በእንተ ስማ ለማርያም ስለ እመ አምላክ - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Friday, November 6, 2015

በእንተ ስማ ለማርያም ስለ እመ አምላክ በእንተ ስማ ለማርያም ስለ እመ አምላክ
 ቤተ ክርስቲያን ሰማይና ምድር ከመፈጠራቸው በፊት ነበረች። ዓለማት ከተፈጠሩ በኋላ በዓለመ መላእክት፣ በዓለመ መሬት በሕገ ልቡና እና በሕገ ኦሪት እግዚአብሔር በመረጣቸው ነቢያትና ካህናቱ አማካኝነት ሰዎችን ከእግዚአብሔር ጋር ስታገናኝ ኖራለች። በዘመነ ሐዲስ ደግሞ በደመ ክርስቶስ ተዋጅታ ሕገ ወንጌልን ስትናኝ እና አምልኮተ እግዚአብሔርን ስታስፋፋ ኖራለች። በእነዚህ አዝማናት ሁሉ ስለ እርሷ ሳይፈሩና ሳያፍሩ አንገታቸውን ለሰይፍ፣ ጀርባቸውን ለግርፋት፣ እግራቸውን ለሰንሰለት የሰጡላት፣ በብዙ መከራዎች የተጋደሉላትን አበው፣ ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ሰማዕታትን እና በእነርሱ መንገድ የተጓዙ ብዙ ሊቃውንትን አፍርታለች (ዕብ ፲፩)።
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሕገ አበውን፣ ሕገ ኦሪትንና ሕገ ወንጌልን አስተባብራ በመያዝ የጥበብ ምንጭ፣ የሥርዓት መፍለቂያ፣ የዕውቀት ባሕር ሆና ሁሉ የተሟላላት ስንድ እመቤት ናት። በማኅበራዊ አገልግሎቷ ደግሞ የድኩማን መጠጊያ፣ ያዘኑና የተከፉ መጽናኛ፣ የማንነትም አሻራ ነች። ለዚህም የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በተለያዩ ገዳማት፣ አድባራት፣ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ የአብነት ት/ቤቶች ተቀዳሚ ተጠቃሾች ናቸው። በተለያዩ ጊዜያት የተንኮልና የክህደት ቋጠሮ ይዘው የመጡ መስሐቲያን (አሳሳቾች) አፍረው የተመለሱት ከአብነት ት/ቤቶቹ በወጡ መምህራን ነው። ከዚህም በተጨማሪ ለሀገር መሪ ለሕዝብ አስተማሪ በመሆን ሕዝብን ያገለገሉ ደጋጎች ከእነዚህ የአብነት ት/ቤቶች በአጠቃላይ ከቤተ ክርስቲያን የወጡ ናቸው። ሌላው ልንገነዘበው የሚገባ ቁም ነገር ቢኖር ገና ያልደረስንባቸው ብዙ እምቅ መንፈሳዊ ሃብቶች ያሉን መሆናቸዉ ነው። ለምሳሌም፦ በዜማዉ የአጫብር፣ የቆሜ፤ በቅኔው የዋድላ፣ የጎንጅ፤ በመጻሕፍት ትርጓሜ የላይ ቤት፣ የታች ቤት እየተባሉ የሚሰጡ ትምህርቶች ይትበሃሎች አሉን። እነዚህ መሠረታቸው የቤተ ክርስቲያን ትምህርትና ሥርዓት ሆነው አካባቢያዊ መልክ ያላቸውን እምቅ እሴቶች ልንፈለፍላቸውና ልንንከባከባቸው የሚገቡ ናቸው። የቤተ ክርስቲያኒቱ አብነት ት/ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት አሁን በዓለም እውቅ ከሆኑት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዱ ከሆነው ከሐርቨርድ ዩኒቨርሲቲ ሥርዓተ ትምህርት ጋር የሚያመሳስለው ነገር ያለው ሲሆን ይህም አግራሞትን የሚፈጥርና የሥረዓተ ትምህርቱን ጥንካሬ የሚያሳይ ነው። ሆኖም የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥረዓተ ትምህርት በዘመን ቀዳማዊ ሆኖ መገኘቱ እጅግ የሚያኮራ ነው። የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ሳይከለስና ሳይበረዝ ተጠብቆ እስከአሁን እንዲዘልቅ ያደረጉት ገዳማት፣ አድባራት፣ አብያተ ክርስቲያናት እና የአብነት ት/ቤቶች ናቸው። ስለሆነም እነዚህ የትምህርት ማዕከላት በተለያዩ ችግሮች ምክንያት እንዳይዘጉ፤ መምህራኑና ተማሪዎቻቸው እንዳይሰደዱ፣ ወንበር እንዳይታጠፍ በጋር እና በተናጠል ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱ የሚታወቅ ነው። ሆኖም ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣቱ የእሳት ማጥፋቱ ሥራ በልማት ቢታገዝና ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት ቢቻል መልካም መሆኑ በቅዱስ ሲኖዶስ እና በምእመናን ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ጉዳይ ነው። ገዳማት አድባራትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና ለኢትዮጵያ ተቆጥሮና ተሰፍሮ የማያልቅ ውለታ የዋሉ፤ እንደ ዓይናችን ብሌን ልንጠብቃቸው የሚያስፈልጉ የተቀደሱ ሥፍራዎቻችን ናቸው፡፡ እነዚህ ገዳማት፣ አድባራትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚመሩ የሊቃነ ጳጳሳቱ መገኛ፣ እና በአፍ በመጣፍ የመጣን አጽራረ ቤተ ክርስቲያን የሚመልሱ የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መፍለቂያ ናቸው፡፡ ገዳማቱ ስለሀገር፣ ስለወገን የሚጸልዩ ከእነርሱም አልፎ ለሌላው መዳን ምክንያት የሚሆኑ መናንያን፣ መነኮሳት መኖሪያ፣ የምእመናን ተስፋ፣ በረከት ማግኝያም ናቸው፡፡ ገዳማቱ፣ አድባራቱና የአብነት ትምህርት ቤቶቹ ለኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ-ሥዕል፣ የፊደል፣ የሥነ-ሕንጻ ምንጭነትና አጠቃላይ የሥልጣኔና የትምህርት ማዕከል በመሆን ያገለገሉና እያገለገሉ ያሉ የሀገር ኩራት ናቸው፡፡ በውስጣቸው የሚገኙት ንዋያተ ቅድሳት፣ ሥነ-ሕንጻዎችና ቅርሶች ለሀገርና ለወገን ኩራት ከመሆን አልፈው ዓለም አቀፍ ቅርሶች እስከ መሆንና ለሀገሪቱም በቱሪዝሙ ዘርፍ ከፍተኛ ገቢ እያስገኙ ያሉ ውድ ሀብቶቻችን ናቸው፡፡ እነዚህ የቤተ ክርስቲያን፣ የሀገር፣ የምእመናን ተስፋና ኩራት እንዲሁም የማንነታችንና የታሪካችን መነሻ የሆኑት ገዳማት፣ አድባራትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ዛሬ ተገቢው ትኩረት ባለማግኘታቸውና በበቂ ሁኔታ አስታዋሽ በማጣታቸው ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠዋል፡፡ ገዳማቱ ሁሉ ካለባቸው ችግር ተላቀው በቋሚነት ራሳቸውን በልማት እንዲችሉ ለማድረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሁሉንም ምእመናን ተሳትፎ የሚጠይቅ ሰፊ ሥራ ይጠብቃታል፡፡ ስለዚህ ወደፊትም ለውጥ እና የተጠናከረ እድገት እስኪመጣ ድረስ ደጋግመን ልናስብበት ይገባል፡፡ በመሆኑም በቀደሙት ቅዱሳን አባቶቻችንን ጽናትና ተጋድሎ ተጠብቀው የቆዩት ገዳማት፣ አድባራትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ዛሬ በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች እየተፈተኑ ነው፡፡ መነኮሳቱ በረኀብና በዕርዛት እየተሰቃዩ ገዳማት እየተፈቱ ነው፡፡ የአብነት መምህራን በተማሪዎቻቸው ብዛት የደመቀ ሰፊ ጉባኤያቸው በምግብ እጦት የተማሪው ቁጥር እየተሸረሸረ፣ መምህራን ወንበራቸው እየታጠፈ ጉባኤውም እየተበተነ ነው፡፡ ከዕድሜ ዘመናቸው የተነሣ ጥንታውያኑ ቅርሶች እና የአብያተ ክርስቲያናቱ ሕንፃዎች እየፈራረሱ ነው፡፡ መጻሕፍትና ንዋያተ ቅድሳቱ ከአያያዝ ጉድለትም ሆነ በአግባቡ የሚጠቀምባቸው ጠፍቶ እየተጎሳቆሉ ነው፣ በተለይ በየገጠሩ በርቀት በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ከልብሰ ተክህኖ እስከ ዕለት መቀደሻ ጧፍ፣ እጣን፣ ዘቢብ እየጠፋ ቅዳሴ እየተስተጓጐለ ነው፡፡ እነዚህ ገዳማት፣ አድባራትና አብነት ትምህርት ቤቶች በአጽራረ ቤተ ክርስቲያን እና በዘራፊዎች ጭምር እየተዘመተባቸውም ነው፡፡ በየገዳማቱ ተመሳስለው በመግባት፣ በችግራቸው ሽፋን መነኮሳቱን በማሳሳት፣ በኣታቸውን ለቀው እንዲወጡ ለማድረግ ከመጣር አንሥቶ ጥንታውያኑን መጻሕፍትና ንዋያተ ቅድሳቱን እስከመዝረፍ ድረስ ብዙ ችግሮች እየተፈጸመባቸው ነው፡፡ በእነዚህ ገዳማት፣ አድባራትና አብነት ት/ቤቶች የሚገኙ አባቶችና አገልጋዮች ይህን ሁሉ ተደራራቢ መከራና ፈተናዎችን እየተጋፈጡ በእግዚአብሔር ቸርነት ጸንተው ቢቆዩም፤ ሃይማኖታዊ እሴቶችና ቅርሶቻችን ተጠብቀው ለትወልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ በየጊዜው በተለያየ አቅጣጫና መንገድ ከየገዳማትና አድባራቱ እንዲሁም አብነት ት/ቤቶች የሚመጡትን የድረሱልን ጥሪ ተግባራዊ ምላሽ መስጠት የምእመናን ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው፡፡ ለነዚህ ገዳማት፣ አድባራትና የአብነት ትምህርት ቤቶች መልስ መስጠት የቤተ ክርስቲያንን ተተኪ በብዛት ማፍራት ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያንን የሀገርን ታሪክና ቅርስ ማስጠበቅና መጠበቅም ነው፡፡ በተጨማሪም ከራሳቸው አልፎ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለሀገር፣ ለወገንና ለዓለም ሰላም ቀን ከሌት የሚጸልዩትን መናኒያን ማትጋት ነው፡፡ ስለዚህም ይህንን የገዳማቱን የድረሱልን ጥሪ መስማት ያስፈልጋል፡፡ የሊቃውንትና አባቶች ካህናት መፍለቂያነታቸው እንዲቀጥል መናንያንና መነኮሳቱ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለሀገርና ለወገን የሚጸልዩት ጸሎት እንዳይስተጓጐል፣ ጥንታውያኑ የብራና መጻሕፍት፣ ገድላትና ተአምራት ሌሎችም የእምነታችንና የማንነታችን መለያ የሆኑ ንዋያተ ቅድሳቱ በዘላቂነት ባሉበት እንዲጠበቁ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እሁንም የነዚህ ጥንታውያን ገዳማት፣ አድባራትንና የአብነት ት/ቤቶች ችግር የሰፋና በርካታ በመሆኑ የሁሉንም ዘርፈ ብዙ ተሳትፎ ይፈልጋል፡፡ በችግር ያሉትን ገዳማት፣ አድባራትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ጥሪ የማንን ፈጣንና ተግባራዊ ምላሽ እንደሚጠብቁ ለማወቅ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ገዳማቱን ከጠባቂነትና ከተረጂነት አላቆ ራሳቸውን በማስቻል መንገድ ቢቀናጅ ገዳማቱን፣ አድባራትና አብነት ትምህርት ቤቶቹን ከተመጽዋችነት ማላቀቅ ይቻላል፡፡ ቀጣይነት ያለው ልማት በጋራ መሥራቱና መተባበሩ ለነገ በይደር ይቆይ ሊባል የማይገባ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም ገዳማት፣ አድባራትና የአብነት ትምህርት ቤቶቹ ከተረጂነት ወጥተው ራሳቸውን በመቻል ታሪክ፣ ቅርስና የትምህርት ማዕከልነታቸው ተጠብቆ፤ በዘላቂነት እንዲቀጥሉ በማድረግ በኩል የሁላችንም አስተዋፅኦ አለ የማባል ነው ፡፡
+++++++++++እግዚአብሔር ገዳማቱን አድባራቱን ከጠላት ይጠብቅልን++++++++++

Post Bottom Ad