ፈተና በክርስትና ጉዞ (ክፍል ሁለት) - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Wednesday, December 27, 2017

ፈተና በክርስትና ጉዞ (ክፍል ሁለት)አንድ ክርስቲያን፤ ክርስቲያን በመሆኑ ብቻ በተለያየ  መልኩ ሊፈተን ይችላል።  ለምሳሌ የግብጽን ክርስቲያኖች ብንመለከት፤ 85% የሚሆነውግብጻዊ እስልምናን ይመርጣል፣የግብጽ መተዳደሪያ የእስላምሻርያ ሕግ እንዲሆን ይፈልጋል፣ የሚሰርቅ ሰው እጆቹ እንዲቆረጡበት ይመኛል፣ ሴቶች እናክርስቲያኖች እንደሁለተኛ ዜጎች ሆነው እንዲኖሩ ያቅዳል። ይህንንም የግብጻውያንን የልብ ትርታበደንብ የተረዱት የእስላም ፓርቲዎች ሴቶች እና ክርስቲያኖች ፕሬዚደንት መሆን እንደማይገባቸው፡እንዲያውም ቁልፍ የሆኑ የሥልጣን ቦታዎችን መያዝ እንደሌለባቸው በመተዳደሪያዎቻቸውአስቀምጠዋል። አሁንም ቢሆን፡ ክርስቲያን ግብጻውያን፡ ፖሊስ መሆን፣ በውትድ ማገልገል፣የእስላም ትምህርት ተቋሞች ውስጥ ገብቶ መማር ወይም ማንኛውም የብሔራዊ የስፖርት ቡድንውስጥ የመሳተፍ መብት የላቸውም። ይህን አሳፋሪ ሁኔታ የዓለም ማሕበረሰብ እንደማያውቅ ሆኖዝም ብሎታል፣ እግዚአብሔር ግን ከቶ አይረሳውም፤ አልረሳቸውምም።
እግዚአብሔርም ለሚወዱት እንደ ሃሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ 8፤28።  ሁልጊዜ እግዚአብሔርን ያለ ማቋረጥ በትእግስት ልንጠብቀው ይገባል። የጻድቁ የዮሴፍን ታሪክ ብንመለከት ወንድሞቹ በቅንአት መንፈስ ተነሳስተው

በሸጡት ጊዜ ሥራቸው ክፋትና ጭካኔ የተሞላበት ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር አምላክ ያንን የክፋትና የተንኮል ሥራቸውን አይቶ ወደ በጎ ለወጠው። ዮሴፍንም በሰው ሃገር በፈርዖን ላይ ተሹሞ ሕዝቡም ሁሉ ለቃሉ ታዛዥ፤ በፈርዖን መንግስት ሁለተኛ ባለ ሥልጣን እንዲሆን አደረገው። ጻድቁ ዮሴፍም ለወንድሞቹ እንዲህ ብሏቸው ነበር፤ እናንተ ክፉ ነገርን አሰባችሁብኝ እግዚአብሔር ግን ብዙ ሕዝብ እንዲድን ለማድረግ ለመልካም አሰበው ዘፍ 45። ምንጊዜም  ሐሰትና ክፉ ነገሮች የሚመነጩት ከዲያብሎስ ቢሆንም “አቤቱ ወደ ፈተና አታግባን” ብለን ሁልጊዜ ልንጸልይ እና እግዚአብሔርን ልንማጸን ይገባል።  አንድ ሰው ቀለል ባለ በሽታ በመዳኑ ምክንያት ፈጣሪውን 
ካመሰገነ፤ በሕይወቱ ውስጥ ለትንንሽ ነገሮች የሚያመሰግን መሆኑን ያመላክታል።  በአንጻሩም አንዳንድ ሰዎች ገና የትምህርት ውጤት እንደጠበቁት ስላልመጣላቸውም ይሁን በኑሯቸው ሁኔታ ስላልተደሰቱ ብቻ እግዚአብሔርን በትንሽ በትልቁ የሚያማርሩ፤ ባልፈጠርኩ ይሻለኛል እስከማለት የሚደርሱ ብዙ ናቸው፤ ይህ ደግሞ ተገቢ አይደለም።  ቅዱሳን አባቶች “ጸጋ ያለ ምስጋና አያድግም” እንዳሉ በማንኛውም ጊዜና ወቅት እግዚአብሔርን ተመስገን ማለት ተገቢ ነው። ምስጋና የማያቋርጥ በረከት ያለው ስለሆነ ካገኘን ፈተና እንድናለን፤ የመጣብንን ፈተና በትእግስት ልንወጣ ያስፈልጋል ምሳሌውንም ከኢዮብ እንማራለን።  
ጻድቁ ኢዮብ ቤተሰቦቹን፤ ጓደኞቹን፤ ዘመዶቹን፤ ሃብቱን ባጣ ጊዜ፤ የሚጠጋው ሰው ባጣ ጊዜ፤ አይዞህ የሚለው ሰው ባጣ ጊዜ፤ ሚስቱም ጥላው በሸሸችው ጊዜ፤ የፈጠረውን ፈጣሪውን አልካደም እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔር ነሳ ብሎ አመሰገነ እንጂ።  ጻድቁ ኢዮብ ይህን ከባድ ፈተና በትእግስት ተወጣው እግዚአብሔርም የሱን ትእግስት ተመልክቶ ከፊት ይልቅ በብዙ ባረከው አከበረው።  ምንጊዜም የሰው ልጅ ፈተና ላይ መውደቁ የማይቀር ቢሆንም እንደ ጻድቁ ኢዮብ በፈተና ጊዜ እንዴት አጥብቀን መጸለይ እንዳለብንና፤ የመጣውን ፈተና እንዴት መወጣት እንደምንችል አስተምሮናል። አንድ አባት እንዲህ ብለው ነበር፤ እመኑኝ፤ “ስለተቀብልናቸው ስጦታዎች ብቻ የምናመሰግን ከሆነ ፍቅራችንን የምንገልጸው ስጦታዎቹን ለሰጠን ለፈጣሪ ሳይሆን ለተሰጡን ስጦታዎች ይሆናል።  ነገር ግን በመከራ ውስጥ እግዚአብሔርን የምናመሰግን ከሆነ ስጦታዎቹን ሳይሆን ፈጣሪያችንን መውደዳችንን እናረጋግጣለን”።  ይህ ማለት እርሱን የምናመሰግነው፤ ሃብትና ክብርን ስለሰጠን ብቻ ሳይሆን የጸጥታና የሰላም ባለቤቶች ስላደረገን፤ ወደ በጎ የሚለውጣቸውን የተለያዩ መከራዎችንም ስለሰጠን እናመሰግነዋለን እንጂ። ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር እጆች በመከራና በፈተና ወቅት ሲሰሩ እንመለከታቸዋለን።   በፈተና ወቅት አምላካችንንና ሥራዎቹን፤ ወደ ሕይወታችን የሚያደርገውን መምጣቱን እና ጥበቃውን፤ ድንቅ ሥራዎቹን እንድናይ ያደርገናል።  በተጨማሪም ያለ መከራ ልናገኛቸው የማንችላቸውን መንፈሳዊ ልምዶች ይሰጠናል።  መጽሐፍ ቅዱስ “ስለ ክርስቶስ ተሰጥታችኋልና ስለ እርሱ ደግሞ መከራ ልጥቀበሉ እንጂ በርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም እንዳለ ፊል 1፤9።


ፈተና ምን እንደሚመስል እስኪ በመጽሐፍ ቅዱስ በቅዱሳን አባቶቻችን ላይ የተከሰተውን ታሪክ እንደ ምሳሌ እንመልከት፤
·        *        
ዮሴፍ 
 
 እንደ ባርያ ተሸጦ በነበረበት ወቅት፤ በፈተና ጊዜ እግዚአብሔር እንዳልተለየው
·       *         በውዴታና በግዴታ እያገለገለ ሳለ በጲጥፋራ ሚስት በሐሰት ክስ ምክንያት ወደ እስር ቤት መውረዱ፤

·       *          ዮሴፍም እግዚአብሔር በእስር ቤት እንደረሳው እያሰበ ለተወሰነ ጊዜ መቆየቱ፤

·       *         እግዚአብሔር ወዳጁን አይረሳምና የዮሴፍን መከራ ተመልክቶ፤ ከእስር ቤት አውጥቶ የግብጽ ቀዳሚ ገዥ እንዳደረገው፤
·        *            መርዶክዮስ መስቀያ ግንዶቹን ካዘጋጀለት ከሐማ ብዙ ስቃዮቹን ተቀብሏል
·       8           ሐማም ሁሉንም ሰዎች እስኪያጠፋ ድረስ በኢ-ፍትሐዊነቱና በጭካኔው ቆይቷል
·       *          እግዚአብሔርም የሕዝቡን ፈተናና መከራ፤ ጸሎት ተመለከተ።  እግዚአብሔርም መርዶክዮስንና ሕዝቦቹን አዳናቸው።  ሐማም ለመርዶክዮስ ባዘጋጀው ግንድ ላይ ተሰቅሎ ሞቷል አስ 7፤10
·        8        ንጉስ ድዮቅልጥያኖስ በቤተ ክርስቲያናችንና በምዕመናን ላይ ያደረሰው ጉዳት መቼም አይዘነጋም።  የብዙ ሰማዕታትን ደም ያፈሰሰ ጨካኝ ንጉስ ነበር።  እግዚአብሔርም ከዚህ ጨካኝ ንጉስ ሕዝበ ክርስቲይንን አዳነ።
·        *        ንጉስ ቆስጥንጢኖስ የክርስትና ኃይማኖት ነጻነትን ባወጀ ጊዜ የክርስቲያኖች ፈተናና ስደት አከተመ።
·        *         ዮዲት ጉዲት በኢትዮጵያ ምድር በክርስቲያኖች ላይ ያደረሰችው ከባድ አደጋ መቼም አይዘነጋም።  ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፤ ብዙ ሰማእታትም የሆኑ አሉ፤ ይህ ለኢትዮጵያዊያን ክርስቲያኖች ከባድ ፈተና ነበር።  ነገር ግን እግዚአብሔር አምላክ ሕዝበ ክርስቲያኑን ታደገው።
ከፈተና ለመዳን ሁልጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል መመገብ ያስፈልጋል።  ፈተናን በጾምና ጸሎት እንዴት ድል እንደምናደርግ ያስተማረን የቃሉ ባለቤት ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።  ከላይ እንደተገለጸው፤ ፈተና ምንጊዜም ከዲያብሎስ መሆኑ የታወቀ ቢሆንም የፈጠረውን ፈጣሪውን ኢየሱስ ክርስቶስን ሦስት ጊዜ ከመፈተን ወደ ኋላ አላለም። 
ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዲይብሎስን
·        *         የመጀመሪያውን ፈተና ያከሸፈበት ቃል የቃለ እግዚአብሔርን እንጀራነት ይገልጻል፤
·        *        የሁለተኛውን ፈተአ ያከሸፈበት
መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ወደ ታች ራስህን ወርውር አለው።
ኢየሱስም፦ ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል አለው።
·       *         የሦስተኛውን ፈተና ያከሸፈበት
 ዲያብሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፥ የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ።
ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው።
ያን ጊዜ ኢየሱስ፦ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና አለው። ያን ጊዜ ዲይብሎስ ተወው፤ እነሆም መላእክት ቀርበው ያገለግሉት ነበር።

ዘወትር ለእግዚአሔር ምስጋና ማቅረብም ሰውን በምድር ላይ መልአክን ያስመስለዋል እንዳለ ኢሳ 6፤13 ሁልጊዜ በፈተናም ሆነ በጥሩ ሁኔታ ባለንበት ወቅት ፈጣሪን ተመስገን ከማለት ወደ ኋላ አንበል።  ምስጋና የባህርይ ገንዘቡ ለሆነ አምላክ በማንኛውህም ወቅት ልናመሰግን ይገባል። አሁን ባለንበት ዘመን ክህደት እንደ ፍልስፍና የበዛበት ዘመን በመሆኑ እግዚአብሔርን የማያውቁ እና ህልውናቸውን የካዱ ብዙ ሰዎች አሉ።  ሃገረ እግዚአብሔር ተብሎ ከሚነገርላት ብርቅየ ሀገራችን፤ ስብሃተ እግዚአብሔር ከሚፈስባት ሃገራችን ውስጥ እንድ ሰው እግዚአብሔር የለም ብሎ መናገሩ፤ ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ጊዜያት መቃጠላቸው፤ ገዳማትን የማረስ፤ አገልጋይ ካህናትን ማንገላታት፤ የካህናትና የምእመናን በስመ ክርስቲያን መንገላታታቸውና ሰማዕት መሆናቸው፤ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ዘረኝነት መስፋፋት እና በጥቅማ ጥቅም እየተደለሉ ቤተ ክርስቲያንን ለሌላ ሃይማኖት አሳልፎ ለመስጠት መሯሯጥ የተለመዱ የቤተ ክርስቲያን ፈተናዎች ሆነዋል። እነዚህን ፈተናዎች እንዴት እንደምንወጣው ከቅዱሳን አባቶቻችን እንማራለን።  ተግተን እንጸልይ ወደ ፈተና እንዳንገባ። በህይወታችን፤ በኑሯችኡን፤ በዘመናችን፤ በአካሄዳችን ሁሉ ሁልጊዜ እግዚአብሔርን ማስቀደም ይኖርብናል።  ይህን ካደረግን እግዚአብሔር አምላክ ከ እኛ ጋር ይሆናል። ፈተናውንም በድል እንወጣለን።
የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ከብዙ ፈተና ይጠብቀን።
ስብሐት ለእግዚአብሔር ኪያነ ዘፈጠረ ከመ ነአምልኮ

Post Bottom Ad