ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዓመታዊ የዕረፍት ክብረ በዓል እና ጻድቁ ተክለሃይማኖት ዓመታዊ የፍልሰተ ዐጽም ክብረ በዓል - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Tuesday, May 21, 2019

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዓመታዊ የዕረፍት ክብረ በዓል እና ጻድቁ ተክለሃይማኖት ዓመታዊ የፍልሰተ ዐጽም ክብረ በዓል


የግንቦት ፲፪ ዝክረ ቅዱሳን። እንኳን ለታላቁ የዓለም መምህር ሊቅ ወርዕሰ ሊቃውንት #ለቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ ዓመታዊ የዕረፍት ክብረ በዓል እና #ለጻድቁ_ተክለሃይማኖት ዓመታዊ የፍልሰተ ዐጽም ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ።


°ክርስቶስ ተንስአ እሙታን
+ በዐቢይ ኃይል ወስልጣን
°አሠሮ ለሰይጣን
+ አግአዞ ለአዳም
°ሰላም
+ እምይእዜሰ
°ኮነ
+ ፍስሐ ወሰላም።
¶ አመ ፲፪ ለግንቦት በዛቲ እለት፥ አዕረፈ አብ ክቡር ቅዱስ መምህረ ኲሉ ዓለም #ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ አፈ ርኄ ሊቀ ጳጳሳት ዘቊስጥንጥንያ።
✍️፩-በዚህች ቀን የዓለም ኹሉ መምህር የሚኾን የቊስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳሳት #የቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ ዕረፍቱ ኾነ።
(ስለአፈወርቅማ ምን እላለሁ? እርሱን መግለጥና መናገር የሚቻል፣ ስለርሱስ የሚነገረውን መስማት የሚቻለው ማን አለ በእውነት? እርሱ በጸሎቱ በፍጹም ምልጃው እንዲረዳኝ በመማጸን ለበዓሉ ማዘከሪያ ያህል ብቻ ጥቂት አበው ከተናገሩት ልዘክር እንጂ)
+ ሊቁ አፈ ሶከር መምህረ ኲሉ ዓለም አባ ዮሐንስ ከእስክንድርያ አገር ሰዎች ወገን ነው። አባቱ አስፋኒዶስ አናቱ ደግሞ አትናስያ ይባላሉ። አባቱ አስፋኒዶስ ልክ እናታችን ቅድስት አትናስያ ሃያ ዓመቷ ሳለ ዐረፈ። በዚህን ጊዜም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን በጥበብ ማሳደግን ያዘች። ቅዱስ ዮሐንስም ገና ልጅ ሳለ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እጅግ የመላበት ነበርና ሰይፍ በክልኤ የኾነአ ገና በልጅነቱ ነበር። ወደ ግሪክ አቴናም ኼዶ በወቅቱ እጅግ የሚደነቁትን የግሪክን ፍልስፍና እና የንግግር ጥበብን ተንሯል። ከፍጹም ዕውቀቱም የተነሳ ያስተማሩት መምህራን ኹሉ ሊባኖስ የተባለውን ጨምሮ የሚተካቸው ቅዱስ አባታችን ሊቁ አፈወርቅ እንደኾነ ይናገሩ ነበር። መምህራን አበውም ይህን ገንዘብ አድርጎ መራቀቁን በማየት "ፍልስፍናን ያመከነ ፈላስፋ" እንደሚባልም ይናገራሉ።
+ እጅግ የሚወደውም ባስልዮስ የሚባል ልዩ ውውዳጅ ነበረው። አብረውም ሊመነኲሱ ባሉ ጊዜ እናቱ ቅዱስ ዮሐንስ እንዲለያት ባለመፍቀዷ አዘነች። ትተኸኝም አትኺድ አለችው። ቅዱስ ዮሐንስም ስለእናቱ ሲል የሚወደውን ባልንጀራውን ሰደደውና እርሱ ግን እናቱ እስካረፈችበት ጊዜ ድረስ አብሯት ቆየ። በቤት ቢቆይም ስንኳ ግን ቤቱን ገዳም እስኪያስመስለው ድረስ ጽኑዕ ተጋድሎን ይጋደል ነበር። እናቱ ቅድስት አትናስያም ካረፈች በኋላ ገና በልጅነቱ ወደ ገዳም ገብቶ መነኰሰ። ከሚወደውም ባልንጀራው ከባስልዮስ ጋራ ጽኑዕ ተጋድሎን መጋደልን ጀመሩ። በአንዲት እለትም ቅዱስ ዮሐንስ አፈ መዐር በገዳም ሳለ አንድ መነኰስ አባት ስለርሱ እንዲህ ተመለከተ። ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስና አቡቀለምሲስ ፍቊረ እግዚእ ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ሲመጡና ቅዱስ ጴጥሮስ የመንግስተ ሰማያትን መክፈቻ ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ ወንጌሉን ሲሰጡትና፣ ከእግዚአብሔርም ተልከው እንደመጡ ሲያነጋግሩት ተመልክቷል። እኒህም ጻድቃን ቅዱስ አባታችን #አፈ_ርኄ #አፈ_ሶከር ቅዱስ ዮሐንስን #ሐዲስ_ዳንኤል ብለው ሲጠሩትም ሰማ። ጻድቅ ሲሲኮስም ይህን ራእይ በተመለከተ ጊዜ ታላቅ የኾመች ሹመትን ይሾም ዘንድ እንዳለ'ው አስተዋለ።
+ አፈ ወርቅ አፈ ዕንቊ የተባለ ይህ ምድራዊ መልአክ ትሩፈ ምግባር ቅዱስ ዮሐንስም በጸጋ መንፈስ ቅዱስ የተጌጠ ነበርና ገና በዲቁና መዐርግ ሣለ መጻሕፍትን ኹሉ ብሉይን ከሐዲስ ተረጎመ። በተለይም ደግሞ የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን መላልሶ አስፋፍቶ ተረጎመ። ከዚህም በኋላ መልአከ እግዚአብሔር ተገለጠለትና ሐዲስ ዳንኤል ሆይ ሊቀ ጳጳሳቱ ከካክህናትና ከዲያቆናት ጋራ ወደ አንተ ይመጣልና ፈቃደ እግዚአብሔር ስለኾነ የሚያዝህን እምቢ አትበለው አለውና ተሰወረው። ከዚያም ይኸው መልአክ ለአባ ፊላትያኖስ ተገልጦ ቅዱስ ዮሐንስን ቅስና እንዲሾመው አዘዘው። በማግስቱም ከካህናትና ከዲያቆናት ጋራ መጥቶ ቅስናን ሾመው።
+ ከዚህም በኋላ በቅስናው ጽኑዕ ተጋድሎን እየተጋደለ ግሩም ጥዑም መጽንዒ ትምህርትና ተግሣፃትን እያስተማረም ሳለ የቊስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳሳት ዐረፈ። በዚህም ጊዜ ሰዉ ኹሉ እና ንጉሱም አርቃድዮስ እጅግ ይወደው ነበርና ለምን እንደሚፈልገአ ሳይነግረው አስመጣውና ባረፈው ሊቀ ጳጳሳት ፈንታ ቅዱስ ኅሩይ መምህረ ኲሉ ዓለም አባታችንን ሾሙት። በዚህም ከተሾመ በኋላ የሚጣፍቱ የሚያጽናኑ እዝናቶችን እና ምዕዳናትን ሲሰጥ ቆየ። በዚህም ቆይታው መምህር ወመገሥጽ ዘኢያደሉ ለገጽ ነበርና ማንንም ሳይፈራናን ማንንም ሳያፍር ይገሥጻቸው ይመክራቸው ነበር። ይህንንም እያደረገ ሳለ የንጉሡ ሚስት አውዶክስያ ተግሣጹን መቀበልን እምቢ ብላ ይባስ ብላ የአንዲትን ድኃ ሴት ገንዘብ ወሰደች። ቅዱሱም እንድትመልስ ብዙ ጊዜ ለመናት። እርስዋ ግን ፈጽሞ እምቢ አለች። ከዚያም አባታችን ወደ ቤተክርስቲያን እንዳትገባና ሥጋ ወደሙን እንዳትቀበል ከለከላት። የዚህን ጊዜም ነገር ትሠራና በሥነ ምግባር ጉድለትና በሃይማኖት ምክንያት አውግዞ የለያቸውን ሊቃነ ጳጳሳት ሰብስባ ክፉ ምክርን አስመክራ ወደ ደሴተ #አጥራክያ አጋዘችው። አባታችን ፍቊር አፈ ዕንቊ አፈ ርኄ ቅዱስ ዮሐንስም በዚያ ሲደርስ ሰዎቹን ከሀድያን ኹነው አገኛቸውና እነርሱን አስተምሮ አሳመናቸው። ሉቁ ፍቊር አባታችን በኹሉ እጅግ የተውደደ ነበርና የሮሜ ንጉሥ አኖሬዎስና ሊቀ ጳጳሳቱ ዮናክኒዶስ ንጉሡ አርቃድዮስ አፈወርቅን ካልፈታው ሰላም እንደማይሆኑ ተናገረ። መልእክታቸውም ለንጉሡ በደረሰው ጊዜ እጅግ አዘነና ቅዱስ ዮሐንስን ወደ ቊስጥንጥንያ አስመለሰው።
+ (እጅግ የሚደንቀው የሊቁ የአባታችን ነገር በስደት እንኳን እያለ ፈጽሞ እግዚአብሔርን አላማረረም። እዲያውም በዓለም በሰላም ኹነው ሳለ የሚጨነቁትን ያጽናናቸው ነበር እንጂ። እጅግ በሚወዳት መልእክትን በምታደርስለት በዲያቆናዊቷ በኦሎምፒያስ በኩል እየላከ ያስተምራቸው ያጽናናቸው ነበር። እንዲያውም በአንድ እለት ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር እንዲብ ብሏል፣ ሰው ራሱን ካልጎዳ በቀር ፈጽሞ ማንም ምንም አይጎዳውም።)
+ ንግሥቲቱም ዳግመኛ ነገር ሠርታ ቅዱሱን ንጹሑን አባት ወደ ዚያች ደሴት አሳደደችው። በዚያም ሳለ በጽኑዕ ድካም ደክሞ ነበርና ዳግመኛ በሮሜ ንጉሥ እና ሊቀ ጳጳሳት ትእዛዝ ሊመልሱት ቢሉ አርፎ አገኙት። ቅዱስ አባታችን ዮሐንስም ማረፉን በሰሙ ጊዜ ሊቀ ጳጳሳቱ ዮናክኒዶስ አውዶክስያን አውግዞ ለያት። እርሷም በጽኑዕ ደዌ በተያዘች ጊዜ ሊቀ ጳጳሳቱን ጽኑዕ ልመና ለምና ከግዝቷ ፈታት። ከደዌዋ ግን መዳን አልቻለችም ነበር። ቅድስት ሥጋውንም ወደ ቊስጥንጥንያ በመለሷት ጊዜ ቁስጥንጥንያ በደስታ ተውጣ መበር። ከቅድስት ሥጋውም እጅግ ብዙ ድንቆች ተገልጠዋል።
+ ይህ ቅዱስ አባታችን በአንድ እለት ንጉሡ አርቃድዮስ "ኢያእመራ እስከ አመ ወለደት ወልደ ዘበኲራ" የሚለውን አንቀጽ እንደምን ነው ተብሊ የሚተረጎም፣ ከወለደች በኋላ አውቋታል ማለት ነውን? እያለ ሲያስም ልክ ዮሐንስ አፈወርቅ ሲመጣ ይጠፋበታል። ከዚያም አንድ እለት አስታውሶ ነገረው። ቅዱስ አባታችንም እንዲህስ ፈጽሞ አትበል ንጉሥ፣ ኢያእመራ ማለቱ ጌታችንን ጸንሳ ሳለ' የጌታችን ኅብሩ ሲለዋወጥ የርሷም ኅብር ይለዋወጥ ነበርና መልኳን አለየውም ማለት ነው። እንዲህ ብሎም ዘርዝሮ ምስጢራቱን ገልጦ ባስተማረው ጊዜ በዚያ የነበረች የቅድስት እናታችን የማርያም ሥዕል "ሠናየ ተናገርከ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ሠናየ ተናገርከ ዮሐንስ ልሣነ ወርቅ" ብላ በጥዑም ምስጋና አመሰገነችው። ከዚህም አንስቶ ዳግመኛም እንዲሁ ከሚያስተምረው ጥዑም የኾነ ትምህርት የተነሳ #አፈወርቅ ተባለ።
+ቅዱስ አባታችንን ቤተ ክርስቲያን የምትጠራው እንዲህ ብላ ነው፥
√አፈ ወርቅ
√አፈ ዕንቊ
√አፈ መዐር
√አፈ ርኄ
√አፈ ሶከር
√አፈ አፈው
√ልሣነ ወርቅ
√አፈ በረከት፣ ርዕሰ ሊቃውንት
√ሐዲስ ዳንኤል
√መምህረ ኲሉ ዓለም
√መምህር ወመገሥጽ ዘኢያደሉ ለገጽ
+ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ እኛንም በዚህ የዓለም ኹሉ መምህር ሊቅ አባት ይማረን፣ በረከቱም ከእኛ ጋር ትሁን ለዘላለሙ አሜን።
ሰላም ለዮሐንስ እንተ አብደረ ስደተ
እምይሳተፍ በግፍዕ መፍቀሪተ ንዋይ ንግሥተ
እምነ አፉሁ ዘወጽአ ሰሚዖ ግዘተ
እንበለ ይዕርግ ላዕለ ወእንበለ ይረድ ታሕተ
መልአከ ሰማይ ቆመ ዐሠርተ ዓመተ።
ሰላም ዕብል ሱታፌ ዮሐንስ በሕማሙ
ሲሲኮስ ስሙ
ክብረ ዮሐንስ አፈወርቅ እንተ ነጸረ በሕልሙ
መራኁተ እንዘ ይሜጥዎ ጴጥሮስ ቀዲሙ
ወእንዘ ይሁቦ ወንጌለ ዳግሙ።
✍️፪-ዳግመኛም በዚህች ቀን በኢየሩሳሌም አገር ወደሚኖር ነቢይ #ዕንባቆም የመላእክት አለቃ #ሚካኤልን እግዚአብሔር ላከው።
+ እርሱም እህል ለሚያጭዱ ሰዎች ምሳ ሊወስድ ወዶ ተሸክሞ ሳለ ቅዱስ ሚካኤል ዕንባቆምን በራሱ ጠጉር አንስቶ ወደ ባቢሎን ወሰደውና ቅዱስ ዳንኤልን በአናብስት ጉድጓድ ውስጥ ሳለ' በዚያ መገበው። ከዚያም መልሶ እህሉን ወደሚያጭዱት ወሰደውና በዚያ ደረሰ። ስለዚህም ለከመረ መልአክ የመላእክት አለቃ ሚካኤል በየወሩ ሁሉ መታሰቢያውን እናደርግ ዘንድ የቤተልርስቲያን መምህራን አዘዙ። አማላጅነቱም ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላመለሙ አሜን።
ሰላም ለህላዌከ ዘምሥዋዐ አብ መቅደሰ
ከመ ታዕርግ ህየ ጸሎተ ቅዱሳን ጢስ
ኀፍረተ መስቀል ወልድ አመ ተዐገሠ
ኢትርአይ በድንጋፄ እንዘ ታንቀዓዱ ነፍሰ
ሚካኤል አድነንከ ወአትሐትከ ርእሰ።
✍️፫-ዳግመኛም በዚህች ቀን ሃይማኖቱ የቀና የንጉሥ በእደ ማርያም ልጅ የኢትዮጵያ #ንጉሥ_እስክንድር የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ እኛንም በቅዱሳን ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።
በእንተ እለይወርሱ ሕይወተ ፍጡራን አኮኑ ለሊከ ፍጡር
ሚካኤል መልአኩ ለእግዚአብሔር
በዘተዓርፍ ነፍሱ ለእስክንድር
ሕንፅ ሎቱ መንበረ ተድላ ወክብር
ከመ ማኅደረከ ሐነፀ በምድር።
✍️፬-ዳግመኛም በዚህች ቀን በኢየሩሳሌም አገር በጎልጎታ ላይ ከፀሐይ በልጦ የሚያበራ ብርሃን #የከበረ_መስቀል_መገለጥ ኾነ።
+ ይኸውም ለኢየሩሳሌም አባ ቄርሎስ ሊቀ ጳጳሳት ኹኖ በተሾመበት ጊዜ በታላቁ ቈስጠንጢኖስም ልጅ በታናሹ ቈስጠንጢኖስ ዘመን ነው። መገለጡም የኾነው ከቀኑ በስድስት ሰዓት ነው። የመስቀሉም ብርሃን የፀሐዩን ብርሃን ሸፍኖ በግልት እየታየ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ቆየ። ሰዎችም ኹሉ ያዩት ዘንድ ከቦታ ኹሉ ይወጡ ነበር። ቅዱስ አባታችን ቄርሎስም እንዲህ ብሎ መልእክት ወደ ንጉሡ ላከ። እንግዲህ እወቅ በከበረ በአባትህ ጊዜ እንደታየው እንዲሁ በዚህም በአንተ በዘመንህ በቀራንዮ ላይ የ ርሃን መስቀል የፀሐይንም ብርሃን ሸፈነው። እስከ ክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብርና እስከ ደብረ ዘይትም ድረስ ተዘረጋ አለው።
+ ዳግመኛም እንዲህ አለው። ንጉሥ ኾይ ከከፋችና ከረከሰች ከአርዮስ እምነት ተጠበቅ። የሚያምኑባትንም ከቶ አትቀበላቸው። በምንም በምን አትሳተፋቸውም። ከዚህም በኋላ ቄርሎስ ይህ የከበረ መስቀል በተገለጸበት ቀን በዓልን አደረገ፣ እርሱም በሥውርና በግልጥ ለሚመጣብን ጠላት ተዋግተን የምንድንበት የጦር መሣሪያችን ነውና በጸና እምነት በምንማፀንበት ጊዜ። ለእግዚአብሔር በመስቀሉ ላዳነን በከበሩ ደሙም ፈሳሽነት ለአነጻን ምስጋና ይሁን፣ ዛሬም ከሚጣላን ኹሉ ይጠብቀን ይቅርም ይበለን ለዘላለሙ አሜን።
ሰላም ሰላም በቃለ አሚን ዕብል
ለዘአስተርአየ ዮም ላዕለ ጎልጎታ መስቀል
እንዘ ያሰምያ በነፍሱ ዕለተ አድንኅኖ ወሣህል
ቄርሎስ ሊቀ ጳጳሳት ዘኢየሩሳሌም ደወል
በውስተ ግጻዌ ጸሐፋ ለዛቲ በዓል።
✍️፭-ዳግመኛም በዚህች ቀን ሰማዕታት የኾኑ #የዲያቆን_ሚናስና #የእስጢፋኖስ መታሰቢያቸው ነው፣ በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✍️፮-ዳግመኛም በዚህች ቀን የመላልዔል ልጅ #የያሬድ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው።
+ ያሬድም መቶ ሠላሳ ሁለት ዓመት ኑሮ ሄኖክን ወለደው፣ ሄኖክንም ከወለደው በኋላ ስምንት መቶ ዓመት ኖረ። ወንዶችንና ሴቶችን ልጆች ወለደ። መላውም ዘመኑም ዘጠኝ መቶ ስልሳ ሁለት ዓመት ኾነው። በዕለተ ዓርብም በሦስት ሰዓት ዐረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ የቀደሙ አባቶቻችንም በረከታቸው ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✍️፯-ዳግመኛም በዚህች ቀን የመነኰሳት ኹኩ አለቃ ሐዋርያና ሰማዕት የታላቁ መምህር የክቡር አባታችን #ተክለሃይማኖት የሥጋው ፍልሰት ሆነ።
+ የፍልሰቱም ምክንያት በሃምሳ ስድስት ዓመት ከዋሻ ውስጥ ወደ አነፁልህ መቃብር ያፈልሱታል ብሎ እግዚአብሔር የነገረው ዘመን በደረሰ ጊዜ፣ ያን ጊዜም ተአምር ተደርጎ ዕውራን አዩ። አንካሶች ተስተካከሉ።
ይህም በወራሴ መንበሩ በአባ ሕዝቅያስ ዘመን ኾነ። ዕለቱም ግንቦት ዐሥራ ሁለት ነው። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ እኛንም ተጋዳይ በሆነ ሰው ጻድቁ አባታችን በተክለ ሃይማኖት ጌታን ደስ በአሰኙት በቅዱሳን ሁሉ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።
ሰላም ዕብል አልዒልየ ቃለ
በፍልሰተ ዐፅሙ ዘገብረ ተክለ ሃይማኖት ኃይለ
እኂዛ በእዴሃ ኅብስተ ተዝካሩ ብሱለ
ሶበ ገሠሠት ብእሲት ዐይና ጽሉለ
እምነ ብርሃኑ አድምዓት ብርሃነ ጽዱለ።
✍️፰-ዳግመኛም በዚህች ቀን በአባታችን ተክለሃይማኖት መንበር ከተሾሙ መምህራን ዐሥራ ሰባተኛ ቊጥር የሆነ የደብረ ሊባኖስ መምህር ክቡር አባ አብርሃም አረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። እኛንም በጸሎቱ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።
ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው፣ በእንተ ቅዱስ መምህረ ኲሉ ዓለም ዮሐንስ አፈ ወርቅ ርዕሰ ሊቃውንት ወበእንተ ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሐዲስ ሐአኣርያ ወበእንተ ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት ወበእንተ ቅዱስ መስቀልከ ወበእንተ ቅዱስ ያሬድ ወልደ መላልዔል ወዲያቆን ሚናስ ወእስጢፋኖስ ወበእንተ አባ አብርሃም ክቡር መሐረነ ለነ ለአባስያን አግብርቲከ ወአእማቲከ አሜን። ኢታጥፍአነ ተዘኪረከ ዘትካት፣ ፍጡነ ይርከበነ ሣህልከ እግዚኦ።
❤❤
+ኦ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አስተብቊዕ ለነ ለውሉድከ ደቂቀ አዳም
+ሰሚዓነ ተግሣፀከ ከመ ንድኃን እምእሳቱ ዘኢይጠፍዕ ወዕጼሁ ዘኢይነውም
❤❤
❤❤አፈ ወርቅ አፈ መዐር ቅዱስ አባታችን ዮሐንስ ልሣነ ወርቅ ሆይ ድኩማን ልጆችህን በምልጃህ አስበን፣ ከማይጠፋው እሳትም ታሻግረን ዘንድ በጽኑዕ ቃልኪዳንህ የማጽነንብሃል።❤❤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር።

Post Bottom Ad