በደብረ ምጥማቅ ከግንቦት 21-25 የአምላክ እናት የድንግል ማርያም መገለጥ] - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Wednesday, May 29, 2019

በደብረ ምጥማቅ ከግንቦት 21-25 የአምላክ እናት የድንግል ማርያም መገለጥ]


በመጋቤ ሐዲስ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ
ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በመዝ ፵፬፥፲፪ ላይ “ወለገጽኪ ይትመሐለሉ ኲሎሙ አሕዛብ ብዑላነ ምድር” (የምድር ባለጠጎች አሕዛብ ኹሉ በፊትሽ ይማለላሉ) በማለት ትንቢትን እንደተናገረላት ብዙዎች ቅዱሳን ቅድስት ድንግል ማርያምን ተገልጻላቸው ለማየት ተመኝተዋል፤ ብዙዎቹም ልመናቸው ተሰምቶላቸው የአምላክ እናት ተገልጻላቸው እጅግ አስደናቂ ውበቷን አይተዋል፡፡ ከነዚኽ ውስጥ በደብረ ምጥማቅ የነበሩ ምእመናን ሌሎችም ብዙዎች ንጹሓን ክርስቲያኖች ይገኙበታል፡፡
ልጇ አስቀድሞ በዘመነ ሥጋዌዉ በደብረ ምጥማቅ እንደ ምትገለጽ በገባላት ቃል ኪዳን መሠረት ከኢትዮጵያ፣ ከግብጽ፣ ከአርመንያ፣ ከሶርያ፣ ከሮም፣ ከጽርዕ፣ ከፋርስ በምድረ በደብረ ምጥማቅ ድንኳን ተክለው፤ አጐበር ጥለው ከግንቦት 21 ቀን ዠምረው እስከ 25 ቀን ድረስ በፍጹም ደስታ የድንግልን በዓሏን ማክበር ይዠምራሉ።
“ወድንግልሂ ታስተርእዮሙ በእሉ ኀምስ መዋዕል ዘእንበለ ጽርዐት ምስለ መላእክት ወጻድቃን ወሰማዕት ምስሌሃ” ይላል፤ እመቤታችን ከግንቦት 21-25 ያለማቋረጥ ከመላእክት ከሊቃነ መላእክት፤ ከነቢያት ከሐዋርያት፤ ከጻድቃን ከሰማዕታት፤ ከደናግል ከመነኮሳት ጋራ ኹና ትገለጽላቸው ነበር፤ አማኒውም ኢአማኒውም ያያት ነበር፤ ያመኑት ክርስትያኖች እምነታቸው ሲጸናላቸው፤ ያላመኑት ደግሞ እያመኑ ከእግዚአብሔር ወልድ ከልጇ ሀብተ ውልድና ስመ ክርስትና ይቀበሉ ነበር፡፡
በጒልላቱ ላይ ስትገለጽ በውስጥ በአፍአ በነፍስ በሥጋ ንጽሕት የኾነችው የቅድስት ድንግል ማርያም የፊቷ ውበትና ብርሃን እጅግ ድንቅ ነበርና ካህናቱም ሕዝቡም ኹሉ ልክ እንደ ኤልሳቤጥ “የጌታችን እናት ለእኛ ትገለጪ ዘንድ እኛ ምንድን ነን” እያሉ ይጮኹ ነበር፤ ርሷም ትባርካቸው ነበር፡፡
የእመቤታችን ፍቅር በእጅጉ የበዛለት አባ ጽጌ ድንግልም በደብረ ምጥማቅ በታላቅ ክብር ተገልጻ ለምእመናን የታየችው የአምላክ እናት ለርሱም ትገለጽለት ዘንድ በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፉ ላይ፡-
“አመ ትበርቂ በደብረ ምጥማቅ ኀምሰ ዕለታተ
ትእምርተ ገጽኪ ይርአይ እስከ ይትነሣእ ዘሞተ
ሚ መጠነ ማርያም ታሥተፌሥሒ ትፍሥሕተ
ኅድጊሰ ጽጌ ፍቅርኪ በጊዜ ንቃሑ መዓልተ
ብፁዕ ዘርእየኪ በሕልሙ ሌሊተ”
(የፊትሽን መልክ ያይ ዘንድ የሞተ ሰው እስኪነሣ ድረስ በደብረ ምጥማቅ ለዐምስት ቀናት ያኽል በተገለጽሽ ጊዜ ማርያም ምን ያኽል ደስ ታሰኚ ኖሯል! በቀን የታየው የፍቅርሽ አበባ ይቅርና ሌሊት በሕልሙ ያየሽ ምስጉን ነው) በማለት ተማፅኗታል፡፡
የእመቤታችን ታማኝ ወዳጅ አባ ጽጌ ድንግል በተመስጦ በመኾን እጅግ ድንቅ የኾነችውን የአምላክን እናት ሥዕል ካየ በኋላ ይኽነን የምስጋና ቃላት ለርሷ ያቀርባል፡-
“ሥዕልኪ ጽግይተ ላሕይ ዘከመዝ ትኤድም በዓለም
እፎ ይሤኒ በሰማይ ላሕየ ገጽኪ ማርያም
ሐሤተ ትእምርትኪ እጽገብ አስተርእዪኒ በሕልም
እስመ አውዐየኒ ነደ ፍቅርኪ ፍሕም
አጥፍኦቶ ዘኢይክል ዝናም”
(ማርያም ሥዕልሽ በዓለም እንዲኽ የምታበራ ከኾነ በሰማይ የፊትሽ መልክ ምን ያምር! አንቺን ከማየት የሚገኘውን ደስታ እጠግብ ዘንድ በሕልም ተገለጪልኝ፤ ዝናብ ሊያጠፋው የማይቻለው የፍቅርሽ እሳት አንድዶኛልና) ብሏል፡፡
ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም ይኽነን መገለጧን በእንዚራ ስብሐት መጽሐፉ ላይ፡-
“ኦ ንግሥት ይገንዩ ለኪ ነገሥት ወለኪ ንግሥታት ይትቀነያ
ወኪያኪ የአኲታ ወለስምኪ ይገንያ
ወለኪ ይሰግዳ ወለክብርኪ የሐልያ
ጢሮስ ወሲዶና ሰብአ ግብጽ ወኢትዮጵያ
ፊንቂ ወሮምያ ማሮን ወአርማንያ
በሥነ ጸዳልኪ ይትፌሥሓ ወበላሕይኪ ይትሐሠያ”
(ንግሥት ሆይ ነገሥታት ለአንቺ ያገለግላሉ፤ ንግሥታትም አንቺን ያመሰግናሉ፤ አንቺንም ያሞግሳሉ፤ ለስምሽም ያጐነብሳሉ፤ ለአንቺ የጸጋ ስግደትን ይሰግዳሉ፤ ለክብርሽም ምስጋናን ያቀርባሉ፡፡ ጢሮስና ሲዶና የግብጽና የኢትዮጵያ ሰዎች፣ ፊንቄና ሮምያ፣ ማሮንና አርማንያ በወጋገንሽ ውበት ደስ ይሰኛሉ፤ በደም ግባትሽም እሰይ ይላሉ) በማለት ገልጦታል፡፡
ልቡናቸው በእጅጉ የበራላቸው አኹን እንዳለንበት ዘመን የቃላትም የምስጋናም ድርቅ ያላገኛቸው በምስጢር ባሕር የዋኙ ቀደምት ሊቃውንት ስለ አምላክ እናት ውበት አምልተው አስፍተው የጻፉ ሲኾን የቆጵሮሱ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ እንዲኽ አላት፡-
☞ ☞ “She was grave and dignifified in all her action…” (እመቤታችን በኹሉም ርምጃዎቿ ጐበዝና የተከበረች ነበረች፤ የምትናገረው በጣም ጥቂት ሲኾን ርሱም ለማድረግ አስፈላጊ በሚኾንበት ብቻ ነበር፤ በጣም ዝግጁ ኾና የምትሰማና በቀላሉ ንግግር ለማድረግ የምትችል ናት፤ ለእያንዳንዱ ሰው አክብሮትና ክብር (ሰላምታ) ትሰጣለች፤ ቁመቷ መኻከለኛ ሲኾን አንዳንዶች ግን ቁመቷ ከፍ ያለ እንደነበር ይናገራሉ፤ ከእያንዳንዱ ሰው ጋር ያለምንም ፍርሀት በግልጽነት ያለምንም ሳቅና መጯጯኽ ትናገራለች፤ በተለይ ፈጽማ ለቁጣ የምትጋበዝ አልነበረችም።
መልኳ እንደ ደረሰ የስንዴ አዝመራ ያማረ ጸጒሯ ቀይማ ነው፤ ዐይኖቿ ብሩሃትና የዋህ የኾኑ ቀለማቸውም ፈዘዝ ያለ ቡናማ ኾኖ የዐይኖቿ ብሌኖች የዘይት-አረንጓዴ ይመስላል፤ የዐይኖቿ ቅንድብ (ሽፋሽፍት) ከፊል ክብና ደማቅ ጥቁር ናቸው፤ አፍንጫዋም ረዥም፣ ከናፍሮቿ ቀይና ምሉእ ሲኾኑ በቃሎቿ ጣፋጭነት የተመላባቸው ነበሩ።
ፊቷ ክብ ሳይኾን ግን እንቁላልማ ዐይነት ቅርጽ ነበረው፤ እጆቿ ረዥምና ጣቶቿም በጣም ረዣዥም ነበሩ፤ ከማንኛውም ያልተገባ ኩራት ሙሉ በሙሉ የነጻች ስትኾን ግድ የለሽነት ፈጽሞ ጨርሶ የለባትም ነበር፤ የሚመጡትን ነገራት በፍጹም ትሕትና ትቀበል ነበር፤ ተፈጥሯዊ ቀለማት ያላቸው (ማለትም በቤት ድር የተሠሩ) ልብሶችን ትለብስ ነበር፤ ይኽም በእጅጉ አብሯት የሚኼደው አለባበስና ይኽ እውነታ በራሷ ላይ በምታደርገው ቅዱስ ልብስ አኹን ቅሉ ሊረጋገጥ የሚችል እውነታ ነው፤ ለማጠቃለል ያኽል በመንገዶቿ ኹሉ በመለኮታዊ ጸጋ የተመላች ነበረች) ይላል፡፡
የመልክአ ማርያም ደራሲም የአምላኩን እናት ቅድስት ድንግል ማርያምን ፊቷን ለማየት ሽቶ በናፍቆት ኾኖ፡-
“ሰላም ለመልክእኪ ዘተሠርገወ አሜረ
ዘያበርህ ወትረ
ፍቅርትየ አንቲ እንተ ታበድሪ ፍቅረ
አርእዪኒ ገጸ ዚኣኪ ማርያም ምዕረ
ዘኢይሰምዖ ካልእ እንግርኪ ነገረ”
(ኹልጊዜ (ዘወትር) የሚያበራ ፀሓይን ጌጥ ላደረገ መልክሽ ሰላምታ ይገባል፤ ፍቅርን የምትመርጪ (የምታስቀድሚ) አንቺ ፍቅረኛዬ ማርያም ሌላ የማይሰማው ነገርን እነግርሽ ዘንድ አንድ ጊዜ ያንቺን ፊት ግለጪልኝ) በማለት ተማፅኗታል፡፡
ልክ እንደ ርሱ የአምላክን እናት ፊቷን ለማየት የተመኙ ብዙዎች ቅዱሳን ነበሩ፤ ለምሳሌም ያኽል ከቅዱሳን አበው መኻከል አባ ይሥሐቅ እመቤታችንን በፍጹም ልቡናው ከመውደዱ የተነሣ ከሠርክ ጸሎት በኋላ ሌሎች መነኮሳት ለመኝታ ወደ የበኣታቸው ሲኼዱ ርሱ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመኼድ በቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ፊት ቆሞ በፊቷ እየተማለለ ሦስት መቶ ስግደትን ይሰግድ ነበር።
በእያንዳንዱ ስግደቱ ላይ “ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ አርእየኒ እመከ አሐተ ሰዓተ” (ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ለአንዲት ሰዓት እናትኽን አሳየኝ) እያለ በመጸለይ ለሰባት ዓመት ከቈየ በኋላ፤ በሰባተኛው ዓመት በታላቅ ግርማ ተገልጻለት የአምላክን እናት ፊት ለማየት በቅቷል፤ ርሷም ምን እንደሚሻ ብትጠይቀው በታላቅ መንፈሳዊ ደስታ በመኾን የንግሥተ ሰማይ ወምድር የርሷን ገጽ ያዩ ዐይኖቹ ሌላ ነገርን ማየት እንደማይፈልጉና ከልጇ እንድታማልደው ብቻ እንደሚፈልግ ነግሯት፤ ርሷም ከሦስት ቀን በኋላ እንደሚያርፍ ክፍሉም ከርሷ ጋር መኾኑን ገልጻለት ባርካው ዐርጋ፤ መልኳን አይቶ በሦስተኛው ቀን ይኽ ቅዱስ አባት ዐርፏል፡፡
በመኾኑም በደብረ ምጥማቅ የተገለጠችላቸው ምእመናን የአምላክን እናት አይተው እንደተደሰቱ፤ ዛሬም ለእኛ ለልጆቿ በረድኤት ትገለጽልን ዘንድ አበው ካህናት ሌሊቱን በሰዓታት ምስጋና፦
“ንዒ ኀቤየ ኦ ድንግል ምስለ ወልድኪ ፍቁርኪ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመ ትባርኪ ላዕሌነ” (ድንግል ሆይ ከተወዳጅ ልጅሽ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋራ ወደ እኔ ነዪ እኛን ትባርኪ ዘንድ (በእኛ ላይ በረከትን እንድታሳድሪ) በማለት ይማፀኗታል፤ በገዳም በበረሓ ያሉት አበውም ምስጋናዋን በማድረስ ፍጹም በረከቷን ሽተው በፊቷ ይማለላሉ፤ ርሷም በወደቁበት በረሐ እየተገለጸች በረከቷን ታድላቸዋለች፡፡
[የአምላክ እናት ሆይ ዛሬም ለእኛ ለምንወድሽ ለልጆችሽ ትገለጪልን ዘንድ እንማፀንሻለን፡፡ [በድጋሚ ፓስት የተደረገ]
ከመጋቤ ሐዲስ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ

Post Bottom Ad