ከፊደላት ተራ ከሆሄ ገብቼ
ክብርሽን ለመግለጽ ሞልቼ አስፍቼ
አበው ሲናገሩ ክብርሽን ሰምቼ
ቃላትን በቃላት መርጬ አሳክቼ
“ሀ” ብዬ ጀመርኩ ልናገር ጸጋሽን
መጽሐፍ ከሚለው በልቤ ያለውን
አባቶች ቅዱሳን ያስተላለፉትን
በሕይወት ከእነርሱ የተቀበልኩትን
በሰባት በሰባት ከተከፋፈሉት
ከላይ እስከታች ከተደረደሩት
እስከነ “ፐ” ድረድ ከተሰበሰቡት
ያንንም ሳመጣው ይህንም ስመዘው
ጥንት የመረጥኩትን መልሼ ስተወው
ፊት ያስገባሁትን ኋላ ስመልሰው
አንዱን አስገብቼ ሌላውን ሳወጣው
ፈጽሜአለሁ ብዬ የጻፍኩትን ባየው
ድንግል ውዳሴሽን ጨረስኩ ሳልጀምረው።