ከክፉ ጐልማስነት ምኞት ግን ሽሽ - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Friday, February 27, 2015

ከክፉ ጐልማስነት ምኞት ግን ሽሽ



(በዲያቆን ንጋቱ አበበ)

2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ ሰዎች በምዕራፍ  2፤22 ላይ እንዲህ የሚል መልእክትን እናነባለን፤ ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፤ በንጹህም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን፤ እምነትን፤ ፍቅርን እና ሰላምን አጥብቀህ ተከተል። ይህን ቃል የተናገረው ቀድሞ ክርስቲያኖችን በማሳደድ እንዲሁም በማስገደል፤ ለኦሪት ሕግ ቀናተኛ ነኝ በማለት ይናገር የነበረውና በመጨረሻም ክርስቲያኖችን ለመግደል፤ ለመጨፍጨፍ እና ለማሳደድ የፈቃድ ደብዳቤ ይዞ ወደ ደማስቆ በሚጓዝበት ወቅት ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾለት ወደ ክርስትና አምነት የተመለሰው ብርሃናተ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ነው። ክፉ፤ ጎልማሳነት፤ ምኞት የሚሉትን ቃላት ለይተን ብንመለከታቸው በክርስትና ሕይወታችን ላይ ለውጦችን ለማምጣት ግልጽ የሆነ መልእክት አዘል ወይም ተሎ የመገንዘብ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። ለምሳሌ ከታላቁ አባት ቅዱስ መቃሬዎስ ገድል ስንመለከት እንዲህ የሚል ታሪክ እናገኛለን።  ትምህርቱም ስለ ትህትና እንጂ ክፉ ነገር ወይም ምኞት
አይደለም።  አባ ወቅሪስ ድንዲህ አለ፦ አባ መቃርዮስን ልጎበኘው ሄድኩና በሕይወት ለመኖት የሚጠቅመኝን አንድ ቃል ንገረኝ አልኩት፡  እርሱም ብነግርህ ሰምተኸኝ ታደርገዋለህ?  አለኝ።  እኔም አምነቴና ፍቅሬ ካንተ የተሰወሩ አይደሉም አልኩት።  አባ መቃርዮስም እንዲህ አለኝ።  በ እውነት እኔ የምግባር ሕይወት ይጎድለኛል።  አንተ ግን ጥሩ ነህ ነገር ግን የዚህ ዓለም ትምህርት የሚያመጣውን ክብርና ዝና አውልቀህ ብትጥልና የቀራጩን ትህትና ብትላበስ በሕይወት ትኖራለህ።  እነዚህን ነገሮች በተነገረኝ ጊዜ ሃሳቦቸ ሁሉ በንነው ጠፉ።  ይቅርታውን በጠየኩትም ጊዜ በላዬ ላይ ከጸለየልኝ በኋላ አሰናበተኝ።  የውስጤ ሃሳቦች ሁሉ ከ እግዚአብሔር ሰው ከአባ መቃርዮስ የተሰወሩ እንዳልሆኑ ተረዳሁ።  ወደ እርሱ በሄድኩ ጊዜም ሁሉ እንዳዳምጠው ከሚያደርገኝ ከጸጋው የተነሳ እርዳለሁ ለ እኔም ትህትናን የምለማመድበት አጋጣሚ ነበር። በማለት ስለ ትህትና እና ፍቅር ገድላቸው ያስተምረናል።  ቅዱስ ጳውሎስ ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ ማለቱ ትህትናን እና ፍቅርን አዘውትረን እንድንከተል ጽፎልናል።



ጎልማሳነት፦ የጎልማሳነት እድሜ ከሃያዎቹ እስከ አርባዎቹ የሚደርስ የእድሜ ዘመን ነው። በዚህ እድሜ ውስጥ ብዙ የእሳትነት ባህርይ የሚንጸባረቅባቸው በመሆኑ፤ የምንሰራቸው ስራዎች በአጠቃላይ በአስተሳሰብ፤ በማህበራዊ ኑሮ፤ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የችኩልነት ባሕርይ የሚታይበት በመሆኑ፤ አብዛኛውን ጊዜ ለሃጢአት ስራዎች እንጋለጣለን።  ለዚህ ሃጢአት ስራ እንዳንጋለጥ ቅዱስ ጳውሎስ የጻፈልንን መልእክት ማንበብ እና መረዳት ይገባል።


ምኞት፦ የሚገባ እና የማይገባ ምኞት አለ።  የሰው ልጅ በማይገባ ምኞት ከተጠለፈ የሰይጣን ፈተና ይበዛበታል። አወዳደቁም በስጋም በነፍሱም ይከፋል።  መጨረሻውም አያምርም ምክንያቱም የማይረባ ምኞቱን ለመፈጸም በሚጥርበት ወቅት በኃጢአት እየተዘፈቀ መሆኑን መረዳት አለበት።  በመጽሐፍ እንዲህ የሚል መልእክት ተጽፏል ኃጢአትም ከአደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች። ያዕ 1፤5 በአንድ ወቅት አንድ አረጋዊ ከአንድ አባት ጋር ሆነው አባታችን አባ መቃርዮስን እንደጎበኙት ተነገረ።  እነርሱም አባታችን ሆይ፤ እንደ አንድ ሰው ሆነን መኖር እንፈልጋለን አሉት። እርሱም አረጋዊውን እንዲህ አለው። “ መጀመሪያ እንደ እረኛ ሁን” ክፉ ትል ተሸካሚ (አስተላላፊ) የሆነች ወፍ በበጎች መካከል ትሎችን ብትዘራባቸው ትሎችን እስከሚገድላቸው ድረስ ለታመመችው በግ መድሃኒት ይሰጣታል። አንድ በግ ተላላፊ የሆነ በሽታ የሚዘራ ከሆነ ግን በሽታውን እስከሚያስወግደው ድረስ መድሃኒት ይጠቀማል። አረጋዊውም የዚህን አባባል ትርጉም ንገረኝ አለው። “ትል የሚዘራው ወፍ እንደ ዲያቢሎስ ነው። በጉ ደግሞ ከአንተ ጋር እንደሚኖረው ወንድም ያለ ነው። ትሎቹ ደግሞ በነፍስ የሚኖሩና በልብ የሚራቡ የአጋንንት ፍትወታትና ክፉ ምኞቶች ናቸው። ትሎች በሰውነት ቁስል ላይ እንደሚኖሩት ማለት ነው። በሽታውን እንደሚያስወግደው መድሃኒት ደግሞ በመንፈስ ማደግ ትህምርትና መድሃኒት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ትምህርት ነው።  ነፍስን የሚያንጿት ነገሮች እነዚህ ናቸው። አጋንንት በእኛ ላይ ክፉ ከሚያሰሯቸው ጠላቶቻችን ከእኩያት ፍትወታትና ከክፋቶች ሁሉ የሚያጠሯት እነዚህ ናቸው። ያን አባት እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ ልጄ ሆይ በ እግዚአብሔር ፊት የተወደደ መስዋእትና መባዕ አድርጎ እስኪያቀርበው ድረስ አባቱን እንደታዘዘው እንደ ይስሐቅ ሁን።  እርሱ ለአባቱ በመታዘዙ በቤተክርስቲያን መዝገብ ውስጥ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ተጽፏልና። የአባታችን የአባ መቃርዮስ በረከታቸው ይደርብንና ይህን የመሰለ ምክር ተቀብለን ከክፉ ምኞት እራሳችንን ማዳን አለብን። ለዚህም የቅዱስ መቃርዮስ ምልጃ እና ተራዳኢነት አይለየን።

ክፍ ነገር፦ የመልካም ነገር ተቃራኒው ክፉ ነገር ነው። በግብር፤ በአንደበት፤ በሃሳብ በተለያዩ የክፉ ስራ ድርጊት የሚፈጸም ሁሉ በሰውም፤ በእግዚአብሔርም የማይወደድ፤ የተጠላ፤ የሚያሳዝን  ነገር ሁሉ ክፉ ነገር ይባላል። በአንድ ወቅት አባ ወቅሪስ ከሌሎች አባቶች ጋር አብሮት ከእርሱ ጋር ተቀምጦ ሳለ አባ መቃርዮስን ሰይጣን በወንድሞች ላይ ይወረውራቸውና፤ ይፈትንባቸው ዘንድ እነዚህን ሁሉ ክፉ ሃሳቦች እንዴት ሊያገኝ ቻለ? ብሎ ጠየቀው።  አባ መቃርዮስም እንዲህ አለው።  በምድጃ እሳት የሚያነድ ሰው በእጁ ብዙ ማቀጣጠያ እንጨት ይይዛል፤ ያንንም ወደ ምድጃው  ከመጣል አያመነታም፤ ወደ ኋላም አይልም። ዲያብሎስም እንደዚህ ነው።  እሳቶችን ይለኩሳል፤ ያቀጣጥላል፤ ከዚያም ወደ እያንዳንዱ ሰው ልቦና ማንኛውንም አይነት የክፉ አቀጣጣይ የሆኑ ነገሮችን ማለትም ርኩሰቶችን ከመጣልና የተለኮሰውን እሳት አብዝቶ እንዲነድ ለማድረግ ወደ ኋላ አይልም።  ውኃ የእሳትን ኃይል እንደሚያጠፋውና አሽናፊው እንደሆነ እናያለን።  እኛን የሚረዳንና የሚጠብቀን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሃይልና ድል የማይነሳው የመስቀሉ ሃይልም እንዲሁ ነው። ድካማችንን ከእርሱ እግር ስር ብንጥል የዲያብሎስ ክፉ ሃሳቦች ከነቅርንጫፎቻቸው ከእኛ ውስጥ ይጠፋሉ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ልባችን በሰማያዊ እሳት በመንፈስ እንዲቃጠልና በሐሴት እንዲሞላ ያደርገዋል። ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ ከክፉ ጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ ያለበትን ምክንያት በቀላሉ ልንረዳ እንችላለን።

Post Bottom Ad