በዲያቆን ንጋቱ አበበ
አንድን ሰው መንፈሳዊ ወይም ክርስቲያን ነው የሚያሰኘው ብዙ መስፈርቶች አሉት። በእርግጥም አንድን ክርስቲያን፤ከርስቲያን ነው የሚያሰኘው ዝም ብሎ ወደ ቤተ ክርስቲያን መመላለሱ ብቻ ሳይሆን በሚኖረው መንፈሳዊ ሕይወትም ጭምር ነው። “እኔ ግን በምሕረትህ ብዛት ወደ ቤትህ እገባለሁ አንተን በመፍራት ወደ ቅድስናህ መቅደስ እሰግዳለሁ” መዝሙረ ዳዊት 5፤7።እንደ አባቶቻችን አገላለጽ መንፈሳዊነት የሚመለከተው የሰውነቱን ማጎንበስ ወይም መንበርከክ ሳይሆን ሰውነቱን ከመንፈሱ ጋር አብሮ አንዲሰግድ ነው። ሁልጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን በምንሄድበት ጊዜ ይህንን ቃል ልናስብና ልንገነዘብ ይገባል። ቅድሴም በምናስቀድስበት ጊዜ ዲያቆኑ የሚያውጀው አዋጅ አለ፤ ይኸውም ስግዱ ለእግዚአብሔር በፍርሃት፤ በፍርሃት ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ስገዱ ይላል። ስለዚህ ወደ ቤተ ክርስቲያን በምንሄድበት ጊዜ ራሳችንን አውቀን፤ ተዘጋጅተን፤ በድፍረት ሳይሆን በፍጹም ፍቅርና ትህትና ከሆነ የመንፈሳዊነት ብርታት መገኛ የሆነ አምላክ እርሱ እግዚአብሔር ስለሆነ ጽናቱንና ብርታቱን ሰጥቶን በሃይማኖታችን ጸንተን ራሳችንን ገዝተን እንድንኖር ይረዳናል። ራስን መግዛት አንዱ የመንፈሳዊነት መገለጫ ነው። ራስን መግዛት ሲባል ምላስን፤ ስሜትን፤ ሃሳብን፤ አካሄድን፤ ሆድን (ምግብን በተመለከተ)፤ ጸባይን፤ የመሳሰሉት ናቸው። በዚህ መሰረት ካልሄድን መጨረሻው የሚጠቃለለው በጥፋት ላይ ብቻ ይሆናል። ለምሳሌ፦ መንፈሳዊነት የማይታይባቸው ግን ወደ እግዚአብሔር ቤት ሁልጊዜ የሚመላለሱትን ሁለት ወንድማማቾች አፍኒንና ፊንሐስን እንመልከት። እነዚህ ሁለት ወንድማማቾች እግዚአብሔርን ሳይፈሩ በድፍረት ወደ ማደሪያው ድንኳን ከሚመጡ ሴቶች ጋር ግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈጸሙ (በዝሙት ረከሱ)፤ የአማላካቸውን የእግዚአብሔርን ቤት አቃለሉት። የእግዚአብሔርን ሕዝብ በዝሙት አረከሱት። እግዚአብሔር አምላክም እነዚህን ሁለት ወንድማማቾች ምናምንቴዎች አላቸው። አባታቸውም ኤሊ ስለ ሰሩት ሃጢአት አይናገራቸውም ነበር። ፊልስጤማዊያንም እስራኤልን ለመውጋት በአፊቅ ሰፈሩ። በሁለቱ ሃገራት መካከል ጦርነት ተካሄደ። ድሉም ለፍልስጤማዊያን ሆነ። የሚገርመው ነገር በነዚህ ሁለት ወንድማማቾችና በአባታቸው ሃጢአት ምክንያት በአንድ ቀን 30 ሺህ ጦር ከእስራኤል ረገፈ። አፍኒንና ፊንሐስም በዚያ ሞቱ (ተቀሰፉ)። ሁለቱ ልጆቹ እንደሚሞቱ ለአባታቸው ኤሊ የተነገረው ተፈጸመ። ኤሊም ታቦተ ጽዮን መማረኳን ሲሰማ ደንግጦ ሞተ። የዝሙታቸው ወይም የሃጢአታቸው መጨረሻው ሞት ሆነ። ወደ ቤተ እግዚአብሔር የሚመላለሱት መንፈሳዊነት የተሞላ ቢሆን ኖሮ ይህ ሁሉ ባልደረሰም ነበር። በመንፈሳዊነት ቢያገለግሉ ኖሮ ከጸጋ ላይ ጸጋ እግዚአብሔር አምላክ ያድላቸው ነበር። ዛሬም በተሰጠን ጸጋ እያገለገልን በአገልግሎታችን ጸንተን በጾም በጸሎት ራሳችንን ገዝተን ልንኖር ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን በመንፈሳዊነት ካልተመላለስን፤ ቅዱሳን አባቶቻችን የሄዱበትን መንገድ ካልተከተልን መጨረሻችን ድፍረት ይሆንና አልፎ ተርፎም የኤሊ ልጆች እጣ ይደርሰናል። ምን አልባት ቅዱሳን አባቶች የራሳቸውን አገልግሎት ፈጽመው ሄደዋል፤ እኛም የራሳችንን የሚሉ ካሉ ተሳስተዋል። ምክንያቱም እግዚአብሔር አምላካችን ታጋሽ አምላክ ነው፤ ነገር ግን የቅጣት እጁን ካነሳ ልክ እንደ አፍኒንና ፊንሐስ የሚመልሰው የለም። በጸሎተ ቅዳሴ ለመሳተፍ ሁልጊዜ ከህሊና መተዳደፍ፤ ከነገር፤ ከጸባይ፤ ከግጭት፤ ከቁጣ፤ ከአድመኝነት፤ ከዘፋኝነት፤ ከስካር፤ ከሟርት፤ ከዝሙት፤ ከመናፍቅነት፤ ከምቀኝነት፤ ከመግደል፤ ከመለያየት እነዚህን ከመሳሰሉት ህሊናን አንጽቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባት ያስፈልጋል። ይህን የማያደርግ ግን ወደ መንግስተ ሰማያት ሊገባ ከቶ አይችልም እንዳለ ገላ 5፤21። መንፈስዊነት ያለው ሰው መጀመሪያ እግዚአብሔርን በማንኛውም በአለው አላማ ውስጥ ያስቀድማል። በተጨማሪም መንፈሳዊነት ያለው ሰው ከማንኛውም ፈተና የሚጠበቀው የአምላኩን ወይም የፈጣሪውን ቃል በእርሱ ውስጥ ሲጠብቅ ብቻ ነው ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፡፡
መንፈሳዊነት የተሞላ ሰው
- * እግዚአብሔር በመረጣቸው ቅዱሳን ላይ አይዘብትም። መዝ 30፤18
- * ቅዱሳን መላእክት የኛን የደካሞችን ጸሎታችንን ወደ ፈጣሪ እንደሚያደርሱ ያምናል። ጦቢ 12፤15 ሉቃ 15፤10 ሐዋ 10፤4-5
- * ቅዱሳን መላእክት ለእኛ ለደካሞች ዘወትር በፈጣሪ ፊት እንደሚቆሙልን (እንደሚያማልዱን) ያምናል። መዝ 148፤2 ኢሳ 6፤3-4 ማቴ 4፤11 ማቴ 25፤31 ማር 8፤38
- * ቅዱሳን በጭንቀት ጊዜ አንደሚደርሱ ያምናል። ዘፍ 16፤7-8 መዝ 33፤7 ዮሐ 20፤12-13 ማቴ 1፤20 ማቴ 28፤5-6
- * ቅዱሳን መላእክት እንደሚያጽናኑ እንደሚመክሩ ያምናል። ዘጸ 24፤20 ዳን 9፤21-22 ዘካ 1፤9 ሐዋ 27፤23-25 ሐዋ 8፤26-27 ዕብ 1፤14
- መላእክትም እንደሚመግቡ ያምናል። መዝ 77፤25 1ኛ ነገስት 19፤5-8
- ቅዱሳን መላእክትም የአብሮት ስግደት እንደሚገባቸው ያምናል። ዘፍ 19፤1 ዘኁ 22፤31 ኢያ 5፤14-15 ዳን 6፤16-17
- ቅዱሳን መላ እክት እንደሚቀጡም ያምናል። ዘፍ 3፤24 ዘኁ 22፤22 2ኛሳሙ 24፤1 መዝ 34፤6 ኢሳ 37፤36 ሐዋ 12፤23 ራዕ 12፤7-8
- ቅዱሳን መላእክት በአደጋ ጊዜ ፈጥነው እንደሚደርሱ በሙሉ ልብ ያምናል። ዘፍ 22፤11 መዝ 90፤11 ዳን 6፤22 ዳን 10፤13 ማቴ 2፤13 ሐዋ 12፤7 ሐዋ 5፤19
- ቅዱሳን፤ ጻድቃን፤ ሰማዕታት ያማልዳሉም የአክብሮት ስግደትም ይገባቸዋል ብሎም ያምናል። ዘፍ 18፤17-19 ዘፍ 18፤23-24 ዘፍ 20፤7 ዘፍ፤3-4 ዘፍ 42፤6-7 1ኛ ሳሙ 28፤14 2ኛ ሳሙ 1፤2 2ኛ ነገስት 1፤13-14 2ኛ ነገ 2፤15-16 2ኛ ነገ 4፤9-10 2ኛ ነገ 4፤32-336 2ኛ ነገ 13፤20-21 2ኛ ነገ 19፤34 1ኛ ዜና 21፤21 ዳን 2፤46 ማቴ 18፤18 ዮሐ 20፤23 ሐዋ 10፤25 1ኛ ቆሮ 6፤1
- ለእግዚአብሔር ምስጋና የሚቀርብበትን የዜማ እቃ ለይቶ ያውቃል። 1ኛ ሳሙ 16፤23 2ኛ ሳሙ 6፤5 1ኛ ዜና 13፤8 1ኛ ዜና 15፤16 1ኛ ዜና 15፤28 ኢዮ 21፤12 መዝ 91፤3 መዝ 150፤3-6 2ኛ ዜና 29፤25 2ኛ ዜና 5፤12
- ይጾማል። ለምን እንደሚጾምና ለማን እንደሚጾም ለይቶ ያውቃል። ይኸውም በሚጾምበት ጊዜ ከመብል ወይም ከመጠጥ መከልከልንና ሃይል ሰጭ ከሆኑ ምግቦች ለምሳሌ እንደ ሥጋ፤ ቅቤ፤ ወተት፤ እንቁላል ነክ የሆኑ ምግቦችን ከመብላት መታቀብን ያውቃል። ጾምን በሚጾምበት ጊዜ ክፉም ከመስማት፤ ክፉም ከማየት፤ ክፉም ከመናገርና ክፉ ከማድረግ መታቀብን ይመርጣል። ጾምና ጸሎት በ አንድነት ርኩሳት መናፍስትን ድል የምንነሳባቸው ትልቁ መሳሪያችን መሆኑን ጠንቅቆ ያውቃል ይረዳልም። በተለይ በጾም ወቅት፤ ጾማችንና ጸሎታችን በፈጣሪ ፊት ተቀባይነት እንዲኖረው ካለው የተራበን ያበላል፤ የታረዘን ደግሞ ያለብሳል ማለት ነው።
- መባን (አስራቱን) መስጠት አንዳለበት ይረዳል።
በዚህ መሰረት ያልተጓዘ ወይም የማይጓዝ ክርስቲያን ወይም መንፈሳዊ የሆነ ሰው ሁሉ፤ ከእግዚአብሔር ያልሆነ መንገድ ስለሆነ ጉዞው ከንቱ ይሆናል። ያላማረ ጉዞ ምንጊዜም መጨረሻው ጥፋት ይሆናል ማለት ነው። እንደነ ናቡቴን የገደለውን አክአብን፤ ፈርዖንን፤ አቤልን የገደለው ቃየልን፤ እንደነ ጎልያድ ያሉትን በትዕቢት ተሞልተው እግዚአብሔርን ያሳዘኑና መንፈሳዊነት ያልተሞላው አካሄድ የሄዱ ስለሆኑ መጨረሻቸው አላማረም ነበር። እኛ ግን መንፈሳዊነትን ከአባቶቻችን ከገድላቸው፤ ከተአምራቸው አንብበን ልንረዳና አካሄዳችንን ልናሳምር እግዚአብሔር በቅዱሳን ላይ አድሮ የሰራውን ድንቅ ድንቅ ተአምራት እያነበብን በንጹህ እምነት ልንከተላቸው ይገባል። የመንፈሳዊነት ኃይል ወይም ጥንካሬ የሚገኘው ከእግዚአብሔር ስለሆነ ዘወትር በጾምና በጸሎት ልንተጋ ይገባል። መንፈሳዊነት የተላበሰ ሰው ምንጊዜም ሁልጊዜ በፈጣሪው በአምላኩ ፊት ሲቆም፤ በፍርሃት፤ ደካማነቱንና ኃጢአተኛነቱን በማወቅ “ጌታየ አምላኬ ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፤ አንተ ደካማነቴን፤ ኃጢአተኛነቴን አይተህ በቃልህ እጸና ዘንድ፤ ሃይማኖቴን፤ ህግህና ስርዓትህን ጠብቄ እኖር ዘንድ አባክህ ብርታትን ስጠኝ ብሎ ሊጸልይ ይገባል። ያለ አንተ ምንም ማድረግ አልችልም በማለት ጸሎቱን ሊያሳርግ ይገባዋል። ዮሐ 15፤5 እግዚአብሔር አምላክም የደካማውን ጸሎቱን ይሰማል። መሳ 16፤28 ምንጊዜም በማንኛውም ጊዜና ወቅት ራስን በመንፈሳዊነት ሚዛን መመርመር ተገቢ ነው። ራስን መመርመር ዋናው የመንፈሳዊነት መገላጫው ነውና። በማንኛውም ጊዜና ወቅት ራስህን በመንፈሳዊነት ደካማ ሆነህ ካገኘኸው ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለህን ህብረት መርምር። ለምሳሌ፦ ሶምሶም የመንፈሳዊነቱን ብርታት ያጣው በእንዝላልነት ስለነበረና መንፈስ ቅዱስ ከሱ ስለተለየ ነበር። መንፈሳዊነቱን ስለ ረሳው በዝሙት ወደቀ መንፈስ ቅዱስም ተለየው፤ መጨረሻው ሞት ሆነ። ስለዚህ ሁልጊዜ ወደ ቤተ እግዚአብሔር እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ እንዳለ ቅዱስ ዳዊት እኛም ወደ ቤተ እግዚአብሔር ስንሄድ ደስ ሊለን ይገባል። ስንሄድም መንፈሳዊነት በተመላው መልኩ መሆን አለበት። ሰውነትህን የእግዚአብሔር መንፈስ የሚያድርበት ቤተ መቅደስ እስኪሆን ድረስ በንጽህናና በቅድስና ራስህን አዘጋጀው። ይህን በማድረግህም በርታትን ወይም ጥንካሬን ከፈጣሪህ ዘንድ ታገኛለህ አንተም ሁልጊዜ ከመትጋት ወደ ኋላ አትበል። የሰው ልጅ መንፈሳዊ ጥንካሬውን የሚያገኘው የፈጣሪውን ቃል በእርሱ ውስጥ ሲጠበቅ ብቻ ነው። ህልጊዜ የፈጣሪህን ሕግና ስርዓት ጠብቀህ ከኖርክ፤ በልብህ ውስጥ ሸሽገህ፤ በአንደበትህ ሁልጊዜ የምትደግመው ከሆነ፤ የፈጣሪህ ቃል ምንጊዜም ኃጢአትን የሚያሳፍር መሆኑን ያሳውቅሃል፤ ጽናቱንና ብርታቱንም ይሰጥሃል፤ እግዚአብሔር አምላክም ሁልጊዜ ካንተ ጋር ከሆነ ማንም አይቃወምህምና፤ ቃሉም እውነት አለው።
ይቆየን………