ግብረ ሰላም - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Sunday, January 5, 2014

ግብረ ሰላም

ግብረ ሰላም ማለት ‹‹ ገብረ ሰላመ››መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ሰላምን አደረገ ፤ተጣልተው የነበሩ ሰማያውያን መላዕክት እና ምድራዊያን ደቂቀ አዳም በመስቀሉ ታረቁ ፤ሰላም ወረደ ማለት ነው፡፡ ይሄውም‹‹የእግዚአብሔር ሙላቱ በእርሱ እንዲኖር በእርሱ በኩልበመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ያሉት ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዷልና ›› በማለት ቅዱስ ጳውሎስ በቆላ 1፤19-20 ፍንትው አድርጎ ክርስቶስ በመስቀሉ ሰላም እንዳደረገ ገልጾት እናገኛለን፡፡ተድያ ካህናት አባቶች ይህንን ብስራትእና የምስራች ይዘው ከቤተ- እግዚአብሔር ወደ ምዕመናን ቤት‹‹ አዋጅ አዋጅ›› በማለት ይሄዳሉ፡፡ትንሳኤውንም ያበስራሉ፡፡ ይህም ምሰጢር አለው ፡፡ጌታችን እና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎ፤ሞቶ፤ወደ መቃብር በወረደብት ጊዜ ሐዋርያት ፍሩኀን ፤ድንጉጻን ነበሩ፡፡በኋላም በ3ኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ በመነሳት ትንሳኤውን በአበሰራቸው ጊዜ ሐሴት አድርገዋል(ዮሐ 20፤20)፡፡በዚህ መሰረት ካህናት የክርስቶስን ትንሳኤ ይዘው ለሐዋርያት  ምሳሌ ለሆኑት ለምዕመናን ክርስቶስ ተነስቷል እያሉ ብስራቱን ይናገራሉ፡፡ካህናት  ለምዕመናን ‹‹የክርስቶስ ቸርነቱ ብዛቱ፤40 ፆሙ 50 ብሉ ማለቱ ፤ጾም እንዳትውሉ ፤ዘር እንዳትመትሩ›› በማለት ጊዜው የደስታ፤የሐሴት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ምዕመናንም በክርስቶስ ትንሳኤ ደስ በመሰኘት ቀንዱ የዞረዉን፤ጮማው የሰባውን ፤ጠላው የጠራውን አዘጋጅተው ካህናትን፤የቤተ-ክርስቲያን አገልጋዮችን በየቤታቸው በመጥራት የትንሳኤውን በረከት በአንድ ላይ ያከብራሉ፡፡ይህም ግብረ ሰላም ይባላል፡፡  
በሌላ በኩል ግብረ ሰላም ማለት ምዕመናን የክርስቶስን ተዝካር አወጣን በማለት ስለ ግርፋቱ፤ስለ መንገላታቱ፤ስለመሰቀሉ እና ስለመሞቱ በማሰብ እና በማዘን የክርስቶስ ምሳሌ የሆኑትን ካህናን በመጥራት ያከብሩታል፡፡በአንጻሩ ካህናት ምዕመናንን አይዟችሁ ክርስቶስ ምንም መከራ ሞት ቢቀበል ሞቶ አልቀረም ከሙታን ተለይቶ ተነስቷል፡፡ በማለት ደስታን ያበስሯቸዋል፤ትንሳኤውን ይሰብኩለቸዋል፤ያረጋጓቸዋል‹‹ሰላም ….እምይእዜሰ፤ይኩን …ፍስሐ ወሰላም ››በማለት ሰላም መታወጁን ይናገራሉ፡፡
     በግብረ ሰላም ጥሪ አድሎ መኖር የለበትም ፡፡አልያ ግብረ ሰላም መሆኑ ይቀራል፡፡ስለዚህ ግብረ ሰላም ለማድረግ አስቀድሞ
በዓብይ ፆም ወቅት ቅድመ-ዝግጅት ማድረግ እና በዓብይ-ፆም ወቅት ሲያገለግሉ የነበሩ ሙሉ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እንዲገኙ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ነገር ግን አሁን አሁን ከኑሮ ውደነቱም፤ትኩረት ካለመስጠትም የተነሳ ይህ ስርዓት ሙሉ በሙሉ ቀረ ባይባልም  ፤ምዕመናንም በተወሰነ መጠን ድግስ በማዘጋጅት የሚያውቋቸውን አገልጋዮች እናመምህራንን ብቻ  በመጥራት ሲያከብሩት ይስተዋላል፡፡ቀድሞ ግን በስፋት ይከበር የነበረው ፣መጀመርያ በተገለጸው መሰረት ነበር፡፡
    በቀድሞ ጊዜ የኢትዮጵያ እናቶቻችን ለካህናት ካላቸው ፍቅር እና ከበሬታ የተነሳ ለግብረ ሰላም ዝግጅት በሚደርጉበት ጊዜ ማክሰኞ የታረደውን ለረቡዕ፤ረቡዕ የተረደውን ለኀሙስ፤ኀሙስ የተረደውን ለአርብ አያደረጉትም፤በዚያው እለት የተዘጋጀውን ሳይውል ሳያድር በዚያው እለት ያቀርቡ ነበር እንጅ፡፡ አሁን አሁንም ይህ ስርዓት በተወሰኑ አካባቢዎች ቀጥሏል፡፡
    ስለ ክርስቶስ መሰቀል፤መሞት በሌለም ጊዜ ሲነገር ይኖራል፡፡ ነገር ግን በዚህ ጊዜ ካህናቱ ‹‹ የክርስቶስ  ብስራቱ መነሳቱ በማለት ›› የክርስቶስን ትንሳኤ አበከረው በየቤቱ ፤በየግበረ ሰላሙ ፤በየቤተ ክርስቲያኑ ይሰብካሉ፡፡በሌላ ጊዜ ካህናት ወደ ምዕመናን ቤት የሚሄዱት በዘመነ ልደት፤በዘመነ ጥምቀት፤በቅዱስ ዮሐንስ ወ.ዘ.ተ ሲሆን ይሄውም እንኳን አደረሳችሁ ለማለት ፤የንስሐ ልጆቻቸውን ለማስተማር እና ለመጠየቅ ነው፡፡
     ግበረ ሰላም ካህናት በሌሉበት አይደረግም፤ቢደረግም ግብረ ሰላም አይባልም፡፡ምክንያቱም ካህናት የክርስቶስ ፤ምዕመናን የሐዋርያት ምሳሌዎች ናቸውእና ፤  ብስራት ያለክህናት፤የለም ፤ካህናት ያበስራሉ ምዕመናን ይበሰራሉ፡፡ግብረ ሰላም ዓላማው መብላት እና መጠጣት አይደለም፡፡የክርስቶስ ሞት፤እንግልት፤ስቅለት ብሎም ትንሳኤው ለማሰብ የሚዘገጅ ዝክር ነው እንጅ፡፡
     በግብረ ሰላም ወቅት ምዕመናን አስፈላጊውን ዝግጅት ካደረጉ በኋላ፤ካህናት በክብር ተጠርተው እንዲገኙ ይደረጋል፡፡ከዚያም በኋላ በካህናት አማካኝነት 
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ….ተብሎ ተጅምሮ አቡነ ዘበሰማያት፤ውዳሴ ማርያም፤ ከዚያም
ጸሎታ ለማርያም ወስእለታ ያድኅነነ ይዕቀቦ እመዓተ ወልዳ
ጸሎታ ለማርያም ወስእለታ ለህዝበ ክርስትያን ይዕቀቦ እመዓተ ወልዳ
ጸሎታ ለማርያም ወስእለታ ለነፍሳተ ሙታን ይዕቀቦእቀቦሙ እመዓተ ወልዳ
ተብሎ ዝክሩን ለዘከሩት ‹‹ ይዕቀብ ለነ ››እየተባለ ይጸለያል፡፡ከዚያም ለህዝበ ኢትዮጵያ ይዕቀባ ተብሎ የተዘጋጅው ጸበል ለህዝበ ክርስትያኑ ይረጫል፤ጸዲቀ መበለቱ ተቆርሶ ይሰጠል፡፡ማዕዱ ቀርቦ ይበላል፡፡ከተበላ በኋላ በሊቃውንቱ ጣዕመ-ዝማሬ ወረብ፤ቅኔ ይቀርባል፡፡በዚህ ጊዜ የሚቀርቡት ያሬዳዊ ወረቦች በሦስት አበይት ክፍል ይከፈላሉ፡፡
1.  ስለ ክርስቶስ ትንሳኤ የሚቀርብ ዝማሬ
   ሊቃውንቱ ውቅቱ ፋሲካ ፤ትንሳኤ ነውና ስለ ክርስቶት ትንሳኤ ፤ስለ ታወጀው ሰላም ፤ሀጥአን፤ጻድቃን፤ቅዱሳን፤ መላዕክት፤ደቂቀ አዳምም ሁሉም በትንሳኤው ደስ መሰኘታቸውን ፤ሰይጣን ድል መነሳቱን ፤ሲኦል መበርበሯን በማሰብ በሚንቆቀቆር ዜማ እየመላለሱ፤ያመሰግናሉ፡፡
ምሳሌ፤-
& ገብረ ሰላመ ወማዕከሌነ/2/
               አናኅሲሆሙ አበሳነ/2/
@  ትርጓሜ፤-፤ክርስተስ አበሳችንን መከራ ተቀብሎ አስወገደልን፤በመካከላችን ሰላምን ሰጠን፡፡በማለት ያመሰግናሉ፡፡
& ረፍት ለእለ ወስተ ደይን/2/
         ትፍስኅት ወሐሴት ለጻድቃን/2/
@  ትርጓሜ፤-በደይን ለነበሩ ሀጥአን ደስታን ሰጠህ፤ለጻድቃንም ፍስሐን አደረክ እያሉ ያመሰግናሉ፡፡
2.  ለዝክሩ ባለቤቶች የሚቀርብ ዝማሬ
   ዝክሩን ወጥተው፤ወርደው፤እጃችን ደከመ ወገባችን ጎበጠ ሰይሉ፤እንደ አብርሐም እና ሳራ እንግዳ ለመቀበል ሳይሰለቹ  ለደከሙ፤ድግሱን አዘገጅተው ፤ሊቃውንቱን የአብነት ተማሪዎችን ስመ ሥላሴ ጠርተው እና አስጠርተው ያበሉትን ምዕመናን ሊቃውንቱ በዝማሬ ያመሰግኗቸዋል፡፡
            ምሳሌ፤
& የኀብከ ዮም መድኃኔዓለም /2/
                እድሜ ማቱሳላ ወአብርሐም/2/
@  ትርጓሜ፤-በዚህ እለት ይህንን ማዕድ አዘጋጅታችሁ ያቀረባችሁ፤እግዚአብሔር አምላክ የአብርሐም፤የማቱሳሌን እድሜ ይስጠችሁ እያሉ ይመርቃሉ፡፡
         ምዕመናንም ምርቃንኑ ከልባችው ተቀብለው፤የዛሬ ዓመት ከቁጥር ሳትጎድሉ፤አገልግሎት ሳታስተጓጉሉ እኛም ሳንጎድል፤ወጥተን ሳንኮበልል በሰላም ጠብቆ ካገናኘን ድግሱን ይዘን እንቀርባለው በማለት ይሳላሉ፡፡
3.  ስለ ቀረበው ክቡር እህል ውሃ/ማዕድ/
         ሊቃውንቱ ፤ስለ ክርስቶስ ትንሳኤ ፤ ስለ ዝክሩ ባለቤቶች በተራ ዝማሬ ካቀረቡ በኋላ ‹‹ የአቤል መስዋዕቱ ተመርጦ  ቀረበ ማዕዱም ህይወት ነው አበበ አበበ ›› በማለት አቤል መስዋዕቱን ተጨንቆ በእግዚአብሔር ፊት እንዳቀረበ፤እና መስዋእቱ ተቀባይነት እንዳገኘ ሁሉ ዛሬ እናንተ በክርስቶስ ፊት ትንሳኤውን አስባችሁ የተመረጠውን ይዛችሁ፤ያልታየውን ደብቃችሁ፤ቀንዱ ሰማይ ጠቀስ ፤ጮማው የሰባውን ፤ ጠላው የጠራውን ጠምቃቹሁ፤ተጠባችሁ፤ተጨንቃችሁ ያዘጋጀቸሁት ድግስ እጅግ ያመረ እና የጣፈጠ ነው በማለት ስለ እህል ውሃው እያመሳጠሩ ያመሰግናሉ፡፡
      ምሳሌ፤-
& ማዕዱ አቢይ/2/ ህብስተ መና/2/
            ወስቴሁ ከመ ወይነ ቃና/2/ በማለት
@  ትርጉም፤- ይህ ማዕድ ምንኛ ታላቅ ነው፡፡እስራኤላውያን የተመገቡት ከሰማይ የወረደ ጠፋጭ መና ነው፡፡ ወይኑም እንደ ቃና ዘገሊላው ወይን እጅግ ጠፋጭ ነው በማለት ያመሰግናሉ፡፡
& ዝልል ተዘጋጀቶ ወረደ /2/ በማጀት አድርጎ/2/
           ብንቀምሰው ወይንና ትርንጎ/2/ 
ይህም ማለት  ፤በማጀት የተዘለለው ጠላ ለመጠጣት ተዘጋጀ/ወረደ/ ፤እንደ ወይን እና እንደ ትርንጎ ጠፋጭ ሆነ ማለት ነው፡፡እንዲህ እያለ ምስጋናው አንድ ሁለት እያለ ይቀጥላል፡፡በዝማሬው ጊዜ ድምጹ ያማረለት፤ ቅኔው የሰመረለት ተማሪ በሽልማት ይዥጎደጎዳል፡፡በግብረ ሰላም ጊዜ የአብነት መምህራን ፍሬ የሆኑት ደቀመዛሙርቶች ሰፊ እድል አግኝተው ዜማ/ቅኔ የሚያቀርቡበት ጊዜ በመሆኑ ሰፊ ቅድመ-ዝግጅት ሳያደርጉ ወደ ግበረ ሰላሙ አይታደሙም ፡፡በመሆኑም የአብነት መምህራን አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ተማሪዎቻችን ከማየት፤ከመሸለም ፤ከማበረታታት እና ያስተማሩዋቸውን የተመረቁ ተማሪዎች ከማስተዋወቅ የዘለለ በዜማው/በቅኔው ላይ ተሳትፎ የላቸውም፡፡በዚህ ጊዜ መምህራን ለተማሪዎቻቸው፤ካህናት ለዲያቆናት ሽልማት ያበረክታሉ፡፡ሽልማቱ ፎጣ፤ነጠላ፤መጽሐፍ ፤መቋምያ፣ጸናጽል እና ብር ወዘ.ተ. ሊሆን ይችላል፡፡
     ግብረ ሰላም በአብዛኛው  በጎንደር፤በደብረ ታቦርእና በጎጃም አካባቢ በስፋት  ይከናወናል፡፡ ስርዓቱ በቀድሞው ጊዜ በሰፊው ይከናወን የነበረ ቢሆንም አሁን አሁን ግን እየቀነሰ መጥቷል፡፡የግብረ ሰላም ፋይዳው ሰፊ ነው ለአብነትም ያህል
*        ስለክርስቶስ መንገላታት፤መሰቀል መሞት ፤ብሎም ክርስቶስ በመካከላችን  ሰላም አደረገ፤ደስታም ሆነ በማለት ፤ካህናቱ ሙሉ በተገኙበት፤የአብነት መምህራን እና ተማሪዎች በሚሳተፉበት፤ግብረ ሰላም ማድረግ በረከተ ስጋ በረከተ ነፍስ ይገኛል፡፡
*        በአብነት ተማሪዎች መካከል መንፈሳዊ ፉክክርን ያጠናክራል፡፡ምሳሌ፤ በቅኔ እና አቋቋም መካከል
*        በምዕመናን እና ካህናት መካከል ያለውን ግንኙነት ያጠናክራል፡፡ይህ ግብረ ሰላም ግን በአሁኑ ሰዓት እየቀረ፤ምዕመናንም እጃቸው እያጠረ መጥቷል ፤ወጭ መቆጠብም ይሁን ትኩረት አለመስጠት ብቻ ስርዓቱ በምዕመናንም በካህናትም ትኩረት ተነፍጎታል፡፡ ስርዓቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረትነት እንዳለው ከላይ በመግቢያው ላይ ለመግለጽ ሞክረናል፡፡ስለዚህ ባለግበረ ሰላሞችን ሰላም እያልን ….ግብረ ሰላሙን እንጠብቅ መልዕክታችን ነው፡፡ 

ይቆየን !!  
በሊቀ ጉባኤ አስካል

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር!!

  

Post Bottom Ad