አባ ገዐርጊ - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Wednesday, May 29, 2019

አባ ገዐርጊ

Image may contain: 1 person
ግንቦት 18-ጌታችን መልአኩን ልኮ ‹‹ተጋድሎህ በመጠን ይሁን›› በማለት ተጋደሎውን እንዲቀንስ ያዘዘው አባ ገዐርጊ ዕረፍቱ ነው፡፡
+ ዳግመኛም ይኽች ዕለት ጌታችን መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት የላከባት ዕለት ናት፡፡ ይኸውም የክብር ባለቤት ጌታችን ካረገ በኋላ በ10ኛ ከትንሣኤውም በ50ኛ ቀን ለደቀ መዛሙርቱ ‹‹ከአብ የሚሠርጽ ሌላ አካላዊ ሕይወት ጰራቅሊጦስን እልክላችኋለሁ›› ብሎ ተስፋ እንደሰጣቸው በሐዋርያት ላይ አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ ወረደ፡፡
+ ሰማዕቱ ቅዱስ ሲኖዳ መታሰቢያው ነው፡፡
አባ ገዐርጊ፡- የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ ደጋግ ጻድቃን ናቸው፡፡ በአደገም ጊዜ የወላጆቹን በጎች የሚጠብቅ እረኛ ሆነ፡፡ ነገር ግን እርሱ የምንኩስናን ልብስ ይለብስ ዘንድ በልቡ ይመኝ ነበር፡፡ 14 ዓመትም በሆነው ጊዜ የእግዚአብሔር ጸጋ አነሳሳችውና በጎቹን ትቶ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሄደ፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣል›› እንዳለ (2ኛ ቆሮ 11፡14) አባ ገዐርጊ ወደ ገዳሙ እየተጓዘ ሳለ በሽማግሌ አምሳል ከይሲ ሰይጣን ተገለጠለትና ከዓላማው ሊያደናቅፈው ፈተነው፡፡ እንዲህም አለው ‹‹ልጄ ሆይ ስለ አንተ አባትህ ልብሱን ቀዶ አየሁት፣ የዱር አውሬ ነጥቆ የበላህ መስሎት አባትህ ያዝናል፣ ያለቅሳል፡፡ ተመልሰህ የአባትህን ልብ ልታጽናና ይገባሃል›› አለው፡፡ አባ ገዐርጊም ደንግጦ አንድ ሰዓት ያህል ሳይንቀሳቀስ ቆመመ፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ ‹‹ከእኔ ይልቅ አባት እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይባውም ደቀ መዝሙሬም ሊሆን አይችልም›› ብሏል ብሎ አሰበ፡፡ ማቴ 10፡37፡፡ ይህንንም ባሰበ ጊዜ ሰይጣን እንደጢስ ሆኖ ተበትኖ ጠፋ፡፡
አባ ገዐርጊም ሰይጣን እንደሆነ ዐወቀ፡፡ በዚያን ጊዜም አስቀድሞም ተገልጦለት የነበረው የብርሃን ምሰሶ ተገለጠለት፡፡ የእግዚአብሔርም መልአክ በመነኩሴ አምሳል ተገለጠለትና አብሮት ተጓዘ፡፡ መልአኩም አባ ገዐርጊን አባ አርዮን ገዳም አደረሰው፡፡ አባ ገዐርጊም ጽኑ ተጋድሎውን ጀመረ፡፡ በገዳሙ 14 ዓመት በታላቅ ተጋድሎ ሲኖር እህል አይቀምስም ውኃም አይጠጣም ነበር፡፡ ለ14 ዓመትም ከመቀመጥ በቀር ምንም አልተኛም፡፡ ከዚህም በላይ ተጋድሎውን በጨመረ ጊዜ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ ‹‹በመጠን ተጋደል›› ብሎታል፡፡ መልአኩም ተገልጦለት ‹‹‹ሥጋህ እንዳይደክም በመካከለኛ ተጋደል› ብሎሃል ጌታ›› ካለው በኋላ ሊሠራው የሚገባውን ሥርዓት ሠራለት፡፡ ሁልጊዜም እስከሚመሽ እንዲጾም፣ ትንሽም እንጀራን እንዲበላ፣ ከእራት ሰዓት እስከ መንፈቀ ሌሊት ስለሥጋው ዕረፍት እንዲተኛ በቀረው ሌሊት እስኪነጋ ተግቶ እንዲጸልይ ሥርዓት ሠራለት፡፡
መልአኩ በሠራለት በዚህ ሥርዓት መሠረት አባ ገዐርጊ ብዙ ዘመን ሲጋደል ከኖረ በኋላ በበረሃ ውስጥ ብቻውን ሊኖር ወዶ በጫካ ውስጥ እየተመላለሰ ሁለት ዓመት ተቀመጠ፡፡ ነገር ግን ጌታችን ተገልጦለት ወደ ቀደመ ቦታው እንዲመለስ አዘዘው፡፡ ደብሩም ከከበሩ መክሲሞስ ዱማትዮስ ገዳም አጠገብ ነበር፡፡ ወደ ደብሩም በተመለሰ ጊዜ አብርሃም ከተባለ ደገኛው ጋር ተገናኙና ሁለቱም በጋራ ለመኖር ተስማምተው ወደ አስቄጥስ ገዳም አበ ምኔት ወደ አባ ዮሐንስ ዘንድ ሄዱ፡፡ እርሱም ቦታ ሰጥቷቸው በውስጧ በተጋድሎ መኖር ጀመሩ፡፡ ያችም ቦታ እስከዛሬ ታውቃ ትኖራለች፡፡ ስሟም በግቢግ ትባላለች፡፡ እርሷም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጣሪያዋን ሰንጥቆ ወደ እነዚህ ሁለቱ ቅዱሳን የወረደባት ቅድስት ቦታ ናት፡፡ እነርሱም በክብር ሰገዱለት፡፡ ጌታችንም ባርኳቸውና አጽናንቷቸው ዐረገ፡፡ በዚያችም ጌታችን በወረደባት መስኮት ብርሃን ተመለከቱ፡፡ እስከዛሬም ድረስ የተከፈተች ሆና ትታያለች፡፡ እነዚህም ሁለት ቅዱሳን ለመኮሳት የሚሆኑ ብዙ ድርሳናትንና ተግሣጻትን ደረሱ፡፡ ከዚህም በኋላ አባ አብርሃም ጥር 2 ቀን ዐረፈ፡፡ ከእርሱም በኋላ አባ ገዐርጊ በ72 ዓመቱ ግንቦት 18 ቀን በሰላም ዐረፈ፡፡ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡
+ + + + +
ሰማዕቱ አቡነ ሲኖዳ፡- ሀገራቸው ግብፅ ብሕንሳ ነው፡፡ መጽሐፍ ሰማዕትም ጻድቅም ይላቸዋል፡፡ ሽኖዳ እየተባሉም የሚጠሩ ሲሆን የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የአክስት ልጅ ናቸው፡፡ ሙሉ ዕድሜያቸውን በገዳም ነው የኖሩት፡፡ በማርቆስ መንበር ላይ ተሹመው በፓትርያርክነት እያገለገሉ እያለ በዘመናቸው ከሃዲው ንጉሥ መክስምያኖስ ነግሦ ስለነበር ክርስቶስን በማመናቸው እጅግ ብዙ አሠቃይቷቸዋል፡፡
ከሃዲው ንጉሥ መክስምያኖስ ወደ እርሱ እንዲመጡ ካደረገ በኋላ በእርሱ ጣዖት እንዲያምኑ ጠየቃቸው፡፡ አቡነ ሲኖዳም በክርስቶስ እንደሚያምኑ ሲነግሩት በምድር ላይ ደማቸው እንደ ውኃ እስኪፈስ ድረስ ጽኑ ግርፋትን አስገረፋቸው፣ ዐይናቸውም ሊወጣ ደረሰ፡፡ በእሥር ቤትም ከጣሏቸው በኋላ የታዘዘ መልአክ መጥቶ ከቁስላቸው ፈውሶ አበረታቸውና ገና እንደሚጋደሉ ነገራቸው፡፡ ንጉሡም ‹‹ሞቶ እንደሆን እዩት›› ብሎ ወታደሮቹን ቢልክም ፍጹም ጤነኛ መሆናቸውን ነገሩት፡፡ ልብሳቸውንም አስወልቆ አይቶ ካረጋገጠ በኋላ ‹‹ታላቅ ሥራይ ነው›› በማለት ዘቅዝቀው እንዲሰቅሏቸውና ከሥር እሳት እንዲያነዱባቸው አዘዘ፡፡ ይህንንም በአባታችን ላይ አደረጉባቸው፡፡ አሁንም ምንም ዓይነት ሥቃይ እንዳልገደላቸው ባየ ጊዜ በብዙ ካሠቃያቸው በኋላ መጋቢት 14 ቀን አንገታቸውን በሰይፍ አስቆርጦታል፡፡ ይኽችም ዕለት መታሰቢያ በዓላቸው ናት፡፡
ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን!

Post Bottom Ad