ወዲበ ዕዋላ - ለጽዮን ልጅ እነሆ ንጉስሽ ጻድቅ እና የዋህ በአህያና በውርጫዋ ላይ ተጭኖ ይመጣል” ዘካ፤ 9፡9 የሚለውን የነቢይ ቃል ለመፈጸም በአህያ ተጭኖ ቤተመቅደስ የገባበት ቀን ነው። በመጋቢት 27 ቀን “በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት ዕትወለድ እምወለተ ወለትከ ወእድኅክ ውስተ መርኅብከ እትቤዘወከ በመስቀልየ ወበሞትየ - አምስት ቀን ተኩል ሲፈጸመም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ፣ ሞቼ፣ ተሰቅዬ አድንሃለው” /ቀሌምንጦስ/ ባለው አምላካዊ ቃሉ መሰረት በማዕከለ ምድር በቀራንዮ የተሰቀለበት “ወገብረ መድኃኒተ በማዕከለ ምድር - በዓለም መካከል መድኃኒትን አደረገ” የሚለው የተፈጸመበት፤ በመጋቢት 29 ቀን “ዘበሞቱ ለሞት ደምሰሶ  - በሞቱ ሞትን አጠፋልን” እንዲል ሙስና መቃብርን ድል አድርጎ የተነሳበት ቀን ነው። “እስመ ውእቱ ቀሰፈነ ወይፌውሰነ ወውእቱ አቁሰለነ ወይሴርየነ ወያሐይወነ በሰኑይ መዋዕል፤ ወአመ ሳልስት ዕለት ንትነሳእ። ወአመ ሳልስት ዕለት ሦጣ ለነፍሱ ውስተ ሥጋሁ - በሶስተኛው ቀን ነፍሱን ከሥጋው ጋር መለሳት፣ አዋሓዳት” የሚለው ትንቢት ተፈጽሟል።

 ስለዚህ ሕዝቡ እነዚህን ቀናት እየጠበቀ ሰኞም ቢውል ፣ ማክሰኞም ቢውል ያከብር ነበር። ማለትም ትንሣኤ /መጋቢት 29/ ሰኞም ቢሆን ማክሰኞም ቢውል በዋለበት ቀን አክብረው ይውላሉ። ነገር ግን ሐዋርያት “ኢይኩን በዓለ ትንሣኤ ዘእንበለ በዕለተ እሑድ - ትንሣኤ ከእሑድ በስተቀር እንዳይውል።” በማለት በዲድስቅልያ ደንግገዋል።

ባሕረ ሐሳብ ለሐዋርያት ተገልጿልን?

ከድሜጥሮስ በፊት ለሐዋርያት እንደተገለጸላቸው አባቶች ያስተምራሉ። ምክንያቱም ከርደተ መንፈስ ቅዱስ በኋላ ከእነርሱ የተሰወረ አንድም ነገር የለምና ነው። ከላይ እንደጀመርነው ጌታችን ከሙታን ተለይቶ ከተነሳ በኋላ መጽሐፈ ኪዳንን ለዐርባ ቀን ለሐዋርያት አስተምሯቸዋል። ጉባዔ ሰርቶ ያስተማራቸው ግን ሶስት ቀናት /የትንሳኤ ፣ የአግብኦተ ግብር ፣ በጥብርያዶስ/ ነው። በሌላው ቀን ለአንዱ፣ ለሁለቱ ፣ ወይም ለሶስቱ ሳይታይ አይውልም ነበር። በዐርባኛው ቀን “አንትሙሰ ንበሩ ሀገረ ኢየሩሳሌም እስከ ትለብሱ ኃይለ እምአርያም - እናንተ ግን ኃይልን ከሰማይ እስከምታገኙ ድረስ በኢየሩሳሌም ቆዩ” በማለት አዟቸው ወደሰማይ በግርማ መለኮት፣ በይባቤ መላእክት ወደሰማይ አርጓል። ባረገ በአስረኛው ቀን፣ ከሙታን በተነሳ በሃምሳኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን ሰደደላቸው። “እንዘ ጉቡዓን ውእቱ ውስተ አሐዱ ቤት ወረደ ላዕሌሆሙ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ከመ ዘእሳት ወተናገሩ በነገረ ኩሉ በሐውርት ከሰተ ሎሙ ኩሉ ምስጢራተ ምድር ዘበሰማያት - በአንድ ልብ በአንድ ቤት ተሰብስበው ሳሉ መንፈስ ቅዱስን በእሳት አምሳል ላከላቸው፤ በሰማይና በምድር ያለውን ምስጢር ሁሉ ገለጸላቸው።” ስለሚል ባሕረ ሐሳብም ተገልጾላቸዋል። ይህም ይታወቅ ዘንድ በዓለ ትንሣኤ ከእሑድ ውጪ እንዳይውል ደንግገዋል። ነገር ግን የትኛው እሑድ የሚለው ግን ልክ እንደ ድሜጥሮስ በተውሳክ ተቀምሮ ስላልተቀመጠ ሕዝቡ ከላይ ባየነው መልኩ በተለያ ሁኔታ ሲያከብር እስከ ድሜጥሮስ ድረስ ደርሷል።

ከበዓላቱም በተጨማሪ ዓመቱ እና ወሩ ሥርዓት በሌለው ሁኔታ እየተከተሉ ይኖሩ ነበር። ይኸውም ሶስት ወር ከአንድ ጳጉሜን /ዘጠና አንድ ቀን / ለማቴዎስ ፣ ሶስት ወር ከአንድ ጳጉሜን /ዘጠና አንድ ቀን / ለማርቆስ፣ ሶስት ወር ከአንድ ጳጉሜን /ዘጠና አንድ ቀን / ለሉቃስ፣ ሶስት ወር ከአንድ ጳጉሜን /ዘጠና አንድ ቀን / ለዮሐንስ አካፍለው፤ አምስተኛውን ጳጉሜን ከነግህ አስከ ቀትር ለማቴዎስ፣ ከቀትር እስከ ሠርክ ለማርቆስ፣ ከሠርክ እስከ መንፈቀ ሌሊት ለሉቃስ፣ ከመንፈቀ ሌሊት እስከ ነግህ ለዮሐንስ፤ ስድስተኛውን ጳጉሜን ለአራቱ መገብተ አውራኅ /ወቅት/ ሊቃነ ከዋክብት ማለትም ለናርኤል፣ ለብርክኤል፣ ለምልኤልና ለሕልመልሜሌክ ለእያንዳንዳቸው  አስራ አምስት ኬክሮስ /ስድስት ሰዓት/ እያካፈሉ ይኖሩ ነበር።

ቅዱስ ድሜጥሮስ አበቅቴና መጥቅዕ፣ የዕለት፣ የበዓላትና የአጽዋማት ተውሳክ ከተገለጸለት በኋላ በሰባት አዕዋዳት አውዶ በዘጠና አንድ ማኅተም አትሞ ለሶስቱ ሊቃነ ጳጳሳት፣ አራተኛ ለኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ ልኮላቸዋል። እነርሱም ለወንድማችን እጹብ ነገር ተገለጸለት ብለው በዓለ ትንሣኤን በአንድ ላይ በዕለተ እሑድ አክብረዋል።

ከድሜጥሮስ በኋላ ባሕረ ሐሳብ  ትምህርት እየተስፋፋ ሄዷል። በተለይም በአስራ ሶስተኛው ክፍለ ዘመን የነበረው አቡሻክር ወይም  ዮሐንስ ወልደ አቤልሄሬም የተባለ የግብጽ ዲያቆን በኋላም እንደመነኮሰ የሚነገርለት ሰው ነው። የድርሰት መጽሐፉ በስሙ ተሰይሞ አቡሻክር ወይም በተለምዶው አነጋገር አውሻኻር ተብሏል። መጽሐፍን በደራሲው ስም የመሰየም የቆየ ልማድ ስለነበረ ነው በስሙ የተሰየመው።

አቡሻኻር የባሕረ ሐሳብን ቀመር ብቻ ሳይሆን ስለ አዕጋረ ጸሀይ ፣ ምህዋረ ጸሀይ፣ ስለኬክሮስ፣ ኬንትሮስ፣ ስለ ሥነ ፈለክ፣ ሥነ ከዋክብት…ወዘተ የሚተነትን የጥበብ መጽሐፍ ነው። እንደ ዮሐንስ አቤልሄሬም አይሁን እንጂ የተለያዩ አባቶችና የኅብረተሰብ ክፍሎች በተወሰነ ደረጃ ተመሳሳይነት ያለው መጽሐፍ ጽፈዋል። እነዚህም፦

·         ሰዒድ ወልደ ጰጥሪቅ

·         መሀቡብ ወልደ መንጋ

·         ሰዒዳውያን አይሁድ /የአይሁድና የዐረብ ተወላጆች/

·         ዮሐንስ አፈወርቅ

·         ቄርሎስ ዘአንጾኪያ

·         ኤጲፋንዮስ ዘመንፈስ ቅዱስ

·          ጊዮርጊስ ወልደ አሚድ

·         ማርቆስ ወልደ ቀምበር ናቸው።         

በተለይም ጊዮርጊስ ወልደ አሚድ አጅግ የተቀናጀና የሚያስደስት መጽሐፍ በዘመን አቆጣጠር ላይ ጽፏል። ከሁሉም በተሟላ ሁኔታ የጻፈው ግን ዮሐንስ ወልደ አቤልሄሬም ወይም አቡሻኻር ወልደ አቤልሄሬም ነው። አቡሻኻር ማለት ወልደ ግሱጽ - የታረመ፣ የተቀጣ፣ በሥርዓት ያደገ ልጅ ማለት ነው። ይህ አባት ለሠላሳ ዘመን ሱባዔ ገብቶ ነገር ግን እግዚአብሔር ባወቀ ሠላሳውን ዓመት እንደ ሶስት ቀን አድርጎለት አቡሻኻርን ጽፏል። ለሠላሳ ዓመት በሱባዔ መቆየቱን ያወቀው እንኳን ከወጣ በኋላ ቤተሰቦቹ ናቸው የነገሩት። በተገለጸለትም መጽሐፍ ውስጥም የባሕረ ሐሳብን ቀመር በሚገባ ቀምሮታል።

እግዚአብሔር ቢፈቅድ በሚቀጥለው ጊዜ የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር መቼ ተጀመረ የሚለውን እንመለከታለን። ይቆየን

Post Bottom Ad