ሃይማኖተ አበው አንድምታ ንባቡና ትርጓሜ (በሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ የአራቱ ጉባኤ ምስክር እና መምህር) የመጨረሻው ክፍል ሦስት - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Thursday, November 12, 2015

ሃይማኖተ አበው አንድምታ ንባቡና ትርጓሜ (በሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ የአራቱ ጉባኤ ምስክር እና መምህር) የመጨረሻው ክፍል ሦስት



አምነው ጸንተውበት ይኖር ዘንድ የተነገረው ነገር ሁሉ በየክፍሉ የተጻፈው ምክንያቱ ምን እንደሆነ ያውቁ ዘንድ ላልተማሩት እውቀት እንድትሆን አባቶቻችን የወሰኗት የደነገጓት የከበረች ሃይማኖት ይህች ናት ሕዝ 3፤1 ዮሐ 20፤31
318ቱ በኒቂያ ጉባኤ የተሰበሰቡ አባቶቻችን የከበረ ዜናቸው የሚዘከርበት ይህች መጽሐፍ ዛሬ በአንድምታ ንባቡና ትርጓሜውን በሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ የአራቱ ጉባኤ ምስክር እና መምህር፤ የመንበረ መንግስት መድሃኔዓለም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ አሳታሚነት በክቡር ሊቀ ሊቃውንት መንክር መኮነን አዘጋጅነት ለሕትመት ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም መታተሙ እጅግ ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ የደስታ ቀን ነው። በክፍል አንድ እንደገለጽኩት መጽሐፉ የተመረቀ ዕለት ጎንደር ያሉ የአብያተ ክርስቲያናት አለቆች፤ የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ጌትነት አማረ፤ የሰንበት ትምህርት ቤት እና የማህበረ ቅዱሳን ተወካዮች፤ የቆሎ ተማሪዎች፤ እናቶች አባቶች እንዲሁም ወጣቶች ከትንሽ እስከ ትልቅ አዳራሹ እስኪጠብ ድረስ በሚገርም እና በሚያስደንቅ ሁኔታ መጽሐፉ ተመርቋል።  መርሐ ግብሩ ከመጀመሩ በፊት ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ በመርሐ ግብሩ የታደሙትን ሁሉ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።  ቀጥለውም ስለ መጽሐፉ ማብራርያ ሲሰጡ ሃይማኖተ አበው፤ የአባቶቻችን ሃይማኖት ማለት እንደሆነና ከአዳም ጀምሮ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ያሉ በሃይማኖት አንድ የሚሆኑ አበው ናቸው በማለት ማብራርያ ሰጥተዋል። በተጨማሪም እነ ባስልዮስ፤ ቄርሎስ፤ ዮሐንስ አፈወርቅ፤ አትናቴዎስ፤ ጎርጎርዮስ፤ ሰለስቱ ምዕት ከሄሬኔዎስ ጀምሮ እስከ አቡ ዘካርያስ ያሉ አ ዕማደ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት አምስቱን አ ዕማደ ምስጢር ከመጽሐፍት ብሉያት እና ከመጽሐፍተ ሐዲሳት ሰብስበው ሃይማኖተ አበው የተሰኘውን መጽሐፍ ጽፈው ከጥንት ጀምሮ እስከ ዕለተ ምጽ አት የሚነሱ መናፍቃንን ተከራክረው የረቱበት፤ አውግዘው የለዩበት ሃይማኖታቸውን ያጸኑበት፤ ም ዕመናንን ከኑፋቄ የጠበቁበት ታላቅ መጽሐፍ ነው ብለዋል። ይሕ መጽሐፍ መታሰቢያነቱ በጉባኤ ቤት ብዙ ሊቃውንትን በማፍራት ለደከሙት አባቶቻችን ለክቡር ጌታው ዶ/ር ሊቀ ሊቃውንት አየለ አለሙ እና ለክቡር ጌታው ሊቀሊቃውንት መንክር መኮነን ይሁንልኝ በማለት ምስጋናቸው አቅርበዋል።  እነዚህ ሊቃውንት አባቶቻችን በአሁኑ ሰዓት በስጋ ቢለዩንም በመንፈስ ግን ከእኛ ጋር አሁን እንዳሉ አምናለሁ ስለዚህ  ደስታቸው ደስታችን ስለሆነ በእነዚህ ሊቃውንት አባቶቻችን ስም እንኳን ደስ አለን እላለሁ በማለት የመግቢያ ንግግራቸውን ቋጭተዋል።


የመጽሐፉ ገጽታ
v መጽሐፉ በአራት አበይት ክፍል ይከፈላል
1)  በአራቱ ክፍላተ ወንጌል አምሳል ከመጀመሪያ እስከ ኤጲፋንዮስ ያለው
2)  ከኤጲፋንዮስ እስከ እመልእልተ ሲኖዲቆን
3)  ከእመልእልተ ሲኖዲቆን እስከ ግዘት
4)  ግዘትና ስምዓት እስከ መጨረሻው
v በእጅ እየተጻፈ ሲነበብ እና ሲተረጎም ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየው ይህ መጽሐፍ ከአበው ሊቃውንት አባቶቻችን ሲያያዝ የመጣው ሕግና ሥርዓት መሰረት ያደረገ ነው።
v በመጽሐፉ ገጾች ላይ የተለያዩ ሥዕለ አድኅኖዎች እና ብጹእ አቡነ እንድርያስ  (በዚህ ጉባኤ ቤት ተምረው የወጡ) ብጹእ አቡነ ኤልሳ፤ (ጎንደር የነበሩ ሊቃነ ጳጳሳት)፤ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት (በዚህ ጉባኤ ቤት ተምረው የወጡበጥ)፤ መምህር ምህረቱ (ገብረ ኢየሱስ) ከቀድሞ የጉባኤ ቤቱ ሊቃውንት መምህራን አንዱ፤ ሊቀ ሊቃውንት መንክር መኮንን፤ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ የመ/መ/መድሃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ እና የአራቱ መጻሕፍት ጉባኤያት ምሥክር መምህር እና አባቶቻችን ፎቶዎች የተንቆጠቆጠ ነው።
v በአጼ ፋሲል ከታነጹት ሰባት አብያተ ክርስቲያን አንዱ የሆነው የጎንደር መንበረ መንግሥት መድሃኔዓለም ቤተክርስቲያን ታሪክም አለበት።
v ጉባኤ ኒቅያ፤ ጉባኤ ቁስጥንጥንያ፤ ጉባኤ ኤፌሶንን በሰፊው ያትታል
v  ይህ መጽሐፍ መታሰቢያነቱ ለክቡራን ሊቃውንት አባቶቻችን ለመምህር ምሕረቱ ገብረ ኢየሱስ፤ ለክቡር ዶ/ር አለቃ አየለ አለሙ፤ ለክቡር ሊቀ ሊቃውንት መንክር መኮንን እና ለጉባኤ ቤታችን ይሁን።
v  ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ስለ መጽሐፉ አዘገጃጀት ሲናገሩ፤ ጽሑፉን በመልቀም፤ በማረም እና በኮምፒውተር በመጻፍ የተባበሯቸውን አመስግነው መጽሐፉን ለመጻፍ ሁለት አመት እንደፈጀባቸው ለታዳሚው አስረድተዋል።
v  መጽሐፉ ጎንደር ተዘጋጅቶ እዚሁ ጎንደር እንደታተመ አስረድተዋል። አክለውም የአንድምታ ንባቡና ምንጩ ጎንደር ስለሆነ የጎንደር ሕዝብ ይህን መጽሐፍ መግዛት ብቻ ሳይሆን አንብበው ተምረው፤ አውቀው ለተተኪው ትውልድ እንዲያስተላልፉ በአደራ መልክ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
v  አምስቱ አዕማደ ምስጢርን ያካተተ ሲሆን
በመርሐ ግብሩ የተሳተፉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያቀረቡትን እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ

1)   በሃይማኖተ አበው አንድምታ ንባቡና ትርጓሜ የምረቃ ሥነ ሥርዓት የቀረበ ሪፖርት በመምህር ፍቅረ ማርያም በመንበረ መንግስት መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን የ፬ቱ ጉባኤያት  ምክትል መምህር
v  በመንበረ መንግስት መድሃኔዓለም ቤተክርስቲያን የአራቱ መጻሕፍተ ጉባኤያት የሚካሄድበት እና በርካታ ሊቃውንት፤ ሊቃነ ጳጳሳት የወጡባት ሲሆን ከታወቁት ሊቃውንት መካከል ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት (በዚህ ጉባኤ ቤት ተምረው የወጡበጥ)፤ ሊቀ ሊቃውንት መንክር መኮንን፤ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ የመ/መ/መድሃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ እና የአራቱ መጻሕፍት ጉባኤያት ምሥክር መምህር፤ ብጹእ አቡነ እንድርያስ  የደቡብ ጎንደር ሊቀ ጳጳስ እና የሲኖዶስ አባል ናቸው።
v  አራቱን ጉባኤያት ለመጨረስ የሚፈጀው የትምህርት ዘመን መጽሐፍተ ብሉያት 8 ዓመት፤ መጽሐፍተ ሐዲሳት 6 ዓመት፤ መጽሐፍተ ሊቃውንት 8 ዓመት፤ መጽሐፍተ መነኮሳት 5 ዓመት ሲሆን በአጠቃላይ የአራቱን ጉባኤ ተምሮ ለመፈጸም የሚፈጀው 27 ዓመት ነው።
v  በዚህ ጉባኤ ቤት የአንድምታ መጻሕፍትን ተምረው በፓትርያርክነት፤በሊቃነ ጳጳስነት፤ በመምህነት፤ በስብከተ ወንጌል የሚያገለግሉ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ከጉባኤው የተቀዳውን የእውቀት ምንጭ የሚደርስ በሃገር ውስጥም ሆነ በሃገር ውጭ ለሚገኙ ምዕመናን የሚደርስ ግንባር ቀደም ጉባኤ ቤት ነው።
v  በጉባኤ ቤቱ የሚሰጠውን ትምህርት አሰጣጥ በተመለከተ
Ø  ጠዋት 2:30 እስከ 3፡00 ድረስ የስብከተ ወንጌል እና የጥያቄ እርማት መርሐ ግብር ሲሆን በጉባኤ ቤቱ የሚገኙት ደቀ መዛሙርት የተምሮ ማስተማሩን፤ የስብከተ ወንጌሉን ትምህርት ከዚሁ ከጉባኤ ቤቱ ከአብነት ትምህርቱ ጋራ የስብከተ ዘዴውን አሟልተው ሰይፍ ዘክሌየ አፉሁ በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ ሆነው ለቤተክርስቲያን እና ለምዕመናን ሙሉ አገልግልት ያስችል ዘንድ ከክቡር ጌታው ሊቀ ሊቃውንት መንክር ጀምሮ ሲካሄድ የነበረ መርሐ ግብር ነው።
Ø  መደበኛው የአንድምታ ጉባኤው ሲጀመር 3፡00 ላይ የዕለቱ ስንክሳር ይነበባል
Ø  በየሳምቱ ዘወትር አርብ መጽሐፈ ሲኖዶስ እና ቄሌምንጦስ ይተረጎማል
Ø  ከሰኞ እስከ አርብ ዘወትር መጻሕፍተ ብሉያት፤ መጻሕፍተ ሐዲሳት፤መጽሐፍተ መነኮሳት እና መጽሐፍተ ሊቃውንት ይነበባሉ ይተረጎማሉ
Ø  የትምህርቱ መርሐ ግብር ከ3፡00 ሰዓት እስከ 6፡00 ከተካሄደ በኋላ በጸሎት እንደተጀመረ በጸሎት ይዘጋል
Ø  ከሰኞ እስከ አርብ ከቀኑ በ10፡00 ሰዓት ደቀ መዛሙርት በጉባኤ ቤቱ ተገኝተው ውዳሴ ማርያም፤መልክአ ማርያም፤ መልክአ ኢየሱስ ደግመው አድህነነ ሕዝበከ ማና ማህረነ አብ በዜማ እስከ ምልጣኑ ከተደረሰ በኋላ 100 እግዚኦታ እና በእንተ ማርያም ይደረሳል
Ø  በተጨማሪም በመባቻ ከ1 እስከ 7 ቀን ድረስ በእየአንዳንዱ የእለቱ ውዳሴ ማርያም መልክአ ኢየሱስ እየገባ ይደገማል የምህላው ጸሎት ይደርሳል
Ø  ጸሎቱ ካለቀ በኋላ ጠዋት የተካሄደው ጉባኤ ሁለተኛ ይደገማል በጸሎት ይፈጸማል
Ø  የደቀመዛሙርቱ ብዛት ቀደም ሲል በቀዳማዊ ሃይለሥላሴ ጊዜ ለዋና መምህሩ ሁለት መቶ ብር ለሶስት ምክትል መምህራን 50 ብር ለእያንዳንዳቸው ለአስር ደቀ መዛሙርት ደግሞ 10 ብር ለእያንዳንዳቸው በወር ይከፈል ነበር። ይህም እስከ ሊቀሊቃውንት መንክር መኮንን ጊዜ የቀጠለ ሲሆን የደቀመዝሙርቱ ቁጥር ግን 20 ደርሷል። በአሁኑ ሰዓት በመድሃኔዓለም ቸርነት በድንግል ማርያም አማላጅነት በአካለ ስጋ የተለዩን በአካለ ነፍስ ግን በጸሎታቸው በትሩፋታቸው ያልተለዩን እና በሚያግዙን በደጋጎቹ አባቶቻችን መምህራን በዶ/ር አለቃ አየለ አለሙ፤ ክቡር ሊቀ ሊቃውንት መንክር መኮንን ጸሎት የደቀ መዛሙርቱ ቁጥር እስከ 70 ደርሷል።
Ø  ሰርከ ሕብስቱን በተመለከተ በቀን ሁለት እንጀራ ይቆነናል።  ሰርከ ሕብስት የሚዘጋጀው ወር በገባ በአምስተኛው ቀን የማሕበረ ሐዋርያት የጽዋ ማህበር እና በበጎ አድራጊዎች በሚገኝ አስተዋጾ ሲሆን በጉባኤው ስም በ2002 ዓ.ም በተቋቋመው ዳቦ ቤት ነው።
Ø  በጉባኤ ቤት ካሉት የብራና መጽሐፍት አሁን የታተሙ መጻሕፍትን በተመለከተ
v  በክብሩ ጌታው ዶ/ር አለቃ አየለ አለሙ የተጻፈ የብራና የአቡሻህር መጽሐፍ እና በበግ ብራና የተጻፈ ፍትሐ ነገስት
v  በክቡር ጌታው ሊቀ ሊቃውንት መንክር መኮንን የብራና መጻሕፍት የተጻፈ 
·         ሃይማኖተ አበው ግዕዝ የብራና እና ሲኖዶስ የብራና ግዕዝ መጻሕፍት
v  በክቡር ጌታው ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ የተጻፈ
·         8ቱ ብሔረ ኦሪት የብራና
·         አራቱ ወንጌልና ግብረ ሐዋርያት የብራና
·         መልእክታተ ጳውሎስ 14ቱ የብራና
·         መዝሙረ ዳዊት ባለ መዝሙረ ድንግል የብራና
·         መጽሐፈ ኢሳይያስ አስራ አምስቱ ነቢያት እና አምስቱ ማኃልየ ማኅልይ ዘሰሎሞን የብራና
·         መጽሐፈ ቄሌምንጦስ የብራና
·         መጽሐፈ ኪዳን 7ቱ ውዳሴ ማርያም እና ቅዳሴ ማርያም የብራና
·         ገድለ አዳም የብራና
·         ገድለ ሐዋርያት የብራና በመጻፍ ላይ ያለ ናቸው። እነዚህ ሁሉ መጽሐፍት በአሁኑ ሰዓት በጉባኤ ቤቱ ይገኛሉ
v  ሕትመቱን በተመለከተ ሊቀሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ የአራቱ ጉባኤ ምስክር እና መምህር እንዳሉት ታላቁ ሊቅ ክቡር ሊቀ ሊቃውንት መንክር መኮነን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቀን ከሌሊት በማሰብ እና በመቆርቆር ለወደፊቱ ጽፈው ያዘጋጁትን ሃይማኖተ አበው እንድምታ ንባቡና ትርጓሜው በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ዘመን እንዲታተም ለጠቅላይ ቤተ ክህነት አቅርበው ነበር።  እንደ እሳቸው ሃሳብ ከቅዱስ ፓትርያርኩ ፈቃድ አግኝተው ለማሳተም ብዙ ጊዜ ከጎንደር አዲስ አበባ እየተመላለሱ ይታተማል እያሉ ሲጠባበቁ ያሰቡት ሃሳብ ሳይሳካ ቀረ አሁን ግን ‹‹ ከመ ይቀርብ ዐመቲሁ አአምረከ ወከመ ከመ ይበጽሕ ጊዜሁ እሌበወከ›› እንዲል ዘመኑ ሲደርስ አውቅሀለሁ ቀኑም ሲደርስ አስብሀለሁ ተብሎ በነብዩ እንደተነገረ በሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ አማካኝነት በጉባኤ ቤቱ ስም ታትሟል።
v  መጽሐፉ የታተመበት ምክንያት የአብነት ት/ቤቶችን ፣የአብነት መምህራንን እና የአብነት ደቀ መዛሙርትን ችግር ለመቅረፍ ሲሆን ይህ መጽሐፍ ሙሉ በሙሉ የቤተ ክርስቲያኒቱን ምስጢራት የያዘ እና ተዋሕዶ ሀይማኖትን የሚሰብክ ፣ሊቃውንት የሚያስተምሩበት እና መናፍቃንን ተከራክረው የሚረቱበት፣መናፍቃን የሚረቱበት፣ተወግዘው የሚለዩበት ስለሆነ ምዕመናንም መጽሐፉን በማንበብ በተዋሕዶ ሃይማኖታቸው እንዲጸኑ የመናፍቃንን ክህደት እና ኑፋቄ  በዚህ መጽሐፍ ከሚያገኙት ምስጢር ምላሽ በመስጠት ጠላቶቻቸውን እንዲያሳፍሩ ሃይማኖታቸውን ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲያስተላልፉ ጠቃሚ በመሆኑ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እና በጉባኤ ቤቱ ስም ገዝተው እንዲያነቡ እና ለትውልድ እንዲያተላልፉ ስል አሳስባለሁ ብለዋል፡፡
v  ይህ መጽሐፍ በኒቂያ የተሰበሰቡ 318ቱ ሊቃውንት አርዮስን አውግዘው የለዩበት፣ አንድ መቶ ሃምሳው ሊቃውንት በቁስጥንጥንያ መቅዶንዮስን አውግዘው የለዩበት ፣ሁለት መቶው ሊቃውንት በኤፌሶን ንስጥሮስን አውግዘው የለዩበት የሃይማኖት መሰረት፣የተዋሕዶ ዐምድ፣ግድግዳ፣ጣርያ እና ክዳን ጉልላት ነው ፡፡ ‹‹ ዐምዳ ውድዳ ለቤተ ክርስቲያን ›. እንዲል ቤተ ክርስቲያናችን ይህን መጽሐፍ በቅዳሴ ጊዜ ከእግዚኦታ ቀጥሎ ሁልጊዜ ታነበዋለች ይኸውም አምስቱ አዕማደ ምስጢርን የያዘ ስለሆነ ምእመናን ስጋወደሙን ከመቀበላቸው በፊት ምስጢረ ቁርባንን አውቀው ተዘጋጅተው ወደ ቅዱስ ስጋው እና ክቡር ደሙ እንዲቀርቡ ነው በማለት ለታዳሚው ደስ በሚል አገላለጽ አስረድተዋል፡፡
v  የመጽሐፉን ሽያጭ ገቢ በተመለከተ ደቀመዛሙርቱ መጠለያ አግኝተው ትምህርታቸው እንዲማሩ እና ተምረው እንዲያጠናቅቁ እና ለጉባኤ ቤት ግንባታ የሚውል ነው በማለት ሪፖርታቸውን አቅርበዋል።

ከዚህ በመቀጠል የቀረበው መርሐ ግብር ቅኔ ነበር።  በመርሐ ግብሩ የተገኙ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ቅኔ አቅርበዋል።  የመጀመሪያ ቅኔ ያቀረቡልን መጋቤ ሐዲስ ምስጢሩ ዘለቀ በኆኅተ ብርሐን ቦሌ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ  ናቸው ቅኔውም፤
§  ብእሴ ጎንደር ይብልዎ ሊቃውንት ለዘበጎንደር ፈድፈደ
       ጦማር ልደቱ ይትናገር አኮኑ ክበበ ጎንደር ተወልደ
§  አምላኪየ አምላኪየ እገይስ ሃቤከ
መጽሐፈ ሊቃውንት መጽሔት ንጽሐ አእምሮ ዘቦቱ
ተሰራ ገጽአ አበሳነ ከመ ንርአይ ቦቱ
                ዋዜማ
§  ኖህ መምህርነ ለትርጓሜ ወንጌል ርግብ አመ ፈነዋ ቀዳሜ
አስተራየ በውስተ አፉሃ ቆጽለ እጽል ትርጓሜ
ከመ ብስራተ ጽድቅ ታብስሮ በትርጓሜ ወንጌል ልምላሜ
ሊቀሊቃውንት መንክር ፍጹመ እድሜ
ዘደምሰሰ ሃጢአተ ድክታሜ
§  ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ ስቡህኒ ውእቱ ወልኡልኒ ውእቱ ለዓለም
መንክር ለኩልነ ግብረ አማኑኤል አምላክነ ዘበህላዌሁ መንክር በጠፈረ ሰማይ በኪነጥበቡ ምጡቅ ለመብረቅ
 ሊቀ ሊቃውንት ወረዶ እመብረቅ
§  መንክር ለኩልነ ግብረ አማኑኤል አምላክነ
ዘበህላዌሁ መንክር በኪነጥበቡ ምጡቅ ለመብረቅ
 ሊቀሊቃውንት ወለዶ መብረቅ
§  ሊቀሊቃውንት መንክር መጽንኢ በተና አእምሮ ረቂቅ
እንተ አይነሰብ እያንጸበረቅ
በከመ ይቤ ኤርምያስ መኮንነ ጽድቅ
በውእቱ ልሳኑ ዘወርቅ
          ስላሴ
ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ ስቡህኒ ውእቱ ወልኡልኒ ውእቱ ለዓለም
እምርሁቅ ዘመጻእነ ዳዊት ነቢይ በከመ ይቤ
ሶቤሃ ለጽዮን ጉባኤ ተዘከርናሃ ፍጡነ
ሰቀልነ ውስተ ኩዋቲሃ እንዚራ ልበነ
ማህሌተ ያሬድ ንህሊ ውስቴታ ለጽርሃ ጽዮን ቤትነ
እስመ በህየተ ስህሉነ ሊቀሊቃውንት መንክር ወእዝራ አቡነ ዘበጸጋ ወለዱ ኪያነ
       መወድስ
ፍታሕ ሊተ እግዚኦ ወተበቀል በቀልየ
እግዚአ ሊቃውንት ኪሩቤል መኮንነ ግርማ
ዘበእንቲአሃ ለምድር ዘአንስት ይነብራ
እምገቦ አዳም አዳም ሊቀሊቃውንት ዘሰምራ
ፈተወ ወአፍቀረ ለሔዋን ትርጓሜ ወንጌል በቃሉ ፈጠራ
ሕይወተ ስጋሁ ከመ ትኩኖ ትርጓሜ ሔዋን ዘልበ ሊቃውንት አብደራ
አምላክነሂ ከሃዴ ኩሎ ደረ ፈጠራ ወገብራ
ዘምስለ አዳም መምህርነ በቃለ ኪዳን ናስተጻምራ
ወብእሲ እይፍልጽ ዘእግዚአብሔር አህበራ
እስመ አዘዘነ አምላክነ መኑመ እያይስራ
የሚቀጥለው መርሐ ግብር ስለ ሃይማኖተ አበው አንድምታ ንባቡና ትርጓሜ አስፈላጊነት በመጋቤ ሐዲስ ኃይለ እግዚዕ አሰፋ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሊቃውንት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ የቀረበ ሲሆን በመጀመሪያ ስለ ትርጓሜ አስፈላጊነት መልእክታቸውን ከማስተላለፋቸው በፊት በጉባኤ ቤት ዘመናቸውን በሙሉ እያስተማሩ ላለፉት አባቶች ክቡር ሊቀ ሊቃውንት መንክር መኮንን እና ክቡር ዶ/ር አየለ አለሙ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።  በመቀጠልም ስለ ትርጓሜ ምንነት ስተተትኑ፤ 
v  ከአዳም መውደቅ በፊት የሰው ልጅ አ እምሮ እጅግ በጣም ብሩህ ነበር።  ከሃጢአት በኋላ የሰው ሃይምሮ በመጨለሙ የ እግዚአብሔር መል እክት በቀጥታ ተስኖታል፤ ምስጢር እና ነገረ እግዚአብሔር ተሰውሮበታል፤ ማስተዋል እና እውቀቱ የተወሰደበት የሰው ልጅ የሚመራው እና የሚተረጉምለት ሌላ ሁለተኛ አካል አስፈልጎታል።  ለምሳሌ የመጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ የንግግር አይነቶች እንደ ህልም፤ ራዕይ፤ እንቆቅልሽ፤ ራዕይ፤ ጥበብ የመሳሰሉት ቃላት ያለ ትርጓሜ መረዳት የማይቻል በመሆኑ የግድ ተርጓሚ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ለምሳሌ ዮሴፍ ለፈርዖን ሕልሙን ተርጉሞለታል፤ ለናቡከደነጾር ደግሞ ዳንኤል ሕልሙን ተርጉሞለታል። ለትርጓሜ መጽሐፍ ጀማሪውም መስራቹም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ለምሳሌ ያህል በትንቢተ ኢሳይያስ 61፤1-4 ሉቃ 4፤16-22 ስለ ጌታችን የተነገረ መሆኑን የዚህ መጽሐፍ ነገር በጆሮአችሁ ደረሰ ተፈጸመ ብሎ ተርጉሞላቸዋል። ማቴ 13፤36 ደቀመዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ተርጉምልን ብለው ሲጠይቁት መልካም ዘርን የዘራ የሰው ልጅ ነው እርሻውም ዓለም ነው  መልካሙም ዘር የመንግስት ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱም የክፉ ልጆች ናቸው ብሎ ተርጉሞላቸዋል።  የጌታችን ደቀመዛሙርትም ከእርሱ በተማሩት መሰረት ትንቢተ ነቢያትን እና ቃለ ወንጌልን እየተረጎሙ ያስተምሩ ነበር።  ከሐዋርያት በመቀጠል የሐዋርያት ደቀመዛሙርት ቅዱስ ቄዴኒዎስ፤ ቅዱስ ድዮናስዮስ፤ ቅዱስ አጢፎስ እና ቅዱስ አርጣኦስ መጻሕፍትን እየተረጎሙ ያስተምሩ ነበር።  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አራቱ ጉባኤያት በመባል የሚታወቁት ብሉይ ኪዳን፤ ሐዲስ ኪዳን፤ሊቃውንት እና መጽሐፈ መነኮሳት ናቸው። ቅዱስ ጴጥሮስ ትንቢት ከቶ ከሰው ፈቃድ ከቶ አልመጣምና ዳሩ ግን ቅዱሳን ሰዎች ከእግዚአብሔር ተልከው በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው ተረጎሙት ሲል ትርጉም በመንፈስ ቅዱስ ብቻ መሆኑን አስረድቷል። በመጨረሻም የዚህ ጉባኤ ቤት ሊቃውንት አባቶችን አመስግነው በተሰጣቸው ውስን ደቂቃዎች ብዙ መልክቶችን አስተላልፈዋል።
 ከአዲስ አበባ የመጡ መጋቤ ሐዲስ አብርሐም አድማሴ የትርጓሜን ታሪካዊ አመጣጥ ለታዳሚው አቅርበዋል።
የአትሮንስ መል እክት
ይህንን ታላቅ መጽሐፍ ስላበረከታችሁልን ምስጋናችን የላቀ ነው። የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታይ የሆንን በሙሉ መጽሐፉን ገዝተን አንብበን ተምረን አውቀን ለተተኪው ትውልድ እንድናስተላልፍ የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን።
  


Post Bottom Ad