ሃይማኖተ አበው አንድምታ ትርጓሜ (በሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ የአራቱ ጉባኤ ምስክር እና መምህር) ክፍል ሁለት - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Wednesday, November 11, 2015

ሃይማኖተ አበው አንድምታ ትርጓሜ (በሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ የአራቱ ጉባኤ ምስክር እና መምህር) ክፍል ሁለት

(አትሮንስ ሕዳር 1 ቀን 2007 ዓ.ም)



          ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ፤ የአራቱ ጉባኤ ምስክር እና መምህር፤ የመንበረ መንግስት መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ በሆኑት ከቀድሞ አባቶች  ሲወርድ የመጣው ሃይማኖተ አበው አንድምታ ንባቡና ትርጓሜው  በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ ታተመ።
መጽሐፉ የተመረቀበት ቀን ጥቅምት  ሲሆን ቦታው በመንበረ መንግስት መድሃኔዓለም ሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሽ ነው። የጎንደር ከተማ ከንቲባ፤ የመንግስት ባለስልጣናት፤ የደብር አስተዳዳሪዎች፤ የማህበረ ቅዱሳን ተወካዮች፤ የተለያዩ የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች፤ ከአዲስ አበባ የመጡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እና ከጉባኤ ቤቱ ተምረው በተለያዩ ቦታዎች የሚያገለግሉ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በሚያስደምም ሁኔታ ተመርቋል።
ይህን መጽሐፍ ልዩ የሚያደርገው በመግቢያ ገጾቹ ላይ የተለያዩ ስዕለ አድኅኖዎች፣ ጎንደር የነበሩ ሊቃነ ጳጳሳት እና ጉባኤ ቤቱ ባፈራቸው ሊቃውንት ፎቶዎች የተንቆጠቆጠ ነው፡፡ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ይህን መጽሐፍ ለማጻፍ የወሰደባቸው ጊዜ ሁለት ዓመት ነው።
ከዚህ ቀደም በክፍል አንድ እንደዘገብነው የሃይማኖተ አበው አንድምታ ንባቡና ትርጓሜ ሲመረቅ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ካደረጉ በኋላ ለታዳሚው እንዲህ በማለት መል እክታቸውን አስተላልፈዋል። የመጽሐፉ ባለቤት ክቡር ጌታው ሊቀ ሊቃውንት መንክር መኮነን እና ክቡር  ጌታው ዶክተር አለቃ አየለ አለሙ ናቸው፡፡ መጽሐፉ ተተርጉሞ የታተመው በጎንደር ከተማ ነው። ብዙዎቻችን እንደምናውቀው የአንድምታ ንባቡና ትርጓሜ ምንጩ ጎንደር ሲሆን ሀገሩ፣ርስቱ፣ጉልቱ እዚሁ ጎንደር ስለሆነ ከምንጩ ሲመረቅ ደግሞ ትልቅ ትርጉም አለው ስለዚህ ሁላችንም በመጽሐፉ ልንጠቀም ይገባል ብለዋል፡፡
 በመቀጠልም የጉባኤ ቤቱ ሪፖርት በመምህር ፍቅረ ማርያም በመንበረ መንግስት መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን የ፬ቱ ጉባኤያት  ምክትል ቀርቧል።
በመቀጠልም በመጋቤ ሐዲስ ምስጢሩ ዘለቀ በኆኅተ ብርሐን ቦሌ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ  መምሕር ቅኔ ቀርቧል፡፡
ቀጥሎም በመጽሐፉ ዙሪያ በመጋቤ ሐዲስ ኃይለ እግዚዕ አሰፋ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሊቃውንት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ የመጽሐፉን አስፈላጊነት እና ምንነት አስረድተዋል።
ከአዲስ አበባ የመጡ መጋቤ ሐዲስ አብርሐም አድማሴ የትርጓሜን ታሪካዊ አመጣጥ ለታዳሚው አስረድተዋል።
  
በመቀጠልም ሊቀ ኅሩያን ነቅዓ ጥበብ እሸቴ በጎንደር ከተማ  በደብረ ምሕረት አቡን ቤት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የቅኔ ምስክር መምህር  ቅኔ ቀርቧል። 
መምህር ትሕትና ተስፋየ በመንበረ መንግስት መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ ደቀ መዝሙር ቅኔ ቀርቧል።
ከቀረበ በኋላ ከደብር አለቆች እና ምእመናን አስተያየት ተሰጥቷል ይህንን አስተያየት በክፍል አንድ አቅርበነዋል፡፡
የመጽሐፉ ምርቃት ፕሮግራሙ ከመጠናቀቁ በፊት ከደብረ ሊባኖስ ገዳም አንድ አባት ለሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ ከእንጨት የተሰራ ያማረ በትረ መስቀል መቋሚያ ሽልማት አበርክተውላቸዋል።  ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐድስም ስለ ተበረከተላቸው ሽልማት አመስግነው ገቢው ግን ለጉባኤ ቤቱ እንደሆነ አስረድተዋል። ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 18 ቁጥር 8 ላይ ያለውን ሃይለ ቃል በማንሳት ‹‹የአባቶቻችን መታሰቢያ ዛሬ ለእኛ ነው፡፤››ብለው መርሐግብሩን   ፈጽመዋል፡፡
በመጨረሻም በመርሐ ግብሩ የመንበረ መንግስት መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ተማሪዎች የሕይወትን መዝገብ ቃሉን ያስነበቡህ የተዋሕዶ አርበኞች ቅዱሳን ዋኖችህ የሚለውን መዝሙር አቅርበዋል፡፡
በመጽሐፉ ምረቃ ጊዜ ከጉባኤ ቤቱ ተምረው በተለያየ ሥፍራ ያሉ፤ አሁንም በጉባኤ ቤቱ እየተማሩ የሚገኙ እና በዚህ ዕለት የታደሙ ሊቃውንት
1. መጋቤ ብሉይ ጸጋየ ጌጡ፡በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን በሰዋሰወ ብርሀን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የብሉይ ኪዳን መምህር
2. .መጋቤ ሐዲስ ኃይለ እግዚዕ አሰፋ፡በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሊቃውንት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ
3 .መጋቤ ሐዲስ ምስጢሩ ዘለቀ፡በኆኅተ ብርሐን ቦሌ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ መምህር
4. .መጋቤ ሐዲስ አባ ሙሴ ደሴ፡በአፍሪካ ሕብረት ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ መምህር እና የቅኔ መምህር
5 .መጋቤ ሐዲስ አብርሐም አድማሴ፡በአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት በቀራንዮ መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ኃላፊ
6. .መጋቤ ሐዲስ ባሕረ ጥበብ አዱኛ፡በምስራቀ ጸሐይ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ መምሕር እና የቅኔ መምሕር
7 መጋቤ ብሉይ ገብረ ማርያም ጥበቡ፡ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን በሰዋሰወ ብርሀን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የብሉይ ኪዳን መምህር
8 .መጋቤ ምስጢር ከሐሊ ጌጡ ፡በታዕካ ነገስት በዓታለማርያም ቤተ ክርስቲያን ስብከተ ወንጌል ኃላፊ  በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡
9. መጋቤ ሐዲስ ልዑል ይባቤ፡በኆኅተ ብርሐን ቦሌ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ኃላፊ
10 መጋቤ ሐዲስ አባ አእምሮ ብሩ ፡በአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት በደብረ መዊዕ አዲሱ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ መምህር
11 መጋቤ ሐዲስ ሳሙኤል አዱኛ፡በአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት አየር ጤና ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን የመጽሐፍ መምሕር እና ስብከተ ወንጌል ኃላፊ
12 መጋቤ ሐዲስ ስቡሕ አዳምጤ፡ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን በሰዋሰወ ብርሀን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲስ  ኪዳን መምህር
ከሪፖርቱ እንደተገለጸው የኔታ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ የሚከተሉትን መጻሕፍት  በብራና የጻፉ ሲሆን  ገና ያልታተሙ በእጅ የተጻፉ የአንድምታ ትርጓሜ መጻሕፍት ናቸው፡፡እነዚህም፡-
ሀ.ስምንቱ ብሔረ ኦሪት የብራና
ለ.አራቱ  ወንጌል እና ግብረ ሐዋርያት የብራና
ሐ.መልዕክታተ ጳውሎስ አስራ አራቱ የብራና
መ.መዝሙረ ዳዊት ባለ መዝሙረ ድንግል የብራና
ሠ.መጽሐፈ ኢሳይያስ 15 ቱ ነቢያት እና አምስቱ መኃልይዘሰሎሞን የብራና
ረ.መጽሐፈ ቀሌምንጦስ የብራና
ሰ.መጽሐፈ ኪዳን ሰባቱ ውዳሴ ማርያም እና ቅዳሴ ማርያም ያለው የብራና
ሸ.ገድለ አዳም የብራና
ቀ.ገድለ ሐዋርያት የብራና በመጻፍ ላይ ያለ ነው፡፡
         
የአትሮንስ መል እክት
ሊቀሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ የአራቱ ጉባኤ ምስክር እና መምህር እንዳሉት ታላቁ ሊቅ ክቡር ሊቀ ሊቃውንት መንክር መኮነን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቀን ከሌሊት በማሰብ እና በመቆርቆር ለወደፊቱ ጽፈው ያዘጋጁትን ሃይማኖተ አበው እንድምታ ንባቡና ትርጓሜው በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ዘመን እንዲታተም ለጠቅላይ ቤተ ክህነት አቅርበው ነበር።  እንደ እሳቸው ሃሳብ ከቅዱስ ፓትርያርኩ ፈቃድ አግኝተው ለማሳተም ብዙ ጊዜ ከጎንደር አዲስ አበባ እየተመላለሱ ይታተማል እያሉ ሲጠባበቁ ያሰቡት ሃሳብ ሳይሳካ ቀረ አሁን ግን ‹‹ ከመ ይቀርብ ዐመቲሁ አአምረከ ወከመ ከመ ይበጽሕ ጊዜሁ እሌበወከ›› እንዲል ዘመኑ ሲደርስ አውቅሀለሁ ቀኑም ሲደርስ አስብሀለሁ ተብሎ በነብዩ እንደተነገረ በሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ አማካኝነት ሊታተም በቅቷል ለዚህም እግዚአብሔር ይመስገን።

   መምህር ፍቅረ ማርያም እንደገለጹት ይህ የሃይማኖተ አበው አንድምታ ትርጓሜ ከአሁን በፊት ያልታተመ በመሆኑ በማንኛውም የአብነት ተማሪ እጅ ያልገባ በመሆኑ መጽሐፉን አሳትሞ ለመላው የአብነት ተማሪ ይጠቀምበት ዘንድ ብዙ ድካም እንደፈሰሰበት ተናግረዋል።
መምህር ፍቅረ ማርያም ስለዚህ መጽሐፍ ምንነት በሪፖርታቸው እንደገለጹት መጽሐፉ የታተመበት ምክንያት የአብነት ት/ቤቶችን ፣የአብነት መምህራንን እና የአብነት ደቀ መዛሙርትን ችግር ለመቅረፍ ሲሆን ይህ መጽሐፍ ሙሉ በሙሉ የቤተ ክርስቲያኒቱን ምስጢራት የያዘ እና ተዋሕዶ ሀይማኖትን የሚሰብክ ፣ሊቃውንት የሚያስተምሩበት እና መናፍቃንን ተከራክረው የሚረቱበት፣መናፍቃን የሚረቱበት፣ተወግዘው የሚለዩበት ስለሆነ ምዕመናንም መጽሐፉን በማንበብ በተዋሕዶ ሃይማኖታቸው እንዲጸኑ የመናፍቃንን ክህደት እና ኑፋቄ  በዚህ መጽሐፍ ከሚያገኙት ምስጢር ምላሽ በመስጠት ጠላቶቻቸውን እንዲያሳፍሩ ሃይማኖታቸውን ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲያስተላልፉ ጠቃሚ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ይህ መጽሐፍ በኒቂያ የተሰበሰቡ 318ቱ ሊቃውንት አርዮስን አውግዘው የለዩበት፣ አንድ መቶ ሃምሳው ሊቃውንት በቁስጥንጥንያ መቅዶንዮስን አውግዘው የለዩበት ፣ሁለት መቶው ሊቃውንት በኤፌሶን ንስጥሮስን አውግዘው የለዩበት የሃይማኖት መሰረት፣የተዋሕዶ ዐምድ፣ግድግዳ፣ጣርያ እና ክዳን ጉልላት ነው ፡፡ ‹‹ ዐምዳ ውድዳ ለቤተ ክርስቲያን ›. እንዲል ቤተ ክርስቲያናችን ይህን መጽሐፍ በቅዳሴ ጊዜ ከእግዚኦታ ቀጥሎ ሁልጊዜ ታነበዋለች ይኸውም አምስቱ አዕማደ ምስጢርን የያዘ ስለሆነ ምእመናን ስጋወደሙን ከመቀበላቸው በፊት ምስጢረ ቁርባንን አውቀው ተዘጋጅተው ወደ ቅዱስ ስጋው እና ክቡር ደሙ እንዲቀርቡ ነው በማለት ለታዳሚው ደስ በሚል አገላለጽ አስረድተዋል፡፡
የመጽሐፉ አሳታሚ ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ የአራቱ ጉባኤ ምስክር እና መምህር ዋና ዓለማ
 በሪፖርቱ እንደተገለጸው የመጽሐፉ ዓላማ አንድና አንድ ብቻ ነው።  ይኸውም በመጽሐፉ ሽያጭ የተገኘው ገቢ የጉባኤ ቤቱ ተማሪዎች የልብስ፤ የቀለብ፤ የመማሪያ እና የመጠለያ ቤት ችግር ለመቅረፍ እና በቀጥታ ገቢው ለጉባኤ ቤቱ ሊሰራ ታቅዶ በ2002ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ ለተቀመጠው ህንጻ ማሰሪያ ሲሆን ደቀ መዛሙርቱ መጠለያ አግኝተው ትምህርታቸውን እንዲማሩ እና ተምረው እንዲያጠናቅቁ ለግንባታው የሚውል ነው ብለዋል መምህር ፍቅረ ማርያም፡፡
ይህ ጉባኤ ቤት የአራቱ መጻሕፍተ ጉባኤያት የሚካሄድበት እና በርካታ ሊቃነ ጳጳሳት ፣ሊቃውንት የወጡበት ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ለአብነትም ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም  የተማሩበት፤ ጌታው ክቡር መምህር ምህረቱ፣ጌታው ክቡር ዶክተር አለቃ አየለ አለሙ፣ጌታው ክቡር ሊቀ ሊቃውንት መንክር መኮነን እና ብጹዕ አቡነ እንድርያስ  የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ተምረውበታል አስተምረውበታልም።


ይቆየን……..ክፍል ሦስትን ይጠብቁ

Post Bottom Ad