(በዲያቆን ንጋቱ አበበ)


የጻድቁ የንጉስ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግስት እሌኒ የጎልጎታን  ተራራ አስጠርጋ የጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል ለማግኘት ወደ ኢየሩሳሌም ዘለቀች።  በዚያን ጊዜ መስቀሉ ድውይን ይፈውስ ነበር፤ ሙታንን ያስነሳ ነበር፤ ደንቆሮዎችም ይሰሙ ነበር፤ ዲዳዎች ይናገሩ ነበር፤ በተለያየ ደዌ በሽታ የተያዙ ሁሉ ይፈወሱ ነበር። በዚህም ምክንያት አይሁድ ይቀኑና ይቆጡ ነበር፤ ስለዚህም አይሁዳዊያን የጌታችንን መስቀል የተቀበረበትን ያውቁ ስለነበርና ብዙ ተአምራትንም ሲያደርግ ያዩ ስለነበር ማንኛውም አይሁድ ከተለያየ ስፍራ ቆሻሻ በማምጣት የጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል የተቀበረበት ቦታ ላይ ይጥሉት ነበር። እንደዚህ እያደረጉ ለሦስት መቶ ዓመታት ያህል መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ቆሻሻ መጣያ በማድረግ ኖሩ።  ንግስት እሌኒም በመጣች ጊዜ
የጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል ያረፈበትን ቦታ እስኪነግሯት ድረስ አይሁዳዊያንን አሰቃየቻቸው። አይሁድም ቦታውን ከነገሯት በኋላ ተራራውንም ኮረብታውንም እንዲጠርጉ አስገደደቻቸው። አይሁዳዊያንም እንደታዘዙት አደረጉ፤  መስቀሉም ከተቀበረበት በክብር ተገልጦ ወጣ። በዚህች ቀንም አከበሯት ለመስቀሉም በዓል መስከረም 17 ቀን እንዲሆን ወስነው አከበሩለት።  ሁሉም ክርስቲያን በአንድነት በመሰባሰብ ከያሉበት አቅጣጫ በመምጣት አብረው የጌታን ትንሣኤ በዓል እንደሚያከብሩ ለመሰቀልም ታላቅ በዓልን የሚያከብሩ ሆኑ።  ክርስቲያኖችም በጎዳና እየተጓዙ ሳሉ ስሙ ይስሐቅ የሚባል አንድ ሳምራዊ ሰው ከ እርሳቸው ጋር ነበር። ከእርሱም ጋር ብዙ ሳምራዊያን ነበሩ።  ይህ ይስሐቅም የክርስቲያን ወገኖች ለምን በከንቱ ትደክማላችሁ፤ ለእንጨትስ እንዴት ልትሰግዱ ትሄዳላችሁ እያለ ይሳለቅባቸው ነበር።  ከክርስቲያን ወገን የሆን ስሙ አውዶኪስ የሚባል አንድ ቄስ ነበር፤ ረጅም ጉዞ ስለተጓዙ አብረውት የሚሄዱት ህዝበ ክርስቲያን የሚጠጡት ውሃ አላገኙም ነበርና ተጠሙ።  በመንገድ ላይ አንድ ጉድጓድ አገኙ በውስጡም መሪር የሆነና የገማ ውሃ አገኙ፤ እጅግም በውሃ ጥማት ተሰቃዩ፤ ይስሐቅም እጅግ ይሳለቅባቸው፤ ይስቅባቸው ነበር፤ የቀናች ሃይማኖት ካላችሁ ይህ የገማና የመረረ ውሃ ተለውጦ እስኪ ጣፋጭ ይሁን አላቸው።  ቀሲስ አውዲኮስም በሰማ ጊዜ  ከዚያ ሳምራዊ ይስሐቅ ጋር  በሃይማኖት ዙሪያ ተከራከረው። ሳምራዊው ይስሐቅም በመስቀል ስም የተአምራትን ሃይልን ካየሁ እኔ በክርስቶስ አምናለሁ ብሎ ቃል ገባለት።  ያን ጊዜም ቀሲስ አውዶኪስ በዚያ በገማ ውሃ ላይ ጸለየ፤ ውሃውም ወዲያውኑ ጣፋጭ ሆነ፤ ከዚህም ውሃ ሕዝቡ በሙሉ ጠጥተው ረኩ ያሉት ከብቶቻቸውም፤ እንስሶቻቸውም ሁሉ ጠጡ።  ሳምራዊ ይስሐቅ ግን በተጠማ ጊዜ በረዋት ያዘው ውሃ ሊጠጣ ፈለገ፤ ነገር ግን ገምቶ፤ ተልቶ አገኘውና መሪር ለቅሶን አለቀሰ። ወደ ቀሲስ አውዶኪስም መጥቶ ከእግሩ በታች ሰገደ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አመነ፤ ቀሲስ አውዶኪስም ጸሎት አድርጎ ያንን የገማ ውሃ ጣፋጭ እንዲሆን ካደረገ በኋላ ሳምራዊ ይስሐቅ ከውሃው ጠጣ።  በዚያም ውሃ ውስጥ ታላቅ ሃይል የሚያደርግ ሆነ፤ ውሃውም ለአማንያን የሚጣፍጥ ሲሆን ለከሃዲያን፤ ለአረማዊያን፤ ለመናፍቃን ደግሞ የሚመር ሆነ፤ በውስጡም የብርሃን መስቀል ታየ፤ በአጠገቡም ውብ የሆነች ቤተ ክርስቲያንን አነጹ።  ሳምራዊ ይስሐቅም ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ በደረሰ ጊዜ ወደ ኤጲስ ቆጶሱ ሂዶ ከቤተሰቡ ጋር የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቀ።

እኛ አሁን ከዚህ ምን እንማራለን? የንግስት እሌኒ በረከቷ ይደርብን አሜን።
በመስቀሉ ላዳነን ለ እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን ለዘለዓለሙ አሜን።