መስክረው የዳኑት እውነት ጨብጠዋል
በዕምነታቸው ፅናት ነገስታት ፈርተዋል
በቅዱሱ መፅሐፍ ተፅፎ አይተናል
ለተላከው መልዓክ ምስጋና ይገባል
የእሳቱን ወላፈን አይተው ሲዘምሩ
በተመስጦ ሆነው ሲታያቸው ክብሩ
ነበልባል ቃጠሎውን አንዳችም ሳይፈሩ
አምላክ ያድነናል ብለው መሰከሩ።
ናቡከደነፆር ንግስናውን ሽቶ
የከለዳውያንን ክስ ተመልክቶ
አፀደቀላቸው አዋጁን አውጥቶ
ለዚህ ወርቅ ምስል በአንገቱ ተደፍቶ
ይስገድ ብሎ አዘዘ ፈተና አዘጋጅቶ።
ለባዕዱ ጣዖት የማይሰግድ ቢኖር
ወደ እቶን እሳት ፈጥኖ እንዲወረወር
በማለት ተናግሮ ክፋት ሲቀምር
ሠልስቱ ደቂቅም ይሰሙ ነበር።
ከዚህ ከሚነደው ከሚጠፋው እሳት
ይችላል ሊያድነን አምላከ አማልእክት
አንፈራም አንክድም ተዋህዶን እምነት
አልፋና ኦሜጋ የደስታችን ሙላት
ብለው አስተማሩን አንዲቷን ሐይማኖት።
ሲድራቅና ሚሳቅ ብሎም አብድናጎም
በተማመኑበት በመድኀኒአለም
በፀሎት ተወስደው ወደ ሠማይ አለም
ለናቡከደነፆር ምላሽን አልሰጡም።
ንጉሱም ተነሳ በንዴት ተሞልቶ
እሳቱን አንድዱት አለ ተቆጥቶ
ከነበረው ይልቅ ሰባቴ አብዝቶ
የሀገሩ ገዢ ህሊናውን ስቶ።
ታሰሩ ነፍሳቱ ሊጣሉ ወደ እሳት
ሃያላኑም መጥተው ሰሩ በታዘዙት
ሠልስቱ ደቂቂን ጨመሩ በቅፅበት
ከነጥምጣማቸው ያለ አንዳች መሳሳት።
አናንያ አዛርያ ሚሳኤልም ገብተው
በዛ በነደደ ውስጥ በጨካኝ ተጥለው
በፅናት በዕምነት ምስጋናን ተሞልተው
መላኩ ገብርኤል ደርሶ አዳናቸው።
ልዑካኑ ከዳር ቆመው ሲመለከቱ
በዕሳቱ ወላፈን ተገርፈው ሲሞቱ
ተገርመው ተደንቀው የተቀመጡቱ
ዘመሩ በደስታ እነዛ ህፃናቱ።
ብሥራታዊው መልዓክ ከሠማያት ወርዶ
በበትረ መስቀሉ በክንፎቹ ጋርዶ
በተሰጠው ሥልጣን እሳቱን አብርዶ
አየነው ሲዋረድ ዕብሪተኛው ዘንዶ
እጅግ ያስደንቃል ይሄ ተዋህዶ።
ዛሬም እንደ ትላንት ከለዳውያኑ
የበግ ለምድ ለብሰው ሐሰት የተካኑ
መስቀሉን ጨብጠው እንደ መምህራኑ
ነፍሳትን ማርከዋል ሀቅ እየከደኑ።
አስተውል ትውልድ ሆይ ልብህን መርምረው
የያዝከው ሐይማኖት ጉድለቱ ምንድነው?
ተማር ከአባቶችህ መቅደሱ ክፍት ነው
የወንጌሉን ፍሬ ቅመስ ከአንድምታው።
አትብረር ዝም ብለህ አስተውል በእርጋታ
ስለ ሁሉም አለ በአጋቤው ገበታ
ጠንክር በእምነትህ አትሁን ልበ መንታ
ይመጣል ይፈርዳል አማኑኤል ጌታ
በቀንና ሌሊት ላፍታ የማንረሳሽ
ኪዳንሽ የፀና የፍቅር አደራሽ
ቅድስተ ቅዱሳን ይጣፍጣል ምልጃሽ
አሳስቢ ድንግል ሆይ ከመሀሪው ልጅሽ።