አቡነ ዜና ማርቆስ - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Friday, February 21, 2014

አቡነ ዜና ማርቆስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን::


አቡነ ዜና ማርቆስ በ፲፫ኛ/13ኛው/ መቶ ክ/ዘመን)
ስለ እመቤታችን፣ ስለሐዋርያት፣ ስለነገስታት፣ ስለጻድቃን፣ ስለሰማዕታት፣ ስለ ቅዱሳን መላእክት በአጠቃላይ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እንወቅ፣ እንመርምር፣ እንጠይቅ፣እንማማር ለዚህም እግዚአብሔር አምላክ እዝነ ልቦናችንን ይክፈትልን፤ የአዲስ ኪዳን ኪሩብ የጸጋ መፍሰሻ ምልዕተ ክብር ምልዕተ ውዳሴ የሆነች እመቤታችን ድንግል ማርያም ምስጢር ትግለጥልን አሜን!!!

† ቅዱሳን ጻድቃን መላ ዘመናቸውን ከጣዕመ
ዓለምና ከተድላ ዓለም ተለይቶ ቤት ልስራ ዘር ልዝራ ሳይሉ ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው አስገዝተው በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በምናኔ ጸንተው የኖሩ ናቸው። 

ቅዱስ አባታችን አቡነ ዜና ማርቆስ ገራቸው ዞረሬ /ጽላልሽ/ ነው። አባታቸው ካህን ዮሃንስ የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አባት የአቡነ ጸጋዘአብ ወንድም ነው። እናታቸው ዲቦራ (ማርያም ዘመዳ ትባላለች። የአቡነ ቀዎስጦስ እህት ናት። በብስቃረ ማርቆስ ወንጌላዊ ህዳር ፳፬ /24/ ተወልዷል። አርባ ቀን ሲሞላው ሊያስጠምቋቸው ቤተ ክርስቲያን ወሰዷቸው። ጸሎተ ጥምቀቱ ደርሶ ከውሃ ውስጥ ሲከቷቸው ቆመው እሰግ ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ብለው 3 ጊዜ ሰግዶአል። ውሃው ፈላ አጥማቂው ቄስ የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አባት የአቡነ ጸጋዘአብ ወንድም ካህኑ እንድርያስ ነበር። እድሜው 72 ዓመት ስለነበር በሕፃኑ ድርጊት ፈርቶ ወደ ቤተ መቅደስ ሮጠ። ቅዱስ ሩፋኤ ከፍርሃቱ አጽናንቶት ከማየ ጸሎቱ ራሱን እንዲቀባ ነግሮት በራ የነበረ ራሱ ጸጉር በቅሎለታል።አቡነ ዜና ማርቆስ 5 ዓመት ሲሞላቸው ወላጆቻቸው ለመምህር ሰጧቸው። በ 3 ዓመት ብሉይንና ሐዲስ አጥንተው በ8 ዓመታቸው ከቅዱስ ቄርሎስ ድቁና ተቀብለው ሲመጡ ሽፍቶች የእጃቸውን በትር ነእሳቸውም ወደ ጌታ ቢያመለክቱ በትራቸው እባብ ሆና ነድፋ ገድላቸዋለች። 30 ዓመት ሲሆናቸው ማርያም ክብራ ለምትባል ደግ ሴት አጋቧቸው። ልማደ መርዓዊ ወመርዓት (ሙሽራውና ሙሽራይቱ) ያድርሱ ብለው መጋረጃ ሲጥሉባቸው በሌሊት ወጥተው ሄዱ። መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል ሀገረ ምሑር አድርሷቸውዋል። በዛም የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በመጥራታቸውና ከንጉሱ (ሀገረ ገዢው) አብላኝ በማለታቸው የኔ አምላክ ማኮስ ነው ኢየሱስ የምትለው ማን ነው ቢላቸው አምላካችን ነው ቢሏቸው ወስዶ ቤተ ጣዖት ቢያሳያቸው ወስደው በእግር ረግጠው አሰጠሙት። መስፍኑ ተቆጥቶ አሰራቸው። መልአኩም ከእስራታቸው ፈቷቸዋል። እንዲያበላቸው ዳግም ሀገረ ገዢውን ቢጠይቁት ተናዶ በጦር ሊወጋቸው ሲል ምድር አፏን ከፍታ ባሕር ሆና አሰጠመችው። እንዲህ እያሉ ብዙ ስለ ጌታ መስክረዋል።
ኋላም ወደ ምድረ ጉራጌ ወርደው ብዙውን አስተምረው ወደ እምነት መልሷል። ብዙዎችም አሳምነው አጥምቋቸዋል። በጸሎታቸውም ብዙ በሽተኞችን ፈውሶ የትሩፋት ሥራን ሠርተዋል። ሃላም አቡነ ተክለ ሃይማኖት ምንኩስና ሰቷቸው ወደ ደብረ አስቦ (በደ/ሊባኖስ ተክልዬ ለ29 ዓመታት የጸለዩበት ቦታ) ሄዱ። ከዚህ በኋላ አቡነ ዜና ማርቆስ ደብረ ብስራትን ገድመው እያስተማሩ ኖረው ፪፻ አናብስት በ፪፻ አናምርት ታጅበው በደመና ተጭነው ብዙ ቦታ በመሄድ አስተምረው አሳምነዋል። ከእረፍታቸው በፊትም ልጆቻቸውን በሙሉ ከየ ሀገሩ ጠርተው ቅዳሴ ቀድሰው ሲያቆርቡ ከብዛታቸው የተነሳ ፀሐይ ልትገባ ስለሆነ ወደ ጌታ አመልክተው አቀብለው እስኪፈጽሙ ድረስ ፀሐይ ባለችበት እንድትቆም አድርገዋል። ከዚህ የበዙ ተዓምራትን ሲያደርጉ ኖረው በተስፋቸው ያመነ በኪዳናቸው የተማጸነ ዋጋውን እንደማያጣ ጌታ ቃል ኪዳን ሰጥቷቸው በተወለዱ በ፻፬ (140) ዘመናቸው ታህሳስ ፫/ 3/ ቀን ዐርፈዋል። 

† የቅዱሳን አኗኗራቸው ድምጸ አራዊቱን ጸብዓ አጋንንቱን ግርማ ሌሊቱን ሳይሳቀቁ ደዋ ጥሰው፣ ደንጋይ ተንተርሰው፣ ጤዛ ልሰው ነው። ይህን ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ።” † በማለት በዕብ.11፡37-38። በረከትና ቃል ኪዳናቸው በምልጃቸው ከምናምን ሕዝበ ክርስቲያን ጋር ለዘላለሙ ጸንቶ ይኑር አሜን።

+ ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣኝ፣ ካለማወቅ ወደ መረዳት ያደረሰኝ አነሳስቶ ላስጀመረኝ አስጀምሮ ላስፈጸመኝ ጥንት ላሌለው ቀዳማዊ ፍጻሜ ላሌለው ድህራዊ ያልኖረበት ጊዜ የሌለ የማይኖርበት ጊዜም የማይኖር የዘላለም ንጉስ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ እግዚአብሔርን በራስ ፀጉሬ ቁትር በአጥንቶቼም ልክ አመሰግናለሁ፡፡

+ በሰማይ ያሉ መላእክት በምድርም የሚኖሩ የአዳም ዘር ሁሉ የሚያመሰግኗት በአማላጅነቷ ሁል ጊዜ የማትለየኝ ከፀሐይ ሰባት እጅ የምታበራ የብርሃን እናት የሁሉ እመቤት የአምላክ እናት ከተመረጡ የተመረጠች ከተለዩ የተለየች ከተከበሩ የተከበረች እናቴ እመቤቴ ድንግል ማርያም በቃላት ልገልጸው ከምችለው በላይ አመሰግናለሁ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን፡፡ ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡

Post Bottom Ad