ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤውን እያካሔደ በሚገኝበት የዛሬ ኀሙስ፣ ግንቦት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Thursday, May 23, 2019

ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤውን እያካሔደ በሚገኝበት የዛሬ ኀሙስ፣ ግንቦት 15 ቀን 2011 ዓ.ም.

ቅዱስ ሲኖዶስ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ላይ ስለሚደረጉ ጫናዎች ይነጋገራል
Sorce = Hara Tewahido ሐራ ተዋሕዶ
• ኻያ አራት የመነጋገርያ አጀንዳዎችን አጸደቀ፤
• የቤተ ክርስቲያን መሪ ዕቅድ ትግበራ ሒደት…
• አራተኛው ዙር የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ…
• የዋና ጸሐፊ እና የዋና ሥራ አስኪያጅ ምርጫ…
• ማጣራት የተካሔደባቸው አህጉረ ስብከት…
• የውጭ አብያተ ክርስቲያን አስተዳደር ይገኙባቸዋል፤
• የአ/አበባና የመንበረ ጸባዖት ቅ/ሥላሴ ጉዳዮች አጨቃጨቁ፤
• ጠ/ሚኒስትሩን ከማድመጥ ባሻገር የመወያየት ፍላጎቱ ነበር፤
***
ኦርቶዶክሳውያን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ ሥርዓተ እምነታቸውን በነፃነት በመፈጸም ረገድ፣ በአንዳንድ ክልሎች በሚገኙ የተቋማቱ የአስተዳደር ሓላፊዎችና ሠራተኞች እየደረሰባቸው የሚገኘው ልዩ ጫና እና አድልዎ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ትኩረት ሰጥቶ ከሚነጋገርባቸው አጀንዳዎች አንዱ ኾኗል፡፡
ምልአተ ጉባኤው ትላንት ከቀትር በኋላ በነበረው ውሎ፣ በተሠየመው የአጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴ የቀረቡ ኻያ አራት የመነጋገርያ ነጥቦችን መርምሮ እንዳለ በመቀበል አጽድቋል፡፡
ወቅታዊውን የአገር ሰላም እና የቤተ ክርስቲያን ችግሮች በቀዳሚነት በአካተተው የአጀንዳው ዝርዝር፥ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሥር በተቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴ ሓላፊነት ቅድመ ዝግጅቱ በመካሔድ ላይ ያለው የቤተ ክርስቲያን መሪ ዕቅድ አፈጻጸምና ከተራዘመው አራተኛው ዙር የሕዝብና ቤት ቆጠራ ጋራ በተያያዘ የቤተ ክርስቲያንን አቋምና ዝግጅት የሚመለከተው ነጥብ ይገኝበታል፡፡
አለመግባባት ያለባቸውና ማጣራት የተካሔደባቸው እንደ ካፋ፣ ደቡብ አፍሪቃ፣ አትላንታ ሰዓሊተ ምሕረት፣ ፊላዴልፊያ ቅዱስ ዐማኑኤል እና የኢየሩሳሌም ገዳማት ያሉ አህጉረ ስብከት ሪፖርቶችንም መርምሮ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡ የሀገረ ስብከት ድልድላቸው እንዲስተካከልላቸው ጥያቄ ያቀረቡ አራት የሰሜን አሜሪካ እና የካናዳ ሊቃነ ጳጳሳትን ጉዳይ መርምሮ እልባት ይሰጣል፡፡
ከእኒህም መካከል፣ የዋሽንግተንና አካባቢው ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ማርቆስ፣ ከተመደቡበት ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ፣ ሀገረ ስብከቱን በተቋማዊነት ለማዋቀር ስላለባቸው ድክመት፤ የዓምባገነናዊነትና የቤተሰባዊነት አካሔድ እንዲሁም በዕርቀ ሰላሙ ሾልከው ከገቡ ተሐድሶአውያን ጋራ ባላቸው ልዩ ግንኙነት፣ በሲያትልና በፖርትላንድ የአድባራት አስተዳዳሪዎችና ካህናት አቤቱታ ቀርቦባቸዋል፡፡ በ41 የአድባራት ሓላፊዎችና አገልጋዮች ፊርማ የተደገፈው አቤቱታው፣ በጳጳሱ ያልተገባ አካሔድ ሳቢያ ከፊሎቹ አድባራት አብረዋቸው ለመሥራት በመቸገራቸው ራሳቸውን መለየታቸውን ጠቅሷል፡፡
“ጳጳሱ የቆየውን የአገልጋዮች አንድነት ለመናድ፣ በጎጥ ከፋፍለው ኅብረታችንን ለመሸርሸር እየጣሩ ከመኾናቸውም በላይ ምእመናንን ሳይቀር እየለያዩ ወደ ቀድሞው የጥል ዘመን ሊመልሱን እየሠሩ ነው፤” ብሏል፡፡ ኹኔታው ወደ አልተፈለገ ውጤት ከመድረሱም በፊት ቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲጣቸው፣ ካህናቱ በአቤቱታቸው ተማፅነዋል፡፡ በጳጳሱ ከለላ ኑፋቄውን በዐደባባይና ቤት ለቤት ከማስፋፋት ያልተገታው ሰርጎ ገቡ ልዑለ ቃል አካሉ፣ ሐምሌ 2 ቀን 1990 ዓ.ም. በቅዱስ ሲኖዶሱ የተላለፈበትን ቀኖና ያልፈጸመበትን ምክንያት በምልዓተ ጉባኤው ፊት ቀርቦ እንዲጠየቅበት አዘክረዋል፤ አኹንም እንግዳ ትምህርት ከማሠራጨት እንዳልተቆጠበና ይኸውም በማስረጃ የተያዘ በመኾኑ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ተመርምሮ የማያዳግም ርምጃ እንዲወሰድበት፣ በሲያትል ማኅበረ ካህናት ደረጃ የተያዘውን አቋም ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በአደረሱት አቤቱታቸው አቅርበዋል፡፡
በሌላ በኩል ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ ለወራት በውዝግብ የቆየውን የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ጉዳይን ጨምሮ በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ እና በዝዋይ ሐመረ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጆች ላይ በቀረቡ ጥናቶች ይወያያል፡፡ በውጭ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳደር እና በተለይም በአንዳንዶቹ፣ በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አፈጻጸም ረገድ ስለሚታዩ መተላለፎች ተገቢውን አቅጣጫና ማስተካከያ ያደርጋል፡፡
በሕገ ቤተ ክርስቲያን ድንጋጌ መሠረት፣ የወቅቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ የሦስት ዓመት የሥራ ዘመናቸውን የሚያጠናቅቁት በዚኹ የምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ እንደ መኾኑ፣ የተተኪዎች ምርጫን ያካሒዳል፤ አልያም ሕጉ እንደሚፈቅደው፣ በሓላፊነት ላይ የቆዩት ኹለቱ ብፁዓን አባቶች ለተጨማሪ አንድ የሥራ ዘመን መቀጠል ይችሉ እንደኾን ይወስናል፡፡
ኮሚቴው፣ የአጀንዳውን ረቂቅ ለውይይት በአቀረበበት ወቅት፣ በተራ ቁጥር(6) የተያዙት፥ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአስተዳደር ችግርና የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጉዳይ ሲጠቀስ፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ መካተት እንደሌለበት ተቃውመዋል፤ ለመካተቱም ዋና ጸሐፊውን ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስን በመውቀሳቸው፣ ኹለቱ አባቶች ኀይለ ቃል ተለዋውጠዋል፡፡
ርእሰ መንበሩ፣ በተጠቀሱት አካላት ላይ ችግር እንደሌለና በአድመኝነት ችግር የሚፈጥሩት ዋና ጸሐፊው እንደኾኑ አድርገው ሲከሡ፤ ዋና ጸሐፊው በበኩላቸው፣ ፓትርያርኩ በልዩ ሀገረ ስብከታቸውም ኾነ በካቴድራሉ የአስተዳደር ችግር መኖሩን አምነው እንዲቀበሉ፣ ይኸውም ከችሎታ ማነስ እንደኾነ በማንሣት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የኹለቱ የተካረረ ኀይለ ቃል ልውውጥ፣ ድምፅ ማጉያውን በማጥፋት ሲገታ፣ ጉዳዩ ግን በአጀንዳነት እንዲያዝ ምልዓተ ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
ከአጀንዳ ማጽደቁ ቀደም ሲል፣ በምልዓተ ጉባኤው የተገኙትን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ንግግር ያደመጠው ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ ሰምቶ ከመሸኘት በቀር ምንም ዓይነት ውይይት አላካሔደም፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግርና ተያያዥ ጉዳዮች፣ ጥያቄና አስተያየት በማንሣት ለመወያየት ፍላጎትና ጉጉት ያላቸው ብፁዓን አባቶች እንደ ነበሩ፤ መርሐ ግብሩም በዚኹ አካሔድ የታሰበበት እንደ ነበር ተጠቁሟል፡፡ ኾኖም፣ ዶ/ር ዐቢይን ከውጭ ከመቀበል ጀምሮ ለምልዓተ ጉባኤው አባላት በማቅረብ ሥነ ሥርዓቱን በራሳቸው የመሩት ርእሰ መንበሩ፣ ዕድሉን ለብፁዓን አባቶች ሳይሰጡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን መሸኘታቸው ታውቋል፡፡gnbogn

Post Bottom Ad