መንፈሳዊ ቅናት - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Monday, March 9, 2015

መንፈሳዊ ቅናት

መንፈሳዊ ቅናት ማለት ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔር እንዲሆኑ፤ በምድር ላይ ፍቅር፤ ሰላም፤ መተሳሰብ፤ መረዳዳትና መከባበር እንዲኖር፤ ያለንን መሻት በአገልግሎት የምንገልጥበት መንገድ ነው።ቅዱስ ጳውሎስ የሰላምን ወንጌል ለሁሉ ለማዳረስ ያለውን መንፈሳዊ ቅናት ሲገልጽ “እዳ አለብኝ ስለዚህ በተቻለኝ መጠን ወንጌልን ለመስበክ ተዘጋጅቻለሁ” በማለት ተናግሯል ሮሜ 1፡14።  ስለዚህ ቅናት የእግዚአብሔር መንግስት ለሁሉ እንድትሰጥ የእግዚአብሔር ህዝብ እንዲበዛ ከልብ ያለ መሻት ነው። 
ክርስቲያን መንፈሳዊ ቅናት ሲይዘው እግዚአብሔርን ይመስላል።  እግዚአብሔር ለህዝቡ ቀናኢ ነውና።  ኢሳ 6፤3-13 መዓቱም የሚመጣው ከተቀደሰ ቅናቱ የተነሳ ነው ህዝ 5፤13።  ለቤቱ ይቀናል ማቴ 21፤13 ስለዚህ ክርስቲያን የእግዚአብሔር መቅደስ ለሆነው ሰው በመቅናት ለመንፈሳዊ አገልግሎት ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል።  ለእግዚአብሔር የሰላም ቃል ኪዳን ይቀበላልና ዘኁ 25፤11-13።  ለአገልግሎትም ይነሳሳል 2ኛ ቆሮ 9፤2
አንዲት እናት አንድ ቀን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ አገኘኋቸውና ሁልጊዜ ህጻኑን ልጃቸውን ይዘው እንደሚሄዱ ስለማውቅ፤ ይህንን ሕጻን ልጅ ሁልጊዜ በዚህ በብርድ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይዘውት የሚመጡት ለምንድን ነው? ብየ ጠየኳቸው። 
እሳቸውም አየህ ልጄ በዚህ ዘመን መናፍቃን በዝተዋል፤ ቴክኖሎጂ የተራቀቀበት ዘመን በመሆኑ፤ ልጆች እንደምታውቀው አብረውህ ተቀምጠውም ሆነ እየበሉም ሆነ እየተጓዙ በስልክ ቴክስት በማድረግ፤ የተለያየ ምስል በመላላክ፤ በአይፓድ….. ሙዚቃ ጀሮአቸው ላይ ለጥፈው ሲወዛወዙ መዋል፤ቀልድና ፌዝን በህይወታቸው ውስጥ የሚዘሩበት ዘመን ሆኖ ስላየሁት እና ፈጣሪያቸውን የዘነጉበት ወቅት በመሆኑ፤ የእኔ ልጅ በዚህ መጥፎ ዘመን በእንደዚህ አይነት አስከፊ ድርጊት እንዳይጠመድብኝ ስል ከልጅነቱ ጀምሬ ማን እንደፈጠረው? ማን ካለ መኖር ወደ መኖር አንዳመጣው፤ ይህንን አለም ከመፍጠሩ በፊት የነበረ፤ አለም ፈጥሮ የሚገዛ፤ የአለምን ፍጥረት የሚመግብ የሚያስተዳድር፤ አለምን አሳልፎ ደግሞ የሚኖር ድንቅ መካር ሃያል አምላክ እንዳለን ማስተማር ግዴታ አለብኝ።  ደግሞም አሁን ልጄ እኔ የማደርገውን እያየ የሚያደርግበት ዘመን ነው እና ስሰግድ ይሰግዳል፤ ስጸልይ አብሮ ይጸልያል፤ ጸበል ስጠጣ አብሮ ይጠጣል፤ ቅዳሴ አብሮ ያስቀድሳል፤ አብሮ ከህጻናት ጋር ፈጣሪውን በዝማሬ ያመሰግናል እና….. አየህ እግዚአብሔር ይመስገን አሁን የኔ ልጅ ያለበት ሁኔታ መልካም ነው፤ ብርዱ ምንም አይለውም የፈጠረው አምላክ የሚያኖር እሱ ነው፤ የሚገድልም እሱ ስለሆነ በቸርነቱ ይጠብቀዋል።  ልጄ ጥሩ ልጅ ሆኖ እንዲያድግልኝና መላ ዘመኑን ፈጣሪውን እያመሰገን እንዲኖርልኝ ምኞቴና ፍላጎቴ ነው። አንተ ግን አትጨነቅ ለማንኛውም እጅጉን አመሰግናለሁ ለልጄ ስላሰብክለት አሉኝ።  ለካስ በውጩ ዓለም ያውም አሜሪካ ውስጥ ይሄም አለ።  እናቶች ለልጆቻቸው እንደዚህ አርቀው ያስባሉበጣም ድንቅና ተአምር ሆኖብኛል።  እግዚአብሔር አምላክ ሃሳባቸውን ይሙላ።  ሌሎችም እናቶች እንደኒህ አይነት እናት መሆን ይገባቸዋል።  መንፈሳዊ ቅናት ሊኖረን ይገባል።  ፈጣሪን የሚያገለግል ልጅ ማግኘት ደግሞ መታደል ነው።
ምንም እንኳ መንፈሳዊ ቅናት የእግዚአብሔር በረከት የሚያሰጥ ቢሆንም በእውቀት እና በጽናት ላይ ካልተመሰረተ ግን ለሃጢአት የሚዳርግ ይሆናል 2ኛ ሳሙ 21፤1-2 ስለዚህ ክርስቲያን ቅናቱ በመንፈሳዊ እውቀትና ጽናት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ያስፈልጋል።  ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምጻም እያነጻ፤ እውር እያበራ፤ ሙት እያስነሳ ከአንዱ ከተማ ወደ አንዱ ከተማ ይሄድ ነበር።  ወደ ሰማርያም በደረሰ ጊዜ የሰማርያ ሰዎች ስላልተቀበሉት ያዕቆብና ዮሐንስ ተቆጥተው ጌታ ሆይ እንደ ኤልያስ እሳት ወርዳ እንድትበላቸው እዘዝ።  ባሉት ጊዜ ጌታችን ቅናታቸው በእውቀት ላይ የተመሰረት ስላልሆነ ገስጿቸዋል ሉቃ 9፤54 ስለዚህ ቅናት በእውቀትና መንፈሳዊ ጽናት ላይ የተመሰረተ ካልሆነ ውጤቱ የከፋ ይሆናል ማለት ነው።
ብዙ ሯጮች በማራቶን ሜዳ አብረው ለመሮጥ እንደሚጀምሩት ሁሉ ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ይሁዳ፤ ከእነ ቅዱስ ጢሞቴዎስ፤ ቅዱስ ማርቆስና፤ ቅዱስ ሉቃስ ጋር ደግሞ ዴማስ መንፈሳዊውን ሩጫ አብረው ለመሮጥ ጀምረው ነበር። ነገር ግን ይሁዳ በገንዘብ ፍቅር ተታልሎ ፤ ዴማስ ደግሞ በተሰሎንቄ ከተማ ተሸንፈው ቅዱሳን ሐዋርያትና አብረዋቸው ይህንን አለም በድል የተወጡት፤ ሌሎች ከደረሱበት ክብርና ጸጋ ሳይደርሱ በመንገድ ቀርተዋል።  ቅዱሳን ይህንን አንድ ጊዜ የሚያስፈራ ሌላ ጊዜ ደግሞ የሚያስጨንቅ መስሎ የሚታየውን ዓለም በድል ያለፉ፤ በገንዘብ ፍቅር ያልተሸነፉ፤ ለዓለም ውበት ያልተንበረከኩና ለጊዜያዊ ነገር ያልተታለሉ ናቸው። በፈተና የሚጸና የተባረከ ነው…… የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና፤ ስለዚህ እነዚህ ቅዱሳን አባቶቻችን እኮ ብዙ ፈተናውን አልፈው ነው ለክብር የበቁት እኛም የቅዱሳኑን ሕይወት ምሳሌ ሆኖን የሕይወትን አክሊል እንድንቀበል እግዚአብሔር አምላክ ይርዳን። 
Post Bottom Ad