
ወደ ቅዱሳን ቦታ በምንሄድበት ወቅት በምን ዓይነት ስሜት እንዴት ባለ ሁኔታና አለባበስ በመሆን መሄድ አለብን፡፡
- ወደ ገዳም የሚደረግ መንፈሳዊ ጉዞ ለመዝናኛና ለጉብኝት ወይም ለሽርሽር አይደለም ነገር ግን በረከትንና መንፈሳዊ ጥቅምን ለማግኘት እንጅ
- የተቀደሱ ነገሮችን ሁሉ በማክበርና በፍፁም ጸጥታ እንጅ በጫጫታና በጩኸት በከተማ እንዳለው ማድረግ እንደሌለብህ አትዘንጋ፡፡ ቅዱሳን በትጋት በመጸለይ ራሳቸውን በጸጥታ ያሳለፉበት ነውና፡፡ ስለዚህ ፍጹም ጸጥታና ነፍስህን በጥልቅ በሆነ ሁኔታ በመጠበቅ ጥልቅ ወደ ሆነው እግዚአብሔር ምስጢር መግባት ትችላለህ፡፡
- መንፈሳዊ ጥቅምን እንዳታጣ ወደ ገዳም በምትሄድበት ጊዜ በመንገድህ ከጓደኞችህ ጋር በመሆን በሳቅ፤ በቀልድና ዋዛ ፈዛዛ ጊዜህን አታባክን፡፡
- በበረከት ፋንታ መርገምን እንዳታገኝ በገዳሙ በምታየውና በምትሰማው ነገር ሁሉ አስተያየት ለመስጠት አትሞክር እንዲህ ቢሆን እንደዚያ ቢሆን ብለህ አትፍረድ፡፡
- ወደ ገዳም ስትሄድ አለባበስህ/ሽ የሚገባና ሌሎችን የማያሰናክል መሆን አለበት፡፡
- በገዳሙ ውስጥ የምታደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ ገዳማውያኑን የሚረብሽ መሆን የለበትም፡፡
- ወደ ገዳም በምትሄድበት ጊዜ ስለዓለማዊ ነገር ምንም ነገር መናንያኑ ፊት አታውራ፡፡
- በቦታው የነበሩ ቅዱሳንን ስም ምግባር ትሩፋታቸውን በሕይወታቸው የነበራቸውን ተመስጦና ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በማሰብ የእነርሱን አሠረ ፍኖት ለመከተል ምን ማድረግ እንዳለብህ አስብ፡፡
- የተጠቀሙ አባቶችን እነርሱን በማግኘት መንፈሳዊ ጥቅምን በረከትን አግኝ፡፡ እንዲሁም የጸሎት መጻሕፍትና ሀሳቦችን ለመጻፍ ማስታወሻ ደብተር መያዝን አትዘንጋ፡፡
- እያንዳንዷ እርምጃ የምትራመድበት ቦታ በቅዱሳን እንባ ማፍሰስ የታጠበ መሆኑንና በተቀደሰ ቦታ እየተንቀሳቀስክ መሆኑን አስብ፡፡
- በገዳሙ የቅዱሳን አማላጅነትን በመማፀን ጸሎታቸው ይደግፍህ ዘንድ በእግዚአብሔር ጸሎትህን አቅርብ፡፡
- ፍጹም በተረጋጋ መንፈስና በጸጥታ በተለየ ቦታ ተቀምጠህ ራስህን መርምር፡፡ ከጉዞውም ምን እንደተጠቀምክ ራስህን በግልጽ ጠይቅ፡፡