ቅዱስ ዲዮስቆሮስ - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Sunday, March 15, 2015

ቅዱስ ዲዮስቆሮስ

ጉስ መርቅያኖስ ብዛታቸው 636 የሆነ  ወደ ሰበሰበው ጉባኤ ቅዱስ ዮስቆሮስንም ከስብሰባው እንዲካፈሉ በተጋበዙ ጊዜ፤ የተሰበሰበዉን ሰው በማየት በሃይማኖት ምክንያት ሊሰበሰቡ የቻሉበት ምክንያት ምንድን ነው ብለው ጠየቁ::  የጉባኤው ታዳሚዎችም የተሰበሰብነው በንጉሱ ትዕዛዝ ነው አሏቸው። ቅዱስ ዲዮስቆሮስም፤ ይህ ጉባኤ ስለ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቢሆን ኖሮ እኔም ተቀምጨ ስለ እግዚአብሔር ፈጣሪነት፤ አዳኝነት፤ ምህረትና ርህራሄ በሰጠኝ አንደበቴ እናገር ነበር፤ ነገር ግን የዚህ ጉባኤ መሰብሰብ በንጉሱ ትዕዛዝ ከሆነ፤ የሰበሰበውን ጉባኤ ንጉሱ እንዳሻው ይምራ አላቸው።  ከዚህም በኋላ አንዱን ክርስቶስን ከተዋሕዶ በኋላ ሁለት ባሕርይ ሁለት ምክር የሚያደርግ የክህደት ቃል በውስጡ የተጻፈበትን የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ልዮን የላከውን ደብዳቤ ቅዱስ ድዮስቆሮስ ቀደደው። መንፈስ ቅዱስ እንዳቀበለው ቅዱስ ድዮስቆሮስ በጉባኤው ፊት እንዲህ በማለት ስለ አምላኩ መሰከረ።  ሰው እንደመሆኑ ወደ ሠርግ ቤት የጠሩት ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ እንደመሆኑ ውሃውን ወደ ወይን ጠጅ ያደረገው ከሃሊ ስለሆነ ሰውነቱና መለኮቱ በሥራው ሁሉ የማይለየው አንድ ነው። በተጨማሪም የ እስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ አባ ቄርሎስ ከተናገረው የአካላዊ ቃል ተዋሕዶ እንደ ነብስና ሥጋ

እንደ እሳትና ብረት ተዋሕዶ ነው ያለውን ቃል ምስክር አድርጎ፤ በማምጣትም አስረዳ። እኒህም ሁለቱ ጠባዮች ስለ ተዋሕዷቸው አንድ ከሆኑ እንዲሁም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ አንድ መሲሕ አንድ ጌታ አንድ ባሕርይ አንድ ምክር ነው እንጂ ወደ ሁለት አይከፍልም አላቸው።  ከዚያ ጉባኤ ከተሰበሰበው ውስጥ ማንም ለመከራከር የደፈር አልተገኘም፤ በውስጣቸውም በዚህ ጉባኤ ነገረ ክርስቶስን በማዛባት፤ እንግዳ በሆነ ኢክርስቶሳዊ ትምህርት በማስተማርና ክርስቲያኖችን ግራ በማጋባት የታወቀውና ስለሆነው ከሃዲ ንስጥሮስ በኤፌሶን ጉባኤ አስቀድሞ ተሰብስበው የነበሩ አሉ። ወደ ንጉስ መርቅያኖስና ወደ ሚስቱ ንግስት ብርክልያ ከእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ ከአባ ዲዮስቆሮስ በቀር ስለ ሃይማኖት ትእዛዛችሁን የሚቃወም የለም ብለው ነገር ሰሩበት።  ቅዱስ ድዮስቆሮስን ወደ ንጉሱ አቀረቡት።   እርሱም ጋር ታላላቅ ሊቃነ ጳጳሳት ኤጲስ ቆጶሳት ከጉባኤው የሆኑ ነበሩ።  ይህ የሃይማኖት ክርክር ከጠዋት እስከ ማታ ድረስ ሆነ።  ቅዱስ ድዮስቆሮስ ግን የከበረችውን ሃይማኖቱን አልለወጠም።  በዚህ የተነሳ ንጉሱና ንግስቲቱ ቅዱስ ድዮስቆሮስ በሃይማኖቱ መጽናቱን ከተመለከቱ በኋላ ተቆጡ፤ እንዲደበድቡትም አዘዙ።  ጭፍሮቹም እንደታዘዙት ቅዱስ ድዮስቆሮስን ደበደቡት፤ ጽሕሙንም ነጩ፤ ጥርሶቹንም ሰበሩ።  ቅዱስ ድዮስቆሮስም፤ የተላጨ ጽሕሙንና የተሰባበሩ ጥርሶቹን ሰብስቦ ወደ እስክንድርያ ላካቸው።  እነሆ የሃይማኖት ፍሬ ይህ ነው አላቸው።  በጉባኤው የተሰበሰቡ ኤጲስ ቆጶሳት በቅዱስ ድዮስቆሮስ ላይ የደረሰውን መከራ ባዩ ጊዜ እጅግ ፈሩ ደነገጡም።  በቅዱስ ድዮስቆሮስ ላይ የደረሰው እኛ ላይ እንዳይደርስ ከመናፍቁ ንጉስ ከመርቅያኖስ በሚያምንበት ሃይማኖት ተስማሙ።  በሲኦል ውስጥ ይቆርጡት ዘንድ ባለው ምላሳቸውም ለክርስቶስ ሁለት የተለያዩ ባሕርያት አሉት ብለው በንጉሱ መዝገብ ላይ በእጆቻቸው ጽፈው ፈረሙ። ቅዱስ ድዮስቆሮስም ተመልሶ ያን በውስጡ የጻፉበትን ደብዳቤ የመጡለት ዘንድ ወደ እሳቸው ላከ።  እነርሱም ላኩለት።  እነርሱ እንደጻፉ በውስጡ እርሱ የሚጽፍ መስሏቸዋልና።  ቅዱስ ድዮስቆሮስ  ግን አባቶቻችን ሐዋርያት ከአስተማሯት ከቀናች ሃይማኖት በኒቂያ የተሰበሰቡ፤ ሃይማኖታቸው የቀና፤ 318 ኤጲስ ቆጶሳት አባቶቻችን ከሰሩት ሕግ የሚወጣውን ሁሉ በደብዳቤው ጽፎ አወገዘ።
  መናፍቁ ንጉስም ተቆጥቶ ጋግራ ወደ ምትባል ደሴት እንዲወስዱት አዘዘ። ከዚያም እንደደረሰ ከ እርሱም ጋር ኤጲስ ቆጶስ አባ መቃርስ አብሮ ተሰደደ፤ ሌሎችም አራት መነኮሳት ከእነርሱ ጋር አብረው ሸሹ። እነዚህ 636 ኤጲስ ቆጶሳት ተቀምጠው በኬልቄዶን ለራሳቸው መመሪያ የሚሆናቸውን መመሪያ ሰሩ።  ቅዱስ ድዮስቆሮስንም ወደዚች ሃገር በወሰዱት ጊዜ ከዚያች ሃገር የሚኖረው ኤጲስ ቆጵስ ጭንቅ የሆነ መከራ ደረሰበት። ይህ ኤጲስ ቆጶስም ንስጥሮሳዊ ስለሆነ ታላቅ ጉስቁልናም አጎሳቆለው በእጆቹ ላይ ድንቆች ታላላቅ ተአምራቶችን እግዚአብሔር እስከገለጠ ድረስ።  ቅዱስ ድዮስቆሮስንም በዚያ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ሰገዱለት አከበሩት፤ እግዚአብሔርም የመረጣቸውን በቦታው ሁሉ ያከበራቸዋልና። አባ ዲዮስቆርስም አባ መቃርስን አንተ በ እስክንድርያ ሃገር የሰማዕትነት አክሊልን ትቀበል ዘንድ አለህ አለው።  ከዚህም በኋላ ከምዕመናን ነጋዴዎች ጋር ወደ እስክንድርያ ላከው።  ቅዱስ ዲዮስቆሮስም በአባ መቃርስ ላይ ትንቢት እንደተናገረ ገድሉን በዚያ ፈጸመ።  ቅዱስ ዲዮስቆሮስም በዚችው በደሴተ ጋግራ መልካም ተጋድሎውንና ቅዱስ የሆነ አገልግሎቱን እያገለገለ፤ ከዚህ አላፊ ከሆነችው ዓለም ወጥቶ የሃይማኖቱን ዋጋ፤ አክሊል ተቀብሎ ወደ ዘለዓለም እረፍት ገባ። እሁን እኛ ከእኒህ ቅዱስ አባት ምን እንማራለን? ምንም ይሁን ምን አንድ ክርስቲያን በተለያየ አይነት መልኩ በሃይማኖቱ የተነሳ ብዙ ፈተና ሊደርስበት ይችላል ነገር ግን ቅዱስ አባታችን እንዳስተማሩን እና እንደመከሩን በሃይማኖት ጸንቶ መኖር የክብርን አክሊል ያሰጠናልና በሃይማኖታችን ጸንተን እነ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ የተጓዙበትን የሃይማኖት መንገድ ለመጓዝ የሚያስችል ጽናት ከእግዚአብሔር እንድናገኝ ተግተን እንጸልይ ለዚህም የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር ይርዳን አሜን።
የቅዱስ ዲዮስቆሮስ በረከቱ ረድኤቱና ጸሎቱ አማላጅነቱ አይለየን አሜን

Post Bottom Ad