ጰራቅሊጦስ - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Saturday, June 6, 2015

ጰራቅሊጦስ


ጰራቅሊጦስ በተለየ አካሉ መንፈስ ቅዱስ የሚጠራበት የመንፈስ ቅዱስ ስም ነው፡፡
 ጰራቅሊጦስ ማለት
አጽናኝ  (መሰተፍሥሒ)
 የሚያስደስት (ከሳቲ)
 የሚገልጽ  (መስተሥርዪ) ኃጢአትን የሚያስተሰርይ የሚል ትርጓሜ አለው፡፡
ከጌታችን ትንሣኤ ከሃምሳኛው ቀን ጀምሮ እስከ ሰኔ አስራ ሰባት ድረስ ያለው ጊዜ ዘመነ ጰራቅሊጦስ ይባላል፡፡
በዚህ ዘመን የሚዘመሩት መዝሙራት የመንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት መሰጠትንና የጌታችንንም ትንሣኤና ዕርገት የሚመለከቱ ናቸው፡፡
እሥራኤላውያን የፋሲካን በግ ካደረጉ በኋላ ከግብጽ ባርነት ነጻ ወጥተዋል::
 ከግብጽ ባርነት እግዚአብሔር ነጻ እንዳወጣቸው ለማዘከርም በየዓመቱ የፋሲካን በዓል ያከብራሉ::
 ከዚህ በዓል ቀጥሎ ሰባት ሱባኤ ሲፈጸም ማለትም 50ኛው ቀን በዓለ ሰዊት / የእሸት በዓል / ያከብራሉ::
 መከር በደረሰ ጊዜ በመጀመሪያ ከሚወቁት እህል ለእግዚአብሔር መሥዋዕት የሚያቀርቡበት ነው፡፡ (ዘሌ.231-39) 
 እነዚህንም በዓላት ለማክበር በዓለም ዙሪያ ተበትነው የሚኖሩት ሳይቀሩ ወደ ኢየሩሳሌም ይመጡ ነበር፡፡
ሐዋርያት ዕርገቱን ዐይተው ነገረ ምጽአትን ከመላእክትም ተረድተው ወደ ማደሪያቸው ተመልሰው የተሰጣቸውን ተስፋ ይጠባበቁ ጀመር፡፡ የተሰጣቸው ተስፋ ‹‹ እነሆ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለው እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ቆዩ ›› ሉቃ 2449 የሚል ነበር ፡፡
 ተስፋውም መንፈስ ቅዱስ በወረደላቸው ጊዜ ሰማያዊ ሃብትን እውቀትን ገንዘብ ታደርጋላችሁ በአራቱ ማዕዘን ትመሰክሩልኛላችሁ የሚል ነው፡፡ (የሐዋ.18-12)

***
ለምን በኢየሩሳሌም ጸንታችሁ ቆዩ አላቸው ? ***ሉቃ 2449

1.    
ከሃይማኖት ከምግባር እንዳይወጡ፤
 መንፈስ ቅዱስ ከመቀበላቸው በፊት ፈሪዎች የሚረሱ ነበሩና ፍርሃታቸው እስከ መካድ እንዳያድርሳቸው ፡፡
በኢየሩሳሌም ቆዩ ባይላቸው ኖሮ ሲገቡ ሲወጡ አይሁድ ያገኟቸውና መከራ ቢያጸኑባቸው ሃይማኖት መካድ ከምግባር መውጣት ይመጣልና ፡፡

2.    
ለመነኮሳት ለገዳማውያን ( ለባህታውያን ) በገዳማቸው ጸንተው መኖር እንዳለባቸው ሲያስተምር ነው ፡፡ 
 ለጊዜው 120 ቤተሰብ ሲሆን ፍጻሜው ለመነኮሳት ነው።  ኢየሩሳሌም የገዳም ምሳሌ ናት፤  ርግብ የታቀፈችውን እንቁላል ትታ በሔደች……. ዙረት ባበዛች ጊዜ እንቁላሉ እንዳይፈለፈል እንደምታደርግ ሁሉ ባዕቱን ትቶ የሚሔድ መነኩሴ ፍሬ አያፈራምና፡፡

3.    
በሃይማኖት መጽናት እንደሚገባ ለማጠየቅ ነው ፡፡
 ምሥጢረ ሥላሴ ምሥጢረ ሥጋዌ ምሥጢረ ጥምቀት ምሥጢረ ቁርባን ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ሁሉ በኢየሩሳሌም ስለተገለጸ ኢየሩሳሌም በሃይማኖት ትመሰላለች።
 በኢየሩሳሌም በሃይማኖት ብትጸኑ ሐዋርያት ያገኙትን ክብር ታገኛላችሁ ሲል ነው  አንድም ኢየሩሳሌም በቤተክርስቲያን ትመሰላለች ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ይፈጸምባታልና በቤተክርስቲያን ብትጸኑ ሐዋርያት ያገኙትን ክብር ታገኛላችሁ ሲል ነው ፡፡

4.    
መንፈስ ቅዱስ ዝርው በሆነ ልቦና እንደማያድር ለማጠየቅ………. ልቡናው በሃይማኖት በትህትና በፍቅር በጸና ላይ እንደሚያድር ለማጠየቅ


ተናግሮ የማያስቀር ምሎ የማይከዳ ልዑል አምላክ ነውና በገባላቸው ቃል መሠረት ሞትን ድል አድርጎ በተነሳ 50ኛው ቀን ባረገ 10ኛው ቀን ለሐዋርያት ፀጋ መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል ሰደደላቸው ፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው መቶ ሃያው ቤተሰብ የሚባሉት
 12 ሐዋርያት
 72 አርድእት
 36 ቅዱሳት አንስት በማርቆስ እናት ቤት በጸሎት ላይ ሳሉ ጌታ ከሙታን ከተነሳ በሃምሳኛው ባረገ በአስረኛው ቀን
ተስፋው ተፈጸመ፡፡ ሐዋ.21 ድንገት ከወደ ሰማይ እንደ ዐውሎ ነፋስ ድምጽ ያለ ነጎድጓድ ተሰማ ያሉበትን ቤት መላው፡፡
ላንቃ ላንቃ ያለው እሳት ሆኖ ታያቸው፡፡ በሁሉም አደረባቸው ኃይል የሚሆናቸውን ሀብት እውቀት ገንዘብ አደረጉ፡፡ የማያልቅ ሃብቱን ጸጋውን ለመቶ ሃያው ቤተሰብ አደላቸው ከዚህም በኋላ ‹‹ 5500 ዘመን ሲፈጸም በሥጋዊ በደማዊ ሰው ሁሉ የባህርይ ሕይወቴን መንፈስ ቅዱስን አሳድርበታለሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ / 12 ሐዋርያትና 36 ቅዱሳት አንስት/ ራዕይ ያያሉ ጎበዛዞቻችሁም / 72 አርድእት / ራዕይ ያያሉ›› ተብሎ በነቢዩ ኢዮኤል የተነገረው ቃል ተፈጸመ (ትን. ኢዮ 228-32)

***
እመቤታችን ለምን ተገኘች?***
   
በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስ ሲወርድላቸው እመቤታችን ከሐዋርያት መካከል ነበረች ፡፡
በዛ የተገኘችው እንደ ሐዋርያት ከፍርሃታቸው እንዳላቀቃቸው ምሥጢርን እንደገለጸላቸው በዓለም ሁሉ ቋንቋ እንዲናገሩ እንዳደረጋቸው ለእመቤታችንም አስፈልጓት አይደለም ፡፡

የሃይማኖት ምልክት ማረጋገጫ እሷ የሌለችበት ምንም ነገር ስለሌለና ስለማይጥም እንጂ እርሷማ የመንፈስ ቅዱስ ቤቱ ማደሪያው ነች እንጂ አዲስ እንዲያድርባት አይደለም፡፡
እመቤታችን ከሴት ሐረግ ስለምትገኝ ስለ እመቤታችን የአቤል ምትክ ሴት ተወለደ እንዲሁም ኖኅ ከእነ ቤተሰቡ ያልጠፋው በዘራቸው እመቤታችን ስላለች ነው፣ በአስቴር ጸሎት እሥራኤላውያን የዳኑት እመቤታችን ስለምትገኝ ነው ፡፡ እመቤታችን በቃና ዘገሊላ በእግረ መስቀሉ የሌለችበት ቦታ ስለሌለ በዚህም ታላቅ ቀን ከሐዋርያት መካከል ተገኝታለች ፡፡ 

በዓላቸው ‹‹በዓለ ሰዊትን›› ለማክበር በኢየሩሳሌም የተሰበሰቡ አይሁድና ወደ አይሁድነት የተመለሱ የተለያዩ ሀገር ሰዎች ድምጽን በሰሙ ጊዜ የሆነውን ለማለየት ለማወቅ ሐዋርያት ወዳሉበት ተሰበሰቡ፡፡
 የጌታችን ደቀመዛሙርት በተሰጣቸው የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ፈሪዎች የነበሩ ደፋሮች ሆኑ፤ ፍጹም እውቀት ተሰጣቸው ከኃጢአትና ከእርጅና ታደሱ፡፡ 72 ቋንቋ ለየሀገሩ ሰው ሁሉ የእግዚአብሔር ቸርነት አስተማሩ፡፡ ሐዋ.27-12 ‹‹ ጉሽ የወይን ጠጅ ጠጥተው ሰክረው ነው ›› እያሉ በሚያላግጡባቸው አይሁድ ፊት እነ ቅዱስ ጴጥሮስ ቆመው በማስተማር ሦስት ሺህ ሰዎችን አሳምነው አጠመቁ፡፡

ዘመነ ጰራቅሊጦስ በተለይም 50ኛው ቀን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹‹ የቤተክርስቲያን የልደት ቀን ›› ሲል ጠርቶታል፡፡ በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተመሰረተችው ቅድስት ቤተክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ፀጋ ተመልታ ለሰው ልጆች ሁሉ የድህነት ጥሪን ማሰማት የጀመረችበት ዕለት ስለሆነ ይህ ስም ተሰጥቷታል፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ባደረገው ስብከት የሕዝቡ ልብ በቃለ እግዚአብሔር ተሞልቶ ሦስት የሚያህሉ በአንድ ቀን ሰዎች ክርስትናን ተቀብለው በማመን ተጠምቀዋል ሥራ 237 -42

ይህም የሆነው ግንቦት 18 እለት ነው ይህ ቀን ጥንተ ጰራቅሊጦስ ሲሆን በቅዱስ ዴሜጥሮስ ቀመር መሠረት ትንሣኤ ከዋለ በኋላ በሃምሳኛው ቀን ወይም ዕርገት በዋለ 10ኛው ቀን እንዲውል ተወስኗል ፡፡ሐዋርያት መልካሙን የምሥራች ተስፋ መድረሱን ቃል ሥጋ መዋሐዱን መከራ ተቀብሎ የሞትን ሥልጣን ሽሮ ከሙታን ተለይቶ በሥልጣኑ መነሳቱ በፍቅርና በድፍረት ይመሰክሩ ዘንድ ይህ ጸጋ ተሰጣቸው፡፡

***
በዐረገ 10ኛው ቀን ስለምን ፀጋ መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት ሰደደላቸው ***

1.    
10ኛው ማዕርግ የገባን ነበርንና ወደ ቀድሞ ክብራችን እንደተመለስን ለማጠየቅ
2.    10
ቱን ትእዛዛት ብንጠብቅ ብንፈጽም ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እንደሚበዛልን ለማጠየቅ
3.    10
ቁጥር የምሉነት የፍጹምነት ምሳሌ እንደሆነ ሁሉ እውነተኛ መንፈስ ቅዱስ እንዳደረባቸው ለማጠየቅ  ::   ዘፍ 317 .ዳን 112

ዛሬም ቢሆን ይህ ጸጋ እግዚአብሔርን እንደ እግዚአብሔርነቱ በንጽህና በቅድስና ለሚያመልኩት ይሰጣል፡፡ ኤፌ 430
 ይህ ማለት ለሁሉም የተለያዩ ቋንቋዎች የመናገር ሃብት ይሰጣል ማለት አይደለም፡፡ ሃብቱ ብዙ የሆነ መንፈስ ቅዱስ በሥላሴ አንድነትና ሦስትነት አምነን የኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክነት ተገንዝበን የእመቤታችንን ዘለዓለማዊ ድንግልና፣ የቅዱሳንን ክብር ተረድተን ስንጠመቅ እንደፈቃዱ ለአንዱ ማስተማርን ለሌላው መዘመርን ለተቀረው እንደወደደ ይሰጣል፡፡ 1 ቆሮ 124 ይህም እያንዳንዱ ምዕመን በተሰጠው ጸጋ ቤተክርስቲያንን እንዲያገለግል ይረዳዋል፡፡ በጽርሐ ጽዮን በሐዋርያት ላይ የወረደው መንፈስ ቅዱስ ጸጋውን ሰላሙን ያድለን፡፡
አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔ


Post Bottom Ad