ምዕመናን ለምን ይወዛገባሉ? - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Friday, November 13, 2015

ምዕመናን ለምን ይወዛገባሉ?


የእግዚአብሔርን ቃል ለራሱ ክብርና ዝና የሚጠቀም ከ እግዚአብሔር ይልቅ ለራሱ ወይም ለድርጅቱና ለወገኑ ክብር የሚያደላ ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ ፊል 2፤3
አባ ኔቅጣስ የተባሉ በጸሎት የተጉ አባት ነበሩ።  እኒህ አባት ስለ ሁለት ሰዎች እንዲህ በማለት ተናገሩ። አንድ ጊዜ ሁለት መነኮሳት በአንድነት እየጸለዩ ለመኖር ወሰኑ።  የመጀመሪያው አባት አብሮት ለመኖር ላሰበው አባት መልካም ምኞትን ተመኘ እንዲህ ሲል “ወንድሜ የሚፈልገውን ሁሉ አደርግለታለሁ” ብሎ ቃል ገባ።  ሁለተኛው አባት ደግም “የወንድሜን ፈቃድ እፈጽማለሁ” ሲል በልቡ ወሰነ።  በዚህ መልካም ፈቃዳቸው ለብዙ ዘመናት በተሳካ ሁኔታ በለጋሥነት አብረው በሰላም ኖሩ።  እኒህ አባቶች ተስማምተው፤ ተፋቅረው፤ ተሳስበው በሰላም ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ ሲኖሩ ዲያብሎስ በእነዚህ አባቶች አምላካቸውን በማስደሰት እና መልካም ሥራን ሲሰሩ ስላየ ቀናባቸው። ዲያብሎስም በበዓታቸው በር ቆመና ለአንደኛው መነኩሴ አባት ርግብ፤ ለሌላኛው መነኩሴ አባት ደግሞ ቁራ ሆኖ ታያቸው።  በዚህን ጊዜ አንደኛው መነኩሴ እርግቧን ተመለከትካት አለው።  ሌላኛው መነኩሴ ደግሞ ቁራ ነው እንጂ ርግብ አይደለም፤ ርግብ እና ቁራ እንዴት አትለይም ብሎ መለሰ።  በዚህን ጊዜ ዲያብሎስ በሁለቱ መነኮሳት ምግባር የቀናባቸውን ያህል ለማጣላት ክፍተት አገኘ።  ወዲያውኑን አንደኛው መነኩሴ ርግብ ናት ሲል ሌላኛው መነኩሴ ደግሞ ቁራ ነው እየተባባሉ መጨቃጨቅ ጀመሩ።  ለአንድ ሰከንድ እንኳ በጠብ ተነጋግረው የማይውቁ አባቶች ነገሩ እየከረረ ሄዶ እስከ ድብድብ ድረስ ደረሱ ያውም ደም እስኪፋሰሱ።  በመጨረሻም የየራሳቸውን ኑሮ ለመኖር ወስነው ተለያዩ። እነዚህ አባቶች መነኮሳት ከሦስት ቀን በኋላ በራሳቸው ላይ ያደረጉትን ማሰብ ጀመሩ። ወደ ልባቸውም ተመልሰው እጅግ ተጸጸቱ። ሁለቱም መነኮሳት አባቶች ከልብ የሆነ ይቅርታ ተጠያይቀው እርስ በ እርሳቸው ታረቁ። ሁለቱም አባቶች በአንድ ጊዜ ሁለት የተለያየ ነገር እንዴት ልናይ እንችላለን? ይህ ከዲያብሎስ መሆን አለበት ብለው ነገሩን ከተረዱ በኋላ እጅግ በፈጸሙት ስህተት አዘኑ።  ለዚህም ፈጣሪያችንን አሳዝነናልና ይቅር ይበለን ብለው በአንድነት እንደለመዱት ሥር ዓት ጸሎታቸውን አቀረቡ። ከዚህ ዕለት ጀመሮ ሞት እስኪለያያቸው ድረስ ያለምንም ጸብ ፈጣሪያቸውን በአንድነት፤ በፍቅር፤ በፍጹም ሰላም፤ በጾም እና በጸሎት እየተጉ ኖሩ ብለው አስተምረዋል።  ከእኛ በፊት የነበሩት ቅዱሳን አባቶቻችን ምሳሌ የሁኑበት ምክንያት ዓለምንና በውስጧ ያሉትን ነገሮች ባይንቁ ኖሮ ቅድስናን አያገኙም ነበር። ለዚህም ነው እኛ የእነሱን ፈለግ ተከትለን የምንጓዘው። አባቶቻችን መነኮሳት ጾምን ይወዳሉ፤ ፍቅርን ይወዳሉ፤ ሰላምን ይወዳሉ፤ በጽድቅ መመላለስን ይወዳሉ፤ ለዚህም ነው የእነሱን የክርስትና ጉዞ እንደምሳሌ አድርገን ልንጠቀምበት የሚገባው።  ከ እነዚህ ሁለት ቅዱሳን መነኮሳት የምንማረውም ፍቅርን፤ ሰላምን፤ አብሮ መኖርን፤ አብሮ መጸለይን፤ መተሳሰብን እና በክርስትና ሕይወት እየኖሩ ሰይጣንን ድል ነስቶ እስከ መጨረሻው በሃይማኖት ጸንቶ መኖርን ነው። የሕይወታቸው አኗኗርም መሰረት ያደረገው በክርስትና የታነጸ ኑሮ፤ ጾም እና ጸሎት ነው።  የተቀደሱ መነኮሳት ሕይወታቸውን ሙሉ ከበዓለ ሃምሳ ውጭ ይጾማሉ።  እንደዚህ ዓይነት ጾም ለነፍሳቸውም ለሥጋቸውም ጠቃሚ ነው። አሁን ከእነዚህ ሁለት መነኮሳት የምንማረው፤ ዲያብሎስ አንድን ሰው መልካም ነገር ሲሰራ በተመለከት ጊዜ ቀስቱን መልካም ወደ ሚሰራው ሰው ላይ እንደሚያነጻጽር እና ወዲያውኑ በዚህ መልካም በሚሰራው ሰው ላይ ሌላኛው እንዲቆጣና ጸብ፤ ግርግር እንዲፈጠር ያደርጋል።  በዚህም የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች የሆኑትን ትዕግስት፤ ትህትና እና በጎነትን እንዲዘነጉ ያደርጋል። ማንኛውም መንፈሳዊ ድርጊት በዲያብሎስ ለሚዘጋጁ መሰናክሎች የተጋለጠ እንደሆነ ቅዱስ መጽሐፍ ያስተምረናል።  ፈቃድ አለኝና መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም ሮሜ 7፤18 በማለት እንደተናገረ አንድ ሰው መልካም የሆነውን መንፈሳዊ ተግባር ለመፈጸም ከተነሳሳ በኋላ ያ መልካም ምግባሩን እንዳይፈጽመው ዲያብሎስ ባለው ኃይል በሙሉ ይቃወመዋል።  ዲያብሎስም በሙሉ ኃይሉ ተጠቅሞ ሊያሰናክላቸው የሞከረው እኒህን አባቶች ምንኛ እግዚአብሔርን በኑሮአቸው ቢያሰድስቱት ነው? አንድ ሰው ከሌላ የሚለየው የራሱ ባሕርይ አለው፤ ለአንዱ የሚሆነው ለሌላው ላይሆነው ይችላል ስለዚህ ከእነዚህ ቅዱሳን መነኮሳት ተምረን አብሮ መጸለይን፤ ተሳስቦ በፍቅር መኖርን፤ መረዳዳትን፤ መተሳሰብን፤ ለሌላው መኖርን፤ በሃይማኖት ጸንቶ መኖርን፤ ዲያብሎስን ድል የምንነሳበትን ጾም ጸሎት ማዘውተርን፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን ገድላትን ተአምራትን ድርሳናትን በማንበብ እና በአጠቃላይ የቅዱሳን አባቶቻችን እና እናቶቻችንን የቅድስና ሕይወት ኑሮአቸውን አብነት አድርገን ልንኖር ይገባል።
ወደ እኛ ሕይወት ልመልሳችሁና በአሁኑ ጊዜ ያለን እኛ የቅድስት ቤተክርስቲያን አገልጋዮችም ሆነ ምዕመናን ከወጭ የሚያዩን ሰዎች ወይም ኢአማንያን (አሕዛብ) በእርግጥ በእነዚህ ቅዱሳን አባቶች ይማራሉ ብለው ይመሰክሩልን ይሆን?  ሃይማኖታችን፤ ምግባራችን፤ ጸሎታችን፤ ምጽዋታችን በአጠቃላይ ያለን የክርስትና ሕይወት የይምሰል የሆነ ስንቶቻችን ይሆን?  በአሁኑ ሰዓት እንደ ወትሮው ቤተክርስቲያናችን በጸረ ተሐድሶ ፕሮቴስታንታዊ እንቅስቃሴ ስትፈተን፤ ስትታመስ፤ ክህነት የሌለው ማንኛውም ግለሰብ ማጥመቅ እንደማይችል እያወቅን አጥማቂ ነን በሚሉ የትም በመጡ ወፍ ዘራሽ ቤተክርስቲያኒቱ ስትመዘበር፤ ባሕታዊ ነን እያሉ በየገዳማቱ እራሳቸውን በሰንሰለት እየገረፉ ወዮልሽ ወዮልህ እያሉ በተቃራኒው ጨርቃቸውን መሬት ላይ አንጥፈው ገንዘብ የሚለምኑ (በተሳሳተ መንገድ ክርስቲያኑን ግራ ሲያጋቡት)፤ የዘፋኝነት እና ፍጹም የዓለማዊ ሕይወት ያላቸው ሆኖ ሳለ የዓለማዊ ዘፈናቸው አልሸጥላቸው ሲል ወደዚህች ቅድስት ቤተክርስቲያን በመምጣት ከአንዱ መዝሙር ቤት በመነጋገር መዝሙር ላወጣ ነው ስንት ትከፍለኛለህ? በማለት መዝሙሩ በሊቃውንት ሳይፈተሽ ድምጿ ወይም ድምጹ ስላማረ ብቻ ህጸጽ ይኑረው አይኑረው የሚያጣራ አካል ስለሌለ አሳትመው ከጨረሱ በኋላ ኑ ተገኙልኝ በዚህ ሆቴል አዳራሽ መግቢያ ዋጋ ይህን ያህል እየተባለ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያኒቱ ስም ሲነገድ፤ በሲዲ የሚሰራጨው የመናፍቃን የስብከት ዓይነት በብዛት በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስም ሲነገድ፤ መናፍቃን መረባቸውን ዘርግተው ሌት ተቀን ሲኖዶስ ድረስ ገብተው ሲሰሩ እኛ ምን እያደረግን ይሆን? መልሱ ዝም እና ለዘብተኝነት እና የገሌ ሰባኪ ቲፎዞ፤ የገሌ አጥማቂ ቲፎዞ ብቻ ሆኗል። ያሳዝናል።  ለግለሰብ ሳይሆን ለቤተክርስቲያን ዘብ እንቁም ካለፉት ቅዱሳን አባቶቻችን የተማርነው ይህንን ነውና።  ጉዞአችን ወዴት ይሆን? እሰቡበት።  በቅርቡ ሲኖዶሱ የወሰነው ውሳኔ ቢያስደስተኝም ተግባራዊ የሚሆነው መቼ እንደሆነ አላውቅም።  እኔ በበኩሌ በግብጻዊያን አባቶች እቀናለሁ ምክንያቱም ለሃይማኖታቸው ቀናኢ ናቸው።  እውነት እነሱ እንዳሉት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለራሷ ጳጳሳት እንዲሾሙ መንፈስ ቅዱስ አልፈቀደም የተባለው እውነት ይሆን? መቼ ይሆን አባቶቻችን ለሃይማኖታቸው ተግተው የሚሰሩት? በግልጽ እንደዚህ መናፍቃን ቤታችን ገብተው ምዕመናኑን ወደ አዳራሽ ሲወስዱት ዓይናችን እያየ ዝም ብለን ኖረን አሁን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርቲያን የምዕመናን ቁጥር በጣም ቀንሷል ብሎ ማውራት እጅግ ያሳፍራል።  ምክንያቱም አይሰሩማ።  እየወቀስኩ ሳይሆን እውነታውን ተናግሮ ካመሸበት ማደር ስለሆነ ነገሩ።  በአሁኑ ሰዓት ለቤተ ክርስቲያኒቱ በመቆርቆር የሚንቀሳቀሱት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ያለበት ማህበረ ቅዱሳን ይሻላል። ለገዳም ይረዳሉ፤ መነኮሳት አባቶቻችንን ይረዳሉ፤ አብነት ትምህርት ቤቶችን ይገነባሉ ይረዳሉም፤ የአብነት ተማሪዎችንም በቁሳቁስ፤ ልብስ፤ ምግብ፤ መጻሕፍት የመሳሰሉትን እየረዱ ይገኛሉ። ሌሎቻችንም የእነሱን ፈለግ ተከትለን ቤተክርስቲያናችንን እንጠብቅ እንጂ የቤተክርስቲያን የበላይ ጠባቂ ሆነው ቤተክርስቲያንን ሊጠብቋት አልቻሉም ምክንያቱም በየተለያየ ጊዜ ጸረ ተሐድሶ ፕሮቴስታንታዊ እንቅስቃሴ በቤተክርስቲያኒቱ ዙሪያ በግልጽ የአብነት ትምህርት ቤት ምንጩን ለማድረቅ በሚተጉበት ሰዓት ዝምታን መምረጣቸው እጅጉን አሳዝኖኛል።  ስለ ሃይማኖቱም የሚፍጨረጨረው ም ዕመናኑ በመሆኑ ጥያቄ ሲያነሳ አይመለከትህም ይህ ስራ የሲኖዶስ ነው ሲኖዶሱ አስካላወገዘው ድረስ አርፋችሁ ተቀመጡ እየተባለ ዝምታን ስንመርጥ ብዙ ም ዕመናን ወደ መናፍቃን አዳራሽ እየሄዱ ይገኛሉ። ሌላው በአዳራሽ እየተሰበሰቡ በሚዲያ የሚያስተላልፉትን የተሐድሶ መናፍቃንን ሴራ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዳወገዙት ሰምተናል በተጨማሪም አውግዘው በቤተክርስቲያኒቱ ስም እንዳይጠቀሙ ውሳኔ ወስነዋል ተብሏል ታዲያ አሁንስ ለምን በቤተክርስቲያኒቱ ስም ይነግዳሉ?  ቢሉ ሲኖዶስን ስለናቁት ይመስለኛል።  ምክንያቱም በአዳራሽ ተሰብስበው የሚሰብኩት የሚዘምሩት የመናፍቃንን እንጂ ተዋሕዶን እንደማይወክልማ ስብከታችው ይናገራል።  አንድም ቀን ስለ ቅዱሳን ሆነ ስለ እመቤታችን ሰብከው አስተምረው የማያውቁ ብቻ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሕግን ሥር ዓት የሚተላለፍ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር እየተባለ ሰውን ማደናገር ስልታቸው እንደሆነ ባንነናል ነገር ግን ይህን የሚያስወግድልን አካል ስለ ሚያስፈልግ አሁንም የእኛ አባቶች ውሳኔአቸው እንደነዚህ ሁለት መነኮሳት አባቶቻችን እንደወሰኑት የተለያየ ሁለት የቴሌቪዝን መርሐ ግብር በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ስም  እንዴት ልናይ እንችላለን? ምግባራቸው አንድ አይነት ስለሆነ ይህ ከዲያብሎስ መሆን አለበት ብለው ነገሩን እንደነዚህ ሁለት መነኮሳት አስበውት ነገሩን እልባት ሊሰጡት ይገባል።  ለምን ሰው ይወዛገባል? ዕልባት ቢሰጡን መልካም ነው እላለሁ። በመጨረሻም እኔ ያነሷኋቸው ውስን ጥያቄዎች እልባት ያገኙ እለት ቤተክርስቲያን ሰላሟን ታገኛለች ብየ አምናለሁ።

መፍትሔ ለማግኘት እንወያይበት....................... እግዚአብሔር አምላክ ቤተክርስቲያናችንን ከመናፍቃን ሴራ ይጠብቅልን ለእኛም የእናታችን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፤ የጻድቃን የሰማዕታት የቅዱሳን የመላዕክት በረከታቸው ረድኤታቸው እና አማላጅነታቸው አይለየን አሜን። 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Post Bottom Ad