ጾም ለምን?(ክፍል ሁለት) - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Wednesday, March 12, 2014

ጾም ለምን?(ክፍል ሁለት)


 ጾም ወደ እግዚአብሔር ለመመለስና ንስሓ ለመግባት ይጠቅማል
ክብር ምስጋና ይግባዉና እግዚአብሔር በምክንያተ ኃጢአት ከእርሱ ስንለይና ከክብር ስንርቅ ወደእርሱ እንመለስ ዘንድ ይሻል፡፡እንዴት መመለስ እንዳለብን የነገረን እንዲህ በማለት ነዉ‹‹በፍጹም ልባችሁ በጾም በለቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ››ኢዩ2-12 ወደ እግዚአብሔር የምንመለሰዉ በጾምና በጸሎት ነዉ፡፡ጾም ለሥርየተ አበሳ ይጾማል፡፡‹‹ወሀበነ ጾመ ለንስሓ በዘይሠረይ ኃጢአት››እንዲል ጾም በደልን አምኖ ጥፋትን ተቀብሎ በፍጹም ትሕትና ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ በድያለሁና ማረኝ ይቅር በለኝ በማለት ምሕረቱንና ይቅርታዉን የሚያገኙበት መሣሪያ ነዉ፡፡
ጾም ፊትን ወደ እግዚአብሔር ማቅናት እንደሆነ በሰብአ ነነዌ ታዉቋል እነዚህ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር የተመለሱት በጾም ነዉና፡፡ኃጢአታቸዉ እጅጉን ገዝፎ ቅድመ እግዚአብሔር ስለደረሰ የጌትነቱ ጨንገር ከመምጣቱ አስቀድሞ ንስሓ እንዲገቡ መሐሪ እግዚአብሔር ነብዩ ዮናስን ላከላቸዉ፡፡ሕዝቡም የነቢዩ ስብከትን ሰምተዉ በክፉ ስራቸዉ ተጸጽተዉ ከሊሒቅ እስከ ደቂቅ ማቅ ለበሱ አመድንም በራሳቸዉ ነሰነሱ፡፡ንጉሱም ከዙፋኑ ወርዶ መጎናጸፊዉን አዉልቆ ማቅ ለብሶ በአመድ ላይ ተቀመጠ፡፡አዕምሮ ጠባይዕ ያላደፈባቸዉ ሕጻናትና እንስሳትንም የንስሓቸዉ ተካፋዮች እንዲሆኑ አደረጉ፡፡በዚህ ጊዜ የፍጥረቱን መዳን እንጂ ጥፋቱን የማይወድ እግዚአብሔር ቁጣዉን በትዕግስት መዓቱን በምህረት መልሶ በይቅርታ ጎበኛቸዉ ከጠቀጣዉ መቅሠፍት አዳናቸዉ፡፡ዮና 3-5-10
ወደ እግዚአብሔር በጾም በጸሎት የተመለሱ ድኅነትን እንዳገኙ ሁሉ ያልተመለሱት ደግሞ ጠፍተዋል፡፡ለምሳሌ ሰብአ ሰዶም ገሞራ እንደ ነነዌ ሰዎች በጾም ወደ እግዚአብሔር ባለመመለሳቸዉ እሳት ከሰማይ ወርዶ አቃጥሎ አጥፍቷቸዋል፡፡ዘፍ 19-23
 ጾም ኃይለ አጋንንትን ለማድከም ጸብአ አጋንንትን ለማብረድና ለማሶገድ ይጠቅማል
ከጽልመት አበጋዝ ግዝፈ አካል ከሌላቸዉ አጋንንት ጋር በምናደርገዉ ዉጊያ ጾም አይነተኛ መሳሪያ ነዉ፡፡አጋንንት ስለተለያዩ ምክንያቶች ትሩፋት መስራት እስኪሳነን ድረስ ይዋጉ ዘንድ ይታዘዛሉ፡፡የሚዋጉንም ነፍሳችን ጾርን ትማር ዘንድ እግዚአብሔርን መፍራታችን መዉደዳችን ይታወቅ ዘንድ ነዉ፡፡
ጌታችን መጾም ሳያስፈልገዉ የጾመዉ በጾም መሳሪያነት ዲያብሎስን ድል ታደርጋላችሁ ሲለን ነዉ፡፡እርሱ ድል አድርጎለታልና ካልጾሙ ካልጸለዩ ሰይጣንን ድል ማድረግ እንደማይቻል ጌታ አስተምሮናል፡፡አንድ ልጁ የታመመበት ሰዉ ሐዋርያት ልጁን እንዲያድኑለት ጠይቋቸዉ ሊያድኑለት አልተቻላቸዉም፡፡ያም ሰዉ ጌታን ‹‹መምህር ሆይ ዲዳ መንፈስ ያደረበትን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼአለሁ በዚያም ስፍራ ሁሉ ይጥለዋል አረፋም ይዳፍቃል ጥርሱንም ያፋጫል አጋንንቱን እንዲያወጡለት ለደቀ መዛሙርትህ ነገርኋቸዉ ሊያወጡት አልቻሉም››አለዉ በዚህን ጊዜ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ ስለ እምነታቸዉ መጉደል ከገሠጻቸዉ በኋላ ወደ እኔ አምጡት አላቸዉ፡፡ወደ እርሱም ባመጡት ጊዜ ያ መንፈስ ወዲያዉ አንፈራገጠዉ፡፡
ርኩሱን መንፈስ ከገሰጸ በኋላ‹‹አንተ ዲዳ ደንቆሮም መንፈስ እኔ አዝሃለሁ ከእርሱ ዉጣ እንግዲህም አትግባበት››በማለት ተረፈ ደዌ እንዳይኖርበት ሙሉ ጤንነትን ሰጠዉ ቅዱሳን ሐዋርያት ጋኔኑን ማስወጣት ባለመቻላቸዉ የጎደላቸዉን ለማወቅና ስህተታቸዉን ለማረም ሽተዉ እኛ ልናሶጣዉና ልጁን ልናድነዉ ያልተቻለን ስለምንድር ነዉ?በማለት ጠይቀዉታል፡፡እርሱም‹‹ዝንቱ ዘመድ ኢይወጽእ ዘእንበለ በጾም ወበጸሎት ይህ ዓይነቱ አብሮ አደግ ጋኔን በጾምና በጸሎት ካልሆነ በቀር ይወጣም››አላቸዉ ማር 9-29
ስለሆነም ጾምን በሥርዓት ወስኖ በሃይማኖት መጾም ለክርስቲያኖች ዲያብሎስን ድል የሚነሱበት ዐብይ ኃይል ነዉ፡፡
   
  ጾም የበጎ ምግባር መገኛ መጀመሪያ ነዉ
‹‹ከኃጢአት ጾር አንዱን ድል ለመንሳት በጾም መድከም የስራ ሁሉ መጀመሪያ ነዉ፡፡››ማር ይስሐቅ አንቀጽ 9 ምዕ 6፡፡መብል ለኃጣዉእ መሰረት እንደሆነ እንደዚሁም ጾም ለምግባር ለትሩፋት መሰረት ነዉ፡፡
ጾም ገንዘብ ያደረጉትን መንፈሳዊ ግብር ያስፈጽማቸዋል፡፡ጾምን የሚያቃልል ሰዉ ሌላውን ትሩፋት ከመስራት ቸል ይላል፤ይደክማል፡የሐኬት ምልክትነትም ኃጢአትን ወደ ሰዉነቱ መርታ ታደርሳለች፡፡በጎ የሆነዉን ነገር ከራሱ ያርቃል፡፡ስለ ማሸነፍ ፋንታ ጾሩ ነጉዶ ይመጣበታል፡፡
ጾም ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት አስፈላጊ ነዉ፡፡በስራ አምላካቸዉን ለመምሰል የወጡ ሁሉ ጾምን የስራቸዉ መጀመሪያ አድርገዋል ምክንያቱም ጾም ከእግዚአብሔር የተሰጎደ(የተሰጠ)ጋሻ ነው፡፡ቅዱሳን ሐዋርያት ወደየ ክፍለ አሕጉሩ ለስብከተ ወንጌል ከመለያየታቸዉ በቅድሚያ ጌታን አብነት አድርገዉ አንድ ሆነዉ ጾመዋል፡፡ስለሆነም ማንኛዉም ስራ ከመጀመራችን በፊት በጾም ፈቃደ እግዚአብሔን መጠየቅ ይገባናል ይህም ልንሰራዉ ያሰብነዉን ስራ በአግባቡ ለመወጣት ያስችለናል፡፡
      ጾም ሕይወተ ዘለዓለምን ለመዉረስ ይረዳናል
ጾም የጽድቅ መሠረት የገነት በር ነዉ፡፡ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአንቀጸ ብጹዓን‹‹ ይርኅቡ ወይጸምዑ በእንተ ጽድቅ አብዝተንማ ከተመገብን ሰዉነታችን ገትቶ ወስኖ ማኖር እንደምን ይቻለናል ብለዉ ከሚበሉት ከሚጠጡት ከፍለዉ የሚራቡ የሚጠሙ ንዑዳን ክቡራን ናቸዉ›› ብሏል፡፡ማቴ 5-6  የሰዉ ልጅ ኃጢአት ካልሰራ ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየዉም፡፡ቤተ መቅደስ ልቦናዉ ከመተዳደፍ የተለየ ከሆነ በእግዚአብሔር ቸርነት ርስቱን ይወርሳል ከዚህም በላይ ለፍቅሩ የሚሳሱ አንድም በመማር በማስተማር በሃይማኖት በምናኔ በንስሓ የሚራቡ ሰዎች ንዑዳን ክቡራን ናቸዉ‹‹ይጠግባሉና››አለ እዚህ ላይ የርኃብ አጸፋዉ ጥጋብ ስለሆነ ይጠግባሉ ሲል  መንግስተ ሰማያትን ይወርሳሉ ማለቱ ነዉ፡፡ 

Post Bottom Ad