ነገረ ማርያም ክፍል ሰባት - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Friday, November 7, 2014

ነገረ ማርያም ክፍል ሰባት

 በቀሲስ ደጄኔ ሽፈራው
፩፡- ወላዲተ ቃል፤
« እግዚአብሔር ተወለደ፤»
ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ፡- ወንጌሉን መጻፍ የጀመረው በምሥጢረ ሥላሴ ነው። «በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልምበእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ (አካላዊ ቃል፡- በአብ ህልው ሆኖ፥ ከአብ፡- በዘመንም በሥልጣንም ተካክሎ ነበረ)፤ በማለት አብን፥ «ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፤» በማለት ወልድን፥ «ይህም በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ (በመንፈስ ቅዱስ ህልው ሆኖ፥ ከመንፈስ ቅዱስ በዘመንም በሥልጣንም ተካክሎ ነበረ)፤ በማለት መንፈስ ቅዱስን አንሥቷል። ዮሐ ፩፥፩። ስለ ሦስቱ አካላትም፦ ሦስት ጊዜ እግዚአብሔር ብሏል። ይኸንን በተመለከተ ቅዱሳን ሐዋርያትን የመሰለ፥ የተመሰገነ፥ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አትናቴዎስ፡- «የአካላዊ ቃል አባቱእግዚአብሔር አብ በተለየ አካሉ አንድ ነው፥ የአብ ልጁ ቃሉ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ወልድም በተለየ አካሉ አንድ ነው፥ የአብ የወልድ እስትንፋሳቸው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም በተለየ አካሉ አንድ ነው።» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፴፩፥፳፩) ቅዱስ ዳዊትም፡- «የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች፤» በማለት አብን፥ «የእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ አደረገችኝ፤» በማለት ወልድን፥ «የእግዚአብሔር ቀኝ ኃይልን አደረገች፤» በማለት መንፈስ ቅዱስን አንሥቷል። መዝ፡- ፻፲፯፥፲፮።
ቅዱስ አትናቴዎስ ደግሞ፡- «አብ አምላክ ነው፥ ወልድምአምላክ ነው፥ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው፤ ነገር ግንሦስት አማልክት አይባሉም፥ አንድ ነው እንጂ።» ብሏል።(ሃይ አበው ፳፭፥ ፬)። ሥላሴ፡- በአካላት ፍጹም ሦስትሆነው፦ «አብ፥ ወልድ፥ መንፈስ ቅዱስ» ተብለው በሦስትስም ጸንተው ቢኖሩም፥ በግብርም አብ ወላዲ፥ ወልድተወላዲ፥ መንፈስ ቅዱስ ሰራጺ፥ ተብለው ቢጠሩ ም ፥በመለኮት፣ በባህርይ፣ በሥልጣን፣ በፈቃድ፣ በህልውና፥አንድ በመሆናቸው፡- አንድ አምላክ፥ አንድእግዚአብሔር፥አንድ ፈጣ ሪ ፥ አንድ ጌታ ተብለውይታመናሉ። ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ፡- « እግዚአብሔርንበጌትነት ከዘመን አስቀድሞ የነበረ፥ ትክክል በሚሆኑበሦስቱ አካላት እንዳለ እናውቀዋለን፤ ከዘመን አስቀድመውየነበሩ፥ ዘመንን አሳልፈው የሚኖሩ ናቸውና፤ በመለኮት አንድናቸውና።» ብሏል። (ሃይ አበው ፺፥፲)። የእስክንድርያው ሊቀጳጳሳት ፊላታዎስም፡- « በስም ሦስት እንደሆኑ፥ በአካል፣በገጽ፣ ሦስ ት ናቸው፤ በአንድ መለኮት አንድነትም አንድናቸው፤» ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፻፭፥፪)
፩፥፩፡- «ቃል»፤
ቅዱስ ዮሐንስ፡- «ቃል»፡- ያለው ወልድን ነው፤ ምክንያቱም፦ በምሥጢረ ሥላሴ፡- አብ ልብ፥ ወልድ ቃል፥ መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ ናቸውና። አብ የራሱንም ሆኖ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ልባቸው ነው፥ ወልድ የራሱንም ሆኖ የአብ የመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው፥ መንፈስ ቅዱስም የራሱንም ሆኖ የአብ የወልድ እስትንፋሳቸው ነው። አቡሊድስ ዘሮሜ «አብኒ ልቡናሆሙ ለወልድ ወለመንፈስ ቅዱስ፥ ወልድኒ ቃሎሙ ለአብ ወለመንፈስ ቅዱስ፥ መንፈስ ቅዱስኒ ሕይወቶሙ ለአብ ወለወልድ፤» ብሏል። አካላዊ ቃል ሲናገር፡- አብ መንፈስ ቅዱስ ቢሰሙት እንጂ የፍጡራን ጆሮ አይሰማውም። በእልመስጦአጊያ ላይ፡- «ወደ ሥጋዊ ጆሮ የማይገባ ነው፤ በዚህ ዓለም ባለ፥ በምድርም በሚናገር ቃል አይደለም። ከአንተ ተገኝታ ፍጥረት ሁሉ በተፈጠረባት ቃል ነው እንጂ፥ በአንተና በእኔ ህልውና ባለ መንፈስ ቅዱስ ህልው ሆኖ የሚናገር ይህ ቃል ነው።» የሚል ተጽፏል። ይህም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ያመሰገነው ምስጋና ነው። «አባት ሆይ! አመሰግንሃለሁ፥ ብሎ ሥግው ቃል አመሰገነ። የማመሰግንህም በእሊህ ሥጋውያን ከናፍር አይደለም፤ እውነትና ሐሰት በሚናገሩበት በዚች አንደበት አይደለም። በዚህ ቃል ነው እንጂ፤» ይላል። (ሃይ አበው፡- ፭፥፩፤ እልመስጦአግያ ጥምር ቃል ነው፥በቁሙ ሲተረጐም፡- ቅድስት ሃይማኖት ማለት ነው)።
ልበ አምላክ የተባለ ቅዱስ ዳዊት፡- በመዝሙሩ፡- «ሣህሉ ለእግዚአብሔር መልዓ ምድረ፥ ወበቃለ እግዚአብሔር ፀንዓ ሰማያት፥ ወእምእስትንፋሰ አፉሁ ኲሉ ኃይሎሙ፤ የእግዚአብሔር ይቅርታው ምድርን ሞላ፥ በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ፥ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ፤» ብሏል። መዝ ፴፪፥፭። በዚህም፡- የአብን፡- ልብነት፥ የወልድን፡-ቃልነት፥ የመንፈስ ቅዱስንም፡- እስትንፋስነት፥ መስክሯል። ምናልባት፡- «የእግዚአብሔር ይቅርታ አለ፥ እንጂ፡- መቼ ልብን አነሣ?» እንል ይሆናል። ነገር ግን፡- የይቅርታ ምንጩ፥ መገኛው፥ ልብ መሆኑን ካስተዋልን፥ መልሱን እዚያው ላይ እናገኛለን። በሌላ በኲል ደግሞ ልብ፥ ቃልና እስትንፋስ የማይለያዩ መሆናቸውን ማስተዋል ይገባል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- ከትንቢት መጽሐፍ ጠቅሶ፡- «የጌታን ልብ ያወቀው ማነው?» ያለው አብን ነው። ሮሜ ፲፩፥፴፬፣ ኢሳ ፵፥፲፫። እንደተባለውም፡- በአብ ልብነት የሚታሰበውን፡- በህልውና ከእርሱ ጋር አንድ ከሆኑ፥ ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ በስተቀር፥ ከፍጡር ወገን የሚያውቀው ማንም የለም። ጌታ በወንጌል፡- «ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፥ አብንም ከወልድ በቀር፡- ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅደው በቀር የሚያውቀው የለም፤» ያለው ለዚህ ነው። ማቴ ፲፩፥፳፯።
አብ፡- ልብ፥ ወልድ፡- ቃል፥ መንፈስ ቅዱስ፡- እስትንፋስ፥ ስለተባሉ፡- ወይም በልብ፥ በቃል፥ በእስትንፋስ፥ ስለተመሰሉ፡- ለአብ የተለየ ቃልና እስትንፋስ፥ ለወልድ የተለየ ልብና እስትንፋስ፥ ለመንፈስ ቅዱስም የተለየ ልብና ቃል አላቸው ማለት አይደለም። እርስ በርሳቸው ህልዋን ናቸው፤ (በአኗኗር አንድ ናቸው)፤ አብ በልቡናነት፡- በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነው፤ (አለ)፤ ወልድ በቃልነት፡- በአብ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነው፤ (አለ)፤ መንፈስ ቅዱስም በእስትንፋስነት፡- በአብ በወልድ ህልው ነው (አለ)። ጌታ በወንጌል፡- «እኔን ያየ አብን አየ፤ እንዴት አብን አሳየን ትላለህ? እኔ በአብ አንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁ ይህ ቃልም ከራሴ የተናገርኩት አይደለም፤ በእኔ ያለ አብ እርሱ ይህን ሥራ ይሠራዋል፥ (በእኔ ህልው በሆነ በአብ ልብነት ይታሰባል) እንጂ። እኔ በአብ እንዳለሁ፥ አብም በእኔ እንዳለ እመኑ፤ ያለዚያም ስለ ሥራዬ እመኑኝ።» በማለት ለፊልጶስ የመለሰለት ለዚህ ነው። ዮሐ ፲፬፥፱። ይኽንን በተመለከተም ፊላታዎስ ዘእስክንድርያ፡- «አብ፡- በወልድ በመንፈስ ቅዱስ አለ፥ ወልድም፡- በአብ በመንፈስ ቅዱስ አለ፥ መንፈስ ቅዱስም፥ በአብና በወልድ አለ፤» ብሏል። ስለዚህ ሥላሴ፡- እንደ አንድ ልብ አሳቢ ሆነው ያስባሉ፥ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው ይናገራሉ፥ እንደ አንድ እስትንፋስ ሕያው ሆነው ይፈጽማሉ እንጂ መለያየት የለባቸውም። የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ኪራኮስ፡- «አብ፡- ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ፡- ራሱ ብቻውን የሚሠራ አይደለም፤ እንዲሁ ወልድም ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ ራሱ ብቻውን የሚሠራ አይደለም፤ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስም፡- ከአብ ከወልድ ተለይቶ፡- ራሱ ብቻውን የሚሠራ አይደለም፤ አብ የሚሻውን፡- ወልድ መንፈስ ቅዱስ ይሠሩታል፡- እንጂ፤ ሥራቸውም እንድ ነው፥ባሕርያቸው አንድ ነውና፤» ብሏል። (ሃይ አበው ፺፩፥፫)።
፩፥፪፦ ቃል አካላዊ ነው፤
በጽርዕ ቋንቋ፡- አአትሪኮን፥ ብርፎሪኮን፥ አተርግዋን፥ የሚባሉ ቃላት አሉ። እነዚህም፡- አካል የሌላቸው ዝርዋን ናቸው። የመላእክት፥ የሰው እና የእንስሳት ቃል አካል የለውም፥ ዝርው ነው። ዝርው ማለት፡- የተዘራ፥ የተበተነ፥ ብትን፥ ብትንትን፥ አንድነት የሌለው ማለት ነው። በምሳሌያዊ አነጋገር ነፋስ የበተነው አመድ ማለት ነው። የወልድ ቃልነት ግን እንዲህ አይደለም፥ አካላዊ ነው። ይኽንን በተመለከተ፦ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘቂሣርያ፦ «ይህንንም ቃል የተባለውን ስም፦ አተርግዋን ፥ ብርፎሪኮን ፥ አአትሪኮን ፥ ከተባሉት ከሦስቱ ዓይነት ቃላትና ከሦስቱ ግብራት ለይተን እናውቃለን። እሊህ እግዚአብሔር የፈጠራቸው ቃላት ናቸው፤ በመጽሐፍ እንደተጻፈ በአካል ያሉ አይደሉም። አተርግዋን (የመላእክት ቃል ነው)፤ በአካላዊነት ያለ አይደደለም፤ ብርፎሪኮንም ነቢያት ከእግዚአብሔር ዘንድ የሰሙት ቃል ነው፤ ይኸውም የትንቢት ቃል ነው፤ በአካል ተለይቶ ያለ አይደለም፤ አአትሪኮን በአየር የሚፈስሰው ቃላችን ነው፤ ከእነርሱም ድምፅ ይገኛል፤ በአካላዊነት ያለ አይደለም። ዘፍ ፲፩፥፯ ፣ ፩ኛ ቆሮ ፲፫፥፲ ፣ዕብ ፩፥፩ ፣ ፬፥፯። የእግዚአብሔር ቃል ግን የማይለወጥ ረቂቅ ከሆነ ከአብ ባሕርይ ተገኝቶ በአካላዊነት ያለ ነው፤ ይኸውም ከአብ ጋር፦ በቅድምና የነበረ፥ ከዘመን የሚቀድም ቀዳማዊ ነው፤ ከእርሱም አይለይም፤ ልደቱ ከእርሱ አያልቅም፤ ያለመለየት በጊዜው ሁሉ ከእርሱ ጋር ከዘመን አስቀድሞ የነበረው ነው እንጂ። ዳን ፯፥፱-፲፬ ፣ ራእ ፩፥፲፫-፲፰። ይህን ቃል፦ አካል ፥ባህርይ የላቸውም፥ ብለን እንደተናገርናቸው ቃላት፦ አካል ባሕርይ የሌለው አታስመስሉት፤ እንደ አብ እንደ መንፈስ ቅዱስ በአካል በገጽ ፍጹም ነው እንጂ፤ ብሏል። (ሃይ፡ አበው ፲፫፥፳፪)። በምሥጢረ ሥላሴ፡- ሦስት አካላት አሉ፤ ለአብ ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ ፍጹም አካል አለው፤ ለወልድ፡- ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ ፍጹም አካል አለው፤ ለመንፈስ ቅዱስም፡- ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክ ፍጹም አካል አለው፤ ብለን ካመንን በኋላ፡- ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ (ቃል) አካል የለውም፥ ማለት አንችልም። ቅዱስ ዳዊት፡- ስለ ሦስቱ አካላት፡- «ፊትህን (ገጽህን) ፈለግሁ፤» በማለት አብን፥ «ፊትህን (ገጽህን) እሻለሁ፤» በማለት ወልድን፥ «ፊትህን(ገጽህን) ከእኔ አትመልስ፤» በማለት መንፈስ ቅዱስን አንሥቷል። መዝ ፳፮፥፰። እንግዲህ ፊት (ገጽ) ካለ መልክም አካልም መኖሩ ግድ ነው።
፩፥፫፦ ለምን? ቃል ብሎ ጀመረ፤
ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ፡- «በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤» በማለት ወንጌሉን መጻፍ የጀመረው ስለ ሦስት ነገር ነው። ፩ኛ፦ ሥላሴ በህልውና (በአኗኗር) አንድ መሆናቸውን ለመግለጥ ነው። ምክንያቱም፡- ከልብ ከእስትንፋስ ተለይቶ ለብቻው በአፍአ (በውጭ) የሚገኝ ቃል ስለሌለ ነው። ፪ኛ፡-ሥላሴ በዘመን መቀዳዳም እንደሌለባቸው ለመግለጥ ነው። ምክንያቱም፡- ልብ፥ እስትንፋስ ቀድመውት ወደኋላ የሚገኝ ቃል ስለሌለ ነው። ይኸንን በተመለከተ ሠለስቱ ምዕት፡- «አብ፡- ከወልድ ተለይቶ የኖረበት ዘመን የለም፤ ወልድም ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ የኖረበት ዘመን የለም፤ መንፈስ ቅዱስም ከአብ ከወልድ ተለይቶ የኖረበት ዘመን የለም፤ --- ጥንት የሌለው ቀዳማዊ ልጅ ያለው እግዚአብሔር አብ ብቻ ነው።--- አብ ከዘመን በኋላ አልወለደውም፥ እርሱ ቀዳማዊ ወልድ፡- ከአብ ጋር በቅድምና የነበረ ነው እንጂ።--- እንደ አብም ሁሉን የፈጠረ ነው። እንዲሁ መንፈስ ቅዱስም፡- ከአብ ከወልድ ጋር በቅድምና የነበረ ቀዳማዊ ነው፤ በሥራውም ከአብ ከወልድ ጋር አንድ ነው፤» ብለዋል። (ሃይ አበው ፲፱፥፮)። ፫ኛ፡- የቃልን ፈጣሪነት ለመግለጥ ነው። ምክንያቱም፡- እግዚአብሔር ዓለማትን የፈጠረው በቃሉ ነውና። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- «ዓለም በእግዚአብሔር ቃል እንደተፈጠረ፥ የሚታየውም ነገር ከማይታየው እንደሆነ በእምነት እናውቃለን።» ያለው ለዚህ ነው። ዕብ ፲፬፥፫፣ ዘፍ ፩፥፩። ቅዱስ ዳዊትም፡- «በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ፤ (ባለማለፍ ጸንተው የሚኖሩ፥ ኅልፈት የሌለባቸው ሰባቱ ሰማያት ተፈጠሩ)፤» ብሏል። መዝ ፴፪፥፮። ቅዱስ ዮሐንስም በበኵሉ፡- የቃልን ቀዳማዊነት፥ እግዚአብሔርነት፥ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በህልውና (በአኗኗር) አንድ መሆን፥ ከተናገረ በኋላ፡- «ወኵሉ ቦቱ ኮነ፤ ወዘእንበሌሁሰ አልቦ ዘኮነ ወኢምንትኒ እምዘኮነ፤ ሁሉም በእርሱ ሆነ፤ (በእርሱ ህልውና በእርሱ አንድነት ተፈጠረ)፤ ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ ምንም የሆነ የለም፤ (ከተፈጠረው ፍጥረት ግን ያለ እርሱ ህልውና ማለትም እርሱ ሳይኖር ምንም ምን የተፈጠረ የለም፤» ብሏል። ዮሐ ፩፥፫።
፩፥፬፦ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤
የብሉይ ኪዳን ዘመን የጨለማ ዘመን ነበረ። ዘመኑን ጨለማ ያሰኘው፡- በአዳም ኃጢአት ምክንያት፡- በሰው ልጅ ላይ የወደቀው የሥጋና የነፍስ ርግማን ነው። ይህም ርግማን በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስን፥ በርደተ መቃብር (ወደ መቃብር በመውረድ) ላይ ርደተ ገሃነምን (ወደ ገሃነመ እሳት መውረድን) ያመጣ ነው። በመሆኑም ለሰው ዘር በጠቅላላ መርገመ ሥጋን እና መርገመ ነፍስን አስወግዶ፦ ይኸንን ጨለማ የሚገፍ ብርሃን ያስፈልገው ነበረ፤ ይህም ብርሃን ያለጥርጥር እግዚአብሔር ነበረ። ቅዱስ ጳውሎስ፡- «ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤» ብሏል። ፩ኛ ጢሞ ፮፥፲፮።
ቅዱስ ዮሐንስ፡- ስለ ራሱ ማንነት፡- «ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክርነት መጣ፤» ካለ በኋላ፡- «ለሰው ሁሉ የሚያበራው (ዕውቀትን የሚገልጠው)እውነተኛው ብርሃንስ ወደ ዓለም የመጣው ነው። በዓለም ነበረ፤ (ይኸውም እንደ እንግዳ ደራሽ፥ እንደ ውኃ ፈሳሽ፥ በዓለሙ የሌለ ሆኖ አይደለም፤ ቀዳማዊ ነው፥ ዓለሙን ያስገኘ ነው፥ (በዓለሙ ውስጥ ከዓለሙም ውጭ ያለ ምሉዕ ነው)፤ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፤ (የሚታየውና የሚያልፈው ዓለም፥ የማይታየውና የማያልፈውም ዓለም፥ ሁሉም በእርሱ ተፈጠረ)፤ ዓለሙ ግን አላወቀውም። (በወዲያኛው ዓለም ቅዱሳን መላእክት፡- የባህርይ አምላክ መሆኑን አውቀው የሚያመሰግኑትን፥ በወዲህኛው ዓለም የሚኖሩ ደቂቀ አዳም ማለትም የአዳም ልጆች አላወቁትም)። ወደ ወገኖቹ መጣ፤ (ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር ብሎ ወደፈጠራቸው ወደ ወገኖቹ መጣ፤ አንድም የበኵር ልጆቼ ወዳላቸው ወደ ወገኖቹ ወደ እስራኤል መጣ)፤ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም። (የባህርይ አምላክ፥ ፈጣሪ፥ እግዚአብሔር፥ ዕሩይ ምስለ አብ ወመንፈስ ቅዱስ ብለው አላመኑበትም)፥ ብሏል። ከዚህም አያይዞ፡-ቢያምኑበት ኖሮ ምን ይጠቀሙ እንደነበረ ሲናገር፡- «ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው። (በገቢረ ኃጢአት፥ በአምልኮ ጣዖት ያሳደፉትን፤ በተፈጥሮ አግኝተውት የነበረውን ነፃነት አደሰላቸው)። እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ፡- (በጥምቀተ ክርስትና፡- ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ተወልደው ልጅነትን አገኙ እንጂ፡-) ከሥጋዊና ከደማዊ ግብር፥ ወይም ከወንድና ከሴት ፈቃድ አልተወለዱም፤» ብሏል።
ነቢዩ ኢሳይያስ፡- « በጨለማ የሄደ ሕዝብ (አምስት ሽህ አምስት መቶ ዘመን በሲኦል የኖሩ ነፍሳት) ብርሃንን አዩ፥ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ (በሞተ ሥጋ በሞተ ነፍስ ለተያዙ ሁሉ) ብርሃን ወጣላቸው፥ በማለት ትንቢት የተናገረው ለዚህ ነበር። ኢሳ ፱፥፪፣ ማቴ ፬፥፲፬። ጌታም ራሱ በወንጌሉ፡- «እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም፤» ብሏል። ዮሐ ፰፥፲፪፣ ፱፥፭።
፪፦ ቃል ሥጋ ሆነ፤ ዮሐ ፩፥፲፬
ቅዱስ ዮሐንስ፦ «ከእግዚአብሔር ተወለዱ፤» በማለት፦ ግዙፋኑ ከረቂቁ ከእግዚአብሔር በመንፈስ በረቂቅ ልደት እንሚወለዱ የተናገረው ያለምክንያት አይደለም። ሰው ከእግዚአብሔር በመንፈስ መንፈሳዊ ልደት ተወልዶ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሚሆን ሁሉ፦ ረቂቁ ከግዙፉ ማለትም፦ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ ግብር ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ የሰው ልጅ እንደሆነ ለመናገር ፈልጎ ነው። በመሆኑም፦ « ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤» ያላቸው፦ እንደቀድሞው ማለትም፦ እንደ ብሉይ ኪዳን ዘመን በረድኤት ፥ በምሳሌ እንዳይመስላቸው ሲል፦ « ያ በቅድምና ነበረ ፥ በአብ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነው፥ እግዚአብሔር ነው ፥ ወደ ዓለም የመጣ ብርሃን ነው፥» ያልኳችሁ አካላዊ ቃል ሥጋ ሆነ ፤ በእኛም አደረ፤ ( በኲነት በመሆን በተዋሕዶ አደረ) ፤» ብሏቸዋል። «ሆነ፤» የሚለውን ይዘው ፦ «ተለወጠ፤» እንዳይሉበትም «አደረ፤» ብሏል። «አደረ፤» የሚለውንም ይዘው « ኅድረት ( መለኮት ሥጋንና ነፍስን አልተዋሃደም) ፤ » እንዳይሉበት «ሆነ፤» ብሎባቸዋል። «ኮነ፤» እና «ኀደረ፤» እንደ አለቃና እንደ ጠበቃ ይጠባበቃሉ። «ኮነ፤» የሚለው ብቻ ተይዞ፦ «ተለወጠ፤» እንዳይባል፦ «ኀደረ፤» ይጠብቀዋል። «ኀደረ፤» የሚለውም ተይዞ፦ «ኅድረት፤» እንዳይባል፦ «ኮነ፤» ይጠብቀዋል።
፪፥፩፦ ቃል ከእመቤታችን የነሣው ነፍስንም ጭምር ነው፤«ቃል ሥጋ ሆነ፤» የሚለውን፦ ንባቡን ብቻ በመያዝ፦ ነፍስን አልነሣም የሚሉ አሉ። ይህም በተዘዋዋሪ ሳይሆን ፥ ፊት ለፊት ከእውነት ጋር መጋጨት ፣ መጣላት ነው። እውነት ደግሞ እግዚአብሔር ነው፤ የነቢዩ የሳሙኤል እናት ሐና ፦ « ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቅቃሉ፤ በሰማይም ያንጐዳጉድባቸዋል፤ እግዚአብሔር እስከ ምድር ዳርቻ ይፈርዳል፤» ብላለች። ፩ኛ ሳሙ ፪፥፲። ነፍስ ከሥጋ ጋር በተዋሕዶ ያለች በመሆኗ፦ አካላዊ ቃል በማኀጸነ ድንግል ማርያም አድሮ፦ በመንፈስ ቅዱስ ግብር ሰው በሆነ ጊዜ ፦ ከሥጋዋ ሥጋ በነሣበት ቅጽበት ፥ ከሥጋ ጋር በተዋሕዶ ያለችን ነፍስም ነሥቷል። ደግሞም ሰው ማለት የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ ነው። ሥጋ ብቻውን ወይም ነፍስ ብቻዋን ሰው አይባሉም። ስለዚህ አካላዊ ቃል ከእመቤታችን የነሣው ሥጋን ብቻ ቢሆን ኖሮ « አምላክ ሰው ሆነ፤» አይባልም ነበር። እርሱም፦ «የሰው ልጅ፤» ተብሎ አይጠራም ነበር። ነገር ግን ሰው የሚያሰኘውን ሥጋን ነፍስንም ከእመቤታችን ነሥቶ በተዋሕዶ ሰው በመሆኑ « የሰው ልጅ፤» ተብሏል።
- «የሰውን ልጅ ማን እንደሆነ ይሉታል?» ማቴ ፲፮ ፥፲፫ ።
- «የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤» ማቴ ፲፮ ፥፳፯።
- «የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ፥ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክት ይመጣሉ፤» ማቴ ፳፭ ፥ ፴፩።
- «የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደተጻፈ ይሄዳል፥ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤» ማቴ ፳፮፥፳፬።
- «ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ፤» ማቴ ፳፮ ፥፷፬።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በምድረ ግብፅ ስደት እያለች ፦ የእግዚአብሔር መልአክ፦ ለአረጋዊው ፥ለዘመዷ ፥ ለጠባቂዋ ፥ ለጻድቁ ፥ ለዮሴፍ ተገልጦ፦ «የሕፃኑን ነፍሰ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ ፥ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እሥራኤል ሀገር ሂድ፤» ብሎታል። ማቴ ፪፥፳። ቃል፦ ነፍስንም ጭምር ባይነሣ ኖሮ ፦ መልአኩ፦ የሕፃኑን(የኢየሱስን) ነፍሰ፤ » አይልም ነበር። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጌቴሴማኒ አጸድ በጸለየ ጊዜ፦ «ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ አዘነች፤» ብሏል። ማቴ ፳፮፥፴፰። ቅዱስ አግናጥዮስ፦ ይኽንን ይዞ፦ «ነፍስን አልነሣም የሚል ፥ እንዲህም የሚክድ ሰው ፥ ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ አዘነች ፥ ያለውን የጌታችን የኢየሱስን ቃል ሰምቶ ፥ እንግዲህ ይፈር፤» ብሏል። (ሃይ አበው ፲፩፥፲፮)። ጌታችን የሞቱንና የትንሣኤውን ነገር ባስተማረበትም ወቅት፦ «ነፍሴንም ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና፤» በማለት ተናግሯል። ዮሐ ፲፥፲፯። ድኅነተ ዓለምን ፦ በመልዕልተ መስቀል በፈጸመ ጊዜ ደግሞ ፦ «ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ተወ፤» ይላል። ማቴ ፳፯፥፶። ጌታችን፦ ስለእኛ አሳልፎ የሰጠው ይህ ነፍስ ከእመቤታችን የነሣው ነው። ማር ፲፭፥፴፯፣ ዮሐ ፲፱፥፴። በሉቃስ ወንጌል ላይ ደግሞ፦ « አባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ አለ፥ ይህን ብሎ ነፍሱን ሰጠ።» ይላል። ሉቃ ፳፫፥፵፮። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፦ ቃል ሥጋንም ነፍስንም እንደነሣ፦ በተናገረበት አንቀጽ፦ «ነሥአ እምድንግል ሥጋ ዘቦቱ ነፍስ ነባቢት ወለባዊት፤ ከድንግል የምትናገር ፥ የምታውቅ ነፍስ ያለችው ሥጋን ነሣ፤» ብሏል። (ሃይ አበው ፷፮፥፴)። ቅዱስ ቄርሎስ ደግሞ፦ «በኋላ ዘመንም ገብርኤል መልአክ ፥ ወደ ንጽሕት ድንግል ማርያም በተላከ ጊዜ፦ ጸጋን ክብርን የተመላሽ ድንግል ሆይ ፥ እግዚአብሔር ከሥጋሽ ሥጋን ፣ ከነፍስሽ ነፍስን ነሥቶ ሰው ይሆናልና ፥ ክብር ላንቺ ይገባል ብሎ በነገራት ጊዜ፦ ሳይወሰን በማይመረመር ግብር ያለዘርዐ ብእሲ (ያለወንድ ዘር) በመስማት ብቻ ቃል በማኅፀኗ አደረ፤» ብሏል። (ሃይ አበው ፸፩ ፥፫)።
፪፥፪፦ የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ፤
ሰው ማለት፦ የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ ነው ብለናል። ቅዱስ ዮሐንስ፦ «ቃል ሥጋ ሆነ፤» ያለው፦ «ሥጋን ብቻ ነሣ፤» ለማለት አይደለም ፥ የነፍስ እና የሥጋን ተዋሕዶ በሥጋ ስም ሲጠራ እንጂ። የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ በሥጋ ስም ወይም በነፍስ ስም ሊጠራ ይችላል።
፪፥፪፥ሀ፦ በሥጋ ስም በሚጠራበት ጊዜ፤
ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት፦ በመዝሙሩ፦ «ስማዕ ጸሎተ ኲሉ ዘሥጋ ዘመጽአ ኀቤከ፤ ወደ አንተ የመጣውን የሥጋን ሁሉ ጸሎት ስማ፤» ብሏል። መዝ ፷፬ ፥ ፪። ይህም የነፍስንና የሥጋን ተዋሕዶ በሥጋ ስም ሲጠራ እንጂ፦ ነፍስ የተለየው ወይም የሌለው ሥጋ ብቻውን ይጸልያል ፥ ማለት አይደለም። በመሆኑም፦ «የሥጋን ጸሎት፤» በማለቱ፦ «ነፍስ የሌለው ሥጋ ብቻውን ጸለየ፤» አያሰኝበትም። ነፍስ የተለየው ሥጋማ ሙት ነው ፥ በድን ፥ሬሣ ፥አስከሬን ነው። ያዕ ፪፥፳፮።
፪፥፪ለ፦ በነፍስ ስም በሚጠራበት ጊዜ፤
ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ፦ በግብረ ሐዋርያት መጽሐፉ ላይ፦ ስለ ዮሴፍ ወልደ ያዕቆብ ሲተርክ፦ «የአባቶችም አለቆች፦ በዮሴፍ ቀንተው ወደ ግብጽ ሸጡት፤ እግዚአብሔር ግን ከእርሱ ጋር ነበረ። ከመከራውም ሁሉ አዳነው፤ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖን ፊትም ሞገስና ጥበብን ሰጠው፤ በግብፅና በከነዓን ሀገር ረኃብና ታላቅ ጭንቅ መጣ፤ አባቶቻችንም የሚበሉት አጡ። ያዕቆብም በግብፅ ሀገር እህል እንዳለ ሰማ፤ አባቶቻችንንም አስቀድሞ ላካቸው፤ ወደ ግብፅም እንደገና በተመለሱ ጊዜ ወንድሞቹ ዮሴፍን አወቁት፤ ፈርዖንም የዮሴፍን ዘመዶች አወቃቸው። ዮሴፍም አባቱን ያዕቆብንና ዘመዶቹን ሁሉ እንዲጠራቸው ላካቸው፤ ቁጥራቸውም ሰባ አምስት ነፍስ ነበረ፤» ብሏል። የሐዋ ፯፥፱-፲፬። ይህም የሥጋን እና የነፍስን ተዋሕዶ በነፍስ ስም ሲጠራ እንጂ፦ ሥጋቸውን በከነዓን አስቀምጠው፦ በነፍስ ብቻ ወደ ግብፅ ወረዱ ፥ ማለቱ አይደለም። ቅዱስ ዳዊትም፦ «ዐይነ ኲሉ ነፍስ ይሴፎ ኪያከ፤ የሰው ሁሉ ነፍስ አንተን ተስፋ ያደርጋል፤» በማለት የሥጋን እና የነፍስን ተዋሕዶ በነፍስ ስም ጠርቷል። መዝ ፻፵፬፥፲፭። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም የሥጋን እና የነፍስን ተዋሕዶ በነፍስ ስም ስትጠራ፦ «ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፤» ብላለች። ሉቃ ፩፥፵፯።
፫፦ ነፍስን ጭምር እንደነሣ የሊቃውንት ምስክርነት፤
ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይኽንን በተመለከተ ያስተማሩት ትምህርት ሁሉ አንድ ነው። ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ፦ «ወልድም ኃጢአት እንደበዛ ባየ ጊዜ ፥ በማይነገርና በማይመረመር ግብር ወርዶ ፥ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን አደረ፤ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀንም በማኅፀኗ ተወሰነ። በእርሷ አድሮ ሊዋሐደው የፈጠረውን ፍጹም ሥጋን በአብ ፈቃድ፥ በመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ ከእርሷ ነሣ። ከፈጣሪነት እንዳናወጣው፦ አብ ፈጠረለት ፥ አንበል፤ ሊዋሐደው እርሱ ፈጠረው እንላለን እንጂ። ከአብ ጋር በሥራው ሁሉ ( በፈጣሪነት)፦ አንድ ጌትነት ፥አንድ አገዛዝ አለውና፤ ሰው ለመሆን በወረደ ጊዜ፥ ሥጋን ይዞ አልመጣም ፤ የሰው ዘር፦ ምክንያት ሳይሆነው፦ ከድንግል ማርያም ሥጋን ነፍስን ነሥቶ ተዋሐደ እንጂ።» በማለት መስክሯል። (ሃይ አበው ፻፲፯፥፱)። ቅዱስ አቡሊድስም፦ «ሥጋ የሌለው እርሱ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋን ነፍስን ነሥቶ ሰው ሆነ፤ እርሱን የምንመስል ሰማያውያን ያደርገን ዘንድ፤ እርሱ ሰማያዊ ነውና።» በማለት አስተምሯል። (ሃይ አበው ፴፱፥፵፮)። የሮም ሊቀ ጳጳሳት፦ አዮክንድዮስም፦ «እግዚአብሔር ከሰማይ በወረደ ጊዜ፦ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀንም ባደረ ጊዜ፦ ከእርሷም ሥጋን ነፍስን ነሥቶ ሰው በሆነ ጊዜ፦ ከሰማይ ሥጋን ይዞ አልመጣም፤ መለኮቱም ከምድር አልተገኘም።» በማለት ተናጎሯል። (ሃይ አበው ፵፬ ፥፪) ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ደግሞ የቅዱስ ዳዊትን ትንቢት ሲተረጉም፦ «ነቢዩ ዳዊት፦ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትም፤ የባሕርይ ልጅህንም ሙስና መቃብርን ያይ ዘንድ አሳልፈህ አትሰጠውም፥ አለ። ይህም ጌታ በተዋሐደው አካል ያለውን የነፍስና የሥጋ ተዋሕዶ ያስረዳል፤ የቀና ልቡና፥ እውቀት ፥ በእርሱ ጸንቶ ይኖር ዘንድ ዳዊት የተናገረው እውነት ሆነ። ነፍስ መለኰትን ተዋሕዳ ወደ ሲኦል ወርዳለችና፤ ሥጋም ሦስት መዓልት ፥ሦስት ሌሊት ፥ በመቃብር ሳለ፦ መለኮት፦ ከሥጋ አልተለየም። አምላክ ሰው የመሆኑን እውነትነት ያስረዳ ዘንድ፦ መለኮትና ነፍስ በሲኦል ምሥጢርን ፈጽመዋልና፤ በሲኦልም በቁራኝነት አልተያዙምና።» ብሏል። (ሃይ አበው ፶፭፥፯)። በዚህም፦ «ቃል ሥጋን እንጂ ነፍስን አልነሣም ፥ መለኮቱ እንደ ነፍሰ ሆነለት፤» የሚሉትን ፈጽሞ አሳፍሯቸዋል። ቅዱስ ኤራቅሊስም፦ «አምላክን ከወለደች ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሣው አካል፦ ሥጋ ከእርሱ ጋር አንድ ሆነ፤ ከባሕርያችን ተገኝቶ ፦ አምላክ የሆነ ሥጋ ነው፤ መንፈስ ቅዱስ ሕይወቱ ሲሆን፦ የምትናገር የሥጋ ሕይወት ነፍስ አለችው፤» ብሏል። (ሃይ አበው ፵፰፥፳፩)። ቅዱስ ቄርሎስም በበኲሉ፦ «ቅዱሳን አባቶቻችን፦ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፦ ከአብ ባሕርይ የተገኘ፦ አንድ ወልድ ፥ ቃል ፥ እንደሆነ ተናገሩ፤ ከባሕርይ አምላክ የተገኘ የባሕርይ አምላክ፥ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ፥ ሁሉ የተፈጠረበት እርሱ፦ ነፍስን ሥጋን ነሥቶ፦ ሰው ሆነ፤ ከድንግልም በሥጋ ይወለድ ዘንድ ወደደ፥ በእኛም ባሕርይ ተገለጠ ፥ ሰው የሆነበት ባሕርይ ይህ ነው።» በማለት የእውነት ምስክር ሆኗል። (ሃይ አበው ፸፪፥፩)

Post Bottom Ad