በየክልሉ በቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች ሪፖርት ቅዱስ ሲኖዶስን አስቆጣ፤ ባለሥልጣናትን ጠርቶ ለማነጋገር ምክክሩን ቀጥሏል - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Friday, May 24, 2019

በየክልሉ በቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች ሪፖርት ቅዱስ ሲኖዶስን አስቆጣ፤ ባለሥልጣናትን ጠርቶ ለማነጋገር ምክክሩን ቀጥሏል

Source = Haratewahido ሐራ ዘተዋሕዶ
የጅማ፣ የኢሉ አባቦር፣ የሰ/ሸዋ፣ የሰላሌ፣ የወለጋ፣ የአሶሳ ሪፖርቶች “ትኩሳት ፈጥረዋል፤”
በስለት አርዶና በጥይት ደብድቦ መግደል፣ንብረት መዝረፍና ማቃጠል፤ማሣቀቅ፤ማፈናቀል፤
የይዞታ መንጠቅ፣ ለተበደሉት ፍትሕ መንፈግ፣ በተለያዩ መደለያዎች እምነትን ማስለወጥ፤
ለባለሥልጣናቱ በሚቀርቡ ጉዳዮች ላይ እየተወያየ ነው፤ በጠቅ/ሚኒስትሩ በኩል ይጠራሉ፤
የሰላም እና የትምህርት ሚ/ሮች፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የክልል መስተዳድሮች ይገኙበታል፤
የጅማ እና የኢሉ አባቦር አህጉረ ስብከት የተለያዩ ወረዳዎች ሪፖርቶችን ይመልከቱ፤
***

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ በተለያዩ አካባቢዎች፣ በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ እየተፈጸሙ ስለሚገኙ ግፎች፣ ትላንት የጀመረውን ውይይት ዛሬም ቀጥሏል፡፡ “ስለ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ችግር ጉዳይ” በሚል በአጀንዳ ተ.ቁ(3) በቀጠለው በዛሬ ዓርብ፣ ግንቦት 16 ቀን 2011 ዓ.ም. የቀትር በፊት ስብሰባው፣ ከየአህጉረ ስብከቱ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቀረቡ ሪፖርቶችን አድምጧል፡፡

ጎሣ ተኮር በኾነና በቤተ ክርስቲያን ጥላቻ ላይ ተመሥርተው በተፈጸሙ ጥቃቶች፥ የተገደሉና የተፈናቀሉ ካህናትና ምእመናን፣ የተመዘበሩና የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት ሪፖርት በየአህጉረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት በዝርዝር ቀርቦ ተሰምቷል፡፡ በጅማ፣ በኢሉ አባቦር፣ በምዕራብ ወለጋ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በሰሜን ምዕራብ ሸዋ – ሰላሌ፣ በድሬዳዋ አህጉረ ስብከት፣ በተለያየ ደረጃ የደረሱ ጥቃቶች በሪፖርቱ ተካተዋል፡፡

ግጭቶችን ሽፋን በማድረግና በቀጥታ የደረሱት ጥቃቶች ዘግናኝነት እንዲሁም፣ በአንዳንድ ምእመናን ላይ ከኢትዮጵያዊ ባህል ውጭ በአስከሬናቸው ሳይቀር የተፈጸመው ግፍ፣ የምልኣተ ጉባኤውን አባላት አስቆጥቷል፡፡ “ትኩሳት ፈጥሯል” በማለት የገለጹ አንድ ብፁዕ አባት፣ በየክልሉ፣ የቤተ ክርስቲያንና የምእመናን መብቶች በግላጭ እየተረገጡ መኾኑ ቅዱስ ሲኖዶሱን በእጅጉ ማሳዘኑን ተናግረዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ በጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳናቸው እንዳሉት፣ የቤተ ክርስቲያን ሐዊረ ፍኖት ጸዊረ መስቀል እንደ መኾኑ በፈተና የተሞላ ቢኾንም፣ ከመቸውም ጊዜ በላይ ራስን የመከላከል አስፈላጊነት በቅዱስ ሲኖዶሱ ታምኖበታል፡፡ በግጭቶች እና ጥቃቶች ገፈት ቀማሾቹ እኛው ብንኾንም፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጉዳዩን የተመለከተው፣ ከአጠቃላይ አገራዊ ሰላምና አንድነት መጠበቅ አኳያ እንደኾነ የተናገሩት ብፁዕ አባት፣ “ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን የምንታደግበትን፣ ችግሩን ለዘለቄታው የምንቋቋምበትን ስትራተጂ እንነድፋለን፤” ብለዋል፡፡

ከዚያ በፊት ግን፣ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የፌዴራል መንግሥት እና የክልሎች መስተዳድሮች፣ እየደረሰብን ያለውን ግፍ ጥልቀትና ምሬት ማሳወቅና ለመፍትሔውም ፊት ለፊት ማነጋገር እንደሚያስፈልግ፣ በዛሬው ውይይት አቋም መያዙን ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት፣ ኹኔታውን በዝርዝር በማብራራትና የቀረቡትን ሪፖርቶች በአስረጅነት በማስደገፍ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥያቄ ለማቅረብና በእርሳቸውም አማካይነት ይመለከታቸዋል የተባሉ አካላት ተለይተው ጥሪ እንዲደረግላቸው ምልአተ ጉባኤው ተስማምቷል፡፡ የቀትር በኋላ ውሎውም፣ ለሰነድ ዝግጅቱ ግምገማ ትኩረት እንደሚሰጥ ተጠቁሟል፡፡

‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡

በጅማ እና በኢሉ አባቦር አህጉረ ስብከት በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ የተፈጸሙ ግፎች

በጅማ ሀገረ ስብከት፡-

በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ፣ በአሕዛብ እየተፈጸመ ያለው በደልና ግፍ ከዚኽ በታች በጥቂቱ ተዘርዝሯል፡፡

ሊሙ ኮሳ ወረዳ፡- በወረዳው ያሉት ክርስቲያኖች ከዐፄ ኀይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ በሠፈራ መኖር የጀመሩ፤ በኋላም በደርግ ጊዜ ወታደር የነበሩትም ሲኖሩበት ቆይተዋል፡፡ በሊሙ ኮሳ ወረዳ፣ በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ ብቻ፣ ዘር ተኮርና የሃይማኖት ጥላቻ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያንን የማጥፋት ዘመቻ በስፋት እየተካሔደ ይገኛል፡፡

ይኸውም፣ ክርስቲያኑን እየነጣጠሉ በየቀኑ በየጫካው መግደልና ብዙዎች አካባቢያቸውን ለቅቀው እንዲሰደዱ የተለያዩ ዛቻዎችን ማድረስ ናቸው፡፡ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ካሉት ወረዳዎች፣ በሊሙ ኮሳ ወረዳ ብቻ፣ ከ2009 – 2011 ዓ.ም. ድረስ ከተፈጸሙት አሠቃቂ ግድያዎች፣ ዝርፊያዎችና የቤት ቃጠሎዎች ውስጥ ለአብነት ያህል የሚከተሉት ተጠቅሰዋል፡፡

1. በሊሙ ኮሳ ወረዳ ጋሌ ሠርጤ (ቡርቃ ጉዲና እና አዲስ ልማት) ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ በሚገኙ ክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመ ግፍ፡-

ከመጋቢት 5 ቀን 2010ዓ.ም. እስከ ሚያዝያ 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ፣ ከ15 በላይ ክርስቲያኖች በአሠቃቂ ኹኔታ ተገድለዋል፡፡ እየደረሰ ባለው ግድያ፣ ዝርፊያ፣ የቤት ድብደባና ዛቻ ምክንያት፣ 185 አባወራ እና 13 ቀሳውስትና ዲያቆናት በድምሩ 198 አባወራዎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ተሰደዋል፡፡
አቶ ገበየሁ ወርቅነህ የሚባሉ፣ ብዙ ጋሻ መሬት የነበራቸው ታዋቂ ባለሀብትና ቀደምት የአካባቢው ነዋሪ፣ ልጆቻቸውን ኹሉ እዚያው ወልደው፣ ድረው፣ የልጅ ልጅ አይተዋል፡፡ ኾኖም አሁን፣ ንብረታቸውን ኹሉ ትተው፣ ቤታቸውን ዘግተው ወጥተው ተሰደዋል፤ እንደ እርሳቸው ኹሉ ሌሎች ብዙ ንብረት ያላቸውም ተሰደዋል፡፡
በ2009 ዓ.ም. ብዙአየሁ አየለ የሚባል ክርስቲያን ጫካ ውስጥ ሞቶ ተገኝቷል፤ እንዴትና በምን ምክንያት ሞቶ እንደተገኘ ስላልታወቀ እንዲሁ ተቀበረ፤ ትጉህ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ነበረ፡፡ በዚያን ጊዜ በሃይማኖት ልዩነነት ምክንያት መኾኑን ማንም አልተገነዘበም ነበር፡፡ ደም በአፍንጫው ይፈስስ ነበር እንጂ አሟሟቱ ባለመታወቁ ወደ ጅማ ሆስፒታል ለምርመራ ተልኮ ነበር፡፡
ጥር ወር 2010 ዓ.ም.፣ የአቶ ጉባይ አደራው ቤትን ሌሊት በመስበር ወደ ውስጥ ሲገቡ ራቁቱን በውስጥ ሱሬ ብቻ ኾኖ በመውጣት ሩጦ አምልጧል፡፡ እርሱን ለመምታት ሲታኮሱ እርስ በርስ ስለተመታቱ (አንዱ እጁ ላይ ተመትቷል)፣ “እርሱ ነው እንዲህ ያደረገን” በማለት ቤቱ ውስጥ ያለውን ንብረት አውድመው ቤተሰቡን አሳድደዋል፡፡ የተመታው ላይ ትኩረት ሲያደርጉም፣ ሚስቱና ልጆቹ ወጥተው ተሰውረዋል፡፡ ጥሩ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የነበረ ሲኾን፣ በአካባቢው ያሉ ከፍተኛ ጥቃቶች በግላጭ የተጀመሩት በእርሱ ላይ ነው፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም የት እንደ ገባ አልታወቀም፡፡
ብዙአየሁ እንዳሰኘው የተባለ ምእመን ተገድሎ ጫካ ውስጥ ተጥሎ ተገኝቷል፤ ችግሩ የተጀመረው የካቲት 13 ቀን 2010 ዓ.ም ነው፡፡
መጋቢት 3 ቀን 2010 ዓ.ም ደግሞ፣ አካባቢውን ለቅቀው ዕቃቸውን በተሸከርካሪ ላይ ጭነው ሲወጡ፣ ግርማ ጋሹ እና ፋንታ ታሪኩ የተባሉ 2 ሰዎችን ከተሸከርካሪው አስወርደው የኋሊት አስረው ገደሏቸው፤ ሹፌሩ ያየውን በወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ቀርቦ አመልክቷል፤ ገዳዮቹ አክራሪ ሙስሊም መኾናቸውንም ታዝቧል፡፡
ግንቦት 7 ቀን 2010 ዓ.ም. አካባቢ አቶ ጋሻው ታመነ የሚባለውን ምሽት 2፡00 ላይ በገደሞ(ገጀራ መሰል ብረት) አንገቱን በመቁረጥ ገደሞውንም ጥለው ሒደዋል፤ የጣር ጩኸት ሲያሰማ ሰው ቢደርስም፣ ወዲያው ነፍሱ ከሥጋው ተለይታለች፡፡ ጋሻው ትዳር ያልያዘ ወጣት ሲኾን፣ ቤተሰቦቹ (ወላጆቹና ወንድም እኅቶቹ) እዚያው ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ቀብረውት፣ “እዚኽ አንኖርም” በማለት አካባቢውን ለቅቀው ሒደዋል፡፡
ሐምሌ 16 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ የአቶ ጌታ እንዳለ ቆርቆሮ ቤት ከነጎተራው(3 ቤቶች) እና የሌሎች 4 ገበሬዎችን ቤቶች አቃጥለውባቸው ከነሙሉ ቤተሰቦቻቸው ተሰደዋል፡፡
ነሐሴ 16 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ ቡርቃ ጉዲና ቀበሌ፣ በጌ የተባለች ሥፍራ ላይ፣ በ81 ቆርቆሮ የተሠራ የአቶ ጌታ እንዳለ ቤት ተቃጠለ፤ በቃጠሎውም አንድ ጎተራ በርበሬ ወደመ፤ እርሱም ከነሙሉ ቤተሰቡ ተሰደደ፡፡
ጉርሙ መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የሰበካ ጉባኤ አገልጋይ የነበረ፣ ስሙ ማርሸት የሚባል፣ በሚሠራበት ሊሙ ኮሳ ገባ ብሎ በሚገኘው እርሻ ልማት አካባቢ በሽጉጥ ተመትቶ ጅማ ሆስፒታል በሕክምና ላይ ይገኛል፡፡
ጥቅምት 2011 ዓ.ም.፣ አቶ ጥላሁን በዜ የሚባል በወርኃ ጽጌ በቤተ ክርስቲያን ሲዘክር ቆይቶ ወደ ቤቱ ሲመለስ ተደብድቦ ላይሞት ተርፏል፤ ለወረዳው የመንግሥት ሓላፊዎች አመልክቶ ምላሽ ሲያጣ ለሕይወቱ ሰግቶ አካባቢውን ለቅቆ ሒዷል፡፡
ኅዳር 8 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ ወንድሙን አሳድደነው፤ እርሱ ቀርቷል ብለው የአቶ ጥላሁን በዜ ወንድም የኾነውን አቶ ዘሪሁን በዜንም፣ በገጀራ አንገቱን ሊቆርጡ ሲሰነዝሩ በእጁ ሲመክት፣ የእጅ ጣቶቹ ተቆርጠው ስለ ተጎዳ እርሱም አካባቢውን ጥሎ ወጥቷል፡፡
በኅዳር ወር 2011 ዓ.ም.፣ የአቶ አሳዬ ዋሌ እና የታናሽ ወንድሙ ሦስት ቤቶች ተቃጥለዋል፤ ጥለውም ወጥተዋል፡፡
በዚሁ ኅዳር ወር 2011 ዓ.ም. ውስጥ፣ የአቶ ሲሳይ ዓለሙ ልጅ ዋለልኝ ሲሳይን፣ ሜዳ ላይ ብቻውን አግኝተው ሊገድሉት ሲሉ፣ “አትግደሉኝ ተዉኝ፤ እቤት ያለውን መሣሪያ አውጥቼ እሰጣችኋለኹ፤” በማለት ሲማፀን ትተውት እቤት ድረስ ተከታትለው በመሔድ መሣሪያውን አውጥቶ እንዲሰጣቸው ቢጠይቁት፣ “ጫካ ውስጥ እንዳትገድሉኝ ፈርቼ እንጂ መሣሪያ የለንም” በማለቱ እስከነአባቱ ከፍተኛ ድብደባ አድርሰውበታል፤ የቤታቸውንም በርና መስኮት ገነጣጥለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ከአካባቢው ወጥተው ተሰደዋል፡፡
የአቶ ተሸመ እንየውም ቤት ተቃጠለ፤ ከነቤተሰቡ ጥሎ ጠፍቷል፡፡
ታኅሣሥ 5 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ ወ/ሮ ጥሩ ካሴ የምትባለውንና አቶ አስቻለው የሥጋት የተባሉትን ክርስቲያኖች፣ ቤቶቻቸውን ደብድበው ንብረቶቻቸውን በመሰባበር አሳደዋቸዋል፤ ልጆቻቸውም ጠፍተዋል፡፡
ታኅሣሥ 9 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ አዲሱ ይታየው የተባለው ክርስቲያን ወደ አጎራባቹ የኢሉ አባቦር ክልል፣ ለእርሻ ሒዶ ሲመለስ፣ አንገቱን በስለት ቆርጠው ገደሉት፤ አስከሬኑም ወደ አማራ ክልል ተወስዶ ተቀብሯል፡፡
ሚያዝያ 4 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ ለሚዘክረው የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጽዋ ቀጤማ ሊያጭድ በሔደበት ሚጡ ወንዝ ዳር፣ አቶ ልየው ጌትነትን፣ አንገቱን ቀልተው በመጸዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ ጥለው በላዩ ላይ የከብት ፍግ ጨምረውበታል፡፡ የመጸዳጃ ጉድጓዱ የአቶ መሐመድ ሃምዛ ሲኾን፣ ቤተሰቡና በእርሻው ሥራ ላይ ያሉ የሚጠቀሙበት ነው፡፡ ወዳጅ ዘመዶቹም፣ ቀጤማ ሊቆርጥ ወጥቶ የጠፋውን አቶ ልየው ጌትነትን ፍለጋ ቢወጡም ሊያገኙት አልቻሉም፤ያገኙትን የደም ነጠብጣብ ተከትለው ሲፈልጉ ግን ለማመን የሚከብድና ለሰው ቀርቶ ለአስከሬን እንኳን የሚሰጠውን ኢትዮጵያዊ ክብር በሚንድ መልኩ ከአጨደው ቀጤማ ጋራ በመጸዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ ቀብረውት ተገኝቷል፡፡ አቶ ታደለ ጌትነት፣ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሚማር ታደለ ልየው የሚባል ልጅና ሌሎችም ልጆች የነበሩት ጠንካራ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ነበረ፡፡
ሚያዝያ 5፣ 2011 ዓ.ም.፣ በጋሌ ሠርጤ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የሚኖር አንድ ወጣት፣ ከሌሊቱ 6፡00 ላይ ከቤቱ ጠርተው በማስወጣት በአሠቃቂ ኹኔታ በጥይት ገድለውታል፡፡
በአዲስ ልማት ቀበሌም እንዲሁ፣ የክርስቲያኖች ቤቶች ተደብድበዋል፤ ክርስቲያኖቹም ተሰደዋል፡፡
በቡርቃ ጉዲና እና በአዲስ ልማት ቀበሌዎች፣ ከ200 በላይ አባወራ ይኖር ነበር፡፡ ኾኖም መጋቢት ወር 2011 ዓ.ም. በተደረገ የክርስቲያኖች ቆጠራ፣ 185 አባወራ ይኖር የነበረ ሲኾን፣ የክርስቲያኖች ግድያና ስደት ስለተባባሰና ሃይ ባይ ስለሌለ፣ ሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ 15 አባወራዎች ብቻ በጋሌ ሠርጤ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከቤተ ክርስቲያኗ ቄሰ ገበዝ (አስተዳዳሪ) ጋራ በድንኳን ተጠልለው ቀርተው ነበር፡፡
በመጨረሻም ሚያዝያ 24 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ የጋሌ ሠርጤ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ቄሰ ገበዝ የኾኑት ቄስ ቢተው ገረመው፣ ለብዙ ዓመታት ሲታገሉ ቢቆዩም ሰሚ አካል ስላጡ፣ የቤተ ክርስቲያኗን ቁልፍ ለጅማ ሀገረ ስብከት በማስረከብ ጥለው ወጡ፡፡
የችግሩ መኖር በመንግሥት የበላይ አካላት ተሰምቶ፣ መከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ አጣሪ ሲላክ፣ በወረዳውና በቀበሌው የሚገኙ የመንግሥት አመራሮች እንዲያጣሩ የሚልኳቸው አክራሪ የኾኑትን መርጠው ነው፤ ጥፋቱን ሸሽገው የቤተ እምነታቸው ተልእኮ የአደራ ቃል በሚመስል መልኩ፣ “የዜግነት ግዴታህን ተወጣ” የሚል ተልእኮም ይሰጣቸዋል፡፡ ወደ ቄሰ ገበዙም በመሔድ፣ “ዝም በል፤ አንድ ምእመን እስኪቀር ድረስ እንኳን መናገር የለብህም፤ ለምን ወደ ሌላ ቦታ ትደውላለህ፤ አርፈህ ተቀመጥ፤” የሚል ማስፈራሪያ ያደርሱባቸዋል፡፡
ከወረዳው ጸጥታ ዘርፍ፣ አቶ ጃፈር የሚባልና አድማ በታኝ ነው፤ የተባለ ግለሰብም በተደጋጋሚ ለዚሁ ጉዳይ ወደ ቄሰ ገበዙ ይመላለስ ነበር፡፡
ይኹን እንጂ ቄስ ቢተው ገረመው፣ እንደ ሌሎቹ ክርስቲያኖች፣ ቤታቸው ሌሊት ሌሊት ሲደበደብ ስለሚያድር፣ ዐይነ ስውር ባለቤታቸውንና 6 ልጆቻቸውን(ሕፃናትን ጨምሮ)፣ ከአንድ ዓመት በፊት፣ ታኅሣሥ ወር 2010 ዓ.ም. ውስጥ ወደ ትውልድ ቀዬአቸው መልሰው ልከው እርሳቸው ግን፣ የእግዚአብሔር ማደሪያ የኾነችውን ታቦተ ኪዳነ ምሕረት ጥሎ ላለመውጣት በጸሎትና በልቅሶ ተግተው ከአንድ ዓመት በላይ ከቅጽር ግቢዋ ሳይወጡ ቆይተዋል፡፡
ኾኖም መከራው ሲበረታባቸው፣ በዙሪያቸውም ያሉ ምእመናን በአሠቃቂ ኹኔታ ተገድለውና ተሰደው ሲያዩ፣ አብረዋቸው የሚቀድሱ 13 ካህናት(1 መሪጌታ፣ 8 ካህናት እና 4 ዲያቆናት) በመከራው ብዛት በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም. ውስጥ ጥለው ሲሰደዱ፣ የቤተሰባቸውም ውትወታ አላስቀምጥ ቢላቸው፣ ምእመናን ሳይኖሩም ታቦትና ካህን ህልውና የላቸውምና፣ ሚያዝያ 24 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ የቤተ ክርስቲያኗን ቁልፍ ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳሰ ሊያስረክቡ ከከተቱበት ደብር ወጥተው ወደ ጅማ ሔደዋል፡፡
ጅማ መድረስ ግን የዋዛ አልነበረም፤ የቄሱ መሔድ ሲሰማ፣ ሊሙ ገነት ድረስ በሞተር ተከትለው፣ ሊሙ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሲገቡ ስላዩዋቸው፣ ጸሎተኛ በመምሰል በዐጸዱ ሥር ኾነው ሲጠባበቁ ባለመውጣታቸው ስልክ በመደወል የትም እንዳይሔዱና በሞተር ይዘዋቸው ለመሔድ እየጠበቋቸው እንደኾነ ይነግሯቸዋል፡፡ ካህኑም፣ ወዴትም መሔድ እንደማይፈልጉ በስልክ ምላሽ ከሰጡ በኋላ ከእይታ ተሰውረው በማምለጥ ጅማ በሰላም ደርሰዋል፤ ሊቀ ጳጳሱን አቡነ እስጢፋኖስን አግኝተው፣ በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ ስለ ደረሰው ግፍ ኹሉ በእንባ ተሞልተው አስረድተዋል፡፡
በ1999 ዓ.ም. የበሻሻ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን መቃጠል፣ 7 ካህናትና ምእመናን መታረድ፣ በሌሎችም ላይ የተፈጸመው ጥቃት ታሪክ የማይዘነጋው ነው፡፡
ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያንን ቤንዚን አርከፍክፈው ማቃጠላቸው፡፡
በቁምቢ ወረዳ፣ ምእመናን ማዕተባችኹን ካልበጠሳችኹ ተብለው ሲጠየቁ ፈቃደኛ ባለመኾናቸው ጣቶቻቸው በገጀራ ተቆራርጧል፡፡
ይህ ኹሉ ሠቆቃ ሲፈጸም፣ “ሽፍታ ናቸው” በሚል ሽፋን የሚጠሩና ለዚኹ እኩይ ተግባር፣ ለሃይማኖታቸው አውቀው የሸፈቱ መኾናቸው ይታወቃል፡፡ ብዙዎችን የገደለ፣ የዘረፈና ያሳደደው አቶ መሐመድ ሳኒ፣ “ሽፍታ ናቸው” ከሚባሉት ቀንደኛው ነው፡፡ የመከላከያ ሠራዊት ሲመጣ፣ ሽፍታ ናቸው የተባሉት የሚገኙት፣ እንደ ሽፍታ ጫካ ሳይኾን፣ በከተማው ውስጥ ለዚያውም የወረዳ ባለሥልጣናት ተብዬዎች በሚያውቋቸው መሸሸጊያዎች ውስጥ መኾኑ ለዚህ ማረጋገጫ ነው፡፡ ከወረዳው ባለሥልጣናትና የፖሊስ አባላት፣ ችግሩን ከመስማትም በላይ ቢያዩም፣ በሃይማኖት መሰሎቻቸው ለኾኑት አጥፊዎች በመወገን ለጋራ ዓላማ የተሰለፉት ጥቂቶች አይደሉም፡፡
ፖሊስ፣ አስከሬን ለማንሣት እንኳን በማግስቱ እንጂ በሰዓቱ አይደርስም፤ የሟችን አስከሬን ለማስመርመር ወደ ጅማ ሲሔድ፣ ለትራንስፖርት፣ ከ6ሺሕ እስከ 7ሺሕ ይከፈላል፤ ተመልሶ መጥቶ ይቀበራል፡፡ ፖሊስ መጥቶ እንኳን አያስቀብርም፤ ተመሳሳይ ጥቃት ሲደጋገም፣ ቤተሰብም ሰሚ ሲያጣ ተሰዶ ይሔዳል፡፡
ጥቃቱ በክርስቲያን “ጥንተ መጠሪያ” በተለምዶ “አማራ ላይ ያነጣጠረ” ይባል እንጂ፣ ግልጽ የሃይማኖት ጦርነት ነው፤ ምክንያቱም፣ በአካባቢው ከአማራ ጎሳ ጋራ አብረው ሰፍረው የነበሩ ከሸዋ የመጡ ኦሮሞዎችም አብረው የገፈቱ ቀመሽ፣ የጥቃቱ ሰለባ ኾነዋል፡፡
2. በጋሌ ጅማቴ ቀበሌ፣ በጫፎ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ በሚገኙ ክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመ ግፍ፤

በዚህ አጥቢያ ውስጥ የኖረን አንድ ክርስቲያን፣ ሌሊት ከቤቱ በማስወጣት በተለያዩ ስለቶች በመቆራረጥ፤ በመጨረሻም በጥይት ደጋግመው በመምታት በክፉ ዘግናኝ አገዳደል በገዛ ቤቱ ደጃፍ ላይ ጨርሰው ጥለውት ሔደዋል፡፡
ከዚህ ወጣት ሞት በኋላ በበነጋው ደግሞ በአካባቢው ያሉትን የክርስቲያኖች ቤት በመደዳው አቃጥለዋል፤ ብዙ ክርስቲያኖችም ላይ ድብደባና ሥቃይ ደርሶባቸዋል፡፡
በወጣቱ ሞትና በተፈጸመው ክርስቲያኖችን ብቻ ለይቶ የማሠቃየት ድርጊት፣ ብዙ የክርስቲያኖች አባወራ ተሰደዋል፤ አሁንም በመሰደድ ላይ ይገኛሉ፡፡
3. በጉርሙ መካነ ጥበብ መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ በሚገኙ ክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመ ግፍ፤

በዚህ አካባቢ ያሉ ክርስቲያኖችም ከላይ በአጎራባች አጥቢያዎች ላይ እንደተፈጸመው ኹሉ፣ አሠቃቂ መከራዎች እየደረሱባቸው ይገኛል፡፡ በጥቂቱ ለመግለጽ ያህል፡-

በአካባቢው ነዋሪ ክርስቲያኖች ላይ የብዙዎቹ ቤት ፈርሷል፤ ከፊሉ ተቃጥሏል፡፡ ባለቤቶቹን ደግሞ በግፍ በመደብደብ ኹልጊዜ በሌሊት ቤታቸውን እየደበደቡ በማስፈራራት ከቦታቸው እንዲለቅቁ ተደርጓል፤ ንብረታቸው ተዘርፏል፤ ሳይወጡ የዘገዩም መሣሪያ እየተተኮሰባቸው ተመትተው ተጎድተዋል፡፡
ሚያዝያ 5 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ በዚሁ ቤተ ክርስቲያን፣ በሰበካ ጉባኤ ሊቀ መንበርነት እያገለገለ የነበረን ቅንና ታታሪ፣ የቤተ ክርስቲያኒቷ የቁርጥ ቀን ልጅ የኾነን አንድ ወጣት፣ ተኩሰው ደረቱ ላይ መትተው ክፉኝ ተገድቶ ነበር፤ ለሕክምና ርዳታ ወደ ጅማ ሆስፒታል ቢሔድም፣ ነፍሱ ከሥጋው ተለይታለች፡፡
በደዴሳ ወረዳ፣ ግንቦት ወር 2010 ዓ.ም ውስጥ፣ 3 ክርስቲያኖች ዴዴሳ ወንዙ ዳር፣ በመሮ ጢሳ ቀበሌ መሻገሪያ በኩል(አትናጎ ወረዳ ክልል ውስጥ) የተገደሉ ሲኾን፣ ሊሙ ገነት ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ተቀብረዋል፡፡ አንደኛው ሩጦ አምልጧል፤ ቤተሰቦቻቸውና ልጆቻቸውም ተሰደዋል፡፡
4. በሊሙ ሰቃ ወረዳ፤

የወረዳው የምእመናን ቁጥር፣ ጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም ላይ፣ 101 አባወራ የነበረ ሲኾን፣ መጋቢት ወር መጨረሻ ላይ 65 አባወራ ቀርቷል፡፡
በወረዳው፣ መሮ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ላይ፣ በግምት 200 ሺሕ ብር የሚያወጣ ባሕር ዛፍ፣ በቄሮ ስም የሙስሊሙ ወጣቶች ተከፋፍለውታል፤ 10ሺሕ ብር የሚያወጣ መጠን ያለው ብቻ ቀርቷል፡፡ ዛፎቹን ወገብ ወገቡ ላይ በመቁረጥም፣ መልሰው እንዳያቆጠቁጥ በማድረግ ተስፋ የማስቆረጥ ተግባር ፈጽመዋል፡፡
ጩንጌ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ ከ100 በላይ አባወራ የነበሩ ሲኾን፣ ብዙዎቹ ተሰደዋል፡፡
ለወረዳው የመንግሥት ሓላፊዎች ፖሊስ ብናሳውቅም ምላሽ አልተሰጠም፤ በወረዳው ላይ ኦርቶዶክስ ተኮር የኾኑ ሰብአዊ፣ ማኅበራዊና ሕገ መንግሥታዊ የመብት ጥያቄዎች ተቀባይነት የላቸውም፡፡
5. አምቡዬ የምትባል ከተማ ላይ (ከሊሙ 17ኪ.ሜ ወደ ጅማ)፣ “ኦሮሞ ብሎ ኦርቶዶክስ የለም” ብለው ጫና በማሳደር፣ አንድ አባወራ፣ ባለፈው የ2011 ዓ.ም. ዐቢይ ጾም በማስገደድ እንዲሰልም ተደርጓል፤ ባለቤቱ ግን፣ “ጾም እስኪፈታ ድረስ ልቆይ” ብላ ምክንያት በመስጠት ቆይታለች፡፡

የቄስ ቢተው መልእክት፡- “ክርስቲያን በየአቅጣጫው እየተገደለና እየተሰደደ ነው፤ ለችግራችንም የሚደርስልን አልተገኘም፡፡ በዚህ ዙሪያ ኦርቶዶክስ ተዳክማለች፡፡ እኔም ከዚህ በኋላ፣ ኦርቶዶክስ ረዳት የላትምና በየትኛው ቦታ ቢሆን ቄሰ ገበዝ ኾኜ አላገለግልም፡፡ ቤተ ክርስቲያን መብቷን ማስከበር አለባት፡፡ ሕገ መንግሥቱም ቢኾን፣ ለኹሉም እኩል የሚሠራ ከኾነ መተግበር አለበት፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰው ይህ ሠቆቃ ለክርስቲያኖች ከደረሰ(ከተማልኝ)፤ ከዚህ በኋላ ብሞትም አይቆጨኝ፡፡”

በኢሉ አባቦር ዞን፤

በኢሉ አባቦር ዞን ሲቦ ወረዳ፣ ሚያዚያ 15/2011ዓ.ም የስቅለት ዕለት፣ በከተማዋ በሚገኘው ታዋቂ መስጊድ ውስጥ ያስተማሩት ትምህርት፣ ክርስርትናን በተለይም የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ከማጥላላት ባሻገር፣ “ሕማማቱና ጾም ጸሎቱ ውሸት ነው፤” በማለት ሕዝበ ክርስቲያኑን አስቆጥቷል፤ ይህንም ሲጠየቁ፣ እንዲህ ያለውን ሰውየውን እንደማያውቁት፤ ከየት እንደመጣ፣ የት እንደሔደ አለማየታቸውን በመግለጽ አስተባብለዋል፤
ጎሬ ከተማ፣ ጎሬ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ፣ አሁን የተተከለውን የታላቁ ሰማዕት የአቡነ ሚካኤል ሐውልት፣ ከቤተ ክርስቲያኑ ፊት ለፊት በሚገኘው ዐደባባይ ላይ እንደሚተከል፣ ከመንግሥት እንዲሁም ከአርበኞች አባቶች ታምኖበት ነበር፡፡ ኾኖም በጎሬ ሬድዮ ጣቢያ በሚሠራ፣ ካሊድ ተብሎ በሚጠራ አክራሪ ሙስሊም አስተባባሪነት፣ ፕሮቴስታንቶችን ጨምሮ፣ “ሐውልቱ ዐደባባይ ላይ ከተተከለ ሞተን እንገኛለን፤ እሳቸው የሞቱት ሲሞቱ ነው፤ ኦሮሞ አይደሉም፤ አናውቃቸውም፤ አይወክሉንም፤“ ብለው በመቃወም፣ አሁን ባለበት ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ እንዲተከል ኾኗል፡፡
ገቺ ማዘጋጃ ቤት ከተቋቋመበት ከ1994 ዓ.ም አንስቶ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሬት ተወስዶ የተረፈውን ዕጣን አዙሩን እስከ ዛሬ ድረስ ፕላንና ካርታ ማግኘት አልተቻለም፡፡
1999 ዓ.ም.፣ ገቺ ጎሌ ጋትራ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ሙሉ በሙሉ በአክራሪ እስላሞች ወድሞ ማኅበረ ቅዱሳን በ260 ሺሕ ብር አሠርቶታል፡፡
ጥቅምት 9 ቀን 2009 ዓ.ም. የተደረገው አገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ በሽፋንነት በመጠቀም፣ የገቺ ደ/ዕ/ቅ/ማርያም ቤተ ክርስቲያን አከራይታ የምትጠቀምባቸው 4 ቤቶች ወድመዋል፡፡ በውስጡ ተከራይተው የነበሩ ሰዎች፣ በሚልዮን በሚቆጠር ብር የሚያወጣ ንብረታቸው ወድሟል፡፡
በዚኹ በለውጥ ሽፋን የጥፋት እንቅስቃሴያቸው፣ ከ1ሺሕ330 በላይ አባዎራዎች የተፈናቀሉ ሲኾን፣ 1ሺሕ 200 የሚኾኑት፣ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ናቸው፡፡
ሚያዚያ 8/2011 ዓ.ም.፣ በገቺ ወረዳ ሴከቻ ገበሬ ማኅበር የሚገኘው ቅ/ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተቃጠለ፡፡ በጣም የሚያሳዝነው፣ የቤተ ክርስቲያኑን መቃጠል ሰምተው ከሔዱ የጸጥታ አካላት መካከል፣ ኢንስፔክተር ግርማ የተባለው ሰው፣ በቤተ ክርስቲያኑ መቃጠል በማዘን ሰው እንዳቃጠለው ሲናገሩ ከነበሩት ውስጥ አንዱን ሰው መትቶ ጉዳት አድርሶበት ተጎጂው ሆስፒታል ገብቷል፡፡ የኢንስፔክተሩ ድርጊት ትክክል እንዳልኾነ ተጠቅሶ ለሕግ የቀረበውን የክሥ አቤቱታ አንቀበልም ብለው ጥለውታል፤ ከሳሾቹ እሰከ አሁን ድረስ ችግር ላይ እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በዚሁ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የጥበቃ ሠራተኛ የነበሩትን አቶ ሙሉጌታ የተባሉትን ሃይማኖታቸውን ቢቀይሩ፣ የቀበሌ ሊቀ መንበር እንደሚያደርጓቸው ቃል ገብተው አስልመው ሊቀ መንበር አድርገዋቸዋል፡፡ ለመሰናዶ ትምህርት ቤት መስሪያ ቤተ ክርስቲያን በሰጠችው መሬት ላይ፣ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መስጊድ ተሠርቶበት ይገኛል፡፡
በገቺ ወረዳ፣ በ1947 ዓ.ም. የተቋቋመውና ሙጫ ገበሬ ማኅበር ውስጥ የሚገኘው፣ የሙጫ ቅድስት ሥላሴ ዕጣን አዙር(የቤተ ክርስቲያን መሬት) ሙሉ በሙሉ የተወሰደ ሲኾን፣ ያም አልበቃ ብሎ ቤተክርስቲያኑ ቅጽር ድረስ ገብቶ እስከ ማረስ ተደርሶአል፡፡
በአጠቃላይ በገቺ ወረዳ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ላይ፣ በአክራሪ እስላሞች የተለያዩ ሴራዎች ምክንያት፣ ካህናት መቀመጥ ስላልቻሉ ጎሌ ተክለ ሃይማኖት፤ ቦረታ መድኀኔዓለም፤ ሴከቻ ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ ዴዴሳ ስኳር ፋብሪካ የሚገኘው በዓለ ወልድ አብያተ ክርስቲያናት ተዘግተዋል፡፡
በዚሁ በገቺ ወረዳ እና በሌሎችም የኢትጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖትን በስም እየጠራ የሚሳደብ፣ የመንዙማ ቪሲዲ በኦሮምኛ ታትሞ የክርስቲያኖችን ሥነ ልቡና እየጎዳ ይገኛል። ይህ ድርጊት ሲፈጸም፣ የመንግሥት እና የቤተ ክህነት ችላ ባይነትን ምእመናን በእጅጉ ይኮንናሉ፤ ያዝናሉ፡፡
167 ዓመት ያስቆጠረው፣ የቦረቻ ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ዕጣን አዙር መሬት ሙሉ በሙሉ በአክራሪ እስላሞች ተወስዷል፡፡
በ2002 ዓ.ም የቦረቻ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ጽላት፣ በአክራሪ እስላሞች የተሰረቀ ሲኾን፣ እስከ አሁን ጽላቱ ሳይመለስ ቤተ ክርስቲያን ተዘግታ ትገኛለች፡፡
በዚህ ወረዳና በሌሎችም ወቅቶች የሚፈራረቅን የፖሊቲካ ርእዮተ ዓለም በመጠቀም በከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣንና በአመራር ደረጃ የደረሱትን ክርስቲያኖች፣ በተለያየ ሰበብ ከሥልጣን እንዲወርዱ እየተደረገ ነው፤ በኢኮኖሚው ዘርፍ ደግሞ፣ የተሰማሩ ክርስቲያን ነጋዴዎች ማስፈራራት፣ ዛቻና ዘረፋ ይፈጸምባቸዋል፡፡
በ1999 ዓ.ም. በዴዴሳ ወረዳ ከሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት፣ የጨሎ መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያንና የቀመቼ ቅ/ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፣ ቃጠሎ ደርሶባቸው፣ ዳግም በምእመናን አስተዋፅኦ ተገንብተዋል፡፡ ኾኖም፣ ታላላቅ የእስልምና መድረሳ ት/ቤት ያለበትና በሌላ በኩል ደግሞ አክራሪነት የሚስፋፋባት የዬምቤሮ ከተማ፣ በዙሪያዋ ያሉት ምእመናን ተረጋግተው እንዳይኖሩ በማስፈራራትና በመዝረፍ ብዙዎች ቦታውን ለቀው እንደሔዱ እማኞች ይናገራሉ፡፡
በ1999 ዓ.ም. ጅማ ሀገረ ስብከት በሻሻ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ዘግናኝ በደል ተፈጽሟል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ተቃጥላለች፤ ካህናትና ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ታርደዋል፤ በገጀራ ተደብድበዋል፡፡ በበሻሻ የተፈጸመውን ግፍ በወቅቱ የነበሩ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዳስተባበሩት እማኞች ተናግረው ነበር፡፡
በ1999 ዓ.ም. በኢሉ አባቦር እና በጅማ በተካሔደው የአክራሪ እስልምና እንቅስቃሴ፣ ክርስቲያኖች ከነበሩበት ቀዬ ለቀው እንዲሔዱ ተገደዋል፤ ምክንያቱም፣ መንግሥት የደረሰውን ግፍና በደል ተመልክቶ ሕጋዊ ርምጃ አለመውሰዱ፣ የልብ ልብ እንዲሰማቸውና በደላቸውን እንዲቀጥሉ መልካም አጋጣሚ ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ከዚህም የተነሳ ብዙዎች ሃይማኖታቸውን በተጽዕኖ ቀይረዋል፡፡ በጅማ ዞን ባሉ ቢሮዎች ውስጥ ያሉ ሠራተኞችን መጠሪያ ስም መመልከት ብቻ በቂ ነው፡፡
ከክልል እስከ ፌደራል ባለ የመንግሥት መዋቅር በመጠቀም ሥልጣን መያዝ፣ የእኒህ ጽንፈኞች ተግባር ኾኗል፡፡ በጅማ ዞንም፣ በሥልጣን ላይ ያሉትና እየተሾሙ የሚገኙት፣ የተወሰኑ ፕሮቴስታንቶችና ጥቂት የሚባሉ ኦርቶዶክሳውያን ናቸው፡፡

Post Bottom Ad