"ፍኖተ ቅዱሳን" - አትሮንስ ዘተዋሕዶ

አትሮንስ ዘተዋሕዶ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሥርዓትና ደንብን የጠበቁ ጽሑፎችና ምስሎች በመ/ር ቀሲስ ንጋቱ አበበ እየተዘጋጀ የሚቀርብበት ድኅረ ገጽ ነው።

Breaking

Post Top Ad

Responsive Ads Here

Wednesday, January 29, 2014

"ፍኖተ ቅዱሳን"

 በቅድሚያ ልናውቅ የሚገባን ነገር አለ።  እሱም ሃይማኖታችንን ጠንቅቀን ማወቅ እና ቅዱሳን አባቶቻችን የሄዱበትን የሃይማኖት መንገድ መከተል ነው። ለምሳሌ፤

1) ፍኖት ማለት መንገድ ማለት ነው:: በመጽሐፍ ቅዱስ የሰው ሕይወት በመንገድ ተመስሏል:: በመንገድ ላይ ሳለህ በጠላትህ እወቅበት ማለቱ በዚህ ዓለም ሕይወትህ በጠላት ዲያብሎስ ላይ ጠቢብ ሁንበት ማለት ነው:: ማቴ 5;25:: የሰው ሕይወት በመንገድ የተመሰለው በመንገድ ላይ አንዱ ሲወጣበት ሌላው አንዱ ሲወርድበት ሁሉም ወደ አሰበው ሲደርስበት እንደሚኖር ሁሉ በዚህ ዓለም ሕይወትም አንዱ ጽድቅ ሠርቶ ከክብር ወደ ክብር ሲሸጋገርበት ሌላው ደግሞ በሚያልፍ ዘመኑ ፍዳው የማያልፍ ኃጢአት ሲሠራ ኖሮ በወደደው ኃጢአት እንደ ጠፍ ጨረቃ ከክብር እያነሰ ስለሚሄድበት ነው:: ቅዱሳን መንገድ በተባለ በዚህ ዓለም ሕይወታቸው በጠላታቸው በዲያብሎስ ላይ አውቀውበት እርሱን ጠቅጥቀው አልፈው ለክብር የበቁ ሲሆን ይህ ብሎግም ይህንኑ የቅዱሳን ጥበብና ተጋድሎ በአጠቃላይም
የሕይወትና የክብር ባለቤት ወደ ሆነው የባህርይ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረጉትን ጉዞ የሚያሳይ ስለሆነ በዚህ ብሎግ ላይ የምናስተላልፋቸው መልእክቶች  የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፤ ቀኖና እና ትውፊትን የጠበቀ ከመሆኑም በላይ ከአባቶቻችን የወረስናቸውን  ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የጠበቀ ትምህርት፤ መዝሙሮች፤ ስብከቶች፤    እና ሌሎች ጥሩ ምክር አዘል ቁም ነገሮችን አትሮንስ ታስተላልፋለች::

2) ሰው የፈጣሪውን ሕግ በማፍረሱ ምክንያት ወደዚህ ዓለም ቀጥሎ ወደ አምላኩ የሚያደርሰውን እውነተኛ መንገድ አጥቶ አምስት ሽህ አምስት መቶ ዘመን ሲባዝን ኖረ:: ይህ ዓመተ ፍዳ ሲያልቅ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነስቶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆኖ ወደዚህ ዓለም መጥቶ ሰውን ከፈጣሪው ጋር የሚያገናኘውን እውነተኛውን መንገድ አስተማረ:: ገላ 4;4:: እርሱም "አነ ውእቱ ፍኖተ ጽድቅ ወሕይወት - የጽድቅና የሕይወት መንገድ እኔ ነኝ" በማለት ከፈጣሪው አንድነት ተለይቶ ከክብር ተራቁቶ የነበረውን የሰው ልጅ ወደራሱ አንድነት ሊያዋህደው እንደመጣ አስረዳ:: እርሱን በፍጽም ሕይወታቸው ለሚመስሉት ወደ ሕይወትና ክብር የምትወስደውን ጠባብ መንገድ በቃል ያስተማረና በተግባር ሠርቶ ሥሩ ያለ ቅዱሳንን የጠራ የተቀበለና ያከበረ እውነተኛው ፍኖተ ቅዱሳን ኢየሱስ ክርስቶስ ለወዳጆቹ ያለውን ፍቅርና ተቆርቋነት እንዲሁም ያዘጋጀላቸውን ክብር ስለሚያስረዳ የአትሮንስ ብሎግ ጉዟችን ቅዱሳን አባቶቻችን የተከተሉትን መንገድ መከተል ነው።

3) ነቢየ እግዚአብሔር ሆሴዕ "ይህን ነገር የሚያስተውል ጠቢብ የሚያውቃትም አስተዋይ ማነው? የእግዚአብሔር መንገድ ቅን ነው ጻድቃንም ይሄዱበታል ተላላፊዎች ግን ይወድቁበታ" ብሎ የጻድቃንን እና የኃጥአንን መንገድ ልዩነት አስረድቷል:: ሆሴ 14:9 ጠቢቡ ሰሎሞን" የጻድቃን መንገድ እንደ ንጋት ብርሃን ነው ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል" ይላል ምሳ 4:18  

ስለዚህ አትሮንስ ብሎግ ጻድቃን የሄዱበትን ቅንና ርቱዕ የሆነውን፤ እግዚአብሔር ቅድስናን እና ፍጹምነትን ለሚሹ ያዘጋጀውን መንገድ ስለሚያሳይ፤ አትሮንስ ብሎግ የምታስተላልፋቸውን ቁም ነገሮች በየጊዜው እንድትከታተሉ ስትል ጥሪዋን ታስተላልፋለች።

የቅዱሳን በረከታቸው እና ረድኤታቸው አይለየን::

Post Bottom Ad