ደገኛው የሰላም አባት ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ዐረፉ - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Wednesday, May 29, 2019

ደገኛው የሰላም አባት ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ዐረፉ

  • ሥርዓተ ቀብራቸው፥ ማክሰኞ፣ ግንቦት 20፣ በ7፡00 በመካነ ሰማዕት ቅ/ገላውዴዎስ ይፈጸማል
source = haratewahido
ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ: የሰሜን ጎንደር ሀገረ   ስብከት ሊቀ ጳጳስ(ከ1927-2011 ዓ.ም.)
His Grace Abune Elsae
***
ቤተ ክርስቲያናችን፣ በሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ፣ ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም. የሾመቻቸው ኤጲስ ቆጶሳት ብዛት፣ የመንበረ ፕትርክናውን ነፃነት ከተቀዳጀች በኋላ ከፍተኛውን ቁጥር የያዘ እንደነበር፣ በወቅቱ ለበዓለ ሢመቱ የተሠራጨው መጽሔት ገልጿል፡፡ “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በአንድ ጊዜ ይህን ያህል ኤጲስ ቆጶሳትን ስታስመርጥ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ከፍተኛውና የመጀመሪያው ነው፤” በማለት፣ የአመራረጣቸውን ኹኔታ በገለጸበት ጽሑፉ አስፍሮ ነበር፡፡

ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ በቀድሞው ስማቸው መምህር ቆሞስ አባ ኅሩይ ፈንታ፣ ከፊት ከቆሙት ተሿሚ ቆሞሳት፣ ከግራ ወደ ቀኝ አራተኛው ናቸው፡፡
ከ40 ዓመት በኋላ ዛሬ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ አባልነት ካሉን 70 ያኽል ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ውስጥ፣ በሹመት ቀዳሚዎቹ፣ በተጠቀሰው ዓመት የተቀቡቱ ሲኾኑ፣ አረፍተ ዘመን እየገታቸው እየተለዩን ናቸው፡፡ ከምስሉና ከዝርዝራቸው ለመረዳት እንደሚቻለው፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስንና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ጨምሮ በዐጸደ ሥጋ የቀሩን የዘመኑ ተሿሚ አባቶች ከሦስት አይበልጡም፡፡ ከእኒህ አንጋፋዎች አንዱ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ ትላንት ቅዳሜ፣ ከቀኑ 11፡30 ላይ በሞተ ዕረፍት ተለይተውናል፡፡
Tir 13 1971 Yeteshomut 13tu Episkoposatበፊት ስማቸው መምህር ቆሞስ አባ ኅሩይ ፈንታ በኋላ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ ነባሩንና ትውፊታዊውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት እንደ ንህብ የቀሰሙ፤ ቢዘምሩ ቢቀድሱ፣ ቢሰብኩ ቢናገሩ፣ ቢተቹ ቢፈርዱ የሚያምርባቸው፤ ሊቅነት ከደግነት የተባበረላቸው ሙሉ አባት ነበሩ፡፡
2 - Copyበዕለተ ሢመታቸው በወጣው መጽሔት እንደሰፈረው፣ ዕድሜአቸው ለትምህርት እንደ ደረሰ፣ በተወለዱበት ደብር በመካነ ሰማዕት ቅዱስ ገላውዴዎስ የድጓ መምህር ከነበሩት መምህር ሙሉጌታ ኀይሉ የቃል ትምህርት እና ጾመ ድጓ ተምረዋል፡፡ ከዚያም ወደ ሸዋ ክፍለ ሀገር መጥተው በደብረ ብርሃን አውራጃ በናስ ማርያም ከአለቃ ቤተ ማርያም ድጓ፣ በምግልዋሻ ገብርኤል ከአለቃ ኀይለ ጊዮርጊስ ቅኔ ተምረዋል፤ እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች ከሚገኙ ልዩ ልዩ መምህራን ዘንድ እየተዘዋወሩ አቋቋም እና ቅኔ ተምረዋል፡፡ ድጓውንና ዝማሬ መዋስዕቱን ጽፈው አመልክተው በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡
ቀጥሎም በደብር ቅዱስ ደብረ ጽጌ ማርያም ገዳም ከመምህር ገብረ ሕይወት ሐዲስ፥ ፍትሐ ነገሥት፣ ትርጓሜ ዳዊት፣ ኪዳን፣ ትምህርተ ኅቡአት፣ ባሕረ ሐሳብ፣ የውዳሴ ማርያም እና የቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ ተምረዋል፡፡ እንዲሁም ከአለቃ መርዓዊ ዝማሬ መዋሥዕት፣ ከአለቃ አፈ ወርቅ ዜማን በማሻሻል፣ ከመሪጌታ ልዑል ቅዳሴ፣ ከመሪጌታ ቀለም ወርቅ ተምረዋል፡፡
ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል በ1945 ዓ.ም. ዲቁና፣ በ1964 ዓ.ም. በደብረ ሊባኖስ ገዳም ምንኩስናን ተቀብለዋል፡፡ በ1965 ዓ.ም. ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል ቅስና፣ በ1969 ዓ.ም. ከብፁዕ አቡነ ሰላማ ቁምስናን ተቀብለዋል፡፡ በአገልግሎትም ረገድ፥ በደብር ቅዱስ ደብረ ጽጌ ማርያም ገዳም፣ በትምህርት ላይ እንዳሉ፥ በቅዳሴ፣ በመዘምርነትና በልዩ ልዩ የገዳም ሥርዓቶች፣ ለዐሥራ አምስት ዓመታት ያኽል አገልግለዋል፡፡ ለኤጲስ ቆጶስነት ማዕርግ የተመረጡት፣ በጋሞጎፋ ክፍለ ሀገር በመምህርነት በማገልገል እንዳሉ ነበር፡፡
ጥር 8 ቀን 1971 ዓ.ም.፣ በመንበረ ፓትርያርኩ የተካሔደው ምርጫ፣ ከ14ቱም ክፍለ ሀገር እና ከአዲስ አበባ፣ በካህናትና በምእመናን የተወከሉ መራጮች የተሳተፉበት እንደነበር የጠቀሰው መጽሔቱ፣ ከቀረቡት 21 ቆሞሳት 12ቱ በድምፅ ብልጫ ማለፋቸውንና በሰሜን አሜሪካ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን በከፍተኛ ድምፅ የተመረጡት አባ ላዕከ ማርያም ማንደፍሮ በኋላ ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ ተጨምረው በጠቅላላ 13 አባቶች ለሢመተ ጵጵስና መቅረባቸውን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የለውጥ ትግል የምታደርግበት ወቅት እንደኾነና ትጋት ባለበት መንፈሳዊ አመራር፣ ካህናትንና ምእመናንን በሰበካ ጉባኤ አደራጅታ የራስዋን ችግር በራስዋ በማስወገድ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን ለመወጣት፣ የእኒህ 13 ኤጲስ ቆጶሳት መመረጥ፣ ለዚህ ዓላማና ተግባር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው መጽሔቱ አትቷል፡፡ ተሿሚዎቹ ቆሞሳት፥ ስለ ኤጲስ ቆጶስነት ሓላፊነትና ተልእኮ፣ ስለ ስብከተ ወንጌል መስፋፋት፣ ስለ ሰበካ ጉባኤ መጠናከር፣ ቤተ ክርስቲያን ለወጣቶች ማድረግ ስላለባት መልካም አቀባበልና ስለ ዓለም አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነትና ስለሌላው የቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ይዘት፣ የሦስት ቀናት ውይይት ማድረጋቸውን አስታውቋል፤ በዓለ ሢመቱም፣ ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም. መፈጸሙን ዘግቧል፡፡

በጅማ ሀገረ ስብከት ኤጲስ ቆጶስነት የተሾሙት ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ ለ41 ዓመታት በዘለቀው አባታዊ አገልግሎታቸው፣ የተጠሩበትን ሐዋርያዊ ተልእኮ በአግባቡ ለመፈጸም፥ ከተማውንና ገጠሩን፣ ደጋውንና ቆላውን ሳይመርጡ በበቅሎ ሳይቀር ወጥተዋል፤ ወርደዋል፤ ጅማን ጨምሮ በካፋ እና ደቡብ ጎንደር እንዲሁም እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው በሰሜን ጎንደር አህጉረ ስብከት፣ ከቅኔ ማሕሌት እስከ ዐውደ ምሕረት፣ ከቢሮ እስከ ዐደባባይ በትጋትና በደግነት አገልግለዋል፤ በሊቅነትና በጥብዓት እየመሩ አስተዳድረዋል፡፡
60897572_10157137184711411_5852031840042352640_n
በተለይም ከ1986 ዓ.ም. አንሥቶ፣ በግፍ እስር ታፍነው የሚገኙትን ሊቁን እንደሥራቸው አግማሴን ለማስፈታት ቅዱስ ሲኖዶስንና መንግሥትን ሳይሰለቹ በመወትወትና በሀገረ ስብከታቸው የሚፈጸሙ ኢሰብአዊ ተግባራትን በመቃወማቸው ምክንያት፣ በኮማንድ ፖስት እስከ መታሰርና በተለያየ መልክ የሚገለጽ መገፋት የደረሰባቸው መኾኑ የሚታወስ ነው፡፡ በታኅሣሥ ወር 2006 ዓ.ም.፣ “አራቱ ኀያላን” የተሰኘውን መጽሐፉን በጎንደር ባስመረቀበት መርሐ ግብር ላይ፥ “ሙሐዘ ጥበባት” የሚለው ስመ ማዕርግ ከብፁዕነታቸው የተሰጠው ጸሐፊ እና የነገረ ቤተ ክርስቲያን ተመራማሪ ዲን. ዳንኤል ክብረት፣ ሃይማኖት፣ ዕውቀትና ጥብዓት አንድም ሦስትም ኾነው የተገለጡባቸው ደገኛ አባት ነበሩ፤ በማለት ከዘመኑ ሐዋርያ የሚጠበቅ የተሟላ አገልግሎት ለቤተ ክርስቲያን ማበርከታቸውን መስክሯል፡፡
ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ዘመነ ክህነት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የካህናት የበላይ ጠባቂ ኾነው ሠርተዋል፡፡ የራብዓይ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ እና የስድስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የፕትርክና ምርጫ በተከናወነበት ወቅት፣ በዕጩነት ከቀረቡት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትም አንዱ ነበሩ፡፡
በቀድሞው አጠራር ጎንደር ክፍለ ሀገር፣ ደብረ ታቦር አውራጃ በመካነ ሰማዕት ቅዱስ ገላውዴዎስ ደብር፣ ከአባታቸው አቶ ፈንታ ወልድየ እና ከእናታቸው ወ/ሮ ወለተ ተክለ ሃይማኖት፣ ግንቦት 29 ቀን በ1927 ዓ.ም. የተወለዱት ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት፣ በአዲስ አበባ አዲስ የልብ ሕሙማን ማእከል እና በባሕር ዳር ጋምቢ ሆስፒታል፣ በመጨረሻም፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል በሕክምና ሲረዱ ቆይተው፣ ግንቦት 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ሠርክ ላይ በተወለዱ በ84 ዓመት ዕድሜአቸው ዐርፈዋል።
የብፁዕነታቸው አስከሬን፣ ነገ ሰኞ፣ ግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ በጎንደር ከተማ መስቀል ዐደባባይ አሸኛኘት ይደረግለታል። ማክሰኞ፣ ግንቦት 20 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ በኑዛዜ ቃላቸው መሠረት፣ በተወለዱበት ደራ ወረዳ አፈር ውኃ እናት መካነ ሰማዕት ቅዱስ ገላውዴዎስ ቤተ ክርስቲያን፣ በ7፡00 ይፈጸማል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ላይ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
የብፁዕ አባታችን በረከታቸው ይድረሰን፡፡

Post Bottom Ad