ዮሐንስ ሐፂር በላይኛው ግብጽ ቴባን በምትባል መንደር በ339 ዓ.ም ተወለደ፡፡ ወደ ገዳም አስቄጥስ የገባውበልጅነቱ ሲሆን ያን ጊዜ አበምኔቱ አባ ባሞይ ይባል ነበር፡፡ አባ ዮሐንስ በተመሥጦው እና በታዛዥነቱየታወቀ አባት ነበር፡፡ በመጀመርያው የአስቄጥስ ጥፋት ጊዜ ገዳሙን ትቶ ወደ ቁልዝም ተጓዘ፡፡ ያረፈውምበዚያ ነው፡፡
1. የጠላቱን ከተማ ለመቆጣጠር የዘመተ ንጉሥ አስቀድሞ የውኃውን መንገድ ይዘጋል፣ የእህሉንም መግቢያይይዛል፡፡ ያን ጊዜ ጠላቶቹ ይራባሉ፣ ይጠማሉ፡፡ በመጨረሻም እጃቸውን ይሰጣሉ፡፡ የነፍስን ፆር ለማሸነፍምበተመሳሳይ መንገድ መጠቀም ይገባል፡፡ አንድ ሰው በጾምና በረኃብ ከጸና የነፍሱ ጠላቶች ይዳከማሉ፡፡
2. እኔ በትልቅ ዋርካ ሥር የተቀመጠንና አራዊት ሊጣሉት የመጣን ሰው እመስላለሁ፡፡ ሊቋቋማቸውእንደማይችል ከተረዳ ሸሽቶ ወደ ዛፉ በመውጣት ነፍሱን ያድናል፡፡ በእኔም የተፈጸመው ይኼው ነው፡፡በበዓቴ ተቀምጬ ክፉ ሃሳቦች ሊቃወሙኝ ሲመጡ፣ ልቋቋማቸው እንደማልችል ባወቅኩ ጊዜ በጸሎት ወደእግዚአብሔር ሸሽቼ እመሽጋለሁ፡፡ በዚያም ከጠላቶቼ ፍላፃ እድናለሁ፡፡
ዮሐንስ ሐፂር
|
3. መለወጥ የምትፈልግን ነፍስ በተመለከተ አባ ዮሐንስ እንዲህ አለ፡- በአንዲት ከተማ ውስጥ ብዙ ወዳጆችየነበሯት አንዲት አመንዝራ ሴት ነበረች፡፡ ከገዥዎቹ አንዱ ቀረባትና ‹መልካም ሴት ለመሆን ቃል ግቢልኝናአገባሻለሁ› አላት፡፡ እርሷም ቃል ገባችለትና ተጋቡ፡፡ ወደ ቤቱም ወሰዳት፡፡ የቀድሞ አፍቃሪዎቿ ያቺን ሴትፈለጓት፣ እርስ በርሳቸውም ‹ያ ልዑል ወደ ቤቱ ወስዷታል፤ ወደ ቤቱ ብንሄድ ይቀጣናል፡፡ ነገር ግን በጓሮበኩል እንሂድ፣ ለርሷም እናፏጭላት፣ የፉጨቱን ድምፅ ስትሰማ ከድርሱ ወርዳ ወደኛ ትመጣለች፣በዚህም ያለችግር እናገኛታለን› ተባባሉ፡፡ ወደ ቤቷም ጓሮ ተጉዘው ያፏጩ ጀመር፡፡ እርሷ ግን የፉጨቱን ድምፅ ስትሰማጆሮዎቿን ደፈነች፡፡ ወደ ውስጣዊው እልፍኝም ገባች፡፡ በሩንም ጥርቅም አድርጋ ዘጋች፡፡ ይህቺ ሴት የኛ ነፍስምሳሌ ናት፡፡ ወዳጆቿ የተባሉም ፈተናዎቿ ናቸው፤ ገዥ የተባለውም ክርስቶስ ነው፣ እልፍኝ የተባለውምዘለዓለማዊው ቤት ነው፡፡ እነዚያ የሚያፏጩት ክፉዎች አጋንንት ናቸው፤ ነገር ግን ነፍስ ሁልጊዝምበክርስቶስ አምባነት ትሸሸጋዋለች፡፡
4. አባ ዮሐንስ ልቡናው ከእግዚአብሔር ጋር ስለነበረ ምድራዊ ነገሮችን ይዘነጋ ነበር፡፡ አንድ ቀን አንድወንድም ቅርጫት ሊወስድ ወደ አባ ዮሐንስ በኣት መጣ፡፡ አባ ዮሐንስም ምን ፈልጐ እንደሆነ ጠየቀው፡፡ ያምወንድም ‹ቅርጫት ፈልጌ ነው› አለው፡፡ አባ ዮሐንስ ወደ በኣቱ ተመለሰና ዘንግቶት ወደ ሽመና ሥራውአመራ፡፡ ጥቂት ቆይቶ ያ ወንድም አንኳኳ፣ አባ ዮሐንስም ወጥቶ ‹ምን ፈልገህ ነው› አለው ‹ቅርጫት ስጠኝብየህ ነበር› ሲል መለሰለት፡፡ ተመልሶ ወደ በኣቱ ሲገባ ልቡናው በሰማያዊ ነገር ስለተመሰጠ ዘንግቶት ወደሽመናው ሥራ እንደገና ገባ፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ ያ ወንድም ሲያንኳኳ አባ ዮሐንስ ተመልሶ ወጣና ‹ምን ፈልገህነው?› አለው፡፡ ‹ቅርጫት ስጠኝ ብየህ ነበር› አለና መለሰለት፡፡ አባ ዮሐንስም እጁን ይዞ እየጐተተ ወደ በኣቱአስገባውና ‹ቅርጫት ከፈለግህ ያዝና ሂድ፣ በእውነቱ እንዲህ ላሉት ነገሮች እኔ ጊዜ የለኝም› አለው፡፡
5. አንድ ቀን አንድ ሰው ወደ አባ ዮሐንስ ሐፂር በኣት መጣና ሥራውን እያየ ያመሰግነው ጀምር፡፡ አባ ዮሐንስዝም አለውና ገመድ መሥራቱን ቀጠለ፡፡ እንግዳውም እንደገና ወሬውን ቀጠለ፣ አባ ዮሐንስም ጸጥ አለው፡፡ለሦስተኛ ጊዜ እንግዳው ወሬ ሲያበዛ፡፡ ‹አንተ ወደ በኣቴ በመግባትህ እግዚአብሔር ወጥቶ ሄደ› ብሎተናገረው፡፡
6. አባ ዮሐንስ እንዲህ አለ፡- ‹የብሕትውናን ኑሮ በከተማ ውስጥ የሚኖር አንድ ሽማግሌ ነበረ፡፡ ያ ሰውበከተማው ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠውና ባለዝናም ነበር፡፡ አንድ አረጋዊ አባት ከማረፉ በፊት ያንን ሰውሊያየው እንደሚፈልግ ለዚያ ሰው ጥሪ ደረሰው፡፡ ያም ሰው በቀን ከተጓዝኩ ሰዎች ስለሚከተሉኝ ለኔ የተለየክብር ይሰጡኛል ብሎ አሰበ፡፡ ስለዚህም በሌሊት ሰው ሳያየው ለመጓዝ ወሰነ፡፡ በመሸ ጊዜም አሁን ማንምአያየኝም ብሎ ተነሣና ጉዞ ጀመረ፡፡ ነገር ግን ሁለት መላእክት ታዝዘው መብራተ ይዘው መንገዱን ይመሩትነበር፡፡ ይህንን የተመለከቱ የከተማው ሰዎች ወደ እርሱ ተሰባሰቡ፣ መላ ከተማው ያንን የመላእክት ብርሃንእያየ ከኋላ ተከተለው፡፡ ከክብር በሸሸ ቁጥር የበለጠ ክብርን አገኘ፡፡ በዚህም ‹ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉይዋረዳል፣ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ከፍ ይላል› የሚለው የወንጌል ቃል ተፈጸመ፡፡ (ሉቃ. 14.11)
7. አባ ጴሜን አባ ዮሐንስ እንዲህ ብሎ መናገሩን ገልጧል ‹ቅዱሳን በአንድ ቦታ የበቀሉ ዛፎችን ይመስላሉ፡፡ከአንድ ምንጭ ጠጥተው፣ ልዩ ልዩ ዓይነት ፍሬ ያፈራሉ፡፡ የአንድ ቅዱስ ሥራ ከሌላው ይለያል፣ ነገር ግንበሁሉም አድሮ የሚሠራው አንድ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡
ዋቢ በበረሓው ጉያ ውስጥ