ቅዱስ ቂርቆስ እድሜው የሦስት አመት ሳለ እናቱ ቅድስት እየሉጣ ከሮሜ ወደ ሌላ ሃገር ሸሽታ ይዛው ሄደች በዚያም የሸሸችውን መኮንኑን አገኘችው። የሚያውቋትም ሰዎች ሸሽታ እንደመጣች ስለተረዱ ለመኮንኑ ነገር ሰሩባት።  መኮንኑም ወደ እርሱ አስጠራትና ስለ አምልኮ ጠየቃት።  ቅድስት እየሉጣም መኮንን ሆይ፡ እድሜው ሦስት አመት የሆነው ሕፃን አለ አማልክቶችህን ማምለክ መልካም እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ያስረዳን ዘንድ እርሱን ጠይቅ አለችው።  ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስም ወደ አለበት ጭፍራውን ልኮ ወደ እርሱ አስመጣው ሕፃኑንም ፊቱ ብሩህና ደስተኛ እንደሆነ አየውና አንተ ደስተኛ ሕፃን ሆይ እንዴት ነህ አለው። ሕጻን አዱስ ቂርቆስም መለሰለት እንዲህም አለው።  አዎ እኔ በጣም ደስተኛ ነኝ ደስታየም ተጠብቆልኛል ላንተ ግን ኅዘንና ለቅሶ ጥርስ ማፋጨትም ነው መጽሐፍ ቅዱስም ለዝንጉዎች ተድላ ደስታ የላቸውም ብሏልና አለው።  እግዚአብሔር አምላክ ኃይልንና ንግግርን ሰጥቶታልና በዚያ ለተሰበሰቡት ሰዎች እስኪደነግጡ ድረስ ብዙ ተናገረ።  ሕፃን ቅዱስ ቂርቆስም ንጉሱን መኳንንቱንና ጣኦታቱን ረገማቸው ከብርታቱም የተነሳ አደነቁ።  መኮንኑም በአፈረ ጊዜ በየአይነቱ በሆነ ስቃይ፡ ታላላቆች አንኳ የማይችሉትን ታላቅ አስጨናቂ የሆነ ስቃይን አሰቃየው።  እናቱ ቅድስት እየሉጣንም ከ እርሱ ጋር እንደ እርሱ በጣሙን አሰ  ቃያት።  እግዚአሔብሔር ግን ያለ ምንም ጉዳት ያነሳቸው ነበር።  ብዙዎች አህዛብም ይህን አይተው አደነቁ ክብር ይግባውና በጌታችን በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት አምነው በሰማእትነት ሞቱ የሰማእትነትንም አክሊል ተቀበሉ።  በሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ላይም የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ አደረበት።  ታላላቅ ድንቅ ተአምራቶችንም ያደርግ ነበር።  ብዙዎች በሽተኞችንም ያድናቸው ይፈውሳቸው ነበር።  ይህንን ያየ መኮንን በታላቅ የናስ ጋን ውስጥ ውሃ ጨምረው በ እሳት ያፈሉት ዘንድ አዘዘ።  የፍላቱም ድምጽ እንደ ክረምት ነጎድጓድ ሆነ ድምጹም በጣም ያስተጋባ ነበር።  ይህን ያየችና የሰማች እናት ቅድስት እየሉጣም ፍርሃትና የሃይማኖት ጉድለት ታየባት።  ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ግን እናቱ ቅድስት እየሉጣን ሁኔታዋን አይቶ ወደ አምላኩ እግዚአብሔር ጸለየ።  ያን ጊዜ ልዑል እግዚአብሔር ልቧን ወደ ሰማይ አሳርጎ ለቅዱሳን ሰማዕታት የተዘጋጁ የብርሃን ማደሪያዎችን አሳያት።  ቅድስት እየሉጣም እንደገና በሃይማኖቷ ጸናች። እግዚአብሔር አምላኳንም አመሰገነችው።  ልጇን ሕፃኑን ቅዱስ ቂርቆስንም ልጄ ሆይ አንተ ከ እንግዲህ አባቴ ነህ እኔም ልጅህ ነኝ አለችው።  ቅድስት እየሉጣም ለልጇ ያች የተወለድክባት እለት ቀኗ የተባረከችና የተቀደሰች ናት አለችው።  የመኳንንቱ ጭፍሮችም እሳት ወደ አለበት ጋኖች ውስጥ ቅዱስ ቂርቆስንና እናቱን ቅድስት እየሉጣን በጨመሯቸው ጊዜ የውሃው ፍላት ወደያውኑን ቀዘቀዘ።  ከ እግዚአብሔር የታዘዘ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወርዶ የ እሳቱን ኃይል አቀዝቅዞታልና።  ይህን ያየ መኮንን ሥጋቸው ተቆራርጦ እስከሚወድቅ ድረስ በመቃጥን ውስጥ አድርገው አንዲጎትቷቸው አዘዘ።  ከ እግዚአብሔርም የታዘዘ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል አዳናቸው።  መኮንኑም በታላቅ ስቃይ ያሰቃያቸው ዘንድ አስቦ እስኪመክር ድረስ በወህኒ ቤት ዘጋባቸው።  በዚህን ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሕጻኑ ቅዱስ ቂርቆስን አረጋጋው አጽናናው።  ስሙን ጠርተው መታሰቢያ ለሚያደርጉለትም  በረከትን እንደሚያገኝ ቃል ኪዳን ሰጠው ።  እግዚአብሔር አምላካችን የሕጻኑ ቅዱስ ቂርቆስና የእናቱ የቅድስት እየሉጣን በረከታቸውንና ረድኤታቸውን ያድለን አሜን። እንኳን ቅዱስ ገብርኤል በዓል አደረሳችሁ!!!
ቅዱስ ገብርኤል ሆይ